ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም ‹‹ከሁለት ያጡ?›› በሚል ርዕስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፍረዱኝ አምድ ላይ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሠራተኞች ለተቋማችን ያቀረቡትን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ዘገባ መሥራታችን ይታወሳል።
ሆኖም በዘገባው ‹‹የእኛም ሐሳብ ሊካተት ይገባ ነበር›› ሲሉ የቀድሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች ቅሬታቸውን አቅርበዋል። እኛም ዳግም በዛሬው የፍረዱኝ ገጻችን የሠራተኞቹን አቤቱታ እንዲሁም የተቋሙን ዋና ዳይሬክተር ምላሽ በማካተት ለሚነሱት ቅሬታዎች ቀጣይ መፍትሔ ምን ይሆናል? በሚል ያጠናቀርነውን ዘገባ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ለትውስታ
ከዓመት በፊት በተደረገው ተቋማትን እንደ አዲስ የማደራጀት ሥራ ተከትሎ በቀድሞ አጠራሩ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የጂኦስፓሻል ዲቪዥን ጋር በአዋጅ እንዲዋሃድ ተደርጓል። ከጅማሮው በውህደቱ ደስተኛ የነበሩ ቢሆንም በሂደት ግን በሁለቱ ውህድ ተቋማት ሠራተኞች መካከል በደመወዝና በጥቅማ ጥቅም ያለው ልዩነት ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የቀድሞ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ሠራተኞች ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ይታወቃል።
ከዲቪዥኑ የመጡት ሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅማቸው አይነካም። ነገር ግን በአንድ ተቋም ተመሳሳይ ሥራ እያከናወኑ ብሎም ለመስክ ሥራ ከከተማ ሲወጡ ያለባቸው ልዩነት እያደረሰባቸው የሚገኘውን የሥነልቦናና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ለሚመለከተው አካል ባገኙት መድረክ እንዳነሱ ቅሬታ አቅራቢዎቹና የተቋሙ የሠው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር የሰጡንን ምላሽ በዘገባው ማብራራታችን ይታወቃል።
ቅሬታቸውን ሲያቀርቡም መዋቅር እንደተሰራና የደመወዝ ጣሪያ (ልዩ ስኬል) ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደቀረበ ይገለጽላቸዋል። ይሁን እንጂ አካሄዱ ግልጽነት ያልተሞላበት ከመሆኑ ባሻገር በአንድ በኩል እንደ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በአዲሱ የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን (ጂኤጂ) እንዳልተጠቀሙ በሌላ በኩል ደግሞ የተነገራቸው የደመወዝ ልዩ ስኬል ተግባራዊ ሳይደረግ ዓመት እንዳስቆጠሩ በቅሬታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ከተዋሃዱና ተቋሙ ኢንስቲትዩት ከሆነ በኋላ ዋና ዳይሬክተሩ በሥራዎች እንደማያሳትፏቸው ብሎም በእኩል ዓይን እንደማይታዩም በቅሬታቸው ገልፀው ነበር። በዚህም ሠራተኞች በተቋሙ ላይ ያላቸው ተስፋ እየተሟጠጠ እየፈለሱ እንደሆነ በቅሬታቸው ማንሳታቸው የሚታወስ ነው።
አዋጁ
በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ ዘጠኝ፤ በኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1079/2010 ዓ.ም ለጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ እንዲሁም ጂኦስፓሻል ዴታና መረጃን በተመለከተ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንደገና መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 860/2006 ዓ.ም ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ተሰጥቶ የነበሩ ሥልጣንና ተግባራት ለጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እንደተሰጠ ይደነግጋል።
በ2010 ዓ.ም የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ እንደገና ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን፤ ከቆይታ በኋላ ደግሞ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ውስጥ የነበረ የጂኦስፓሻል ዲቪዥን በጋራ ኢንስቲትዩቱ መቋቋሙን እንዲሁም ተጠሪነቱ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሆኖ መቋቋሙን ያመለክታል።
አቤቱታው
ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የጂኦስፓሻል ዲቪዥን ወደ ኢንስቲትዩቱ የተቀላቀሉት ቅሬታ አቅራቢ ሠራተኞች፤ በአገሪቱ በተለይም የመሬት አስተዳደሩ ዘርፍ ከፍተኛ የጂኦስፓሻል መረጃ ግብዓት ቢጠይቅም ይህንን ለማሟላት የሚችል ቁመና ያለው ተቋም እንዳልነበር ግን ያስታውሳሉ።
በመሆኑም በተቻለ መጠን በቴክኖሎጂ አቅርቦትና አጠቃቀም ዙሪያ ይስተዋል የነበረውን ክፍተት መሙላት ይቻል ዘንድ የጂኦስፓሻል ዲቪዥን መቋቋሙን በመግለጽ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ዲቪዥኑ የተመሠረተው በዘርፉ የነበረውን ክፍተት ለማጥበብ ታስቦ ቢሆንም የቀድሞ ካርታ ሥራዎች ድርጅት በመቀጠል ደግሞ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ሠራተኞች ግን ተግባሩን እንደ መልካም ወስዶ ከመመልከት ይልቅ ‹‹የእኛን ሥራ ወሰዱ›› በሚል ተገቢነት የራቃቸው አመለካከቶችን በሰፊው ሲንፀባርቁ እንደነበር ያነሳሉ። ዲቪዥኑን የማጥላላት አዝማሚያዎች ይታዩም ነበር።
በቆይታ ግን ተልዕኳቸው ተመሳሳይ በመሆኑ በዘርፉ በሠው ኃይልና በቴክኖሎጂ ያለውን ሐብት በተበታተነ መንገድ ከመጠቀም ይልቅ ማዋሃዱ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን መንግሥት አምኖ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንዳደረገ ይገልፃሉ። በዚህም ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ የሚገኙ ሠራተኞች የረጅም ዓመታት የሥራ ልምድን ኢንሳ ከነበረው በቴክኖሎጂና በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት የተጠናከረ ትኩስ የሠው ኃይል የተደራጀው ዲቪዥን ጋር ማዋሃድ አስፈላጊ መሆኑን አምኖ በአዋጅ እንዲቋቋም ይወስናል።
ሁለቱ ተቋማት በጋራ ቢሠሩ የበለጠ ለውጥ ማምጣት ይቻላል በሚል እሳቤ ተዋህደው ተቋሙ ኢንስቲትዩት እንዲሆንና ምርምር ተካትቶበት አዲስ ኃላፊነት እንደተሰጠውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያብራራሉ። ይሁን እንጂ ቀድሞ በተለያዩ ተቋማት ላይ በሚሠሩበት ወቅት የነበረው ‹‹ሥራችን ተወሰደ›› የሚል አስተሳሰብ ቀጥሎ በኢንስቲትዩቱ ተዋህደው በአንድ ተቋም ሲሠሩም በአንዳንድ ግለሰቦች እየተንፀባረቀ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተስተናገደው የሠራተኞቹ ቅሬታም የተጋነነና አንዳንዱም ትክክለኛ ያልሆነ ነው ይላሉ። ሁኔታውም ከመፍትሔ ይልቅ ቀድሞ የነበረውን መቃቃር የሚያባብስ ነው ባይ ናቸው።
ከዲቪዥኑ ወደ ተቋሙ ሲዋሃዱ በርካታ ጥቅማ ጥቅሞቻቸውን ትተውና ለአገር ቅድሚያ በመስጠት እንደሆነ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ አዲስ መዋቅር እንደተሠራና የተጠናው መዋቅርም ለሁሉም ሠራተኞች ከጤና አገልግሎት በተጨማሪ በርካታ የሥራ ውጤታማነትን የሚያሳድጉ ጥቅማ ጥቅሞችን ያካተተ እንደሆነ ገልጸው፤ መዋቅሩ በአጭር ጊዜ ፀድቆ ወደ ሥራ ሲገባ የኢንስቲትቱ ሠራተኞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሠራተኞችን አሳምነው እንዳመጧቸው ያስታውሳሉ። እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ መዋቅሩ ሳይፀድቅ በመቆየቱ ከዲቪዥኑ የመጡት ሠራተኞች ላይ የመሰላቸት እንዲሁም የሥራ ተነሳሽነት መውረድ እንደሚታይም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ።
ወደ ኢንስቲትዩቱ ሲመጡ ከፍተኛ ተነሳሽነት የነበራቸው ሠራተኞች እንደነበሩ ገልፀው፤ እንደ ማሳያ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ብሎም 24 ሰዓታትን በሥራ ላይ ያሳልፉ እንደነበር ያነሳሉ። ለዚህም ደግሞ በሥራ ሰዓት መገኘት አግባብ በመሆኑ ሥራ መግቢያ ሰዓትና መውጫ ላይ ጠብቆ የሚወስድና የሚመልስ ትራንስፖርት አገልግሎት መመቻቸቱ ሠራተኛው ሙሉ ትኩረቱ በሥራው ላይ አድርጎ ስኬታማ እንዲሆንም በማገዝ ረገድ ጉልህ አስተዋፅዖ ነበረው ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት መዋቅሩ ባለመጽደቁ የተነሳ ፕሮጀክቶች በተፈለገው ደረጃ ሊሰሩ አለመቻላቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህ መዋቅር በተጠበቀው ፍጥነት ሳይፀድቅ በመዘግየቱ ሠራተኞቹ ላይ ካሳደረው ተፅዕኖ ባሻገር በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚታየው የደመወዝና የአበል ልዩነቶች ቅሬታዎችን ፈጥሯል።
ኢንሳ የደህንነት ተቋም በመሆኑ ከመንግሥት በልዩ ሁኔታ የተፈቀደለት የደመወዝ ጣሪያ አለ። በዚህም ተቋማቱ ሲዋሃዱ ደመወዛቸውንና ጥቅማ ጥቅሞቻቸውን ይዘው ሊመጡ ችለዋል። ይህንን መነሻ በማድረግ የቀድሞ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ሠራተኞች ጥያቄ ማንሳታቸው ተገቢ ቢሆንም፤ የደመወዝ ጥያቄው ግን የቆየ መሆኑን ነው የሚናገሩት። ጥያቄው የረጅም ዓመታት እንጂ ከኢንሳ የዲቪዥኑ ሠራተኞች ወደ ተቋሙ መዋሃዳቸውን ተከትሎ የመጣ አዲስ ጥያቄ አለመሆኑን ከግንዛቤ መክተት እንደሚገባም ይገልፃሉ።
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተሠራው ዘገባ ላይ ቅሬታው ተገቢ እንደሆነ የሠራተኞቹን አቤቱታ አጠናክረው ምላሽ የሰጡት የተቋሙ የሠው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተርም ለዓመታት በተቋሙ የቆዩ፣ ችግሮቹን በጥልቀት የሚያውቁ፣ በቦታው ላይ የነበሩ እንዲሁም የሠራተኛው የቆየ የደመወዝ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ከማድረግ ይልቅ ከኃላፊዎች ጋር አብረው ምላሽ ሲሰጡና ሠራተኛው ለመብቱ እንዳይሟገት ዝም ያሰኙ የነበሩ ናቸው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሌላ ጎዳና ቆመው ከዲቪዥኑ የተቀላቀሉት ሠራተኞች የሚያገኙትን ደመወዝ በማንሳትና ልዩነቱን በማስፋት ሁኔታው እንዳይረጋጋ በዘገባው የሰጡት ምላሽ ትክክለኛ መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ ችግሮችን ለማስፋት የመፈለግ አዝማሚያ የሚያመላክት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው እኩይ ተግባር ነው በማለት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ዳይሬክተሯ የሰጡትን ሐሳብ ይኮንናሉ።
ተመሳሳይ የመስክ አበል አለመኖሩ ከዲቪዥኑ ለሄዱ ሠራተኞችም የሚያሳዝንና አንድ ሥራ እየሰሩ ተመሳሳይ ቦታ ማደርና ለመመገብ ያለመቻል የሚፈጥረው ስሜት ሊገለጽ የማይችል ነው ይላሉ። ነገር ግን ደግሞ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የውሎ አበል ይዘው ወጥተው ሥራቸውን ሠርተው ይመለሱ የነበሩ ሠራተኞች በአሁኑ ወቅት ከዲቪዥኑ የመጡ ሠራኞች የውሎ አበላቸው ከፍተኛ በመሆኑ መስክ ወጥቶ ሥራን ለመስራት እንደማይችሉ መግለጽ ተገቢ አይደለም። ከሰሞኑም መስክ ላለመሄድ የመፈራረም አድማ የሚያደርጉ ሠራተኞች እየተፈጠሩ ነው። በሥራ ላይ የሚፈጠሩ ቅሬታዎች ቢኖሩም ሥራን እየሠሩ እንጂ በማቆም የሚፈጠር መፍትሔ ባለመኖሩ ይህን መሰል ያልተገቡ ድርጊቶችም ሊቆሙ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ከደመወዝ በተጨማሪ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም የዲቪዥኑ ሠራተኞች ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሥራዎችን ይሠሩ ስለነበር ታሳቢ ተደርገው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በልዩ ስኬል የተፈቀዱ ሲሆኑ፤ ተሽከርካሪዎቹም በመንግሥት ባጀት ሳይሆን ፕሮጀክት እስከሚጠናቀቅ የሚቆዩና ሥራዎችን በአግባቡ ለማከናወን የሀብት ውስንነቱ እንዳይገታው ታሳቢ በማድረግ የተሰጡ ናቸው ይላሉ።
መኪናዎቹ በኪራይ የሚመጡ የፕሮጀክት ሥራ ማስፈፀሚያ እንጂ ከመንግሥት ካዝና ወጪ ተደርገው የሚከፈልላቸው አይደሉም። ዲቪዥኑ ቀድሞም ሥራውን ሲሰራ ግዴታ ዳይሬክተር ካልሆነ መኪና አይመደብም የሚል እሳቤ የለውም። በዚህም የሚሠራውን ሥራ እንጂ ግለሰብንና የተሰጠውን ኃላፊነት ብቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሳይሆን የሚመደበው ሀብት ለማን እና ለምን ዓይነት ሥራ መመደብ ይገባዋል? ሲመደብስ ምን ዓይነት ውጤት ይመጣል ብሎ ሥራን መዝኖ ነው ተሽከርካሪ የሚመደበው። በመሆኑም ተሽከርካሪ ሲመደብ ለጋራ ሥራ ለተቋማዊ ለውጥ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው።
በዚህም መመደቡ የሚያመጣው ውጤት እንጂ መመዘን ያለበት የተመደበለትን ግለሰብ አይደለም ባይ ናቸው። ጥቅማ ጥቅሞች የተጠበቀላቸውም መመሪውን መሠረት ባደረገ መልኩ ቢሆንም ሕግን ባለማወቅ የሚነሱ ቅሬታዎች በመኖራቸው ልዩነቱን የሚያሰፋ እንቅስቃሴ ከማድረግ በፊት ለምን ተደረገ? ብሎ ሁኔታውን በተገቢው መንገድ ማጤን ይገባል።
አንዳንዶቹ ሠራተኞች በዘገባው በቅሬታ የሚያነሷቸው ችግሮች ግነት የተሞላባቸው ናቸው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በዚህ መልኩ የቀረበው ቅሬታም ቀድሞም በሁለት ተቋማት ላይ ሆነው የነበረውን ቅሬታ የበለጠ የሚያሰፋና የውህደት መንፈስን የሚረብሽ ነው ይላሉ። በቅሬታዎቹ ካፌው አደረገ የተባለው መቶ በመቶ የዋጋ ጭማሪ ሐሰተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።
በውህደታቸው ወቅት ካፌውን ይመራ የነበረው የሠራተኞች እድር ከስሮ እንደነበር አስታውሰው፤ በዋና ዳይሬክተሩ አነሳሽነት በቀረበ ሀሳብ እንደ አዲስ ሶሻል ኮሚቴ ተቋቁሞ ሊሠራ ችሏል። ኮሚቴው ላይም በርካታውን ቁጥር በአባልነት የሚይዙት የቀድሞው የኤጀንሲው ሠራተኞች ሲሆኑ፤ ከዲቪዥኑ ግን አንድ ሠው ተካትቷል። ዋጋ ትመና የወጣውም በሠራተኞች አስተያየት ተሰጥቶበት ነው ይላሉ። በዚህም በእያንዳንዱ አገልግሎት ላይ የሠራተኞችን አቅም ያገናዘበና ከአንድና ሁለት ብር ያላለፈ ጭማሪ ሊደረግ ችሏል።
ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በአዋጅ ተዋህደው የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች በመሆናቸው ‹‹እነርሱና እኛ›› እያሉ ከፋፍሎ ማቅረቡ ተገቢ ባይሆንም በአሁኑ ወቅት የቀድሞ የኤጀንሲው ባለሙያዎች እንደተገለሉና በሥራዎች ላይ እንደማይሳተፉ ዋና ዳይሬክተሩም ከዲቪዥኑ ከመጡ ሠራተኞች ጋር ብቻ እንደሚሠሩ ተደርጎ የቀረበው ቅሬታ ግን ትክክል አይደለም ይላሉ። የሠራተኞችን ተሳትፎ የሚሻ ማንኛውም ሥራ ሲኖር ከዲቪዥኑ የመጡትንና የኤጀንሲው ሠራተኞች በጋራ እንደሚሳተፉ ይገልፃሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መዋቅሩ ሲሠራም በፍጥነት ይሁን እንጂ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ እንደነበር ነው የሚናገሩት።
‹‹ከዲቪዥኑ ለመጡ ሠራተኞች ታደላለህ›› በሚል ስብሰባ ላይ ለተነሳባቸው አስተያየት ማንኛውም ሠራተኛ ቢሮ በመገኘት ሊያነጋግራቸው እንደሚችል ዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ ሰጥተው እንደነበር ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያስታውሳሉ። ሥራን መሠረት ያላደረጉ የጎንዮሽ ግንኙነቶችና ትስስሮች አለመኖራቸው በመልካም ጎን ሊታይ እንደሚገባው በመግለጽ፤ ለውህደቱ አስቸጋሪ እየሆነ ያለውም ይህን መሰል አሉባልታና መሠረተ ቢስ ወሬዎች በመሆናቸው ሊታረሙ ይገባል ይላሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ መዋቅሩ ባለመጽደቁ ድልድል ሊሠራ አለመቻሉንና ብዙ ክፍተት እንደተፈጠረ በማንሳት፤ ሁለት ኃላፊዎች ያሉበት አንድ ክፍል እንደሚገኝም ነው የሚናገሩት። ቋሚ የግንኙነት ጊዜ አስቀምጦ ሥራዎችን እየገመገሙ መሄድ ላይም ክፍተት እንዳለና ነባራዊ ሁኔታውን በመረዳት ግን ሥራቸውን እየሠሩ ቅሬታቸውን ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ቅሬታ ሳያሰሙ በተወሰነ የሠው ኃይል ከፍተኛ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል። ከተዋሃዱ በኋላም በየወለሉ ተመሳሳይ የሥራ ባህርይ ያላቸው ክፍሎች በአንድ ክፍል እንዲጣመሩ ተደርገዋል። ነገር ግን መዋቅሩ ባለመጽደቁ የሥራ ሪፖርት የሚቀርበው ለየሥራ ኃላፊዎች እንዲሆን አድርጎታል።
ተቋሙ የምርምር ተቋም በመሆኑ መዋቅሩ ከሌሎች አቻ የምርምር ተቋማት መነሻ ተደርጎ የተሠራ ነው። በዚህም ከዩኒቨርሲቲም የሠው ኃይልን የሚጋብዝ መሆን ይኖርበታል። ነገር ግን ከዲቪዥኑ የመጡ ሠራተኞች በኢንስቲትዩቱ በእንጥልጥል ያደሩ ጉዳዮች በመኖራቸው ለትምህርት የሄዱ፣ የሥራ ልምድ የሚያጽፉም አሉ። ይህም ሌላኛው መዋቅሩ ባለመጽደቁ የመጣ ክፍተት ነው።
የደመወዝ ጉዳይ የግለሰቦች ጥያቄ ሲሆን፤ የአገሪቱ ጥያቄ ግን በጂኦስፓሻል ዘርፍ የሚመራና ትልልቅ ችግር ፈቺ ምርምሮችን የሚያከናውን የሠው ኃይል ማፍራት እንደሆነ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያብራራሉ። በመሆኑም እንዲፀድቅ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተላከው መዋቅር ሲሠራ አገሪቱ በዘርፉ ያለባትን ችግር በጥልቀት በፈተሸ መልኩ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ይህን ታሳቢ አድርጎ ምላሽ እንዲሰጥ ይጠይቃሉ።
ዋና ዳይሬክተሩ
የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ፤ በሠራተኞች የቀረበው ቅሬታ ምንጩ ይታወቃል ይላሉ። ቀደም ሲል የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ ወይንም በቀድሞ አጠራሩ የካርታ ሥራዎች ድርጅት እንዲሁም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ስር የጂኦስፓሻል ሥራዎችን የሚሠራ ዲቪዥን ነበር። በሁለቱ ተቋማት የሚገኙት እነዚህ ሥራዎች ግን በተልዕኮ አንድ ዓይነት ሥራ የሚሠሩ በመሆናቸው በጋራ ይሠሩ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ተልዕኳቸው ተመሳሳይ በመሆኑ አንዱ የሌላውን ሥራ የሚወስድ በሚመስል ሁኔታ በቀረቤታ አብሮ ለመሥራት ያለው ዝግጁነት ያልዳበረ ሆኖ ይስተዋልም ነበር። ይህም በሁለቱ ተቋማት መካከል ትክክለኛና ተገቢ ያልሆኑ ቅሬታዎችን ፈጥረው ቆይተዋል።
ሁለቱ ተቋማት ወደ አንድ እንዲጣመሩ በአዋጅ ኢንስቲትዩቱ እንዲቋቋም ሲደረግ በዋናነት ሁለቱን ተቋማት በአመለካከት በማቀራረብ ወደ አንድ የተቀራረበ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። ጥረቶቹ መልካም ግንኙነት ተፈጥሮ ሁለቱም ዘንድ የነበሩ ጥሩ የሚባሉ የአስተሳሰብ በተለይ ደግሞ በሥራ ላይ ያሉ ልምዶችን በማካፈል አንድ ወጥ የሆነ ጥሩ ሣይንሳዊና ፈጣሪ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ዕቅድ ይዘው እየሠሩ መሆናቸውንም ይጠቁማሉ። ይህንን ለማምጣት ተቋሙ በተሰጠው አዲስ ተልዕኮ የሚመጥን መዋቅር መሥራት ቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ ወስዶ ሠርቷል።
መዋቅሩ ተሠርቶ ወደ ሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥያቄው የቀረበ ሲሆን፤ ይህን ለማስፈፀም ክትትል እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ በሚፈለገው ፍጥነት ባለመፅደቁ በተቋሙ የሚስተዋሉት ሁለት ዓይነት አሠራሮች የሲቪል ሰርቪስ ሲመራ የነበረው የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሠራተኞች የተለያዩ መዋቅራዊ አደረጃጀት ስለነበራቸው ከደመወዝ መነሻም አንፃር የተለያዩ ሊሆኑ ችለዋል።
ይህም ተደማምሮ አላስፈላጊ የሆኑ ቅሬታዎችን ሲያስነሱ ቆይተዋል። አዲሱ መዋቅርም ቅሬታውን ቢያንስ የደመወዝ ስኬላቸውንና ሌሎች የአበልና ጥቅማ ጥቅሞች ተመሳሳይ የሆነ መዋቅር እንዲኖር ለመንግሥት አቅርቧል። ጥያቄው ምላሽ ሲያገኝም ይህን መሰል ልዩነቶች የሚጠቡበት ሁኔታ ይፈጠራል። መዋቅሩ ፀድቆ ሲመጣ ከደንብ፣ ከደመወዝ፣ ከመስክ ሥራ የውሎ አበል ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎች ይፈታሉ በሚል ዋና ዳይሬክተሩ ዕምነታቸውን ይገልፃሉ።
የሁለቱን አካላት ለማዋሀድ አዲስ መዋቅር መኖር ይኖርበታል የሚሉት ዶክተር ቱሉ፤ አዲሱ መዋቅር ተመሳሳይ የሥራ ባህርይ ያላቸው ወደ አንድ የሥራ ክፍል ያመጣቸዋል በማለት ቀጣይ ቅሬታዎቹን እንደሚፈታ ያስረዳሉ። በአሁኑ ወቅት ግን ተመሳሳይ የሥራ ባህርይ ያላቸውን ክፍሎች በጊዜያዊነት በአንድ ሁኔታ አቅደው የሚሠሩበት ሥርዓት በመፍጠር በጋራ እያቀዱ ሥራቸውንም በጋራ እያከናወኑ ይገኛሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሙያዊ (ቴክኒካል) ሥራውን ከመሥራት አንፃር ብዙ ያጋጠሙ ችግሮች የሉም። ለዚህም የምድር ቅየሳ ላይ የሚሠሩ ከዲቪዥኑ የመጡት እንዲሁም በኤጀንሲው በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች በጋራ እንደሚያቅዱና ዕቅዳቸውንም ወደ ተግባር በጋራ እንደሚሠሩ ለማሳያነት ያቀርባሉ።
ሠራተኞችን በእኩል አይመለከቱም በሚል የቀረበውን ቅሬታ አስመልክቶ ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ፤ ተቋሙ ሁለቱም የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች መሆናቸውን አምኖ በመቀበሉ ከሁሉም ሠራተኞች ጋር በአንድነት፤ ለመሥራት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም መዋቅሩ በተሠራበት ወቅት እያንዳንዱ በአመራር ደረጃ የሚገኙ የሠራተኞች ኃላፊዎች ከሁለቱም ወገን በመዋቅሩ ላይ ተሣታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል። አስተያየትም ተሰጥቶበታል።
የ2011 ዕቅድ እንዲሁም የተያዘው 2012 ባጀት ዓመት ዕቅድ ሲታቀድ ውይይት ተደርጎበት በሀሳብ ዳብሮና መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ከኤጀንሲው የነበሩት እንዲሁም ከዲቪዥኑ የመጡት የተዋሃዱት ሠራተኞች አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ በዕቅዱ ላይም አስተያየት እንዲሰጡና በጋራ እንዲያቅዱና እንዲፀድቅ ተደርጓል። ይህም ኢንስቲትዩቱ በሚሠራቸው እያንዳንዱ የሥራ እንቅስቃሴ ሁሉንም ሠራተኞች በእኩል ዓይን ተሳታፊ እያደረገ እንደሚሄድ ይታወቃል። በመሆኑም ከዚህ ጋር ተያይዞ የቀረበው ቅሬታ ምን መነሻ ያደረገ እንደሆነ ግልጽ ያልሆነ ነው ሲሉም ተችተውታል።
ሁለቱ ሠራተኞች የተለያየ ባህል አላቸው የሚሉት ዶክተር ቱሉ፤ በአመለካከት፣ በሥራ ባህል ሁለቱም ጋ የነበረው ባህል ይለያያል በማለት ሁኔታውን ያስረዳሉ። ከሁለት የተለያየ የሥራ ባህል የመጡ ሠራተኞች ሲሆኑ፤ በአስተሳሰብ፣ ግንዛቤና ለሥራ ያላቸው ተነሳሽነት፣ ቅንነት፣ ታታሪነት እንዲሁም በቡድን የመሥራት ባህል የተለያየ በመሆኑ ይህንን ወደ ተቀራራቢ ደረጃ ለማምጣት በአመራር ደረጃ የተሠሩ ሥራዎች አሉ። አጠቃላይ ሠራተኞችን በማሰባሰብ በግንዛቤና በአስተሳሰብ ላይ ወጥነት የተሞላበት ዕይታ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ከዚህ ባሻገር የሶሻል ኮሚቴ ተቋቁሟል።
የተቋቋመው ሶሻል ኮሚቴ ተቋሙ በቀጣይ ሁለቱ በተለያየ የሥራ ባህልና አካባቢ ሲሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ወደ ተቀራራቢ ሳይንሳዊ አመለካከት እንዲያዳብሩ ከማድረግ አንፃር የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ እንደሚሆን ታምኖ የተቋቋመ ነው። ኮሚቴው በቀጣይነት ሠራተኞቹ ጋር በቀረቤታ እየሠራ ተቀራራቢ የሆነ ሣይንሳዊና ፈጠራ የተላበሰ ሠራተኛ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።
ኮሚቴው ዋናው ዓላማው በወር ሣይንሳዊ የሆኑ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ሁሉም ሠራተኛ በወር አንድ ጊዜ ሣይንሳዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዲያደርግ ያለመ ነው። በዚህም ሠራተኞች እንዲቀራረቡ ማድረግ ይቻላል ተብሎ ይታሰባል። ይህም ሠራተኞች እርስ በእርስ ከሥራ ግንኙነታቸው ውጪም ቤተሰባዊ መንፈስን እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል ተብሎ ታቅዷል።
በቀጣይ ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ በመቶኛ የተወሰነ ገንዘብ በመቆጠብ ሶሻል ኮሚቴው የሚያከናውናቸው ተግባራት ይኖራሉ። በተለይም ሠራተኛ ሐዘን ሲያጋጥመው በማጽናናት ደስታውንም በመካፈል በሥራ ቦታ ላይ ካለው ግንኙነት ባለፈ የበለጠ ማህበራዊ ትስስሩን በማጠናከር የሚጠበቀውን ሥራን መሠረት ያደረገ ተመሳሳይ ዕይታ ያላቸው ሠራተኞች እንዲኖሩ እየተሠራም ነው።
አንደኛው የሶሻል ኮሚቴ ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር የካፍቴሪያ በተለይም የምግብ አገልግሎት ላይ ይሠራል። ተቋሙ የሚገኝበት አካባቢ በዋጋቸው ከፍ ያሉና በከተማዋ ከፍተኛ ሥምና ዝና ያላቸው ሆቴሎች የከበቡት ነው። ይህም የሠራተኞችን ወርሃዊ ገቢ የማይመጥንና ኪሳቸውን የሚፈትሽ በመሆኑ ሶሻል ኮሚቴው ይህን ችግር መነሻ ባደረገ መልኩ ሠራተኞች ሳይቸገሩ ከሥራ ቦታቸው ሳይርቁና ገቢያቸውን ያገናዘበ አገልግሎት እንዲያገኙ ይሠራል። ይህም ሠራተኞች ሥራቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያከናውኑ ለማገዝ ያስችላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ካፌው አደረገ በተባለው የዋጋ ጭማሪ ቅሬታ ላይ ዋና ዳይሬክተሩ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ካፍቴሪያው ቀደም ሲል በኤጀንሲው የሠራተኞች እድር ሲመራ እንደነበር ያስታውሳሉ። ሆኖም ግን እድሩ ካፍቴሪያውን ለመሥራት በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ በመግባቱና ኪሳራ ውስጥ በመውደቁ ሥራውን ለማቆም በመገደዱ እንዳሳወቋቸው ይናገራሉ። ይህ አገልግሎት መቆሙ ሠራተኞች የሚመገቡበትና ሻይ ቡና አገልግሎት እንደማያገኙ በመገንዘብ የሥራ አካባቢን ምቹ ከማድረግ አንፃር ሌላ አማራጭ አፈላልገዋል። ለዚህም ከአስተዳደር አካላትና ከሚመለከታው ክፍሎች ጋር በመምከር የሌሎች ተቋማት ነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ ከተደረገ በኋላ የካፍቴሪያ ሶሻል ኮሚቴ ተቋቁሟል።
ውሳኔው ሲወሰን አጠቃላይ ከሠራተኞች ጋር አራት ያክል ጊዜያቶች መድረኮችን በመፍጠር ውይይት ተደርጎበታል። ዋጋውም በእጅጉ አነስተኛ ነው። ሁኔታውም በሠራተኞች በሙሉ ይሁንታን አግኝቶ ኮሚቴው እንዲቋቋምና ሠራተኞቹ በየወሩ ከደመወዛቸው ላይ እየቆጠቡ የካፍቴሪያውን ሶሻል ኮሚቴ በገቢ እንዲደግፉ በማድረግ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። የዋጋ ለውጥ ሲደረግም ቀደም ሲል በእድር ሲመራ ከነበረው የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጓል። ኮሚቴው ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ አጠቃላይ የኢንስቲትዩቱን ሠራተኞች አቅም ባገናዘበ ሁኔታ እንጂ ከዲቪዥኑ የመጡትን ሠራተኞች ማዕከል አድርጎ የተሰላ አይደለም።
መዋቅሩ የካቲት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተላከ ሲሆን፤ መዋቅሩ ኢንስቲትዩቱ በአዲስ መልክ ሲቋቋም የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ነው። ተልዕኮውም ቀደም ሲል የጂኦስፓሻል መረጃዎችን በማሰባሰብ የተለያዩ ካርታዎችን ሲያመርት ቆይቷል። መረጃዎቹ በዋናነት የመንግሥት የሥራ አስፈፃሚ አካላት ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ግብዓት የሚሆኑ በአጠቃላይ የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን የሚረዱ መረጃዎችን ሲያመርት ቆይቷል።
በዲቪዥኑ በኩል ደግሞ የጂኦስፓሻል መረጃዎች ከማምረት በተጨማሪ በተቋሙ የሚመረቱ የጂኦስፓሻል መረጃዎችና በሌሎች ተቋማት የሚመረቱ የጂኦስፓሻል መረጃዎች ለመንግሥት ተጠቃሚ አካላት፣ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዩኒቨርሲቲዎች እና ለተለያዩ አካላት መረጃው በቀላሉ የሚደርስበትን ቴክኖሎጂ ሲያበለጽጉ ቆይተዋል።
ሥራዎቹን በማስቀጠልና ፈጣሪ የሆኑ ምርምሮችን በመሥራት የማሕበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ብሎም ማሕበራዊ ችግሮች መፍታት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ መዋቅር ነው። መዋቅሩ ፈጣሪ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን በተለይ በአራተኛው የኢንደስትሪ ሽግግር ላይ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና ሴክተሩ መጫወት ስለሚችል ይህንን ለማድረግ እንዲያስችል ታስቦ የተዘጋጀ መዋቅር ነው። መዋቅሩ በልዩ ስኬል እንዲፀድቅ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀርቧል።
የጂኦስፓሻል መረጃዎች የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን፣ የከተማ ልማቱን ለማፋጠን፣ የትራንስፖርት ዘርፉ እንዲሁም የተለያዩ የመንግሥት ልማትን ለማፋጠን የሚሠሩ ዘርፎች የሚጠቀሙትን መረጃ የሚያመርት በመሆኑ መረጃው በሚፈለገው ጥራትና ብቃት ከማቅረብ አንፃር የተሻለ ቁመና ሊኖረው ይገባል። በመሆኑም ዘርፉ ተወዳዳሪ ሆኖ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባ መወጣት እንዲችል ጥያቄው ወደ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መሄድ እንደሌለበት ታምኖ የተጠናው መዋቅር ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተልኳል።
መዋቅሩ በተቻለ ፍጥነት ቶሎ ፀድቆ ወደ ሥራ ለመግባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የሚገልጹት። መዋቅሩ ቀደም ሲል በ2011 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተልኮ ‹‹አይሆንም›› የሚል ምላሽ ተሰጥቶ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ውይይት እየተደረገና አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በቀጣይ መዋቅሩ ሲፀድቅም ሠራተኞች ምደባ ተከናውኖላቸው መደበኛ የሆነ ተገቢው የሥራ ክፍፍል ይደረጋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ የሚፈልጋቸው የመገኛ ቦታ ወይንም የቦታ መረጃ የሚሰጥና መሰል መተግበሪያዎችን (አፕሊኬሽኖችን) በመሥራት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በዋናነት መደገፍ ስለሚያስፈልግ ይህንን ቁመና ለማምጣት የምርምር ተቋም መሆን ይገባዋል። በተያያዘ ሠራተኞችን ለማቆየት እንዲሁም ደግሞ ሌሎች ተመራማሪዎች ለመሳብ መሥራት እንደሚያስፈልግ ታምኗል። ለዚህም ደግሞ የደመወዝ ጉዳይ በልዩ ስኬል እንዲታይ ተጠይቋል።
ዘርፉ ለአገሪቱ ከሚጫወተው ቁልፍ ፋይዳ አንፃር በልዩ ስኬል ቢፀድቅ የተሻለ ተቋማዊ ዝግጁነት እንደሚኖረውና የተለያየ መንግሥታዊ ልማታዊ ተልዕኮዎች ከመደገፍ አንፃር መሪ ሚናን ለመጫወት ያስችለዋል። ስለሆነም በዚህ ሁኔታ እንዲታይ በድጋሚ ጥያቄ ቀርቧል። ስለሆነም እነዚህ ጉዳዮች በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኙም ነው የሚገልጹት።
የተቋሙ የበላይ አመራሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተቋሙ ለብዙ ዘመናት የተለያዩ ችግሮች ያሉበት በመሆኑና ብዙም ትኩረት መሰጠት የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ። በተለይም ተወዳዳሪ ሆኖ ከደመወዝ መነሻና ጣሪያ አንፃር በተለይደግሞ የቀድሞ የኤጀንሲው ሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ ያለው ተቋም በመሆኑ በርካታ አቅም ያላቸው ሠራተኞች ወደ ሌላ ተቋም እየፈለሱ ሄደዋል።
በመሆኑም ተቋሙ ከሠው ኃይል አደረጃጀትና ዝግጁነት ጋር ተያይዞ ብዙ ተግዳሮት የገጠመው በመሆኑ በቀጣይ ተቋሙ የተሻለ መዋቅር እንዲኖረው ያሉትንም ሠራተኞች በማቆየት የተሻለ ሥራ እንዲሠራ ሌሎች ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎችንም በማምጣት ለአገሪቱ የተሻለ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ለማስቻል አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የተቋሙ ሠራተኞች ግንዛቤ እንዲይዙና እንዲደግፉ፤ የአስተዳደሩን ኃላፊዎች የሚሠሩትን ሥራም እንዲያግዙ ዋና ዳይሬክተሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ተቋሙ የተሰጠውን ኃላፊነት ማሳካት የሚያስችለው መዋቅር ሳይፀድቅ የቆየበት ምክንያት ምን ይሆን? የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞችስ ከመዋቅር አለመጽደቅ ጋር ተያይዞ የሚያነሷቸው በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ቀጣይ መፍትሔው ምንድን ነው? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ምላሽ እንዲሰጥ ያደረግነው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012
ፍዮሪ ተወልደ