የገበያ ገዱ የቆመለት የአንዲት ቀን ገበያው ወይም ሽያጩ የዓለምን የመረጃ መረብ የሽያጭ ክብረ ወሰን የተሻገረ ይሆንለታል፡፡የመገበያያ አውታር የሌለው ደግሞ ምንም ምርጥ ዕቃ ቢኖረው የሚሸጠውን ዓይን ዓይኑን እንዳየ ውሎ ያድራል፡፡ ይህ ሁነት የነባራዊው ዓለም ሁለት ገጽታ ነው፡፡
ስመ ጥሩውና ዝነኛው የቻይና የኢንተርኔት የንግድ ኩባንያ ‹‹አሊባባ››ባለፈው ጊዜ በአንድ ነጠላ ቀን ብቻ በራሱ ተይዞ የቆየውን የዓለምን የኢንተርኔት ዕለታዊ የዘጠኝ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የዕለት ሽያጭ ክብረወሰን በማሻሻል ከ13 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረሱን የዓለም መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው ይታወሳል፡፡
ይህ የንግድ ተቋም በልዩ የሽያጭ ፌስቲቫል ላይ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ምርቶችን ለሽያጭ ማቅረብ በአንድ ደቂቃ ከ120 ሺህ በላይ የግዢ ጥያቄዎችንና 60 ሺህ ክፍያዎችን ማከናወኑና በሞባይል አማካይነት በአንድ ሰዓት ውስጥ 27 ሚሊዮን ግብይቶችን መፈጸም መቻሉ ፤ የሸጣቸውን የኤሌክትሮኒክስና የመዋቢያ ዕቃዎች ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦችን በአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን መልዕክተኞች፣ በ400 ሺህ መኪኖችና በ200 አውሮፕላኖች ለገዢዎች ማድረስ መቻሉ የተደራሽነቱን ጉዳይ የተሳካለት ንግድ ያሰኘዋል፡፡
ከነገዱ አይቀር እንዲህ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የንግድ አውታር የአሊባባ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጃክ ማ ነው ሰሞኑን ወደ አገራችን መጥቶ የተስፋ ራዕይ ያሰነቀን፡፡ በዳቮስ የዓለም የምጣኔ ሀብት ጉባዔ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የአሊባባ ቡድን ሥራ አስኪያጅ ተገናኝተው ማውራታቸው የትብብር ምዕራፉን ከፋች መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡
በዚያ ወቅት እንደተነገረው ጃክ ማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የለውጥ መርሐ – ግብር አድናቂ ስለነበሩ አብረው ለመስራት መልካም ፍላጎታቸውን የገለጹበት፣ ቡድናቸው ከሚሰራው ከኢንተርኔት ንግድ ጋር በተያያዘ ለሀገራችን የሚጠቅሙ ነገሮችን ለመስራት የተስማሙበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጉብኝቱ ወቅት አሊባባ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት እንዲያደርግ ግብዣ በማቅረባቸው ጃክ ማ በህዳር ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀው ነበር። ያ መልካም አጋጣሚ የፈጠረው ቀጠሮ የንግድ ተቋሙን ኃላፊ ወደ አገራችን አምጥቶ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አስችሏቸዋል፡፡ ደርጅታቸው አሊባባም ከኢትዮጵያ ጋር በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ለመገንባት ስምምነት ፈርሟል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛው ኢኮኖሚዋ የተመሰረተው በግብርና ላይ ቢሆንም በቀጣይ ለኢኮኖሚው በተሰጠው ትኩረት በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ለሚፈጠረው ሥራ ከወዲሁ ጅምር ተግባር ለማከናወን በቴክኖሎጂው ዘርፍ በስፋት መሰማራቷ የአፈጻጸሙ ግማሽ ርምጃ ይሆናል፡፡
እንዲህ አይነቱ የኢንተርኔት ግብይት ዘርፍ ጥሩ የኢንተርኔት የትስስር አገልግሎትና የተማረ የህብረተሰብ ክፍል የሚሻ ቢሆንም በተለይም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሥራ ፈላጊ ወጣት በመሆኑ አሊባባ ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረጉ ውጤታማነቱ ከወዲሁ እንደሚረጋገጥ አያጠያይቅም፡፡
ኩባንያው በዓለም ዙሪያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለ40 ሚሊየን ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ቢሆንም እስካሁን ከአፍሪካ በሩዋንዳ ብቻ ነው ሥራውን እየከወነ የሚገኘው፡፡ የአሁኑ ጉብኝትም ኩባንያው ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ስራውን ለማስፋፋት የያዘው እቅድ አንድ አካል ነው፡፡
የአሊባባ ግሩፕ መስራችና ባለቤት ጃክ ማ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ ማእከል ግንባታ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ጅማሬ በመሆኑ በቀጣይ አፍሪካውያን በኤሌክትሮኒክ ንግድ ከአውሮፓውያን፣አሜሪካውያንና ቻይናውያን እኩል ተፎካካሪ ለመሆን እንደሚያስችላቸው ያላችውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
በዚህ የዲጂታል ኢኮኖሚ አማካኝነት በአነስተኛ ቢዝነስ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ሥራ ፈጣሪዎች ዓለም አቀፍ ንግድ ለማካሄድ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስኬት ወጣት ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የተቀሩ የአፍሪካ ሀገራትንም ከዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያነሳሳቸውም ተናግረዋል፡፡
እውነት ነው ይህ የኢትዮጵያ ውጥን ተግባራዊ ሆኖ አሁን የተያያዝነው የለውጥ ጅማሬ ፍሬ ማፍራት ሲጀምር የዜጎቻችን ስራ አጥነት ይቀረፋል፤ ሁለንተናዊ እድገት ይመጣል፤ ለዚህ ሁሉ መሰረቱ ሠላም በመሆኑ የውጥናችን ስኬት ሰላማችን መሆኑ ሁሌም ሊታወስ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012