አዲስ አበባ፡- በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ ትናንት በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚታዩ ችግሮችና በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ከተቋማቱ ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በዕለቱ በተቋማቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችንና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በሚመለከት መወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የሚኒስቴሩ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ጫኔ እንዳሉት፤ በተቋማቱ ውስጥ የትምህርት ጥራት፣ ደንብና መመሪያ ጠብቆ ያለመሥራት ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡
ከትምህርት ጥራት ችግሮች መካከል በርቀት ትምህርት ዘርፍ ዕውቅና ከተሰጣቸው ማዕከላት ውጭ በገጠር ወረዳዎች ቲቶሪያል በማይሰጥበት ሁኔታ ትምህርት መስጠት፣ ተማሪዎች ለፈተና ሲቀመጡ መፅሐፍ እያገላበጡ መሥራት፣ በከፍተኛ ደረጃ መኮራረጅና በቡድን መሥራት በዚህም የውጤት ግሽበት መታየት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቂ ቤተ መፅሐፍት ቤተ ሙከራ የመሳሰሉት ግብዓቶች ሳይሟሉ የትምህርት ተቋም መክፈትም በጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውን ባለሙያው ያመላከቱት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ህግና መመሪያን ተከትሎ አለመሥራትም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ችግር እየሆነ መምጣቱን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራም ከፍቶ ተማሪ ሳያስጨርሱ መልሶ መዝጋት፣ የተፈቀደውን የትምህርት ኮርስ ተማሪዎች ሳያጠናቅቁ ዲግሪ መስጠት፣ ተማሪዎች ማስረጃ ሲጠይቁ ፈተናህ ጠፍቷል በሚል እንደገና ተጨማሪ ገንዘብ ማስከፈል፣ ያልተፈቀደ የትምህርት ፕሮግራም ከፍቶ ማስተማር የመሳሰሉት ከችግሮቹ መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው ከከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ተገቢው ድጋፍና ክትትል እንደማይደረግላቸው፣ ከፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ጋር ተያይዞም ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግርና ሙስና መኖሩን፣ እንዲሁም በርካታ የማያሰሩ አዋጆችና አሰራሮች መኖራቸውን እንደ ችግር አንስተው እንዲስተካከልላቸው ጠይቀዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ በበኩላቸው በባለሙያ እጥረት ምክንያት አሁን ያሉት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሙሉ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የጎደላቸውን ግብዓት እንዲያሟሉ በቅርብ ተከታትሎ ድጋፍ አለማድረጉን አመላክተዋል፡፡
የኤጀንሲውን የሰው ኃይል ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የድጋፍና ክትትል ማዕቀፍ በቅርቡ ተዘጋጀቶ የተጠናቀቀ መሆኑንና በውይይት ዳብሮ ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የኤጀንሲውን አሰራር በተመለከተ የቀረቡትን ችግሮች ለመፍታትም በቀጣይ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግና ችግሮቹም ካሉ ለማስተካከል አጠቃላይ የአሰራር ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው፤ በዘርፉ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበር በቅንጅት የሚሠሩበት የአጋርነት ማዕቀፍ በማዘጋጀት በሥራ ላይ እንዲውል የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡
አላሠራ ያሉ አዋጆች መመሪያዎች ተሻሽለው እንዲከለሱ በማድረግ ሥራ ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ሊያስጠብቁ የሚችሉ ስታንዳርዶች ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ በማዘጋጀት በሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
በይበል ካሳ