መንገድ ምናባቱ አይባልም ከቶ፤
የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ፤
ያለው ባለቅኔ ማን ነበር? የዘንድሮ መንገድ ግን በተቃራኒው ሰዎችን ሲወስድ እንጂ ሲመልስ ምነው አልታይ አለ?!…ጎዳናው በየዕለቱ ቀጥፎ የሚያስቀረው ነፍስ ምነው በዛሳ?!..
አዎ!… አውራ ጎዳናው የሞት ባህር ሆኗል፡፡በየደቂቃው፣ በየሰዓቱ፣ በየዕለቱ ሞትን አንግሷል፡፡የሚስትና የልጆቹን ጉንጭ ስሞ፣ “በሠላም ያሳደርከን አምላክ በሠላም አውለን” ብሎ ከቤቱ የወጣ አባወራ (እማወራ) በድንገት አውራ ጎዳናው ላይ የሚቀርበት እውነታ ከገጠመኝነት አልፏል፡፡ክስተቱ ልጆችን በአንድ ጀምበር ወደጎዳና ገፍቷል፤ አንዳንዶችንም ሜዳ ላይ በትኗል፤ ሕይወታቸውን አመሳቅሏል፡፡
የአንዷን ቀን አሳዛኝ ገጠመኝ እንይ፡፡ህዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም፤ ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ፣ ከመቱ ወደ አዲስ አበባ እና ከቢሾፍቱ ወደ አዳማ ከተማ ሲጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ብቻ እንደዋዛ የ49 ወገኖቻችንን ሕይወት መንጠቁን ሰምተናል፡፡
አደጋውን በዝርዝር ስናይ ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ 20 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ በተለምዶ ሀይሩፍ በመባል የሚጠራ ተሽከርካሪ በኤጄሬና ሆለታ ከተሞች መካከል ከሲኖ ትራክ ጋር ተጋጭቶ አደጋ ደርሷል። በትራፊክ አደጋው የ17 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ያለፈ ሲሆን፤ በሌሎች ሦስት ሰዎች ላይ ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡
በተመሳሳይ ዕለት ከመቱ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ኦዳ ባስ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋም የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል። አውቶቡሱ ገተማ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የተገለበጠ ሲሆን፤ በአደጋው የ17 ሰዎች ህይወት ቀጥፏል።
በዚሁ ዕለት ከቢሾፍቱ ከተማ ወደ አዳማ ከተማ ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ15 ሰዎች ህይወት ስለማለፉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ያሳዝናል፤ የሞቱት ወገኖቻችንን ነፍስ ይማር!…ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ፈጣሪ መጽናናትን ይስጥልን፡፡
ጎዳና ላይ የቀሩ ዕንቁዎቻችን፡-
ኮሜዲያን አለባቸው ተካ
ከዛሬ 14 ዓመት በፊት ወደጅማ ሲጓዙ በደረሰባቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ኮሜዲያን አለባቸው ተካና የካሜራና የኤዲቲንግ ባለሙያው ይልማ ቀለመወርቅ ህይወታቸው ማለፉን እናስታውሳለን፡፡አለባቸው የመጀመሪያው የቶክ ሾው አቅራቢ ነበር፡፡ከአርቲስት ልመንህ ታደሰ ጋር በመሆን የስታንድአፕ ኮሜዲ ጀማሪ ነው፡፡በስሙ የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን አቋቁሞ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
አንዳንድ ባልደረቦቹ አለባቸው ተካን ሲያስታውሱ “… ለራሱ ከመኖር ይልቅ ለሌሎች መኖርን ይመርጥ ነበር” ያሉ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ “የደግነት አባት” ይሉታል፡፡
አርቲስት ሰብለ ተፈራ (እማማ ጨቤ)
በበርካታ ፊልሞችና ድራማዎች ላይ ተውናለች፡፡በተለይም በፋና ሲተላለፍ በነበረው ‹‹ትናናሽ ፀሐዮች›› በተሰኘው የራዲዮ ድራማ እማማ ጨቤ የተሰኙ ገጸ ባህሪ በመወከል ተጫውታለች።
ቅዳሜ ምሽት በኢቢሲ ይተላለፍ በነበረው ቤቶች ድራማ ላይም ትርፌ በሚለው ገፀባህሪዋ በርካታ ተከታታዮችን አፍርታለች፡፡
አርቲስት ሰብለ ተፈራ መስከረም አንድ ቀን 2008 ዓ.ም በባለቤቷ በሚሽከረከር መኪና በመጓዝ ላይ ሳሉ ሳሪስ አካባቢ በደረሰ አደጋ ህይወቷ ማለፉን የምናስታውሰው በከፍተኛ ቁጭት ነው፡፡
የባህል ሙዚቀኛው ሀብተሚካኤል ደምሴ
በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ድምፃውያን ሀብተሚካኤል ደምሴ አንዱ ነው፡፡ግሩም የመሰንቆ ጨዋታውና ለዛ ያለው ድምፁ በቀድሞውና በአሁኑ ትውልድም መወደድን አትርፎለታል፡፡በተለይ በመዲናና ዘለሰኛ እንዲሁም በሠርግ ዘፈኖች ይታወቃል፡፡ሀብተሚካአል የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችና ድምፃዊ ብቻ ሳይሆን ተዋናይም ነበር፡፡
የ64 ዓመቱ አንጋፋ የሙዚቃ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም ረፋድ ላይ በደረሰበት የመኪና አደጋ ነበር፡፡በዕለቱ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም መግቢያ አካባቢ መንገድ በማቋረጥ ላይ ሳለ ከአስኰ ወደ ፒያሳ በሚሄድ ሀይገር ባስ ተገጭቶ አቤት ጠቅላላ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም፡፡
ቁጥሮች ይናገራሉ
በዓለም ላይ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ከሚመዘገብባቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው አዲስ አበባ በዓመት 25 ሺ የሚጠጋ የተሽከርካሪ አደጋ ይመዘገባል፡፡ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሰዎች እንደሚኖሩባት በሚነገርላት ከተማዋ በየዓመቱ በርካቶች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡በአገሪቱ ከሚገኙ አጠቃላይ ተሽከርካሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሲርመሰመሱ ይውላሉ፡፡
በከተማዋ ያለው የተሽከርካሪ ብዛትም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ብሉምበርግ ግብረ ሰናይ ዓለም አቀፍ የመንገድ ደኅንነት ኢንሼቲቭ ሪፖርት ያሳያል፡፡በከተማዋ ያለው የነዋሪዎች ቁጥር ከ2005 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ በሰባት በመቶ ሲጨምር የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ደግሞ በ119 በመቶ መጨመሩን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በትራፊክ አደጋ 478 ሰዎች ሞተዋል፣ 3,133 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 24 ሺ 928 የተሽከርካሪ አደጋዎች በየዓመቱ ተመዝግበዋል፡፡
በከተማዋ በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉት አብዛኞቹ እግረኞች ናቸው፡፡የ2010 ዓ.ም ሪፖርት እንደሚያሳየውም በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 76 በመቶ የሚሆኑት እግረኞች ናቸው፡፡19 በመቶ የሚሆኑት የመኪና አሽከርካሪዎች፣ አምስት በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሞተረኞች ናቸው፡፡
በአማራ ክልል በ2012 ሩብ ዓመት ብቻ 618 አደጋዎች ደርሷል፡፡በዚህ አደጋ 183 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። 105 ከባድ፣ 114 ቀላል አካል ጉዳት ደርሷል፡፡እዚህ ውስጥ ቁጥራቸው ያልተካተተ ሊኖር እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡
አቶ ይበልጣል ታደሰ በአማራ ክልል የመንገድ ትራንስፖርት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። በአማራ ክልል ከመስከረም ወዲህ ያለው የትራፊክ አደጋ እየጨመረ መሆኑን ያስረዳሉ። ከፍተኛ የሆነ የሰው ሞት ያስከተሉ አደጋዎች ከመስከረም ወዲህ መመዝገባቸውን በመጥቀስ፤ በ2011 አጠቃላይ የአደጋው ብዛት 2,591 መሆኑን ያስታውሳሉ።
ከእነዚህ መካከል 1‚109 ሰዎች ሞተዋል፡፡የደረሰው የጉዳት መጠን በንብረት ሲሰላ ደግሞ፤ ከ97 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ለውድመት ተዳርጓል።
በኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ የትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ተመስገን እንደሚሉት፤ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ 1095 የትራፊክ አደጋ የተከሰተ ሲሆን፣ የ433 ሰዎችም ሕይወት አልፏል።
በዚህ ዓመት በደረሰው የትራፊክ አደጋ የወደመውን ንብረት በገንዘብ አስልተው ሲናገሩም 63 ነጥብ ሰባት ሚሊየን ይገመታል ይላሉ።
የትግራይ ክልል ትራፊክ ፖሊስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ብርሃነ መስቀል በበኩላቸው በክልላቸው በ2011 ዓ.ም ብቻ 1‚512 አደጋዎች ማጋጠማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በዚህ አደጋ 386 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ 79 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል ብለዋል።
ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ እንደሚሉት ከሆነ በክልላቸው አጠቃላይ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አቅደው እየሠሩ መሆኑን ተናግረው፣ የትራፊክ አደጋ ሲሰላ ከትራፊክ ፍሰቱ ጋር በንጽጽር እየተሰላ መሆን እንዳለበት በመጥቀስ የትራፊክ ማናጅመንቱ ካለው ትራፊክ ፍሰት ጋር አብሮ እንደማይሄድ ጠቅሰዋል።
አቶ አዲሱ ተመስገን የኦሮሚያ ክልል ብዙ የትራፊክ ፍሰት ያለበት እንደመሆኑ መጠን የትራፊኩ አደጋ በዚያው ልክ እንደሚበዛም ያብራራሉ።
በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የ4‚597 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ ማለፉን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡የትራፊክ አደጋው አገሪቱ ካላት አነስተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር አኳያ ሲታይ እጅግ የከፋ በመሆኑ አፋጣኝ ዕርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በትራፊክ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ2010 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በአራት በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡በዓለም አቀፍ ደረጃም በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ሲያጡ ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ደግሞ ቀላልና ከባድ አደጋ ይደርስባቸዋል፡፡
የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች ምንድናቸው
ወደ አገሪቱ የሚገባው የተሽከርካሪ ብዛት ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም የሚደርሰው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።
ለዚህ ሁሉ አደጋ የትራፊክ ማኔጅመንቱ ያለውን የትራፊክ ሥርዓት ለመምራት በሚችል መልኩ የተዘረጋ አለመሆኑ እንደሆነም ይታመናል፡፡
ዋና ዋና የትራፊክ አደጋዎች አሽከርካሪም እግረኛም የሚፈጽሙት ስህተት መሆኑን፣ የማሽከርከር ሥራ ያለውን ከባድ ኃላፊነት ያለመገንዘብ ለአደጋ ምክንያት ናቸው፡፡
የመንገድ ችግር፣ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር ከሚደርሱ የመኪና አደጋዎች ጥቂቱን እንደሚይዙ በመጥቀስ አብዩን ድርሻ የሚይዘው የእግረኛና የአሽከርካሪ ስህተት መሆኑን አጽንኦት ይሰጡታል።
ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አሳዛኝ አጋጣሚዎችን ለመቀነስ በየደረጃው የሚሠሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ሺዎችን ከሞትና ከከፋ አደጋ መታደግ ነው፡፡ቢሮው ያወጣው ሪፖርትም አሳሳቢ ለሆነው ለዚህ ማኅበራዊ ጉዳይ ዕልባት ለመስጠት የሚደረገው ጥረት በፖሊስና በሕግ አስከባሪ፣ በከተማው አስተዳደርና በነዋሪዎች ዘንድ በምን መልኩ መቀጠል እንዳለበት የሚያሳይ ምክረ ሐሳብም ይዟል፡፡
በፖሊስና በሕግ አስከባሪ አካላት በዘመቻ የሚደረጉ የቁጥጥር ሥራዎችን ሳያቋርጡ መሥራት፣ ጠጥቶ ማሽከርከር ላይ የሚደረገው የትንፋሽ ፍተሻን አጠናክሮ መቀጠልና ይህንንም በበቂ ለመሥራት የአልኮል መጠን መለኪያ መሣሪያዎች አቅርቦትን መጨመር፣ ተንቀሳቃሽና ቋሚ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎችንና የፍጥነት መለኪያ ራዳሮችን መጠቀም፣ አደጋ ይበዛባቸዋል ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ የመሳሰሉ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ለከተማው አስተዳደር አካላትም እንዲሁ የተሻሻሉ የፍጥነት ገደብ ምልክቶችን በተለያዩ አካባቢዎች እንዲተክሉ ተመክረዋል፡፡
እንደማሳረጊያ
በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ ቁጥር ዕለት ወደ ዕለት የመጨመር አዝማሚያ ስለማሳየቱ የተመዘገቡ ቁጥሮች ይናገራሉ፡፡አንዳንዶች ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ የቻለው የተሸከርካሪ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ይህም ሆኖ ግን ከፌዴራል የትራንስፖርት ባለስልጣን የተገኙ መረጃዎች ይህንን አያሳዩም፡፡
በኢትዮጵያ አንድ ተሽከርካሪ በአማካይ ለ100 ሰዎች ይደርሳል፡፡ኢትዮጵያ በታሪክ ከአፍሪካ አገራት ቀደም ብላ መኪና ለማስገባትና ለመጠቀም ብትችልም በአሁን ሰዓት ያለው የመኪና ብዛት ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑ የተረጋገጠ ሆኗል፡፡
እስካለፈው ዓመት አጋማሽ ድረስ ድረስ በኢትዮጵያ ያለው የመኪና ብዛት 977 ሺ 349 ነው፡፡ይህም ሆኖ የህብረተሰቡ መኪና የመጠቀም ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ በሀገራችን የሚገኘው የተሽከርካሪ ቁጥር በፍጥነት እያደገ መምጣቱ እውነት ነው፡፡
በአሁን ሰዓት አለ ተብሎ የሚገመተው አንድ ሚሊየን ተሽከርካሪ ውስጥ 62 በመቶ የሚሆነው በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ለንጽጽር ያህል የሌሎች አገራትን እንመልክት፡፡ካደጉት አገራት ተርታ የተሰለፈችው ስውዲን ዘጠኝ ሚሊየን ሕዝብ ይዛ ከአምስት ሚሊየን በላይ ተሽከርካሪ ሲኖራት ጎረቤታችን ኬንያ ከ50 ሚሊየን የማይበልጥ ህዝብ ይዛ ከሦስት ሚሊየን በላይ መኪኖች አሏት፡፡ኬንያ በሦስት እጥፍ እንደምትበልጠን ልብ ይሏል፡፡እናም በአጭሩ የአደጋው ቁጥር ማሻቀብ ከመኪና መብዛት ጋር የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩን ልብ ማለት ያሻል፡፡
ከተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ችግር ይልቅ አደጋዎች ከ70 በመቶ በላይ የሚከሰቱት በአሽከርካሪዎች እና በእግረኞች ጥፋት እንደመሆኑ እነኚህ ወገኖች ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ማከናወኑ አደጋን በመቀነስ ረገድ የሚኖረው ድርሻ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
የመኪና መንጃ ፈቃድ ሥልጠና ሥርዓት መፈተሽ፣ የአሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃድ በሙስና እንዳይሰጥ ጥብቅ የመከታተያ መንገዶችን መዘርጋት፣ ጫት ቅሞ እና መጠጥ ጠጥቶ የማሽከርከርን አስከፊነት በተመለከተ ግንዛቤ መስጠትና ህብረተሰቡን የቁጥጥር አካል በማድረግ በአጥፊዎች ላይ የተፋጠነ ዕርምጃ መውሰድ፣ ትርፍ የሚጭኑ የህዝብ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ቁጥጥርን ማጠናከርንና በዚህም ረገድ ህብረተሰቡንም ማሳተፍ፣ የትራፊክ ግንዛቤ የመደበኛ የትምህርት ሥርዓት አካል እንዲሆን ማድረግና ለእግረኞች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥርዓቶች ማከናወን፣ በአጥፊዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት ቆንጣጭ እንዲሆን ማድረግ ወዘተ… ችግሩን ለመቅረፍ ሊያግዝ እንደሚችል ይታመናል፡፡ከምንም በላይ ደግሞ ህብረተሰቡ በትራፊክ ማኔጅመንት ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ መሞከሩ ለተሻለ ውጤት አጋዥ ይሆናል፡፡(ማጣቀሻዎች፡- ኢቲቪ፣ ፋና፣ ሪፖርተር እና አዲስ አድማስ ጋዜጦች፣ የጀርመን ድምፅ፣ ቢቢሲ…)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 24/2012
ፍሬው አበበ