በሀገራችን የጤና ጠንቅ በመሆን አሁንም ድረስ የሚታወቀው ኤች አይቪ /ኤድስ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፤ እናትና አባትን ያለጧሪ ህፃናትን ያለአሳዳጊ አስቀርቷል፡፡ በሀገር ልማት ላይም ደንቃራ እስከመሆን ደርሶም ነበር፡፡ ይህን ገጽታ ለመቀየር በተደረገው ርብርብ ከኤች አይቪ ጋር ተያያዞ ይደርስ የነበረውን የሞት መጠን እ.ኤ.አ በ2000 ከነበረበት 83 ሺህ በ2017 ወደ 15 ሺህ 600 ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ የበሽታውን ወረርሽኝ ለመግታት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የተገኘውን ድል ተከትሎ የተፈጠረው መዘናጋት ግን የበሽታው ስርጭት እንዲያንሰራራ ማድረጉ ይገለፃል፡፡ ነፃ የኤች አይቪ ምርመራ፣ በበሽታው ስርጭትና አሳሳቢነት ላይ እየተካሄዱ የሚገኙ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች፣ ቫይረሱ ያለባቸው ነፍሰጡሮች ከኤች አይቪ ነፃ የሆነ ህፃን እንዲገላገሉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች በቫይረሱ የመያዝ ዕድልን እያጠበበው ቢመጣም፤ አሁንም በሽታው ሥጋት እየሆነ ይገኛል፡፡
በሽታው በእርግጥም ሥጋት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2018 በወጣ መረጃ መሰረት 649 ሺ የሀገሪቱ ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል 12 በመቶው ህፃናት ናቸው፡፡ ሀገሪቱ በዚሁ ዓመት ብቻ 11 ሺ ሰዎችን በቫይረሱ ሳቢያ በሞት አጥታለች፡፡ በየዓመቱ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም 23 ነው። ይህም በቀን 64፣ በወር እንድ ሺ 915 አካባቢ በሰዓት ደግሞ 3 ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ መረጃው ይጠቁማል፡፡
ይህ አሀዝ በቀላሉ የሚታይ ሊሆን አይገባም፡፡ ችግሩ ደግሞ እየተከሰተ ያለው መከላከል የሚያስችል ተሞክሮ እያለ ነው፡፡ ቫይረሱን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል በተከናወኑ ተግባሮች ለውጥ ማምጣት እንዲሁም በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎች የሚደረገው የህክምና አገልግሎትም ዜጎች እንደቀደመው ጊዜ በቫይረሱ ሊያዙ እና ሊሞቱ የሚችሉበትን ዕድል ትርጉም ባለው መልኩ ላቃለለች ሀገር ይህም ጥሩ ዜና አይደለም፡፡
እ.ኤ.አ በ2016 በተካሄደ ጥናት ኤች አይቪ ጎጂ መሆኑን እያወቁ የሚንቀሳቀሱ ሴቶች 20 በመቶ፣ ወንዶች ደግሞ 38 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሴቶች እና ወንዶች የእድሜ ክልል ደግሞ ከ15 እስከ 49 ባለው ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ አሀዝ በራሱ ግንዛቤ ላይ በስፋት መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑ አመላካች ነው፡፡ ተሞክሮዎችን በመቀመር እና የተለያዩ ስልቶችን በመከተል ዜጎችን ከመዘናጋት ለማውጣት አሁንም በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡
መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል መጠንቀቅ ይገባል ምክንያቱም ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እያንሰራራ ይገኛል፡፡ እርግዝናን በኮንዶም ጭምር መከላከል ሲቻል በሴቶች በኩል የእርግዝና መከላከያ በተለይም ከግብረ ሥጋ ግንኙነት በኋላ የሚወሰደውን መጠቀም በስፋት እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህም ኤች አይቪ በስፋት ሊተላለፍ የሚችልበት ዕድል እየተፈጠረ ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡ ይህን ችግር መፍታት ደግሞ የሚቻለው ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ በስፋት በመሥራት ነው፡፡
የመከላከል እና መቆጣጠሩ ሥራ በእርግጥ ሀብት ይፈልጋል፡፡ በሽታው ተስፋፋቶ እንዳለፈው ጊዜ የበርካታ ዜጎችን ህይወት በስፋት ከመንጠቁ፣ አዛውንቶችና ባልቴቶችን ያለጧሪ ህፃናት ያለአሳዳጊ ከማስቀረቱ፣ ዜቶችንም ከአምራችነት ከማስወጣቱ እንዲሁም በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎች መድሃኒት መግዣ ብዙ ቢሊዮን ብር ለመመደብ ከመዳረግ በፊት ለሚከናወን የመከላከልና መቆጣጠር ተግባር በመንግሥት በኩል በቂ በጀት መመደብ ይኖርበታል፡፡
ህዝቡንም ለግንዛቤ ማስጨበጥም ሆን ለፋይናንስ ምንጭነት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለጋሾች ትኩረታቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሊያደርጉ ስለሚችሉ እንዳለፈው ጊዜ ለኤች አይቪ መከላከል እና መቆጣጠር የሚውል በቂ ገንዘብ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም የህብረተሰቡን አቅም በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ህብረተሰቡ በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎች የሚያደርገው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ለመከላከልና ለመቆጣጠሩ ሥራም ድጋፍ ሊያደርግ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት በኤች አይቪ ኤድስ ላይ በትኩረት በመሥራት በቫይረሱ የመያዝ ሁኔታን እ.ኤ.አ በ2020 በ50 በመቶ እንዲሁም በ2030 ደግሞ ቫይረሱ የህዝብና የሀገር ሥጋት እንዳይሆን ለመሥራት ማቀዱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህን ለማሳካት ህዝቡ ከመንግሥት ጎን መቆም ይኖርበታል፡፡
ህዝቡ ኤች አይቪ ኤድስ እንዳለፈው ርብርቡ ግንዛቤውን በማሳደግ ራሱን እና ሌሎችንም በመጠበቅ ለመከላከልና መቆጣጠረው የሚያስፈልገውን ሀብት በማዋጣት ጭምር መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ኤች አይቪ ላይ የሚኖር መዘናጋት የሚያስከፍለውን ዋጋ ከወዲሁ በመገንዘብ መንግሥት ህብረተሰቡን ይዞ ከዚህ ያስመዘገበው ውጤት ለመድገም በትኩረት መሥራት ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2012