• 80 በመቶ አካል ጉዳተኛ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው
ጎንደር፡- በቀጣሪዎች የአመለካከት ችግርና የስራ ቦታ ምቹ አለመሆን ከ95 በመቶ በላይ የተማሩ አካል ጉዳተኞች ስራ አጥ መሆናቸው ተገለጸ:: ከ80 በመቶ በላይ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ አካል ጉዳተኛ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውም ተጠቁሟል::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አበበ የኋላወርቅ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ፁሁፍ እንዳመለከቱት፤ በአገሪቱ ከህብረተሰቡም ሆነ ከራሱ ከአካል ጉዳተኛው ከሚመነጩ የተሳሳቱ ግምቶች፣ ከቀጣሪዎች የአመለካከት ችግርና ከስራ ቦታ ምቹነት መጓደል ከ95 በመቶ በላይ የተማሩ አካል ጉዳተኞች ስራ አጥተው እራሳቸውን ማስተዳደር እንዳይችሉ ሆነዋል ::
ዶክተር አበበ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ አካል ጉዳተኞች 2.8 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከ80 በመቶ በላይ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ አካል ጉዳተኛ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን፤ በርካታ አካል ጉዳተኞች ባሉበት ሀገር አካል ጉዳተኞችን ያላሳተፈና ያላማከለ ፖሊሲም ሆነ ህግ ማውጣት ሀገርን መጉዳት እንደሆነ አስረድተዋል::
እንደ ዶክተር አበበ ገለፃ፤ ባደጉት ሀገራት አካል ጉዳተኝነት ከስኬት መንገድ አያግድም:: በርካታ አካል ጉዳተኞች እራሳቸውን ከመቻል አልፈው በአለም አቀፍ ደረጃ ተፅእኖ መፍጠር የቻሉት ብዙዎች ናቸው:: በሀገራችን አካል ጉዳተኞች ከሚደርስባቸው ስነ ልቦናዊ ጫና በተጨማሪ ተቋማዊ የሆነ በደል በግልፅ ይፈፀምባቸዋል::
የሰውን ልጅ ጥቁር ቀይ ብለን እንደምንለየው ሁሉ ህብረተሰቡም አካል ጉዳተኝነትን እንደ ልዩነት ማየት አለበት:: እንዲሁም እራሳቸው አካል ጉዳተኞች ተምረውና በተማሩበት ተቀጥረው ክህሎታቸውን ካላጎለበቱ በስተቀር ውይይት በማድረግና ጊዜያዊ መፍትሄ በማፈላለግ ብቻ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም ::
ዶክተር አበበ ‹‹በርካታ ህጻናት ሳይማሩ ሀገሪቱ የጀመረቻቸውን የእድገት ፖሊሲዎቿን ማሳካት አትችልም:: እንደ ጤነኛ ሕፃናት አካል ጉዳተኛ ህጻናትም የወደፊት የሀገሪቱን እጣ ፈንታ በመዳፋቸው የያዙ በመሆናቸው በመንከባከብ ከራሳቸው አልፈው ለሀገር የሚጠቅሙ ማድረግ ያስፈልጋል:: የጥገኝነት ስሜትን እንዳያዳብሩና በስነ ልቦና ጠንካራ ለማድረግም ማስተማር ይገባል›› ብለዋል::
የአካል ጉዳተኞች ቀን ‹‹የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ መሪነት በማጎልበት የ2030 የልማት አጀንዳን ውጤታማነት ማረጋገጥ›› በሚል መሪ ሃሳብ በሀገራችን ለ27ኛ ጊዜ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ ተከብሯል::
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012
ሞገስ ፀጋዬ