አንድነት የሚለውን ቃል የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት “አንድ መሆን፣ በባህርይ በግብር መሳተፍ፣ መተባበር፣ መጣመር” በማለት ይተረጉመዋል። ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ግጽው በበኩላቸው ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት በሚል በ1951 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው፤ “ብዙው ማህበር በህገ መንግስት ምክር ቤት አንድ አካልና አንድ ባህርይ ሆኖ መስራት” ብለው ተርጉመውታል። በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀውና በ1993 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ አንድነት የሚለውን ቃል “ህብረት” በማለት በአንድ ቃል ይገልጸዋል። ለአንድነት መሰረት የሆነውን “አንድ ሆነ” የሚለውን ቃልም፤ “ተባበረ፣ ተስማማ፣ ተቀራረበ፣ ተመሳሰለ” በማለት ይተረጉመዋል።
ከጥቂት የአገላለጽ ልዩነት በስተቀር ሦስቱም መዝገበ ቃላት አንድነት ለሚለው ቃል የሰጡት ትርጉም ተመሳሳይ ነው። ይኸውም የቃሉ ትርጉም የሚያመለክተው መተባበር፣ መተጋገዝ፣ አብሮ መኖር፣ የጋራ በሆኑና አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ አንድ ሆኖ መቆም፣ ተቀራርቦና ተደጋግፎ መስራት፣ ልዩነቶችና ብዙነቶች ቢኖሩም በጋራ ዕሴቶች ላይ ተስማምቶ በህብረት አንድ ላይ መኖርን ነው።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንድነትን በተመለከተ ከአንዳንድ ወገኖች የሚሰሙ ገለጻዎችና ትንተናዎች ከዚህ ቀደም ከምናውቀው የአንድነት ትርጓሜ በእጅጉ የተለዩና ብዙዎቻችን ግራ የሚያጋቡ ሆነዋል። አንዳንዶቹማ እንኳስ የአንድነት ትርጉም ሊመስሉ ይቅርና ከተለመደው ትርጓሜ ፍጹም የሚቃረኑ በመሆናቸው “ሃሳቦችም በዝግመተ ለውጥ ትርጉማቸውን ይቀይራሉ እንዴ? ብለን በግርምት እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ናቸው።
በዚህ ረገድ አዘውትረው ከሚሰሙና “በአዲስ መልክ ሥራ ከጀመሩ” አዳዲስ የአንድነት ትርክቶች ውስጥ “አንድነት የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንዳይከበር፣ ባህላቸውና ማንነታቸው በአደባባይ ወጥቶ እንዳይታይ ያደርጋል። በአጠቃላይ ብሔር ብሔረሰቦችን ይውጣል” የሚለውና ከትክክለኛ ትርጉሙ በተቃራኒ አንድነትን “ጨቋኝና አንባገነን” አድርጎ የሚስለው አዲስ ተረክ ዋነኛው ነው። “አንድነት ማለት አሃዳዊነት ማለት ነው። ይህም የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ጥቅማቸውን ያስቀረባቸው ነው፤ አሁን ያለው ፌዴራሊዝም ያልተዋጠላቸውና አሃዳዊ ሥርዓት እንዲመለስ የሚፈልጉ የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች የሚያራምዱት ኋላቀር አስተሳሰብ ነው” የሚለውም በአዲስ መልክ ተቀነባብረው ከተለቀቁ የአንድነት “ግልብጥ ሪሚክሶች” መካከል በስፋት እየተደመጠ የሚገኝ ተወዳጅ ዜማ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት ይናገራሉ።
እነዚህ ሁለቱ በርካታ “አድናቂዎችን” በማግኘት አዲሱን የአንድነት “የትርክት ሰንጠረዥ” በቀዳሚነት እየመሩ መሆናቸውን እኔም በተደጋጋሚ የታዘብኩት ጉዳይ ነው። አለፍ ሲልም “ከነጭራሹ አንድነት የሚባል ነገር የለም፣ በአንድነት ስም አሃዳዊነትን ለማስፈንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለመገደብና ብሔር ብሔረሰቦችን ለመዋጥ በማጭበርበሪያነት የሚያገለግል ‘የውሸት አንድነት’ ነው ያለው” በማለት ይወነጅላሉ። በጉዳዩ ላይ የራሴን ምልከታ እንዳቀርብ የተገደድኩበት ምክንያትም ይኼው ነው።
ለመሆኑ ግን አንድነትን አስመልክቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀረበ የሚገኘው እንዲህ ዓይነቱ አዲስ ትርክት እውነታው ምን ያህል ነው? የትርክቱ አራማጆች አንድነትን በዚህ መንገድ እንዲተረጉሙትና እንዲያቀነቅኑት ያደረጋቸው ምክንያት ምን ይሆን? በእርግጥ እነርሱ እንደሚሉት አንድነት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚያፍን ነገር ነውን? ብሔር ብሔረሰቦችን የሚውጠውስ ማነው? አንድነት ወይስ አንባገነንነት? አንድ እንሁን የሚሉ ሰዎችስ በእርግጥ ፍላጎታቸው ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን መቃወም፣ ፌዴራሊዝሙን ማፍረስና ወደ አሃዳዊ ሥርዓት መመለስ ነውን? “የውሸት አንድነትስ” ሊኖር ይችላልን? ሃሳቡን ትክክል ወይም ስህተት ነው ብሎ ለመናገር የግዴታ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ተመስርቼ በጉዳዩ ላይ ያለኝን የግል ምልከታ ላቅርብ።
ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ወደ አደባባይ የወጣውና ዋነኛ መመሪያውን የ “መደብ ክፍፍል” ባደረገው የማርክሲሳዊ-ሌኒናዊ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ተቦክቶ ተጋግሮ በአገራችን ፖለቲከኞች ሳይታኘክ የተዋጠው የ “እኛ” እና እነርሱ” የጎራ ፖለቲካ ጥቅም ላይ ከዋለ ወዲህ ግን ሁሉም ነገር ትርጉሙ እየተለዋወጠ የመጣ ይመስላል። ምክንያቱ ደግሞ ተደጋግሞ እንደሚገለጸው ያለ “መደብ” መኖር የማይችለው የነ ስታሊን ርዕዮተ ዓለም ሁሉንም ነገር በተቃርኖ እየከፈለ የሚመለከትና እየፈረጀ የሚመድብ፣ ሲፈልግም የራሱን አዲስ ብያኔ የሚሰጥ መሆኑ ነው።
ወደ ግራ በሚያስቡ የምስራቅ ፖለቲካ ነጋዴዎች ተፈብርኮ በ1960 ዎቹ የእኛን ሃገር ገበያ የተቀላቀለው ግራ ገቡ ርዕዮተ ዓለም ዓላማዬ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኝን የመደብ ክፍፍል በማስቀረትና የእርስ በእርስ ጭቆናን በማስወገድ “ፍትሐዊነትንና እኩልነትን” ማስፈን ነው ቢልም ምኞቱ ተሳክቶ ገበያው ውስጥ ገብቶ ምርቱን መሸጥ ሲጀምር ግን “ግብር ማንነትን ይናገራልና” እውነተኛ ማንነቱ እየተገለጸ መጣ። ሃሳቡ መሬት ላይ ወርዶ ዓላማውን ለማሳካት በተግባር ሲንቀሳቀስ ድብቁ ማንነቱም ከተደበቀበት ሃሰተኛ ዓለም ወጥቶ ራሱ በትክክለኛው ስሪቱ ይታወቅ ጀመር።
“እኩልነትን ለማስፈን” የሚታገለው ከፋፋዩ ርዕዮት ዓለም ተቀባይነት የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ እስኪፈጥር ድረስ መልካም መስሎ ለመታየት ያጠለቀው ጊዜያዊ የማስመሳያ ጭንብል ነበር። እናም ጊዜው ደርሶ በእኛም አገር በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነትን አግኝቶ በ “አማኞቹ” አማካኝነት የወቅቱ ፖለቲካ ዋነኛ መመሪያ ሆኖ “ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም”፣ “ሶሻሊዝም”፣ “ህብረተሰባዊነት” … እየተባለ በየአገራቱ መተግበር የጀመረው ግራ እጁን እየሰበቀ “ለህዝብ እኩልነት” የሚታገለው ግራ ርዕዮተ ዓለም የማስመሰያ ሽፋኑ ተገልጦ እውነተኛ ማንነቱ ሲታይ እውነታው ሌላ ሆኖ ተገኘ። ትልቁ ዓላማው “እኩልነትን” በማስፈን ሽፋን ህዝብን ከፋፍሎ መግዛትና የማይነቃነቅ ስልጣን መያዝ መሆኑ ታወቀ። ማንነቱም “የእኩልነትና የፍትህ ተሟጋችነት” መሆን ሳይሆን “ራሱን ከሁሉ በላይ ለማድረግና ፍጹም የበላይነቱን ለማስጠበቅ የሚሯሯጥ አንባገነንነት” ሆነ።
ከዚያስ…? ከዚያማ ህዝብን አቅመ ቢስ ለማድረግና እንዳሰበው በፍጹም የበላይነት ለመግዛት የሚያስችለውን የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት ሥራው ሁሉ ህዝብን መከፋፈል ሆነ። ይህን ዓላማውን ከግብ ለማድረስም ለእርሱ ያልተመቸውንና እንዲጠፋ የሚፈልገውን ሁሉ ለማጥፋት የሚያስችል የ “ፍረጃ” ስልትን ተግባራዊ አደረገ። ይኸውም በመጀመሪያ እንዲጠፋለት የሚፈልገውን ነገር የሚያጥላላና በሌላው ዘንድ በጠላትነት እንዲታይ የሚያደርግ የራሱን አዲስ የዳቦ ስም ያወጣለታል። ቀጥሎ ከዚህ አካል በተቃርኖ ሊቆም የሚችልና በሂደትም ሊያጠፋልኝ ይችላል ብሎ የሚያስበውን “ተቀናቃኝ ጠላት” ይፈጥርለታል።
በዚህም የራሱን አንባገነን ሥርዓት መፍጠር ይችል ዘንድ መጥፋት አለበት ብሎ የሚያስበውን የዘመኑን ንጉሳውያን ስርዓት “ጨቋኝ” የሚል ስም በመስጠት ሥራውን “ሀ” ብሎ ጀመረ። በንጉሳውያን ሥርዓቱ ጨቋኝ ሥርዓት የተማረረውና በአስመሳዮቹ የ “እኩልነት እናሰፍናለን” ቅስቀሳ ተታልሎ “አዲስ ጨቋኝ” እየመጣበት መሆኑን ያልተገነዘበው ምስኪኑ ህዝብም የተሻለ ሥርዓት ይመጣልኛል በሚል ተስፋ ከሶሻሊስታውያኑ ጋር ተባበረ። የፍረጃ ስልታቸው ሰርቶ አስመሳዮቹ ህዝብን በገዥዎች ላይ በጠላትነት አስነስተው የቆየውን የንጉሳዊ ሥርዓት አፍርሰው የራሳቸውን ሥርዓት ማንበር ቻሉ።
የሥልጣን መንበሩን ተቆናጠጡ። የቋመጡለትን የበላይነትና አይነኬ የስልጣን ኃይል የመፍጠር ምኞት በፍጥነት አሳኩ። ቀጥለውም ለርዕዮት ዓለማቸው ስጋት ይሆናሉ ብለው ያሰቧቸውን ሃብታሞችንም “ቡርዧ፣ በዝባዥ” በሚል ከፈረጇቸው በኋላ “ወዛደር፣ ላባደር” በሚል ደሃውን የህብረተሰብ ክፍል በአዲስ ስም አደራጅተው በጠላትነት አስነስተውባቸዋል። እንዲህ አንዱን በአንዱ ላይ እያስነሱ የማይፈልጉትን ሁሉ በማጥፋት ተራቸው ደርሶ እነርሱም እስኪጠፉ ድረስ የተቆጣጠሩትን የዓለም ክፍል በፍጹም ፈላጭ ቆራጭነት ለዘመናት ገዝተዋል። በዚህ ረገድ የማይፈልጉት ከሆነ ህዝብም ቢሆን ከማጥፋት የማይመለሱትን እነ ስታሊንን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ የማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ወራሾችም ገሚሶቹ ሳያውቁ በጥራዝ ነጠቅነት፣ ቀሪዎቹ ደግሞ እያወቁ በራስ ወዳድነት ባለፉት ሃምሳ ዓመታት መርዛማውን ርዕዮተ ዓለም በአገር ላይ በስፋት አሰራጭተውታል።
እናም አገር ምድሩን ሁሉ ጠላት በጠላት አድርገውት አርፈዋል። የሃሳቡ አፍላቂዎች እንኳን እንደማይጠቅም አይተው በጊዜ ያረገፉትን ከፋፋይ ርዕዮተ ዓለም የእኛዎቹ አብዝተው ተሸክመውት አገርና ህዝብን በጥላቻ ሸክም እያስጨነቁት ይገኛሉ። ስለሆነም ጠላትነቱን ህዝብ ድረስ ወስደው ከ “ጨቋኝ ሥርዓት” ና ከ “ተጨቋኝ ህዝብ” አልፈው “ጨቋኝ ህዝብ” ና “ተጨቋኝ ህዝብ”ም ፈጥረው ህዝብን እርስ በርስ ማባላት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ለዚህም ህዝቡ በአንድ ላይ ቆሞ በተባበረ ክንድ ከጥቅም ማማቸው እንዳያወርዳቸው በ“ሃሳብ” የተራቀቁት የዘመኑ ስታሊናውያን አንባገነኖች “አንድነት” የሚለውን ሃሳብም ለማጥፋት በተቃራኒው የሚቆም ጠላት በማፈላለግ ከተጠመዱ ቆይተዋል።
ቃላትን ከማያልቀው መዝገበ ቃላታቸው እየመዘዙ ትርጉሙን የሚያዛባና አንድነት የሚለው እሳቤ እንዲጠላና በጠላትነት እንዲፈረጅ የሚያደርጉ አዳዲስ ትርጓሜዎችን ጥቅም ላይ በማዋል አንድነትን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ከምንጊዜውም በላይ በርትተው እየሰሩ ይገኛሉ። አንድነትን በጠላትነት ለማስፈረጅም የራሳቸውን አዲስ ትርክት ፈጠሩ። ለአንዲት አገር ህዝቦች የጋራ ደህንነትና ህልውና ዋስትና የሆነውን አንድነትንም “የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚያፍን፣ ጭቆናን የሚያመጣ፣ ማንነትን የሚውጥ ወዘተ… በሚል በህዝብ እንዲጠላ የሚያደርግ አዲስ የጥላቻ ትርጉም ሰጡት። ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትን ለዘመናት ህዝብን ሲጨቁኑበት የኖሩበትን የፍረጃ ስልታቸውን በመጠቀም በወርቃማው የአንድነት እሴት ላይ አጥላይና አግላይ ሃሰተኛ የውንጀላ ዘመቻቸውን ከፈቱበት።
ይሁን እንጂ የቱንም ያህል ውንጀላው ቢበዛ እውነታውን አይቀይረውም፤ አንድነት ያው አንድነት ነው ሌላ ትርጉም የለውም። እነርሱ እንደሚሉት በምንም ተዓምር አንድነት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ሊጨፈልቅ አይችልም፤ “የውሸት አንድነት” የሚባል ነገርም የለም። “ውሸት” የሚሆነው እነርሱ እንደሚያደርጉት ለብሔር ብሔረሰቦች መብት በመቆርቆር ሽፋን የራሱን የበላይነት ለማምጣት አብረው የሚኖሩ ህዝቦችን የሚከፋፍለው “የሀሰት ተቆርቋሪነት” ነው። ይህም ለብሔር ብሔረሰቦች ያዘኑ በመምሰል የራስን የበላይነት ለማስፈን የሚደረግ ድብቅ የአንባገነንነት ፍላጎት ነው። እናም የህዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚነፍገውና ማንነታቸውን የሚጨፈልቀው መደጋገፍንና መተባበርን መሰረት ያደረገውና ለእኩልነት በጋራ የሚሰራው አንድነት ሳይሆን፤ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅና በሌሎች ላይ የበላይ ሆኖ ለመኖር “አንድነትን እያጥላላ” ህዝብን ከፋፍሎና አዳክሞ ለመግዛት የሚሞክረው አንባገነንነት ነው።
ለአንድነት ሌላ ስም በመስጠትና ከእውነታው በተቃራኒ ለቃሉ አሉታዊ ትርጉም በመፈብረክ አንድነት ላይ ዘመቻ የከፈቱ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አዲስ ትርክት ውስጥ የገቡበት ምክንያት እንደሚሉት አንድነት ህዝብን የሚጎዳ ነገር ሆኖ አይደለም። አንድነት የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚነፍግ፣ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚያጠፋ፣ ወደ አሀዳዊ ሥርዓት የሚመልስ፣ ብሔር ብሔረሰቦችንም የሚውጥ ስለሆነም አይደለም። እነርሱም ለህዝብ አስበው አይደለም። ምክንያታቸው ሌላ ነው። ድብቅ አጀንዳ አላቸው።
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት እነዚህ ሰዎች ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር “መብት” እና ለህዝቦች “እኩልነት” በሚል ሽፋን የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደም የሚታትሩ፣ እነርሱ ብቻ የበላይ ሆነው ለመኖር የሚፈልጉ ጊዜ ያለፈበት የ “እኔ አውቅልሃለሁ” የግራ ፖለቲካ “ሌጋሲ አስቀጣዮች” ናቸው። በለመዱት የ “ጨቋኝ-ተጨቋኝ” የሃሰት ፍረጃ ፖለቲካቸው “ምናባዊ ተጨቋኝ” ፈጥረው የጭቁን ተቆርቋሪ መስለው ለመጨቆን የሚዳክሩ አስመሳይ አንባገነኖች ናቸው። በፍረጃ ትርክታቸው ህዝብን አለያይተው፣ በጠላትነት አቧድነው ተከፋፍሎ የተዳከመ ህዝብን ያለ ተቃውሞ በበላይነት ቀጥቅጦ ለመግዛት አዛኝ መስለው የሚቀርቡ ቅቤ አንጓቾች ናቸው።
አንድነትማ የተራራቀውን ያቀራርባል፣ የተቃቃረውን ያስማማል፣ በልዩነቱ ምክንያት አብሮ መኖር አቅቶት የተለያየውን አንድ ያደርጋል፣ በብዙነቶችና በልዩነቶች ስምምነት፤ በጋራ ጉዳዮች ደግሞ ህብረት እንዲፈጠር ህዝቦች በፍቅርና በሰላም አብረው እንዲኖሩ ያደርጋል እንጂ እንዴት አድርጎ መብትን ያፍናል? እንዲያውም “የአንዲት አገር ዕድገትና ታላቅነት የሚለካው በህዝቦቿ አንድነት ነው” እንዲሉ ታላቁ ንጉሠ ነገሥት አጼ ቴዎድሮስ ስምምነትና ህብረት የጋራ ዕድገትና ብልጽግና ይፈጥራል እንጂ እንዴት አንድነት ጭቆናን ይወልዳል?
አገራዊ አንድነት ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተጋመደ፣ የተሰናሰለና የተዋደደ መሆኑን አመላካች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ “የአገራችን ብሔሮች እጣ ፋንታ በጋራ ለማደግ የተሰራ ብቻ እንጂ ተለያይተን ወይም ተነጣጥለን ሉዓላዊ አገር ሆነን፤ የነጠላ ህልውናችንን አስጠብቀን በሰላም መቆየት አንችልም። አገራዊ አንድነታችን የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ማስጠበቅ ጉዳይ ጭምር ነው” ማለታቸውስ የአንድነትን ውድ ዋጋ የሚገልጽ አይደለምን?
እናም እላለሁ አንድነትን የምታጥላሉ ሰዎች መንገዳችሁን መርምሩ፣ ራሳችሁን ተመልከቱ። የሚበጀው እርሱ ነው። የቱንም ያህል ትርጉሙን ለማጣመም ብትሞክሩ፣ እንዲጠላ ብትጥሩ እውነታውን መቀየር አትችሉም። አንድነትን የሚጠላም አታገኙም። ዛሬም ነገም ወደፊትም አንድነት አጥፊ ሆኖ አያውቅም! በዘመቻ ብዛት በፕሮፓጋንዳ አይለወጥም። አንድነት አንድነት ነው፤ ትርጉሙም ኅብረት ነው፣ ኅብረትም ኃይል ነው። ኃይል ደግሞ በፊዚክስ ህግ የማይጠፋ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ፀንቶ የሚኖር ማለት ነው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2012
ይበል ካሳ