ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአገራት መካከልም ሆነ በአገር ውስጥ ለሚነሱ ግጭቶች ስረ መሰረት ኢኮኖሚ ነው። ከዚህ በፊት ያስተናገድናቸው የዓለም ጦርነቶችን ስንመለከት ቀጥተኛ መነሻቸው ፖለቲካዊ መልክ ቢኖረውም ዋነኛ ስረ መሰረታቸው ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር ዓላማ እንዳለው ይታወቃል። የቅኝ ግዛት ዋነኛ ዓላማም ኢኮኖሚውን መቆጣጠር ነው። በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አገራት የተከሰቱ የርስ በርስ ግጭቶችም ዋነኛ መንስኤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው።
ኢኮኖሚ ለግጭት መነሻ የሚሆንባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ። መንስኤ ከሚሆኑ ምክንያቶች አጠቃላይ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ ኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ የተፈጥሮ ሃብትን ለመቆጣጠር የሚደረግ ሩጫ፣ በህገወጥ መንገድ ለመበልፀግ የሚደረግ ፉክክር፣ ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ግጭቶች የብሄር፣ የሃይማኖት ወይም ሌላ የፖለቲካ ቅርጽ ይዘው ሊከሰቱ ይችላሉ።
በአገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከመሬት ላራሹ ጀምሮ የተነሱ አመፆችና በኋላም የተከናወኑ የትጥቅ ትግሎች የተለያዩ ፖለቲካዊ ስያሜ ቢሰጣቸውም ዋነኛ ስረ መሰረታቸው ግን የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው።
ባለፉት 28 አመታት ኢህአዴግ እነዚህን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታት የሄደባቸው መንገዶች በመጠኑም ቢሆን መረጋጋትን እየፈጠረ ቢሄድም ችግሮቹን ሙሉ ለሙሉ መፍታት ባለመቻሉ እና ቀስ በቀስም በመልካም አስተዳደር ችግሮችና በሌብነት መስፋፋት ምክንያት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍሉ በመጥፋቱ ግጭቶች እየበረቱ ሊሄዱ ችለዋል። በመጨረሻም እነሆ አሁን ለመጣው ለውጥ እርሾ ሆኗል።
ለውጡን ተከትሎ መንግስት የኢኮኖሚ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን ቢያደርግም አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ፊቱን ወደኢኮኖሚው እንዳይመልስ የሚያደርጉ ፖለቲካዊ ችግሮች አልጠፉም። በተለይ እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ብሎም የህግ የበላይነት እየተሸረሸረ መምጣት አሁንም ኢኮኖሚው በሚፈለገው ልክ እንዳይጓዝ ትልቅ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል። ያም ሆኖ ግን መንግስት የኢኮኖሚ ጉዳይ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።
የኤፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2012 የጋራ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ትኩረት ካደረጉባቸው ውስጥ አንዱ የኢኮኖሚ ጉዳይ እንደነበር ይታወሳል። ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው በያዝነው በጀት አመት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በኑሮ ውድነት ለችግር እንዳይጋለጡ ለማድረግ መንግስት የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችን ከውጭ በማስገባት ገበያውን ለማረጋጋት እንደሚሰራ የገለፁ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎንም ህገወጥ ንግድን በመቆጣጠር የዋጋ ንረቱ እንዳይባባስ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
መንግስት የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ስራዎችን መጀመሩ የሚታወስ ነው። በተለይ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመንደፍ የጀመረው ጥረት አገሪቱ ያለባትን የኢኮኖሚ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሆን ምሁራን ይገልጻሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የጀማመራቸው ስራዎችም ተስፋ ሰጪዎች ናቸው።
ለአብነትም የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበውና በእያንዳንዱ ቤት ተደራሽ የሚሆነው ግዙፍ የዳቦ ፋብሪካ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው። ከዚህም ባሻገር በቅርቡ በአማራና በኦሮሚያ የሚገኙ ባለሃብቶች በመቀናጀትና ወረትን በማሰባሰብ ከአገርም አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የስራ እድሎችን የሚፈጥሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመክፈት ያደረጉት ምክክር ተስፋ ሰጪ ነው።
ይሁን እንጂ እነዚህ ተስፋ የሚያጭሩ የእድገትና የብልጽግና መሰረቶች እውን የሚሆኑት ሰላምና መረጋጋት ሲፈጠር ነው። በተለይ ሰላም ሰፈነ ተብሎ ሲታሰብ በድንገት የሚያገረሹት ግጭቶችና ጥለው የሚያልፉት ጥቁር የሞትና የሃብት ውድመት አሻራ በዘላቂነት ካልቆመ ብልጽግናን ማምጣት አዳጋች በመሆኑ ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ለኢኮኖሚው ትልቅ መደላድል መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ከዚህም ጎን ለጎን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የህግ የበላይነት የሚሰፍንበትና ባለሃብቱም ሆነ መላው ህብረተሰብ በሁሉም ስፍራ እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ የሚሰራበት፣ በዚህም ሰፊ የስራ እድሎች የሚፈጠሩበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት። ይህ ሲሆን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይፈታሉ፤ ብልጽግናም እውን ይሆናል።
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2012