የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጅማሮ የሚቆጠረው ከሰው ልጆች የዘፍጥረት ታሪክ መነሻውን አድርጎ እንጂ ትናንት ተብሎ በሚገለጽ ታሪክ የለውም። ማንኛውም ሕዝብ ሰብዓዊ መብቱና ሉዓላዊ ክብሩ ሊከበርለት ግድ የመሆኑን ያህል ይህንኑ የማይገሰስ ተፈጥሯዊ መብቱን በመጠቀም “ለራሴ ራሴ አላንስም፤ ብቁ ነኝ” በማለት ሙሉ በኩለሄ አዋጅ እያወጀ ብቻነቱን መርሁ ቢያደርግና የማኅበራዊ ተራክቦን ሕግ ቢጥስ እንኳን በራሱ አምሳል የተፈጠረው የሰው ዘር ቀርቶ ተፈጥሮ ራሷ አሜን ብላ አትቀበለውም።
ሕዝብ ከሕዝብ በንግድ፣ በባህል ልውውጥ፣ በጋብቻ፣ በጦርነት፣ በሰላም፣ በትምህርት፣ በተፈጥሮ በረከት ክፍፍል፣ በፖለቲካ ወዘተ… አማካይነት ይገናኛል፣ ይቀራረባል፣ ይዛመዳል፣ ይፋቀራል፣ ይዋለዳል፣ ይጣላል፣ ይታረቃል፣ ይዋሃዳል ወዘተ…። “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚመሰለው በተጓዥ ወንዝ እንጂ በረጋ ኩሬ አይደለም” የሚባለውም ስለዚሁ ነው።
በቴክኖሎጂና በሳይንስ ጥበብ ዓለም ጠባለች፣ ረቅቃለች፣ ሰልጥናለች እየተባለ የሚነገረውም የምድራችን ተፈጥራዊ ወርድና ስፋት እየተሸበሸበና እየተኮማተረ ስለሄደ ሳይሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እየሰፋና፣ እየረቀቀ፣ እየተወሳሰበና እየተጋመደ ከመሄዱ የተነሳ ነው። ሕዝብ ለሕዝብ ሲገናኝ ጥበብና ዕውቀት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ባህልና ቋንቋ ይበዳደራል፣ ይዋዋሳል፣ ይኮራረጃል፣ የዕውቀትና የተሞክሮ ልምድም ይጎለብታል። በዚያው ልክ ዕድገትና ሥልጣኔው እያበበና ፍሬ እያፈራ ይሄዳል።
አለዚያማ ዓለማችን እንደ ትንሽ መንደር ጠባለች እየተባለ የሚነገረው (ምንም እንኳ አባባሉ ብዙ መሻሻል የተደረገበት ቢሆንም) አምስተኛዋ ትልቋ ፕላኔታችን ከ13,000 ኪሎ ሜትር ዲያሜትሯ ተሸብሽባ አንሳለች ለማለት አይደለም። በእቅፏ አቁራ የያዘችውን 70 ከመቶ ያህል ውሃዋንም አፍስሳ ጨርሳለች ማለት አይደለም። ከሜሪኩሪና ከቬነስ ቀጥላ ለፀሐይ ሦስተኛ ጎረቤት የመሆኗን ክብርም በጠብም ሆነ በግጭት ለመልቀቅ አልተገደደችም። የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ማዕከል (NASA) በቅርቡ ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው ከ3800 በላይ ምድራችንን አከል ፕላኔቶችና ከዋክብት መርምሬ አግኝቻለሁ ቢልም የምድራችንን ሞገስና ክብር ይጋፋሉ ተብሎ ግን ምስክርነት አልተሰጠም። እንዲያውም የተቀሩት ታዋቂ ፕላኔቶች በሙሉ የተሰየሙት በግሪክና በሮማዊያን አማልክት ስም ሲሆን፤ ዓለማችን (EARTH) ግን ግብሩ እንኳ ቢቀር ቢያንስ ከስያሜ አንፃር ከዚህን መሰል የባዕድ አምልኮ መታወቂያነት ክብሯን አስጠብቃ ኖራለች።
የሕዝብ ለሕዝብ እንቅስቃሴ ሲፋጠን ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ንግድና ባህል፣ ቋንቋና ዕውቀት ያብባል፣ ይፋፋል፣ ይበለጽጋል። እርግጥ ነው ክፋትና አመጽ፣ ጥፋትና ጦርነት፣ መብትህን ልቀቅልኝና አልለቅም እየተባለም በእኩይ ፍላጎትና አልጠግብ ባይነት ቅራኔ መፈጠሩ ተፈጥሯዊ ነው። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከላይ እንደተመለከተው በተቃርኖ የተሞላ በረከተ መርገም (A Blessings in disguise) ይሉት ዓይነት ባህርይ ቢኖረውም ቅርርቡ ይቅርብን በሚል ስምምነት በአዋጅም ሆነ በግዴታ ሊቆም የማይችል ተፈጥሯዊ ሂደት ነው።
ከጥቂት ዐሠርት ዓመታት በፊት በኮምፒውተር አምራችነቱ በተቀዳሚነቱ የሚጠቀሰው IBM ግዙፍ ኩባንያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማይ ስባሪ የሚያህልና አንድ ትልቅ ክፍል የተለቀቀለት ኮምፒውተር ፈብርኮ በሥራ ላይ ባዋለበት ወቅት የዓለማችን ተመራማሪ ሳይንቲስቶች በውጤቱ በመርካት “ዓለም እንደ አንድ መንደር ጠበበች” የሚል ገለጻ እንዳስተዋወቁ አይዘነጋም።
ውሎ አድሮ ግን ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተርን እና በኬብል የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየተስፋፉ ሲመጡና በየግለሰቦች ቤት አናት ላይ የዲሽ ሣህኖች መሰቀል ሲጀምሩ “ዓለም እንደ አንድ መንደር ጠባለች” የሚለው አገላለጽ አርጅቶ “ዓለማችን እንደ አንድ ቤት ጠባለች” በሚለው ብሂል ተተካ።
የዓለምን እንደ ቤትነት መጥበብ የሚያውጀው መፈክርም ዕድሜው ሊረዝም አልቻለም። ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች (በጭን ላይ የሚቀመጡ ኮምፒውተሮች እንደማለት ነው) ሲፈጠሩ ዓለም እንደ አንድ ቤት መጥበቧ ነፍሶበት “ዓለምን ጭናችን ላይ አስቀምጠን እሹሩሩ እያልን ገበናዋን መበርበር ተቻለ” እየተባለ ተንቆለጳጰሰ።
ይሄው የጭን ላይ ኮምፒውተር ገና ከድክድክ ዕድሜው ሳይላቀቅ በእጅ መዳፋችን ላይ እያስቀመጥን የምንጠቀምባቸውና (Palm Top Computers) ከትልልቅ ኮምፒውተሮች የማይተናነሱት የእጅ ስልኮቻችን በገፍ እየተመረቱ ለዓለም ሕዝብ መሠራጨት ሲጀመር “ዓለም ከጭናችን ከፍ ብላ በእጃችን መዳፍ ውስጥ ገባች” ተብሎ ተሞካሸ። ይሄኛውም ቴክኖሎጂ ገና የለጋ ዕድሜ የልደት ሻማውን ለኩሶ ሳይጨበጨብለት በፊት ከክብሪት ሣጥን ያነሱና በሁለት ጣት የሚያዙ ስልኮች/ኮምፒውተሮች (Fingur Top Computers) ተፈብርከው የዓለምን ጉዳጉድ ገበና መጎልጎል ሲጀምሩ “ዓለም ሁለት ጣታችን ውስጥ ገባች” እየተባለ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከበሮ ይደለቅለት ገባ። ነገ ደግሞ ከልብሳችን አዝራር ያነሱ ኮምፒውተሮች/ስልኮች ሲፈበረኩ ምን ስያሜ እንደሚሰጣቸው ከወዲሁ ከመጨነቅ ለጊዜ ጊዜ መስጠቱ መልካም ይሆናል። “ቦ ጊዜ ለኩሉ!” እንዲሉ። እግረ መንገዴን ግን “ዓለማችን እንደ አንድ መንደር ጠባለች” በማለት ያረጀውን ቢሂል በድፍረት በየሚዲያውና በየስብሰባው የሚናገሩ የሀገሬ ሹማምንትና ግለሰቦች ዓለም ወደ ሁለት ጣት ደረጃ መጥበቧን እንዲረዱና ብሂሉን እንዲያርሙ አደራ አኖራለሁ።
ይሄንን የተራዘመ ትንተና መስጠት ያስፈለገው የሕዝቦች መቀራረብና መዋሃድ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ ለባህልና ቋንቋ መወራረስ፣ ለዕውቀትና ለጥበብ መዋዋስ እንደምን እንዳገዘ ለማሳየት ነው። እርግጥ ነው በሁለት ጣቶቻችን ውስጥ የገባችው ግዙፏ ዓለማችን ለፈጣኖችና ለትጉሃን ሀገራት እንደ ጣት ቀለበት የሥልጣኔ ቃል ኪዳን በመሆን ስታፋቅራቸው፣ ለአንዳንድ ዳተኛና “እንቅልፋም ሀገራት” ደግሞ ቴክኖሎጂውና ሳይንሱ፣ ፖለቲካውና ዲፕሎማሲው እያንገዋለለ ወደ ጎን ስለሚገፋቸው ሁሌም ሕዝባቸው እንዳላዘነ፣ በርሃብና በጦርነት እንደታመሰም ይኖራል። በሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ አይከፈትም ተብሎ የተጠረቀመው የአንዳንድ ሀገራት በር ቴክኖሎጂና ሳይንሱ በግድ እያንኳኳ ማስከፈቱ ስለማይቀር ቀድሞ መንቃቱ ብልህነት ነው።
ለበርካታ ዘመናት የሕዝብ ለሕዝብ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲቋጠርና ሲፈታ፣ ሲተረተርና ሲወሳሰብ፣ ሲሞካሽና ሲንቋሸሽ የኖረው በመደበኛው የመንግሥት ለመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ብቻ እንደነበር ይታወቃል። እያንዳንዱ መንግሥት በተወዳጀውና ልቡ በፈቀደው ሀገር መርምሮና አጣርቶ፣ የጋራ ተጠቃሚነቱን አረጋግጦና ይበጀኛል ብሎ ሲያምንበትም የኤምባሲ ጽ/ቤቶችን በመክፈትና ዲፕሎማቶችን በመመደብ ሲሰራ ዘመናትን አስቆጥሯል። “ሀገር ሲጠብ የኤምባሲ ጽ/ቤት ይሆናል” እየተባለም ሲሞካሽ ኖሯል። ይሄም ሁሉ ውጤት ቢገኝም እንኳን የአንድ ሀገር የኤምባሲ/ቆንስላ ጽ/ቤቶች በየሀገሩ የሚሰጣቸው ከለላና ጥበቃ እንደ አልማዝ የደደረ፣ እንደ ብረት የጠነከረ ነው የሚለው አባባል በዚሁ መከረኛ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች አማካይነት በቀላሉ ስለሚበረበርና ስለሚደፈር ስጋት መጋረጡ አልቀረም።
መደበኛውና መንግሥታዊው የዲፕሎማሲ ሥራ ከዓለም አቀፉ ምህዳር ማሊያውን ሰቅሎ ጭራሹኑ ከመጫወቻው ሜዳ በቀላሉ ይሰናበታል የሚለውን “ሟርት” ለጊዜው ትተን ስጋቱን ንቆ ማለፍ እንደማይገባ ግን የዘርፉ ጠበብት መተንበያቸው አልቀረም። የትንቢቱ መፈጸም አለመፈጸም ክርክር ለጊዜው ይቆይና ወደ ተሻለው ሃሳብ ማቅናቱ ይበጃል።
ዛሬ ዛሬ መንግሥታት ስለ አንድ ሀገር በወቅታዊ ወይንም በአሳሳቢ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ በዳጃፋቸው ጽ/ቤቱን የተከለውን ሀገር አምባሳደር ወይንም ቆንስላ ጠርተው ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በሚጠይቁት ቅጽበት እንኳንስ ለጠያቂው መንግሥት ይቅርና በግለሰቦችም ደረጃ መረጃው በሮኬት ፍጥነት ቀድሞ ስለሚለቀቅ ዲፕሎማቱ ከጠሪው ቢሮ ሳይደርስ መረጃው ቀድሞ ዓለምን ያዳርሳል።
ድምጻዊው ማህሙድ አህመድ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት፤
ያ የተደነቀው ተብሎ በራሪ፣
ገጠር ተሰደደ አሁን የታል ጋሪ።”
ብሎ እንዳንጎራጎረው ለዘመናት በመርከብ፣ በባቡር፣ በአውሮፕላንና በፈጣን ጄቶች በመጓጓዝ ሲሰራበት የኖረው መንግሥታዊው የሕዝብ ለሕዝብ መደበኛ ዲፕሎማሲ ዕድሜ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እንጂ ዘርፉ በተለያዩ ስልቶች እየተሻሻለ መጥቶ አጋሮቹን አበራክቷል።።
ይሄ መደበኛ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ እንደተጠበቀ ሆኖ የህትመት ውጤቶች፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች፣ ባህላዊና ስፖርታዊ ተልዕኮዎች፣ ዘመን ወለዶቹ የማሕበራዊ ትስስር መረቦች፣ የቱሪስትና የትምህርት ጉዞዎች ወዘተ… የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ መከወኛነት እንደ አማራጭ መታየት ከጀመሩ ሰነባብቷል።
ከዕድሜ ጠገቡ፣ ከነባሩና ከልማዳዊው (Traditional) መንግሥታዊ ዲፕሎማሲ ጎን ለጎን ዘመኑ የሚፈቅደው መልከ ብዙ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ለብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንዳለው ከታመነበት ሰነባብቷል መባሉ አለምክንያት አይደለም። የአለባበሳቸው ፕሮቶኮል ከተጠበቀ፣ የንግግር ቋንቋቸው ከተመጠነና የእርምጃቸው ፍጥነት ከተመጠነው መንግሥታዊ ዲፕሎማቶች ጎን ለጎን በየሀገሩ ካሉት ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተውጣጥቶ የሚካሄደው የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ብዙ ትኩረት እየሳበ መምጣቱን ለመመስከር ነው።
የስፖርትና የባህል ልዑካን፣ የመገናኛ ብዙኃን ባልደረቦች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ሰልፈኞች፣ ነጋዴዎችና ቱሪስቶች፣ ምሁራንና በየዓለማቱ የተበተኑ የዲያስፖራ ዜጎች በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚጫወቱት ሚና የላቀ ውጤት ሊያስገኝ ስለመቻሉ መንግሥታት በአሜንታ ካጸደቁም ቆይቷል።
የሀገሬ ኢትዮጵያ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ተልዕኮ በጠየመና በደበዘዘ መልኩ ብዥታ እንደሸፈነው መተግበር ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ መንግሥታዊ ዕውቅና ተሰጥቶት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት በኩል በይፋ እንቅስቃሴ መደረግ የተጀመረው ከአምስት ዓመታት በፊት ነበር። ከታህሣስ ሰባት እስከ 11 ቀን 2007 ዓ.ም ከ70 በላይ ልዑካንን ያካተተው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በግብጽ ያደረገው ጉዞ በመጀመሪያነቱና በአብነት ይጠቀሳል። በመቀጠልም ከተለያዩ የማኅበረሰብ አባላት የተውጣጡ ቡድኖች ያሉበት ሁለተኛው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በዚያው ዓመት ጉዞ ያደረገው ወደ ሱዳን ካርቱም ነበር። በእነዚህ ሁለት ሀገራት የተደረገው ጉዞ ዋነኛ ዓላማ በዓባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት ለየሀገራቱ መንግሥታትና ሕዝቦች ለመግለጽና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፋሰሱን ሀገራት በጋራ ይጠቅም ካልሆነ በስተቀር ጉዳት እንደማያስከትል “ሕዝባዊ መተማመኛ” ለመስጠት ነበር።
በጉብኝቱ ወቅት በተደረጉት በርካታ የጋራ ውይይቶች የግብፁን ፕሬዚዳንት አብድል ፈታህ ኤል ሲሲን ጨምሮ ከበርካታ የየሀገራቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የፓርላማ አባላት፣ ነጋዴዎችና ምሁራን ጋር ውይይቶችና የሀሳብ ለውውጥ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ ጉዞ ያደረገው ከሰኔ 17 እስከ 20/2010 ዓ.ም በጅቡቲ ነበር። የጅቡቲው ተልዕኮ ዋነኛ ዓላማ የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትሥሥር ይበልጥ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ጉዳይ ለመነጋገርና ለመመካከር ነበር። በጉብኝቱም ወቅት ከጂቡቲው ፕሬዚዳንት ከክቡር ኢስማኤል ኦማር ጊሌ እና ከተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችና ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር በርካታ ውይይቶችና ጉብኝቶች ተደርገዋል። በየሀገራቱ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ጋር የነበረው ቆይታም እጅግ መልካም የሚሰኝ ብቻ ሳይሆን በእነርሱ በኩል ይጠየቁና ይነሱ የነበሩ መሰረታዊ ጥያቄዎችና ችግሮች ከየሀገራቱ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር አንዳንድ ምላሾች መሰጠታቸው ከተገኙት ስኬቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በጉብኝቱ ወቅት ከልምድና ከተሞክሮ ማነስ የተነሳ የሚታረሙና መሻሻል የሚገባቸው አንድንድ አጋጣሚዎች የተስተዋሉ ቢሆንም በአጠቃላይ ሲታይ ግን የሦስቱም ሀገራት ጉብኝቶች የተሳኩ ነበሩ ማለት ይቻላል። አራተኛው ጉዞ የተደረገው በዚሁ ሣምንት ከህዳር 16 – 20/ 2012 ዓ.ም በአፍሪካዊቷ ሀገር በዩጋንዳ ሲሆን፤ ስለጉብኝቱ አጠቃላይ ውጤት በሚቀጥለው ጽሑፌ ዝርዝሩን ለማቅረብ እሞክራለሁ። በአራቱም ሀገራት ጉዞዎች የተሳተፉት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት በሙያቸውና በተጽእኖ ፈጣሪነታቸው ታምኖባቸው የተመረጡ ስለነበሩ ኃላፊነታቸው “ሀገርን በጫንቃ የመሸከም ያህል” የሚከብድ መሆኑ በጋራ ያስማማል።
ኢትዮጵያ ልጆቿን ወደ አራቱ ሀገራት በመላክ ሰላማዊና የትብብር ድምፅዋን ማሰማቷ እንደተጠበቀ ሆኖ የግብፅና የሱዳን መንግሥታትም የየሀገራቸውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖችን ደጋግሞ በመላክ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ሥር እንዲሰድና የሺህ ዘመናት ጉርብትናው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን ሚና ተጫውተዋል። በተለይም ለሁለተኛ ጊዜ ከህዳር 11 እስከ 14/2012 ዓ.ም ሀገራችን የተገኘው የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የተልዕኮው ዋነኛ ዓላማ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ሱዳንን በገጠማት ፈተና ሳይሰለቹ ሀገራዊ ችግራቸው እንዲቃለል ለተጫወቱት ሚና ምስጋና ለማቅረብ ዓላማ ያደረገ ነበር። በጉብኝታቸው ወቅትም ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፓርላማችን አፈ ጉባዔ ከተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን ከክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ውይይቶችን ያደረጉ ሲሆን፤ የአንድነት ፓርክንና ሌሎች የልማት ተቋማትንም ለመጎብኘት ችለዋል።
ሁልጊዜም አዳዲስ ጅምሮች ከአንዳንድ እንከኖችና ቅንጅቶች ነጻ ናቸው ማለት ባይቻልም የተደረጉት ሙከራዎች በሙሉ አበረታች ውጤቶች እንደተገኙባቸው መገንዘብ አያዳግትም። ለወደፊቱም ቢሆን ዘመኑ ግድ ስለሚል ብቻ ሳይሆን በቅቡልነቱም ዓለም አቀፍ አሜኔታ ባተረፈው መሰል የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዞ በተወሰኑ ሀገራት ብቻ ከመታጠር አልፎ አድማስን በማስፈት መሥራት እንደሚገባ ማሳሰቡ መልካም ይሆናል።
እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ ዲፕሎማት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ስፖርተኛው በሚውልበት ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ፣ የጥበብ ባለሙያዎች በሚጋበዙባቸው ሀገራት፣ ነጋዴው በሚንቀሳቀስባቸው ዓለም አቀፍ ገበያዎች፣ የመደበኛና የኢመደበኛ የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች በሚያሰራጯቸው መረጃዎችና ሃሳቦች፣ የባህልና የቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻዎች በሚደርሱባቸው የዓለም ክፍሎች፣ ተማሪዎችና የዲያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትም እንዲሁ የሀገራቸውን ስምና ክብር ከፍ አድርገው እንዲያጎሉ የዜግነት አደራ አለባቸው።
ለሀገራቸው ሉዓላዊነት መከበር፣ ሰላምና ብልፅግና ዋቢ ሆነው እንዲቆሙም ግዴታ አለባቸው። ኢትዮጵያ ከፍ አድርጋ ለልጆቿ የምታስተላልፈው የአደራ ጥሪ ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 24/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ