የሀገራችን ግብርና በተስፋና በስጋት ውስጥ ይገኛል። በአንድ በኩል ለግብርና ሥራው ትኩረት በመሰጠቱና የ2011/2012 ምርት ዘመን የተሳካ ቅድመ ዝግጅት በመደረጉ እንዲሁም ለእርሻ ሥራ አመቺ የሆነ የክረምት ዝናብ ስርጭት የዘንድሮውን የምርት ዘመን የተሻለ ምርት እንዲጠበቅ አድርጎታል። ከዚሁ በተጻራሪ ደግሞ አየር ጠባዩ ለግብርና ስራው አመቺ የሆነውን ያህል ለአንበጣ መንጋ፤ለግሪሳ ወፍና ልዩ ልዩ ሰብል አጥፊ ተባዮች መራባት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብም በደረሱ ሰብሎች ላይ ስጋት ፈጥሯል።
የ2011/2012 የሰብል ዘመን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የመጨረሻው ዓመት ነው። ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት የተንጠባጠቡ ስራዎችን ለማካካስ ርብርብ የተደረገበት ዓመት ነው። ለአርሶ አደሩ የግብዓት አቅርቦት በስፋት ከመሰራጨቱም በተጨማሪ ለዘመናዊ የግብርና ሥራ መሰረት በሚጥል መልኩ በሀገሪቱ ካሉ 830 ወረዳዎች ውስጥ በ422ቱ በኩታ ገጠም ማሳ ገበያ መር የእርሻ ልማት ተግባራዊ የተደረገበት ዓመት ነው። የዝናብ ስርጭቱም ለግብርና ሥራ አመቺ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዘንድሮ ከ382 ሚሊዮን እስከ 406 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንዲጠበቅ አድርጎታል።
የዝናቡ ስርጭትና የሙቀቱ ሁኔታ ለእርሻ ሥራው አመቺ የሆነውን ያህል በዛኑ መጠን ለልዩ ልዩ ተባዮችና የሰብል በሽታዎች መፈልፈልና መራባት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።በተለይም ለበረሃ አንበጣ ፤ለግሪሳ ወፍ፤ ለስንዴ ዋግ፤ለመጤ የበቆሎ በሽታና ለሌሎች ተባዮች የተመቸ ሁኔታ ተፈጥሯል።ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ባልተቋረጠ ሁኔታ ከየመንና ከሶማሊ ላንድ በኩል የአንበጣ መንጋ ወደ ሀገራችን ገብቷል።
የበረሃ አንበጣው በትግራይ፤በአፋር፤በሶማሌ፤በአማራ ክልሎችና በድሬዳዋ ተከስቷል። የግሪሳ ወፍ ደግሞ በአፋርና ሸዋሮቢት ተከስቷል። እነዚህን የሰብል ጠንቆች ለመቋቋም በአራት አውሮፕላን በመታገዝ ከ96 ሺህ ሊትር በላይ የኬሚካል ርጭት በመደረጉና ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ሌሎችም ተያያዥ ስራዎች በመሰራታቸው በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሳያይደርስ ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል።
ይሁን እንጂ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ አሁንም ከባድ ስጋት ነው።በሀገራችን በተለምዶ እንደሚታወቀው ከጥቅምት እስከ ጥር ድረስ የበጋ ወር ሲሆን በዚህ ወቅት በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ልዩ ልዩ ሰብሎች ለአጨዳ የሚደርሱበት ወቅት ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ወሳኝ ወቅት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ተከስቷል።የብሄራዊ ሜትሮሎጂ የአየር ሁኔታ ትንበያ እንደሚያመላክተውም ለዝናብ መፈጠር ምክንያት የሚሆኑ የሜትሮሎጂ ክስተቶች ከሰሜን ህንድ ውቅያኖስ እርጥበት አዘል ንፋስ ያለማቋረጥ እየገባ በመሆኑ መላው ሀገሪቱን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ እንደሚቀጥል ይታመናል። በአንዳንድ አካባቢዎች የመደበኛ ያህል በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከመደበኛውም ከፍ ያለ ዝናብም እንደሚኖር ይጠበቃል ።
ይህ ሁኔታ ከባድ ስጋት እና አደጋ የሚፈጠር ነው። በተለይም የደጋና የቆላ ጥራጥሬዎችና ሰብሎች ለአጨዳ የደረሱ ከመሆናቸው አንጻር ዝናቡን ቀድመን ሰብሎችን መሰብሰብ ካልቻልን በጥራትም ሆነ በመጠን የከፋ ጉዳት ይደርሳል። እስካሁንም ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ መሰብሰብ የቻልነው 5ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተዘራውን ሰብል ነው። ይህም በመቶኛ ሲሰላ 48 በመቶ ብቻ ነው።
ይህም ማለት ከግማሽ የዘለለው የሰብል ምርት ገና አልተሰበሰበም።ስለዚህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ እንዲኖረው በማድረግ ሰብሎችን የማሰባሰብ ሥራ ማከናወን ካልተቻለ ቸግሩ የከፋ ይሆናል። ስለዚህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት የደረሱ ሰብሎችን በማጨድና ወደ ጎተራ በማስገባት ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012