በየትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በይበልጥ ራሳቸውን በጣም ውስብስብና እርግጠኛ መሆን በማይቻልበት ምህዳር ውስጥ ማግኘታቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ለውጥ በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና በፓርቲው አደረጃጀት እንዲሁም በውጫዊ ከባቢያዊ ሁኔታ ውስጥ መደበኛ ክስተት ነው።
የዴሞክራሲ ስርዓት ባሉባቸው አገራት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜው የሚጠይቀውን ለውጥ በማድረግ በሚገኙባቸው ማህበረሰቦች ዘንድ ተቀባይትን እያገኙ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ የለውጥ ምክንያቶችን በመቀበል ረጅም ርቀት መጓዝ የቻሉ እንደሆነ ካለው ዓለምአቀፍ ልምድ መረዳት እንችላለን። በተመሳሳይ መልኩ ራሳቸውን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመውና ለውጠው የማይጓዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የሚዳከሙበት ወይም የሚጠፉበት እድል እንደሚኖርም ያለው ልምድ ያሳየናል። የዜጎቻቸውን ፍላጎትና ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ራሳቸውን እያስተካከሉ የሚሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘለግ ያለ ጊዜን መጓዝ ይችላሉ።
በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከግብጽ እስከ ቺሊና ታይላንድ በቅርብ ጊዜ የተከሰቱ ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ተግዳሮት የፈጠሩባቸው ሲሆን፤ በተለይም ዜጎችን የሚወከሉበትን አዳዲስ መንገዶች እንዲፈልጉና የዴሞክራሲ ተሳትፎ መንገዶች ቀጥተኛ እንዲሆን ያደረጉበት ሁኔታ ተከስቷል። አዳዲስ የመረጃና የቴክኖሎጂ ውጤቶችም በፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠሩት ተጽዕኖ ከፍተኛ ሲሆን፤ እንደ ማህበራዊ ሚድያ የመሳሰሉት የዜጎችን የፖለቲካ ሀሳብ መግለጫን ያቀላጠፉ ለውጦች ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰሩበትን መንገድ እንዲቀይሩና እንዲያሻሽሉ ያስገደዷቸውም ሁነዋል።
በቅርብ ጊዜ በጀርመን በፓርቲ ሪፎርም ላይ የተሰራው ፕሮጀክት ላይ በተደረገው ገለጻ ከወቅታዊ (ዘመናዊ) ልኬቶች ጋር የድርጅት መዋቅር ለዘመናዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሁነኛ አጀንዳ እንደሆነ ያስረዳል። በማህበረሰቡ ውስጥ ተወዳጅና ቅቡል ለመሆን ፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን እስካሁን ከሰሩበት በበለጠ ሁኔታ በቁርጠኝነት (resolutely) ሊቀይሩ እንደሚገባ ተወስቷል። ይህንን ለማድረግ ከምንኖርበት ከባቢያዊ ሁኔታ ጋር ሊጣጣሙና ብዝሀነት ያለውን ነባራዊ ዓለም ሊያረካ የሚችል ትልም ሊኖራቸው ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪም የዲሞግራፊ ለውጥ የዲጂታል አብዮት እንዲሁም ማህበራዊ መዋቅር ልዩነት ባመጧቸው ተጽዕኖዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እቅዶቻቸውን ግቦቻቸውንና ስልቶቻቸውን ማጤን እንዳለባቸው በተለይም ለተቀየረው ማህበረሰብ ሲባል እያጣጣሙ መሄድ እንዳለባቸው ግልጽ የሆነ ጉዳይ መሆኑን ይሄው በጀርመን በፓርቲዎች ሪፎርም ላይ የተደረገው የጥናት ፕሮጀክት ያስረዳል። በመቀጠልም በ21ኛው ምእተዓመት የሚገኙ ዘመነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች(contemporary political parties ) ምን መምሰል አለባቸው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ለዜጎች ራሱን እንዴት ተወዳጅ አድርጎ መለወጥና መስራት ይችላል የፖለቲካ ፓርዎች ውጤታማ ከሆኑ ካምፓኒዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ታላላቅ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ምን አይነት ተሞክሮ መውሰድ አለባቸው የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ያወሳሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጭው ጊዜ የፖለቲካ ሁኔታዎች በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ካለባቸውና መለወጥ ካለባቸው በአደረጃጀታቸውና ሌሎች መሰረታውያን ላይ በቂ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርጅታዊ መዋቅርና ሂደቱ በጣም ፈጣንና ተለዋዋጭ የሆነውን በዙሪያው የሚታየውን የፖለቲካ ከባቢያዊ ሁኔታ ማንጸባረቅ የቻሉ እንዲሆኑ ፓርቲዎች ራሳቸውን ማብቃትና መላመድ የሚችሉበትን ሁኔታ እንደሚፈጥርና ራሳቸውን እያዘጋጁ መሄድ እንዳለባቸው ይታመናል። ይህ ማለት ዙሪያውን መተንተንና ከአዳዲስ ክስተቶች ጋር ራስን እያዋሃዱና እያላመዱ በይበልጥም ከፓርቲው ውሰጥ የሚገኘውን መጠነ ሰፊ ግብአት ጥቅም ላይ በማዋል የሚመጣ ለውጥ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ፖርቲዎች በህዝብ ዘንድና በአባሎቻቸው ቅቡልነታቸው እንዲሁም ያስቀመጧቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግቦች በተሻለ ሁኔታ የተሳኩ እንዲሆኑና ጊዜውን የሚዋጅ አስፈላጊ የሆነ ምላሽ ለመስጠት ያስችላቸው ዘንድ ሪፎርም ያደርጋሉ። በፖለቲካ ፖርቲዎች ዘንድ በተለያየ ደረጃዎችና መንገዶች ሪፎርሞቹን ማካሄድ እንደሚችሉ መረዳት እንችላለን። የፖርቲዎችን ውስጣዊ ሁኔታ ማጠናከር /strengthening the internal life of Political parties / በተወሰነ መልኩ በነዚህ መገለጫዎች ሊካተት ይችላል።
The potential publicity surrounding the event is an important incentive to adopt organizational innovations. Consistent with the undaerlying rationale of a reform as opposed to organizational change more generally, ‘going public’ with ‘something positive’ and catching the eye of the media and the public is just as—if not more—important than the substance of the change itself. (Gauja, 2017)
በፖለቲካ ድርጅት የሪፎርም ሥራዎች ላይ ሶስት መነሻ የሆኑ አብይት ጉዳዮች በጽንስ ሀሳብ ደረጃ የሚቀርቡ ሲሆን፤ አንደኛው በፖርቲው ውስጥ ያለውን እርካታ ለማሻሻል ከመጣ ፍላጐት የመነጨና የአባላት ቁጥር ለማዝለቅ ከመጣ ተቋማዊ ዕቅድ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው። ሁለተኛው በድርጅቱ ውስጥ የሰፈነውን የኃይል ሚዛን ለማስተካከል ካለመ ስልታዊ ፍላጐት ጋር የተቆራኘ ሲሆን፤ የግለሰቦችን የተጽዕኖ አቅም ለመጨመርና የሌሎች ቡድኖችን ኃይል ለመቀነስ ያለመ ይሆናል። ሶስተኛው ደግሞ በድርጅቱ ታሪክና በርዕዮተ ዓለሙ አውድ ዙሪያ መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችን ለማስመዝገብ ፍላጐትን ያነገበ የተደራጀ ኃይል መኖሩ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው ተነሳሽነት በውስጣቸው ያለውን ዴሞክራሲ ለማበልጸግ በጣም ጉልህ የሆኑ ሪፎርሞችን ያደርጋሉ። የፖለቲካ ድርጅቶች በርከት ባሉ አገሮች የውሳኔ ሰጭ ሂደትን በተመለከተና የዕጩና የአመራር ምርጫዎችን ሂደት በተመለከተ ለአባሎቻቸው የበለጠ ክፍት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይገለጻል። በዚህም ምክንያት መደበኛ አባላት ከዚህ በፊት በፓርቲው ልሂቃንና ጦማሪያን ተይዘው የነበሩ ሚናዎችን የመያዝ እድል እንደተፈጠረላቸውና በፓርቲው ጉዳዮች ላይ በንቃት የመሳተፍ እድል እንደተከፈተላቸው ይታወቃል።
ከዚህ ዓለምአቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን እንዲሁም በፅንሰሀሳብ ደረጃ ከተቀመጠው ባሻገር ከልምድም እንደምናየው ኢህአዴግ ባለፈባቸው የታሪክ ወቅቶች ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ በአደረጃጀት በአሰራር በፕሮግራም በርዕዮተዓለም በታክቲክና በስትራቴጂ ለውጦችን እያደረግ የዘለቀ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ለዚህም በተለያዩ ጉባኤዎች በተለያየ ዘርፍ ያደረጋቸው ለውጦች ምስክር ናቸው።
አሁን በምንገኝበት ወቅት ደግሞ ባሉት ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ መንስኤዎች ድርጅቱ ሲፈተን የቆየና መለስተኛ ጥገናዊ ለውጦችን ሲያደርግ በመጣበት ልክ ሳይሆን መሰረታዊ ለውጦችን በማድረግ ምላሾችን በመስጠት ገፅታውን መቀየር ያለበትና በሚጠበቀው ልክ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዳይናሚክስ ሊመጥን በሚያስችል ሁኔታ ለውጦችን ማካሄድ የሚገባው ጊዜ ላይ እንገኛለን።
በሀገራችን የቅርብ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመንግሥትን ስልጣን ተቆጣጥሮ የቆየ የፖለቲካ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በፖለቲካውና በኢኮኖሚው መስክ ግዙፍ ሚና የነበረው የፖለቲካ ድርጅት መሆኑ ግልፅ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ተጨባጭ የሆኑ የመጡ አዎንታዊ ለውጦች እንደነበሩ ሁሉ በርካታ ስህተቶች አብረው የተፈጸሙበት ወቅት እንደነበር ይታወቃል። አሁንም በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ከዚህ አዳፋ ታሪክ በመላቀቅ በአዲስ ምዕራፍ ለመጓዝና ቀጣይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የቤት ሥራዎችን ለማከናወን ኢህአዴግ ራሱን በተገቢው ሁኔታ ሪፎርም አድርጎ መምጣት ይኖርበታል።
የፖለቲካ ፖርቲዎች ሪፎርም እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው ውጭዊና ውስጣዊ ሁኔታዎች ሲኖር ተለዋዋጭ ከሆነ እያደገ ከሚመጣው የህዝብ ንቃተ ህሊና የዓለም አቀፍ ሁኔታና እንዲሁም ከባቢያዊ ሁኔታዎች ወሣኝ ሚና የሚጫወቱ ናቸው። ከዚህ ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲው የደረሰበትን የተቀባይነት ችግር ወይም ጉዳት ሊያስተካክል በሚችል መልኩ ሪፎረም ሊያካሂድ ይችላል። Party reform was also seen as an appropriate way in which to address the negative public perceptions caused by political scandals.
አሁን የተጀመረው የግንባሩ ውህደት የድርጅቱን መሰረታዊ የሆነ የአደረጃጀትና ሌሎች የፓርቲ መሰረታውያን በማስተካከል ብቻ የሚወሰን ሳይሆን እንደ ገዥ ፓርቲ እያደረጋቸው ያሉ አጠቃላይ ለውጦችን ብቻም ሳይሆን የፓርቲውን ገፅታ በተጨማሪም የሚቀይርለት ይሆናል።
ከግንባሩ የአደረጃጀት ለውጥ ጋር በተያያዘ የድርጅቱ ሪፎርም ሥራ የተለወጠ መልክ እንዲኖረውና በአዲስ መንፈስ ሥራዎችን መስራት የሚያስችለው እንደሚሆን ይጠበቃል። የፖለቲካ ፓርቲ ሪፎርም ሥራ በሂደትና በውጤትም አብሮ ሊሄድ የሚችል ሁለቱንም ያጣመረ ሥራ እንደሆነ ጽሁፎች ይገልፃሉ። በሂደት ደረጃ የፓርቲ ሪፎርም ለፖለቲካ ድርጅቱ በህዝብ ዘንድ ያለውን ገጽታ የሚያሻሽልበትና ፓርቲው ሪብራንድ ማድረግ የሚያስችልበትን ሁኔታዎች የሚያመቻችለትና ትኩረት መደረግ በሚገባቸው የቅድሚያ ሥራዎች ላይ ለማመላከትና ፓርቲው ውስጥ ያለውን የስልጣን ግንኙነት ለመለወጥ የሚያስችለው እንደሆነ ይገለፃል። በዚህ እይታ የፖርቲ ሪፎርም ከተለመደው የተቋም ሪፎርም በላይ እንደሆነና ቅቡልነትና የብራንዲንግ ሥራዎችንም የያዘ መሆኑንም ያመለክታል።
As an outcome, reform is captured in deliberate and often very public changes to parties’ organizational rules and/or processes. As a process, reform offers the party the opportunity to ‘rebrand’ and publicly alter its image, to emphasize certain strategic priorities over others, and to alter relationships of power within the party. In this sense, party reform is also much more than organizational change—it is equally a process (rather than being exclusively outcome oriented) and a legitimating or branding activity. (Gauja 2017)
በግንባሩ ውስጥ ለበርካታ ጊዜ የተፈተሹ ችግሮችን ለማስተካከል በተለይም በአካባቢያዊ ማንነትና በሀገራዊ አንድነት መካከል የሚታየውን ዝንፈት ለማስተካከል ሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች ቁርጠኛ መሆን የሚገባቸው ሲሆን፤ ትናንት ሲዳከርበት በነበረው ሁኔታ መቀጠል አደጋው ለሁሉም መሆኑን በመገንዘብ የጋራ የፖለቲካ ሥራዎችን መስራት የሚገባ ነው ብዬ አምናለሁኝ። በጣም በተለጠጠ ጽንፈኛ ብሄርተኝነት የፖለቲካ አውድ ውስጥ አስማሚና ሀገርን የሚገነባ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በአደረጃጀት ይህንን ሊደገፍ የሚችል አማራጭ ይዞ መምጣቱ ለሀገራዊ አንድነት እንዲሁም ያለውን የተካረረ አቋም ለማለዘብ ጉልህ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ በግንባሩ ውስጥ የነበሩ ሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች የመጡበትን የኋላ ጉዞ በመቃኘት ያለውን መልካም እድል በመጠቀም አሁንም በዚህ ወሳኝ ታሪካዊ ምእራፍ ላይ ስማቸውን በማደስ በጋራ መንቀሳቀስ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። ይሄንን አጋጣሚ በማምከን በተጀመረው የለውጥ ምእራፍ ላይ የምናበረክተው አንዳችም በጎ ነገር የሌለ ሲሆን፤ ተቀራርቦ ለመስራት ያሉ ችግሮችንም በጋራ ለመቅረፍ እንዲሁም ተጠናክረው መሰራት ያለባቸውን ጉዳዮች ለማከናወን አመቺ ስለሆነ ይህንንም በውል በማጤን ከዜሮ ድምር የፖለቲካ ስሌት በመውጣት በጋራ መቆም ያስፈልጋል።
በግንባሩ ውስጥ የሚታዩት የሀሳብና የተግባር መነጠል እንዲሁም በየብሄራዊ ድርጅቶች መካከል ያሉት ፅንፍ የወጡ ሁኔታዎችን ሊቀይር በሚችል መልኩ እየተሰራበት ያለው የውህደት አጀንዳ ለሁሉም መልካም እድል እንደሆነ በመገንዘብ ለጋራ ስኬት በመረባረብ ባንድ ላይ መቆም የሚበጅ ይመስለኛል። ይሄኛው እድልን አለመጠቀም የሚያመጣልን ምንም አይነት ወደፊት የሚያራምድ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ምእራፍ በማገዝ የተሻለ ታሪክ መስራት ይኖርብናል።
ማጣቀሻዎች (References)
Adrienne Lebas (2011). From Protest to Parties: Party-Building and Democratization in Africa. Oxford University Press.
André Laliberté and Marc Lanteigne (2008) The Chinese Party-State in the 21st Century Adaptation and the Reinvention of Legitimacy.
Anika Gauja(2017). Party Reform The Causes, Challenges, and Consequences of Organizational Change. Oxford University Press.
Charles S. Mack(2010) When Political Parties Die: A Cross-National Analysis of Disalignment and Realignment.
Charlotte P. Lee (2015) Training the Party Party Adaptation and Elite Training in Reform-era China Cambridge University Press
David B. Truman Party Reform, Party Atrophy, and Constitutional Change: Some Reflections The Academy of Political Science, Vol. 99, No. 4 (Winter, 1984-1985)
Donna Lee Van Cott (2005). From Movements to Parties in Latin America: The Evolution of Ethnic Politics. Cambridge University Press.
Giovanni Sartori. (2007) Parties and Party systems. Oxford University Press
Kalowatie Deonandan, David Close, and Gary Prevost (2007) From Revolutionary Movements to Political Parties Cases from Latin America and Africa. PALGRAVE MACMILLAN.
Presenatation of Results of Project on Party Reform in Germany (2015) Legitimation and Self Efficacy: Future Impulses for Party Democracy.
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2012
በአንተነህ መሉ (ረዳት ፕሮፌሰር)