ለበርካታ ዓመታት ሲደራረቡብን የኖሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮቻችን አሁንም ድረስ ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ነው። ዓለም በስልጣኔና ብልጽግና ብዙ በተጓዘበት በዚህ ወቅት እንኳ በርካታ ዜጎቻችን በድህነትና ከድህነት ወለል በታች በሆነ አኗኗር ውስጥ ይገኛሉ።
እንኳንስ የተቀናጣ ህይወት ሊታሰብ ሆድን ሞልቶ ማደርና፣ ደከም ያለች መጠለያ እንኳ ማግኘቱ ለብዙዎች እንደ ሰማይ የራቀ ነገር ሆኗል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የህብረተሰብ ክፍላችን ውሎ የሚገባበት ሥራ እንኳን ስለሌለው ወላጅ ቀድሞ ያሳደገው አንሶት ወጣትን ጧሪ የሆነባቸው ሁኔታዎች ተጨባጭ መገለጫዎቻችን ናቸው።
ስለሆነም ዛሬ ላይ የምንሰራው ልማት የትናንቱንና የዛሬውን ውዝፍ የሚያቃልልና ለነገውም ስንቅ መሆን ካልቻለ እንደ ሃገር መቀጠላችን አጠያያቂ መሆኑ አይቀሬ ነው። ዴሞክራሲ የሚሰፍነውም ሆነ ሰላም የሚረጋገጠው ድህነት በአስተማማኝ ሁኔታ ከሃገራችን ሲወገድ ብቻ ነው። በርካታ ሥራ አጥ ባለበትና የኑሮ ውድነቱ ታላቅ ፈተና በሆነበት ሁኔታ ሰባራ ስንጣራ ምክንያቶች ላልታሰበ ግጭትና አደጋ እንደሚዳርጉን ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።
ከላይ ከዘረዘርናቸው ችግሮች ለመውጣት ትልቁ መሳሪያ ደግሞ ትምህርት ነው። ድህነትን ማፍረሻ ትልቁ መሳሪያ ትምህርት ነውና። ለዚህም ሲባል ሃገሪቱ በሌላት አቅሟ ቢሊዮን ብሮችን መድባ ትምህርትን ከአጸደ ህጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች በከፍተኛ መጠን አስፋፍታለች። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎቻችንም በትጋት የትምህርትን ማዕድ በመቋደስ ላይ ይገኛሉ።
ይህ በእንዲህ ባለበት ሁኔታ ግን በአፀደ ህጻናትና በአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እንኳ ባልታየ መልኩ በጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አነሳሽነትና በሴራ ጠንሳሾች አቀጣጣይነት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የማይጠበቁና ተገቢ ያልሆኑ አፍራሽ ድርጊቶች በዩኒቨርሲቲዎች ሲፈጸሙ እየተስተዋለ ነው።
ለኳስ ያውም ለእኛ ምናችንም ላልሆነ በአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ ምክንያት አላስፈላጊ ግጭት እየተፈጠረና ግጭቱ የብሄር መልክ አያያዘ የሃገሪቱ ተስፋ የሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህይወት ሲቀጠፍ ተስተውሏል። ይኸንንም ተከትሎ የግጭቱ አነሳሾች ችግሩን በሃሰት ዜናዎችና ፎቶዎች ጭምር በመደገፍ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት እንዲስተጓጎል አድርገዋል።
አብዛኛው ተማሪ በእውነተኛ የኢትዮጵያዊነት ገመድ የተጋመደና አርቆ አስተዋይ በመሆኑ ከሸፈ እንጂ የግጭቱ ጥንስስ በአገራዊ ህልውናችንም ላይ አደገኛ እንቅፋት መሆኑ ባልቀረ ነበር። ይሁንና ተማሪዎቹ ለግጭትና ለብጥብጥ ቅስቅሳው ጆሮ ባለመስጠታቸው ተደግሶ የነበረውን የሞት ድግስ የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርስ እንዲቀጭ ለማድረግ ችለዋል።
በዩኒቨርሲቲዎች ሰላምን ከማስፈንና ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል በማድረጉ ሂደት ግን ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያደረጉት አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ አዎንታዊ ሚና ነበረው። የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና እናቶች ችግር በተከሰተባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች በበቀል ስሜት ተነሳስተው ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርሱ በማድረግ፣ ተደናግጠው ከዩኒቨርሲቲዎች ለወጡ ተማሪዎች መጠለያና ወላጅ በመሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከታላላቅ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅና ኢትጵያዊነትን የሚመጥን አኩሪ ተግባር ነውና ደግመን ደጋግመን ልናመሰግናቸው ይገባል።
ለአብነትም ያህል በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረ አለመረጋጋት ተደናግጠው ዩኒቨርሲቲውን ጥለው የወጡ ተማሪዎች ነበሩ። ይህንንም ተከትሎ የአካባቢው ማህበረሰብ ተማሪዎችን እንደ ልጆቹ በመቀበል ከቤቱ አስጠግቶ እያበላ፣ እያጠጣ እየተንከባከበ ችግር ላይ እንዳይወድቁ አድርጓል። ዩኒቨርሲቲው ሲረጋጋም እንደ ወላጅ እጃቸውን ይዞ ለዩኒቨርሲቲው አስረክቧል።
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ መልኩ ተማሪዎች ወደ ብጥብጥ እንዳያመሩ ትምህርት እንዳይስተጓጎልና ግጭቶች እንዳይፈጠሩ የአካባቢው ማህበረሰብ ተማሪዎችን በማወያየትና በመምከር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህም በተጨማሪ ከኪሳቸው ገንዘብ አውጥተው ጭምር ምሳ በመጋበዝ የተማሪዎቹ አንድነት የሚጠናከርበትን ሁኔታ አመቻችተዋል።
በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን እንደ ልጆቹ በመውሰድና ለደህንነታቸው ጥበቃ በማድረግ፣ ግጭቶች እንዳይስፋፉና ጉዳት እንዳይደርስ፣ ብሎም ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲቀጥል የተጫወቱት ሚና ከእውነተኛ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ አኩሪ ተግባር ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2012