የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አባል ድርጅቶች በአንድ ፓርቲ ሥር የማዋሀድ ሥራ እነሆ ተጀምሯል። 36 አባላት ያሉት የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ በመጀመሪያ የተመለከተው የፓርቲውን ውህደት አሳታፊነትና አካታችነት በተመለከተ ነበር። ቀጥሎም በፓርቲው ፕሮግራም እና ሕገ ደንብ ላይ ውይይት አድርጎ 180 አባላት ወደአሉት የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ (ምክር ቤት) እንዲተላለፍ ወስኖ የነበረ ሲሆን፤ ምክር ቤቱም ሰሞኑን ባደረገው ስብሰባ የውህደት ሀሳቡን ተቀብሎ አጽድቋል።
በዚህ የውህደት ሀሳብና ሒደት ላይ የኢህአዴግ መሥራች አባል የሆነው ህወሓት በልዩነት ራሱን ከማግለሉ በተጨማሪ ህዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ላለመሳተፍ መወሰኑን አስታውቆ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። የተቀሩት ሶስቱ ኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች አጋር የሚባሉትን የሶማሌ፣ የሐረሪ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል፣ የጋምቤላ ክልል ገዥ ፓርቲዎችን በመያዝ ውህደት ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ሒደት በማፋጠን ላይ ይገኛሉ። ሰሞኑን እንደተሰማው የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕዴን) እና የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ባካሄዱት ጉባኤ ወደ ብልፅግና ፓርቲ ለመቀላቀል ወስነዋል።
ጥቂት ነጥቦች ስለብልጽግና ፓርቲ
-የፌዴራል ሥርዓቱን የሚያስቀጥል መሆኑ፣
-ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የማይነካ መሆኑ፣
-አጋር የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያካተተ ድርጅት የሚፈጥር መሆኑ፣
-ብሔራዊ ማንነትን (አገራዊ አንድነት) ከብሔራዊ ማንነት ጋር በማስታረቅ፣ ከሚለያዩ ታሪኮች ይልቅ አንድ በሚያደርጉት ላይ በማተኮር፣ የሚጓዝ መሆኑ፣
-የቋንቋ ብዝሃነት የሚያከብር መሆኑ (የአዲሱ ፓርቲ የሥራ ቋንቋዎች ከአማርኛ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ፣ ሱማልኛ፣ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች…እንዲሆኑ ስለመ ታቀዱ)፣
-ፓርቲው በፕሬዚዳንት እና በምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ መሆኑ፣
-የፓርቲ አባልነት ለማንኛውም ዜጎች ክፍት መሆኑ፣
– የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት ጨምሮ አመራሮች የኃላፊነት ዘመን ለመገደብ መመሪያ እንደሚወጣ በመተዳደሪያ ረቂቅ ደንቡ መቀመጡ፣
-ፓርቲው ክልላዊ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንደሚ ኖራቸው (ማለትም የእንቶኔ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርን ጫፍ ጽ/ቤት፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የቀበሌ ጽ/ቤቶች በተዋዕረድ እንደሚኖሩት..) ታውቋል።
የልዩነት ሀሳብ መነሳት
በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባዔ የግንባሩ የውህደት ሀሳብ ላይ ጠንካራ አቋም መውሰዱ የሚታወስ ነው። በዚህ ጉባዔ ላይ ህወሓት ተስማምቶ የወጣ መሆኑ ቢታወቅም ወደአፈጻጸም ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ ተቃውሞውን በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ሲገልጽ ቆይቷል። በሰሞኑ የኢህአዴግ ስብሰባ ላይ በተመሳሳይ መልኩ የውህደቱን ሀሳብ እንደማይደግፍ በመግለጽ የልዩነት አቋሙን አሳውቋል። ከስብሰባው በኋላም ጠ/ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አሕመድ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን በግል አነጋግረው ለማግባባት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሳያስገኝ መቅረቱ ተሰምቷል።
የህወሓት የልዩነት መሠረታዊ ሀሳብ ምንድነው የሚለውን እዚህ ማንሳት ሚዛናዊ ጭብጥ ለመያዝ ሊረዳ ይችል ይሆናል። ህወሓት ‹‹ በውህደት ስም ኢህአዴግን አፍርሶ ሌላ ፓርቲ ለማቋቋም ማሰብ አገርን የሚበትን ተግባር ነው!›› በሚል በቅርብ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ውህደቱን አጥብቆ ተቃውሟል።
መግለጫው በሐተታው እንዳሰፈረው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል አንድ ሊያደርግ የጋራ የአመለካከትና የተግባር አንድነት የለም። “…ከውህደት በፊት የሚያዋህድ አመለካከትና እምነት መለየት አለብን። ኢህአዴግንና አገርን እየበተኑ ካሉት የተገዙ ደባል አመለካከቶች የሚለይ መስመር እና አጥር በጠራ መልኩ ሳይለይና ሳይቀመጥ ውህደትን ማሰብ አይቻልም። በደፈረሰ አመለካከትና በአንድነት ሊሰምሩ በማይችሉ እሳትንና ጭድ አስተሳሰቦችን በተሸከመ ኢህአዴግ ውህደት ቀርቶ በግንባርነት ለመቀጠል አይቻልም። እንደዚህ ያለ የተበተነ ድርጅት ወደ አንድ ፓርቲ ውህደት ይመጣል ብሎ ማሰብ በራሱ ድርጅቱን ከመበተን አልፎ አገርን የሚበትን ተግባር ነው ።….”
የህወሓት በቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል?
ብዙዎች ይህ ጥያቄ ከልብ ያሳስባቸዋል። አንዳንዶች ህወሓት በተቃዋሚ ፓርቲነት መቀጠል የሚከለክለው ነገር እንደማይኖር ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ራሱ ህወሓትን ጨምሮ ሌሎች ወገኖች ደግሞ አካሄዱ ሀገሪቷን ሊበትን እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
የህወሓት ልሳን የሆነው ወይን መጽሔት በቅርብ ዕትሙ መጪው ምርጫ ባይካሄድ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለማለፍ የራስ ገዝ ግዛት (ዲፋክቶ ስቴት) መመስረት እንደሚያስፈልግ ምክረ ሀሳብ የያዘ ሰነድ ማውጣቱ ምናልባት ቀጣዩ የህወሓት የጉዞ አንድ አማራጭ አቅጣጫ እሱ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ማጫሩ አልቀረም።
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ስለሚዋሀዱ ፓርቲዎች በአንቀጽ 92 ንዑስ አንቀጽ 3 እንዲህ ይላል። “ውህደት የፈጠሩ ፓርቲዎች አባል የነበረና በማናቸውም ደረጃ ያሉ ፣ ተመራጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የነበረ ሰው በውህደቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ መቀጠል የማይፈልግ ከሆነ የግል ተመራጭ እንደሆነ ተቆጥሮ የቀረውን የምርጫ ዘመን ያጠናቅቃል።”
ይቀጥልናም መዋሀድ በራሱ ስለሚያስከትለው ውጤት ይዘረዝራል። የአዋጁ አንቀጽ 92 ንዑስ አንቀጽ 1 በአሁኑ ሰዓት ኢህአዴግ በእጁ የሚገኙ ሐብቶች ምን ይሆናሉ ለሚለው የአንዳንድ ወገኖች ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ይሰጣል። “የውህደት ውጤት የሆነው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የተዋሀዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወራሽ ይሆናል። የተዋሀዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መብትና ግዴታ ይተላለፍለታል።”
ኢህአዴግ ማንነው?
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አራት አባል ድርጅቶችን ያቀፈ ነው። እነሱም የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ናቸው።
ኢህአዴግ በህወሓትና በኢህዴን (በአሁኑ አዴፓ) የተመሠረተው በ1981 ዓ.ም ነው። የመጀመሪያውን ጉባዔ በጥር ወር 1983 ሲያካሂድ ከመሥራች አባላቶቹ በተጨማሪ ኢህዴን ውስጥ የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆችንና ሌሎችንም ኦሮሞዎች በማሰባሰብ ኦህዴድን የመሠረቱ ሲሆን፤ ከደርግ የኮበለሉ መኮንኖች የመሠረቱት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያውያን መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢዴመአን) በመጨመር በአራት አባል ፓርቲዎች ጉባዔውን አካሂዷል።
ኢህአዴግ ስሙ እንደሚያመለክተው ግንባር ነው። በምሥረታው ወቅት የተሰጠው ስያሜ ተገቢ የነበረ ቢሆንም የመንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላም በዚህ ስያሜ መቆየቱ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። ግንባር ማለት ተዋጊ በመሆኑ ስያሜው ተቀይሮ አባል ፓርቲዎች ጋር ውህደት እንዲያደርግ በውስጡም ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እንደነበሩበት የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በኢህአዴግ ስድስተኛ ጉባዔ ተሻሽሎ በጸደቀው የመተዳደሪያ ደንብ መሰረት ኢህአዴግ ከፍተኛ የሥልጣን አካላት የሚከተሉት ናቸው።
የኢህአዴግ የአመራር አካላትና ልዩ ልዩ መዋቅሮች የኢህአዴግ ጉባዔ፣ የኢህአዴግ ምክር ቤት፣ የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የኢህአዴግ ሊቀመንበር፣ምክትል ሊቀመንበር፣ የቁጥጥር ኮሚሽን፣ የኢህአዴግ ጽ/ቤትና የፓርላማ መዋቅር፣ የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ፣ የኢህአዴግ የወጣቶች ሊግ፣ የኢህአዴግ የበታች አካላት ናቸው።
የኢህአዴግ ጉባዔ ከፍተኛው የሥልጣን አካል ሲሆን፤ ከሁለት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ይሰበሰባል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጉባዔው ከስድስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ሊያራዝመው ይችላል።
የኢህአዴግ ምክር ቤት ከጉባዔው ቀጥሎ የሚገኝ ከፍተኛ የአመራር አካል ነው። ተጠሪነቱም ለጉባዔው ነው። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሁሉም የአባል፤ ድርጅቶች የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በእኩል ድምጽ የተቋቋመ ነው። ተጠሪነቱ ለኢህአዴግ ም/ቤት ነው።
ተደጋግመው ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ኢህአዴግ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎችን ብቻ በሚያስተዳድሩ አራት ፓርቲዎች ብቻ ለምን ሊወሰን ቻለ? ሌሎቹ አጋር ፓርቲዎች ማለትም የሶማሌ ክልልን የሚመራው ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ)፣ አፋር ክልልን የሚመራው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ ጋምቤላ ክልልን የሚመራው የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕአዴን)፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሚመራው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ)፣ ሐረሪ ክልልን የሚመራው የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) የመሳሰሉ ፓርቲዎች በአጋርነት ብቻ ተወስነው ሊቆዩ የቻሉበት ምክንያት ምንድነው የሚለው በቂ መልስ ሳያገኝ ቆይቷል።
ይኸም ሆኖ ግን ባለፉት 25 ዓመታት አጋር ድርጅቶቹ ከኢህአዴግ ጋር በተግባር አይዋሀዱ እንጂ ሁሉም ፓርቲዎች የኢህአዴግ መመሪያና ውሳኔ አክብረው የሚያስፈጽሙ ናቸው። በሌላ አነጋገር የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች የሚያደርጉትን በሙሉ አሟልተው ሲፈጽሙ የኖሩ ናቸው።
ስለሆነም የኢህአዴግን አባል ፓርቲነት መታወቂያ ባይዙም ልክ እንደ ግንባሩ አባል መንቀሳቀሳቸው በወረቀት ላይ አባልነታቸው ያልጸደቀ ግን አባላት የሆኑ ፓርቲዎች ያደርጋቸዋል።
የኢህአዴግን መተዳደሪያ ደንብ ስንመለከትም እነዚህ አንድ የፖለቲካ ድርጅት እንዴት አባል መሆን እንደሚችልም የደነገገውን መመልከት እንችላለን። በድንጋጌው መሠረት አባል ለመሆን የኢህአዴግን ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀት፣ ብሄራዊ የፖለቲካ ድርጅት ወይም በአንድ ክልል የሚገኙ በርካታ ብሔራዊ አብዮታዊ ወይንም ህብረብሔራዊ ድርጅት መሆንና የመሳሰሉትን አጋር ድርጅቶቹ ከበቂ በላይ የሚያሟሉ ነበሩ።
በመጨረሻም የአጋር ድርጅቶች የበይ ተመልካች መሆን በአዲሱ ውሁድ ፓርቲ እንደሚያበቃ መነገሩ ጥያቄውን ለመመለስም መልካም አጋጣሚ መሆኑ በመነገር ላይ ይገኛል።
የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ
የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በመቅረጽ ረገድ የፓርቲው የረጅም ጊዜ መሪ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። በትጥቅ ትግሉ ዓመታት የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና ከማዖ ‹የአዲሱ ዴሞክራሲ› ፍልስፍና ጋር የሚመሳሰል ነበር። ማለትም በኢኮኖሚ ግቡ ሶሻሊዝምን ማስፈን፤ በፖለቲካ ግቡ ደግሞ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የነገሰበት ስርዓት ዕውን ማድረግ ነው። ነገር ግን ፓርቲው ስልጣን ሊይዝ በተቃረበበት ዓመታት የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲና ካፒታሊዝም በማጋደሉ፣ ኢህአዴግ ይህን ያገናዘበ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍልስፍና ለውጥ አደረገ።
እከተለዋለሁ የሚለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ በፖለቲካ ግቡ ሊበራሊዝምን ማስፈን፤ በኢኮኖሚ ግቡ ደግሞ ኢንዱስትሪ (ካፒታሊዝም) እንደሆነ ገለጸ። እናም የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም በሚደረግ ሽግግር ፖለቲካው የሚመራበት ስርዓት ነው።
አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግቦቹ መሳካት የሚሰራ ጠንካራ የፖለቲካ አመራር (ፓርቲ) መገንባት ያስፈልጋል ይላል። የመሪ ድርጅቱ አወቃቀርም በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ የተቃኘ ይሆናል፤ በዴሞክራሲ ማዕከላዊነት መርህ መሰረት የፓርቲ ውሳኔዎች የሚተላለፉት ከፓርቲው የበላይ አመራሮች ሲሆን፤ ሌሎች የፓርቲ አባላት ኃላፊነት መመሪያውን ተቀብለው ማስፈጸም ነው፤ በዚህም ለውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ብዙም ግምት አይሰጥም።
የኢህአዴግ አብዮታዊ አስተምህሮ እንደሚለን፤ ዴሞክራሲን ለማስፈን የህዝብ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል፤ ይህም ከዴሞክራሲ (ከነጻነት) ዳቦ ይቀድማል የሚል ዕምነት የያዘ ይመስላል። በጥቅሉ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ጠንካራ የመካከለኛ ገቢ ያለው መደብ መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው ያስፈልጋል። የኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካዊ ፍልስፍናውን እንደየጊዜውና ሁኔታው የሚቀያይር መሆኑ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ዋነኛ መለያ ባህሪ ነው።
ይህ ለሶስት አሥርት ዓመታት ከኢህአዴግ ጋር የተጓዘ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም በአዲሱ ውሁድ ፓርቲ እንደማይቀጥል እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የውሁዱ ፓርቲ ተግዳሮቶች
የውህደቱ አካሄድ በኃይል ጭምር ለመቀልበስ የሚያልሙ ኃይሎች በፍጥነት ሁከትና ግርግር ወደማ ቀጣጠል ሊሸጋገሩ የሚችሉበት ዕድል ጠባብ አይሆንም። ይህ ሁኔታም የዘንድሮ ምርጫ ሊያውክና እንዳይካሄድም አንድ ምክንያት እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። የምርጫው አለመካሄድ በራሱ የገዥውን ፓርቲ ተቀባይነት በማሳጣት የባሰ ቀውስና ግርግር ለመፍጠር ለማይተኙ ኃይሎች ምቹ መደላድልን ሊፈጥር ይችላል።
በተጨማሪ የብሔር ፌዴራሊዝም ፖለቲካ ነጋዴዎች የመጨረሻ ዕድላቸውን የሚሞክሩት ግጭቶችን እዚህም እዚያም በማቀጣጠል ሊሆን እንደሚችል መገመት ነቢይ መሆንን አይጠይቅም። እናም አዲሱ ውሁድ ፓርቲ ይኸን ከፊቱ የተጋረጠ ከባድ ፈተና በብቃት ለማለፍ ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በቅርበትና በቅንጅት ሊሰራ የሚችልበትን አቅጣጫ ሊነድፍና ሊተገብር ይገባል። (ማጣቀሻዎች፡- የኢህአዴግ ይፋዊ ድረገጽ፣ አዲስ ስታንዳርድ፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ፋና ብሮድካስቲንግ፣ ሸገር ኤፍኤም…)
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2012