በአገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጪ የሚገቡ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ኬሚካሎች በአገር ውስጥ ተከማችተው እንደሚገኙ ይታወቃል። አንዳንዱ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ሌላው ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሰው ልጆች መገልገያነት ጥቅም ላይ እንዳይውል በዓለም የጤና ድርጅት የታገደ ነው። እንደዚህ አይነቱ ለሰው ልጅ ጤናም ሆነ ለአካባቢ አደገኛ የሆነ ኬሚካል በማን እጅ ? ምን አይነት? ምን ያክል መጠን ያለው ኬሚካል በአገር ውስጥ አለ የሚለውም በውል አይታወቅም።
እንዲሁም ማን ምን አይነት ኬሚካሎችን በምን ያህል መጠን ወደ አገር ውስጥ አስገብቷል፤ ወይም ያስገባል የሚለውም በሀገር ደረጃ በደንብ ተለይቶና ክትትል ተደርጎበት የተሰነደ መረጃ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይሄ የሚያሳየው ምንም አይነት ኬሚካል ማንኛውም ተቋም ሲያስገባ የሚከታተለው፣ የሚቆጣጠረው እና የመጠቀሚያ ጊዜው ሲያልፍም የሚያስወግደው ሀላፊነት ያለው ተቋም የሌለ መሆኑ ነው። ይህም በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል። ስለዚህ ይህንን ስራ ሊሰራ የሚችል ባለቤት መኖር አለበት።
የአካባቢና አየር ንብረትና ለውጥ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የቁጥጥር እና የክትትል ስራውን ለማድረግ በተንቀሳቀሰበት ወቅት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ከሀያ ዓመት በፊት ወደ ሀገር ቤት የገባ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የተመረተ 1ሺ400 ቶን ዲዲቲ እንዲሁም 20 ቶን ነባር የትራንስፎርመር ዘይት መኖሩን አረጋግጧል።
ይህንን ማስወገድ የተቋሙ ሀላፊነትና ተግባር ባይሆንም በሀገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት በውጪ ሀገር ለማስወገድ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል። ማስወገጃ ግምታዊ ወጪው ከአራት ነጥብ ዘጠኝ እስከ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ዶላር የሚደርስ መሆኑንም ገልጿል።
ይሄ ለሰው ልጆች እንዲሁም ለአካባቢ ከፍተኛ ጠንቅ ነው። የሚወገደውም በውጪ ሀገር ነው። እንደእነዚህ አይነት እና ሌሎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ኬሚካሎች ለማስወገድ ሀገሪቱ በዓመት 20 ሚሊየን ዶላር ታወጣለች። ይሄ ትልቅ የሀገር ሀብት ነው። ይህንን ሀብት ለሌሎች የልማት ስራዎች ማዋል ቢቻል ለምሳሌ በአንድ ሚሊየን ዶላር አሁን ባለው የገንዘብ ምንዛሬ (30 ሚሊየን ብር) አንድ ትምህርት ቤት መገንባት ቢቻል በሃያ ሚሊየን ዶላር ሀያ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ማስገንባት ይቻላል።
ወይም ደግሞ ሁለት እጅግ በጣም ዘመናዊ ሆስፒታሎችን ማስገንባት ያስችላል። በአንድ ደሀ ሀገር ይህንን ያክል ወጪ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበትን ኬሚካል ለማስወገድ ማውጣት “በቡሀ ላይ ቆረቆር “እንደማለት ይሆናል።
የኬሚካሉ ማስወገጃ ጊዜ እየዘገየ በመጣ ቁጥር፣ ቀጣይነት ያለውና በፍጥነት ማስወገዱ ሳይቻል ሲቀር ደግሞ የኬሚካሉ አደገኛነት እያየለ ለማስወገጃ የሚወጣው ወጪም እየናረ ይሄዳል። ያም ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ በተቋም ደረጃ በባለቤትን የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ኬሚካሎችን የሚያስወግድ ተጠያቂ ተቋም አለመኖሩ እጅግ አሳሳቢና አስገራሚም ጉዳይ ነው።
በቀጣይም አገር ለከፍተኛ ወጪ እንዳትዳረግ፣ በተከማቸ ኬሚካል ምክንያት የከፋ አደጋም እንዳይገጥም አገር አቀፍ የኬሚካል ልየታና ቆጠራ ማድረግ ይገባል። ሊያስወግድ የሚችል ህጋዊ ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል። እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥር መስመሩን ማጠናከር ይገባል።
አሁን ባለው ሁኔታ ግልጽ በሆነ መልኩ በየተቋማት ተከማችቶ የሚገኝና የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች የሚያስወግድ አካል በግልጽ የተቀመጠ እና ስራውን የሚሰራ ተቋም አለመኖሩ ትልቅ ክፍተት ነው። በመሆኑም መንግስት የጉዳዩን ክብደት በመገንዘብ ህጋዊ ባለቤት ሊሰጠው ይገባል። ተጠያቂነት ያለው አሰራርም ሊሰፍን ይገባል።
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2012