መንግስት የዜጎቹን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለበት።በምርጫም ይሁን በሌላ መንገድ ወደ ስልጣን የወጣ ማንኛውም መንግስት እመራቸዋለሁ የሚላቸውን ዜጎች ስላምና ደህንነት መጠበቅ፣ የኑሮ ውድነት ማቃለል፣ መልካም አስተዳደር በማስፈን ፈጣን አገልግሎት መስጠት፣ ወዘተ ይጠበቅበታል።ነገር ግን ይህንን ተግባር ብቻውን ሊወጣው አይችልም።
በሃገራችን በአሁኑ ወቅት የሰላም፣ የኑሮ ውድነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን አለመሆን፣ የስራ አጥነት፣ ወዘተ ችግሮቸ አሉ።እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግስት ትልቅ ኃላፊነት ቢኖርበትም መላው ህዝብ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች፣ ባለሃብቶች፣ ታዋቂ ሰዎች ወዘተ የድርሻቸውን ካልተወጡ ውጤታማ መሆን አይቻልም።ስለሆነም ሁሉም ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
መንግስትና ህዝብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።ስለሆነም መንግስት ስራውን ሲሰራ ህዝብም አብሮት መሆን አለበት።ህዝቡ ችግር ነጋሪ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄው አካል መሆን ይገባዋል።ህዝብ የመፍትሄ ሃሳቦችን ከማመንጨት በተጨማሪ ለመንግስት ተገቢውን መረጃ በተገቢው ወቅት በመስጠትም ሆነ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ተባባሪ በመሆን ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።ይህን ማድረግ ካልቻለ መንግስት ብቻውን የፈለገውን ስራ ቢሰራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።ስለሆነም ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት መወጣት አለበት።
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰተው የሰላም መደፍረስ መንስኤና ተሳታፊዎችም የአካባቢው ሰዎች ናቸው። እነዚህን ሰዎች ደግሞ የአካባቢው ህዝብ በቀላሉ ሊለያቸው ይችላል። ነገር ግን ሰላም ማስከበር የመንግስት ስራ ብቻ ነው ብሎ በማሰብ ችግሮች ሲፈጠሩና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት እስከሚያስከትሉ ድረስ ቆሞ ይመለከታል።
በመጨረሻም መንግስትን ያማርራል።ይህ ተገቢ አይደለም። ቢሆንም ቀድሞ ትንሽ ጥረት አድርጎ የጎደለውን መንግስት ሳይሞላ ሲቀር መውቀስ ተገቢ ነው። ስለሆነም ለሰላማችን በቅርበት መስራት ያለብን ራሳችን ነን። ቢያንስ ለግጭት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ቀድመን በማወቅና በማቃለል ኃላፊነታቸን ልንወጣ ይገባል።
ሌላው የሃገራችን ችግር የስራ አጥ ወጣት ቁጥር መብዛት ነው። ሁሉንም ወጣት የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የመንግስት የመቅጠር አቅም ውስን መሆኑ ይታወቃል። በመዋቅሩ ሁሉንም ከከፍተኛ ትምህርት የተመረቁ ወጣቶችን መቅጠር አይችልም። ሁሉም ሰው ደግሞ ተቀጣሪ መሆን የለበትም።
በተማረው ሙያ ስራ ፈጥሮ ቀጣሪ መሆንንም ማሰብ አለበት።ለዚህ የሚሆን መነሻ ካፒታል በመስጠቱ ሂደት ደግሞ ወላጆችም የድርሻቸውን ማበርከት፣ መንግስትም ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና የብድር አቅርቦት በማመቻቸት መተጋገዝ አለባቸው።ስራ ከተጀመረ በኋላም ክትትልና ድጋፍ አስፈላጊ ነው።ይህንንና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የመንግስትን ሸክም ማቃለል ተገቢ ነው።
የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችም ለወጣቱ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠርና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረት በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝበው መስራት ይጠበቅባቸዋል። ባለሃብቶች ከባንክ የሚበደሩት ገንዘብ የህዝብ ነው፣ መንግስት የሚሰጣቸው የማበረታቻ ድጋፎችም ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ሰጥተው አትራፊ እንዲሆኑ ነው።ስለዚህ ምንም እንኳ ለትርፍ የሚሰሩ ቢሆንም ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች በመስራትና የዋጋ ንረትን በመቀነስ ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
የስራ አጥ ቁጥር ሲበዛና ኑሮ ሲወደድ በመንግስት ላይ ጥያቄ ለማንሳት በሚደረገው ጥረት ግጭት ሲፈጠር የባለሃብቱ ንብረትም ኢላማ መሆኑ አይቀርም።በተግባርም በአለፉት ዓመታት በተከሰቱ ግጭቶች ይኸው ታይቷል።ስለዚህ ቀድሞ መንግስትን የሚያግዙ ስራዎች መስራት አስፈላጊ መሆኑ መገንዘብ ተገቢ ነው።
የሃይማኖት አባቶች፣የሃገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች፣ ታዋቂ ሰዎች ለሃገር ሰላምና መልካም ስነ ምግባር ያለው ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።ሁሉም በየእምነቱ የሰው ልጅ ክቡር፣ሰላም ደግም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማስተማር መልካም ስነምግባር ያለው ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ኃላፊነታቸው ሊወጡ ይገባል።
መንግስት በመዋቅሩና በትምህርት ቤቶች ይህ ስራ ሊሰራ ይችላል። ብቻውን ግን በቂ አይደለም። ስለሆነም እነዚህ ወገኖች በእምነት ተቋሞቻቸውና በማንኛውም መድረክ ኃላፊነታቸውን መወጣት ከቻሉ ሃገር ሰላም ይሆናል። ታላላቆች የሚከበሩባትና ሽማግሌዎችም የሚጦሩባት አገርም መገንባት ይቻላል።
ሲጠቃለል እንኳን የድሃ ሀገር መንግስት ይቅርና የሃብታም ሃገራት ጠንካራ መንግስታት ሁሉንም ችግር መፍታት አይችሉም። ዜጎች ህግ በማክበርና በማስከበር ተባባሪ መሆን ካልቻሉ የሚፈለገው ውጤት አይመጣም። ስለሆንም መንግስት ብቻውን የሚፈታው ችግር ስለሌለ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ።
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2012