ክፍል ሁለት
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ከሰሞኑ የተከበረውን የሳይበር ሳምንት ሰበብ አድርገን ባለፈው ሳምንት በረቡዕ የጋዜጣ ዕትማችን በዚሁ ርዕስ የመጀመሪያውን ክፍል ጽሁፍ ማቅረባችን ይታወሳል። ተከታዩን ክፍል እነሆ!
ሕገ ወጥ የኮምፒውተር ዳታ ይዘትን የማሰራጨት ወንጀሎች
በኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 መሰረት የመጀመሪያው የኮምፒውተር ወንጀል በኮምፒውተር፣ በኮምፒውተር ሥርዓት፣ በኮምፒውተር ዳታ ወይም ኔትወርክ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው። ሁለተኛው ደግሞ እነዚህን በመጠቀም የሚፈጸም ወንጀል ነው። ሕገወጥ ዳታን ማሰራጨት ደግሞ ሶስተኛው የወንጀሎች ዘውግ ነው። “ሌሎች ወንጀሎች” ተብለው በሕጉ የተቀመጡ ዘውግ-አልባ ወንጀሎችም አሉ።
በህጋችን የተቀመጠው ሶስተኛው የኮምፒውተር ወንጀሎች ዘውግ በኮምፒውተር፣ በኮምፒውተር ሥርዓት (ሲስተም) ወይም ኔትወርክ አማካኝነት ሕገወጥ የኮምፒውተር የይዘት ዳታን ማሰራጨት ነው። በሕጉ አገላለጽ “የኮምፒውተር ዳታ” የሚባለው በኮምፒውተር ሥርዓት አማካኝነት ሊተነተን የሚችል ማንኛውም የይዘት ዳታ፣ የትራፊክ ዳታ፣ የኮምፒውተር ፕሮግራም ወይም ደንበኞችን የሚመለከት ማንኛውም ኢንፎርሜሽን ነው።
ሕገወጥ የይዘት ዳታ የማሰራጨት ወንጀሎች ከሚባሉት ውስጥ የመጀመሪያው ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸም ጸያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ወንጀል ነው። ይህም ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ወይም አዋቂ ሰው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ መስሎ ወሲባዊ ድርጊት በግልጽ ሲፈጽም የሚያሳይ ስዕላዊ መግለጫ፣ ፖስተር፣ ቪዲዮ ወይም ምስል የኮምፒውተር ስርዓትን በመጠቀም ሆነ ብሎ ማዘጋጀት፣ ማሰራጨት፣ ለሽያጭ ማቅረብ፣ ማከፋፈል፣ ሌሎች እንዲያገኙት ማመቻቸት ወይም ይዞ መገኘት ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ንግግሮችን፣ ስዕሎችን፣ የጽሁፍ መልዕክቶችን ወይም ቪዲዮዎችን በኮምፒውተር ስርዓት አማካኝነት በማሰራጨት ወይም በመላክ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን ለወሲባዊ ድርጊት ማነሳሳት ወይም መመልመልም የሳይበር ወንጀል ነው።
በተለመደው አነጋገር አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ሕጻናት ይባላሉ። ሕጻን ማለት ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ስለመሆኑ የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ ደንግጓል። ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ (ኢሞራላዊ) ድርጊት የሚባለው ጠቅላላ አነጋገር ግን “እንዲህ ማለት ነው፤ መለኪያው ይሄ ይሄ ነው” ለማለት ያዳግታል። ምክንያቱም ሞራል (መልካም ጠባይ) የሚባለው ከሰው ሰው፣ ከማህበረሰብ ማህበረሰብ፣ ከሐይማኖት ሐይማኖት የተለያየ አተያይና አንድምታ ስላለው ነው። ያም ሆኖ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ የተለያዩ ልሂቃን ከጻፏቸው ስንክሳሮች መቃረም እንደምንችለው የአንድ ድርጊት ሞራላዊነት (ኢሞራላዊነት) የሚለካው ከማህበረሰቡ ወግና ልማድ፣ ባህልና እምነት እንዲሁም ከአካባቢውና ከጉዳዩ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እየተመዘነ መሆን ይገባዋል።
የተነሳንበትና በአገራችን የሳይበር ሕግ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ ናቸው ተብለው የተዘረዘሩት አድራጎቶች በአንድ ማህበረሰብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ማዕዘናተ-ዓለም ጸያፍ፣ ክብረ ነክ፣ ጨዋነት የተጓደለባቸው፣ አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊቶች በመሆናቸው ኢሞራላዊነታቸው አይጠረጠርም። በመሆኑም ሕጋችን ባለንበት ዘመነ-ቴክኖሎጂ የኮምፒውተር ሥርዓትን በመጠቀም እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ የይዘት ዳታዎችን ማሰራጨት ወንጀል አድርጎ መቅጣቱ ይበል የሚያሰኘው ነው።
ሕገወጥነት ያላቸውን የዳታ ይዘቶችን ማሰራጨት በሚለው የሳይበር ወንጀሎች ዘውግ ስር የተመደበው ሁለተኛው ድርጊት የሰዎችን ነጻነትና ክብር መንካት ነው። ይህም የኮምፒውተር ስርዓትን በመጠቀም በሚሰራጭ ጽሁፍ፣ ንግግር፣ ቪዲዮ ወይም ስዕል አማካኝነት በሌላ ሰው ወይም በተጎጂው ቤተሰቦች ላይ ከባድ ጉዳት ወይም አደጋ ለማድረስ በማሰብ ማስፈራራት ወይም መዛት ነው። በተጨማሪም ተጎጂውን ወይም ቤተሰቡን የሚመለከት መረጃ ወይም መልዕክት በተደጋጋሚ በመላክ፣ በማሰራጨት ወይም የተበዳዩን የኮምፒውተር ኮሙዩኒኬሽን በመከታተል ፍርሃትን፣ ስጋትን ወይም የስነ-ልቡና ጫናን መፍጠርም የሰውን ነጻነትና ክብር መንካት ነው።
የሥም ማጥፋትም እንዲሁ በዚሁ ሥር ይመደባል ነው። ይኸውም የሌላውን ሰው ክብር ወይም መልካም ሥም የሚያጎድፍ ጽሁፍ፣ ንግግር፣ ስዕል ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል በኮምፒውተር ሥርዓት አማካኝነት ማሰራጨት ነው። በሕብረተሰቡ መካከል አመጽ፣ ሁከት ወይም ግጭት እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ጽሁፍ፣ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ድምጽ ወይም ማንኛውንም ሌላ ምስል ሆነ ብሎ ማሰራጨትም የሳይበር ወንጀል ነው።
እነዚህን ድንጋጌዎች በማስቀመጡ አዋጁ ሀሳብን በነጻ በመግለጽ መብት ላይ ልጓም በማበጀት የግለሰቦችንና የማህበረሰብን መብት ብሎም የአገርን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ሚዛናዊ ለመሆን ሞክሯል። ይሁንና ድንጋጌው ከትችት ፍላጻ አላመለጠም።
“አርቲክል 19” የተሰኘው የመብት ተሟጋች የዓለም የሰብዓዊ መብቶች እናት በሚባሉት በዩኒቨርሳል ዴክለሬሽን ኦን ሒውመን ራይትስ እና በኢንተርናሽናል ኮቨነንት ኦን ሲቪል ኤንድ ፖሊቲካል ራይትስ አንቀጽ 19 ላይ የተጠቀሰውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መነሻ በማድረግ የተቋቋመ ነው። በአዋጁ ዙሪያ ባሰፈረው ጽሁፍ ታዲያ ድንጋጌዎቹ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚያቀጭጭ በመሆኑ ከአዋጁ እንዲሰረዙ ይሞግታል። ከሁሉም በላይ አንዳንድ አገራት በሳይበር ሕጋቸው የሥም ማጥፋትን መደንገጋቸው በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ጭምር ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን በመጥቀስ የአገራችንን አዋጅ በጽኑ ይኮንናል።
እርግጥ ነው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 29 የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት ተረጋግጧል። በዚሁ መሰረት ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው። “ይህ ነጻነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሁፍ ወይም በሕትመት፣ በስነ ጥበብ ወይም በመረጠው በማንኛውም ዓይነት የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና፣ የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል። ይሁንና የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል መብቶቹ በሕግ ሊገደቡ ይችላሉ” ይላል ሕገ መንግስቱ።
ይህን መሰረት አድርገን የኮምፒውተር አዋጁን ስንመዝነው በመርህ ደረጃ አርቲክል 19 እንዳለው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ይገድባል። ነገር ግን ድንጋጌዎቹ ከአዋጁ ሙሉ በሙሉ መሰረዝ አለባቸው በሚል መደምደም አይቻልም።
እርግጥ ነው ድንጋጌዎቹ ጋዜጠኝነትን በተለይም የምርመራ ዘገባን ያኮስሳል። ጋዜጠኛም ሆነ ማንኛውም ሰው የሹማምንትንና የአብሮ-በል ቱጃሮችን የሙስና ቅሌት መረጃዎችን የኮምፒውተር ሥርዓትን በመጠቀም ይፋ እንዳያደርግ ፍርሃትን ያጭራሉ። በድንጋጌዎቹ ውስጥ “ከባድ ጉዳት ወይም አደጋ”፤ “በተደጋጋሚ ማሰራጨት” ወዘተ… የሚሉት ቃላት ያልተተረጎሙ በመሆናቸው ለትርጉም የተጋለጡ ሆነዋል። እናም ድንጋጌዎቹ ጋዜጠኝነትንና የምርመራ ዘገባን በተመለከተ ልዩ ጥበቃ የሚያደርግ ሃሳብ ሊያካትቱ ይገባቸዋል የሚለው የሚያስማማ መንገድ ነው።
ከዚህም ሌላ አዋጁ በመግቢያው ላይ “የሕጉ ድንጋጌዎች ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም አለባቸው” የሚል አንቀጽ ሊያካትት እንደሚገባው “Cybercrime in Ethiopia: Lessons to be Learned from International and Regional Experiences” በሚል እያሱ ተከተል እ.ኤ.አ. በ2018 ለማስተርስ መመረቂያ ባሰናዳው ጽሁፉ ላይ ያሰፈረውን ምክረ ሀሳብ መተግበሩም ጠቃሚ ነው።
የሰውን ነጻነትና ክብር ከመንካት ጋር በተያያዘ አከራካሪ የሆነው ሌላው ጉዳይ የአገልግሎት ሰጪዎችን የወንጀል ተጠያቂነት ነው። አገልግሎት ሰጪዎች (በኮምፒውተር ሥርዓት አማካኝነት ቴክኒካዊ የዳታ ፕሮሰሲንግ ወይም የግንኙነት ስርዓት አገልግሎት የሚያቀርቡ ለምሳሌ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ፣ ሰርች ኢንጂንስ፣ የማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ድረ-ገጾች) በሚያስተዳድሩት የኮምፒውተር ሥርዓት አማካኝነት ለተሰራጨ ሕገወጥ የይዘት ዳታ የወንጀል ተጠያቂነት ተጥሎባቸዋል።
አርቲክ 19 ድንጋጌው ሙሉ በሙሉ ከአዋጁ እንዲሰረዝ ነው የሚሞግተው። ሕጉ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎቻቸው እንዲሁም ቀጣሪ ኩባንያዎች እና መስሪያ ቤቶች ለሰራተኞቻቸው በሚያቀርቡት አገልግሎት ምክንያት የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን በመጥቀስም ሙግቱን ያጠናክራል። በምትኩም በአገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሲቪል ግዴታ ብቻ (ማሳወቅ፣ የገንዘብ ቅጣት፣ መታገድ፣ መዘጋት) እንዲጣልባቸው ይመክራል።
በተቃራኒው ግን እያሱ ተከተል ከላይ በጠቀስኩት የመመረቂያ ጽሁፉ ላይ የአርቲክል 19ን ሙግት በመንቀፍ አገልግሎት ሰጪዎች በሕጉ በወንጀል የሚጠየቁት በመርህ ደረጃ ሳይሆን በሕገወጥ የዳታ ስርጭቱ ላይ እውቀትና ተሳትፎ ካላቸው ብቻ በመሆኑ የሚጠየቁበት አመክንዮ ቅቡልነት ያለው መሆኑን ያሰምርበታል።
ያም ሆነ ይህ የአገልግሎት ሰጪዎች ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ መሆን አለባቸው የሚለው የአርቲክል 19 ሙግት ውሃ የሚያነሳ አይመስልም። በድንጋጌው በግልጽ እንደተመለከተው አገልግሎት ሰጪዎች በሕገወጥ ዳታው ላይ ተሳትፎ እና እውቀትም ካላቸው በወንጀል ሊጠየቁ ይገባል። ከዚህ ውጭ ግን አዋጁ መታገድና መዘጋትን የመሳሰሉ ርምጃዎችንም ማካተት ይኖርበታል።
ከሁሉም በላይ የወንጀል ቅጣቱን በተመለከተ ነጻነትና ክብር የሚነካ ሕገወጥ ዳታ ያሰራጨውን ሰው ለመቅጣት የተቀመጡት የእስራት ቅጣቶች በአገልግሎት ሰጪዎች ላይም እንደሚጣሉ መደንገጉ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ሊስተካከል ይገባዋል። አገልግሎት ሰጪው ግለሰብ ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል ከሆነ ተጠያቂነቱም በዚሁ አግባብ ተለይቶ ኃላፊነት ያለበትን አካል ለይቶ ተጠያቂ በሚያደርግ አግባብ መቀረጽ አለበት።
የምርመራ፣ የማስረጃና የሥነ-ሥርዓት ሳንካዎች
አዋጁ ከምርመራና ማስረጃ ከማሰባሰብ ጋር በተያያዘ ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ ድንጋጌዎችን አካቷል። በዚህም በወርሃ-የካቲት 2003 ዓ.ም. በጸደቀው የአገራችን የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ ውስጥ የተቀመጡትን አቅጣጫዎች ሕጋዊ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል። ይሁንና በምርመራ፣ ማስረጃና የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎቹም ላይ ቁልፍ ሳንካዎች አሉበት።
የመጀመሪያው ለመንግስት አካላት የተለጠጠና ተቀባይነት የሌለው ሰፊ ሥልጣን መስጠቱ ነው። የምርመራም ሆኑ የመከላከል ስራን የሚያከናውኑ አካላት ሊኖራቸው የሚገባው ሥልጣን ሕጋዊነት፣ ተመጣጣኝነት (Proportional) እና አስፈላጊነት (Necessity) የተባሉትን ሕግ ማርቀቅ (Legal Drafting) መርሆዎች የተከተለ መሆን አለበት። ሕጎች ይህንን መሰረት ካላደረጉ የመንግስት አካላት የዜጎችን መብት እንዲጥሱ ያግዟቸዋል።
በዚሁ መሰረተ-ሀሳብ የኮምፒውተር አዋጁን ድንጋጌዎች በምንቃኝበት ወቅት ለመንግስት አካላት የተለጠጠ ሥልጣን የሚሰጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለዚህ የመጀመሪያው ማሳያ ለፖሊስ የተሰጠው ሥልጣን ነው። በአዋጁ መሰረት መርማሪ የኮምፒውተር ዳታ ለማሰባሰብ የብርበራ ሥራውን ሲያከናውን ብርበራ በተከናወነበት የኮምፒውተር ሥርዓት ውስጥ የቀረውን ዳታ በምንም መልኩ ተደራሽ እንዳይሆን (ማጥፋትንም ጨምሮ) የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ይህ ሥልጣን ሕጋዊነት የጎደለውና ተመጣጣኝ ያልሆነ (Disproportionate) ነው። ምክንያቱም መርማሪ አካል ተቀዳሚና ብቸኛ ሥራው ማስረጃዎችን ማሰባሰብ፣ መተንተን፣ ማጠናቀርና የመወሰን ሥልጣን ላለው የምርመራው መሪ አካል (ዓቃቤ ሕግ) መስጠት ነው። ከዚህ ውጭ ግን ከወንጀሉ ጋር የተገናኘም ይሁን እንደሕጉ አነጋገር “በተበረበረው ኮምፒውተር ውስጥ የቀረውን ዳታ” ተደራሽ እንዳይሆን የማድረግ ሥልጣን ለመርማሪ መሰጠቱ አግባብነት የለውም። ይህም ፖሊስ በብርበራ የሰበሰበውን ዳታ ለምን ያክል ጊዜ ይዞ ማቆየት አለበት የሚለው በአዋጁ ካለመገለጹ ጋር ተዳምሮ አንዳንድ ሥነ-ምግባር የሌላቸው መርማሪዎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የመደራደሪያ መሳሪያ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ግልጽ ነው።
ሌላው አከራካሪ ጉዳይ መርማሪ በብርበራ እንዲያዝ የተፈለገውን የኮምፒውተር ዳታ የፍርድ ቤት የብርበራ ፍቃድ በወጣበት የኮምፒውተር ሥርዓት አማካኝነት ሊገኝ በሚችል ሌላ የኮምፒውተር ስርዓት ውስጥ የተከማቸ መሆኑን በበቂ ምክንያት ሲያምን ድጋሚ የፍርድ ቤት ፈቃድ ሳይጠይቅ የብርበራ ስራውን ማከናወን ወይም ደራሽነትን (access) ማግኘት እንደሚችል የሚገልጸው ነው።
ይህ በአንድ የብርበራ ፈቃድ ሌላ ኮምፒውተርንም እንዲበረብር ሥልጣን የሚሰጠው ድንጋጌ ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 26 (የግል መብት) ጋር የሚቃረን በመሆኑ ሕጋዊነት የጎደለው ነው። ዶክተር ክንፈ ሚካኤል ይልማ “Some Remarks on Ethiopia’s New Cybercrime Legislation” በሚል በሚዛን ሎው ሪቪው መጽሄት ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ድንጋጌው የግለሰቦችን መብት የሚጋፋ መሆኑን በመጥቀስ መኮነናቸውም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።
ከብርበራ ትዕዛዝ ጋር በተያያዘ ጥያቄ የሚነሳበት ሌላው ጉዳይ መርማሪ ከምርመራው ጋር በተያያዘ ዳታ ለማየት ወይም ለማግኘት እንዲችል ለፍርድ ቤት ሲያመለክት ፍርድ ቤት ጥያቄውን ካመነበትና ጉዳዩ የሚመለከተውን ሰው መጥራት ካላስፈልገው ማንኛውም ሰው በእጁ የሚገኘውን ዳታ ለመርማሪው እንዲሰጥ ወይም እንዲያሳይ ሊያዝ እንደሚችል በአዋጁ መቀመጡ ነው።
የሳይበር ወንጀሎች ልዩ ባህርይ እንደተጠበቀ ሆኖ ድንጋጌው “Due Process of Law” የሚባለውን የሕግ መርህ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው። ማለትም መረጃ እንዲሰጥ የተፈለገው ሰው ተጠርቶ፣ ቀርቦ፣ አድምጦ፣ ተደምጦ፣ ተከራክሮ፣ በቂ ምክንያት ይኑረው አይኑረው ተረጋግጦ ከእርሱ የሚፈለገውን መረጃ እንዲሰጥ ሊታዘዝ እንደሚገባ የተቀመጠውን መርህ የጣሰ ነው።
ከሥነ-ሥርዓት ጋር በተያያዘ በአዋጁ ውስጥ የተካተተው አከራካሪ ነጥብ የማስረዳት ሸክም ጉዳይ ነው። በአዋጁ መሰረት በመርህ ደረጃ በክሱ ላይ የተመለከተውን ፍሬ ነገር የማስረዳት ሸክም ያለበት ዓቃቤ ሕግ ቢሆንም መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን ካስረዳ እና ፍርድ ቤት የማስረዳት ኃላፊነቱን ወደተከሳሹ ማዞር አስፈላጊ መሆኑን ካመነ የማስረዳት ሸክሙ ወደ ተከሳሹ ሊዞር ይችላል።
በመርህ ደረጃ የዳበረውና በአዋጁም ተቀባይነት ያገኘው ሥርዓት መንግስት ከሳሽ ሆኖ የወንጀል ክስ ሲያቀርብ የማስረዳት ሸክሙ በትከሻው ላይ የተጣለበት መሆኑ ነው። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በውሳኔዎቹ ዓቃቤ ሕግ ክሱን የማስረዳት ሸክም ያለበት መሆኑን በማተት አስገዳጅ የሕግ አተረጓጎም መርህን አስቀምጧል።
ነገር ግን የሳይበር አዋጁ ዓቃቤ ሕግ መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን ካስረዳ የማስረዳት ሸክሙን ወደተከሳሽ እንዲዞር መፍቀዱ በብዙ መልኩ ሕጸጾች ያሉበት ነው። የሳይበር ወንጀሎች ቴክኒካዊ ግንዛቤ በሁሉም አካላት ገና አልዳበረም። ምርመራውም ሆነ የክርክር ሂደቱ ለአገራችን የሕግ ሥርዓት አዲስና ያልጎለመሰ ነው። አዋጁም ቢሆን መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉበት ተመልክተናል። “መሰረታዊ ፍሬ ነገር” የሚለው ቃል በራሱ በሕጉ አልተተረጎመም።
በእነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ታዲያ የማስረዳት ሸክምን ወደተከሳሽ እንዲዞር መፍቀድ አግባብነት የለውም። “ዓቃቤ ሕግ መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን አስረድቷልና የማስረዳት ሸክሙ ወዳንተ ዞሯል” በሚል ብይን መስጠትም የተከሳሽን ንጹህ ሆኖ የመገመት ሕገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ ነው እስከሚል የሙግት ጠርዝ ሊወስደን ይችላል።
በመሆኑም ድንጋጌውን ከአዋጁ በማስወጣት በሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት ዓቃቤ ሕግ ክሱን በበቂ ሁኔታ በማስረጃ ካላረጋገጠ ተከሳሹን በነጻ ማሰናበት፤ ክሱን ካስረዳ ደግሞ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን በመስጠት ንጹህ መሆኑን እንዲያረጋግጥ፤ ካላረጋገጠ ግን ጥፋተኝነቱን ማወጅ አግባብነት ያለው ሥነ-ሥርዓት ነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2012
በገብረክርስቶስ