ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነሻው በውል ያልታወቀ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሰላም ያሳጣ ብሎም ቤተሰብንና አገርን ስጋት ላይ የጣለ የሰላም ችግር መከሰቱ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ቀውስ መፍትሄ ይሆን ዘንድ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በእርግጥ የጉዳዩ አሳሳቢነት የጀመረው ዛሬ አለመሆኑ ይታመናል፡፡ችግሩ ስር እንዳይሰድ በማሰብ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ መምህራንም ሆኑ ሌሎች አካላት እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ከእነዚህ መካከል አንዱ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር እንዳለው ፉፋ ናቸው፡፡ዶክተር እንዳለው በየዩኒቨርሲቲው ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ቢቀርፍ በሚል አንድ ጥናት በራሳቸው ተነሳሽነት አካሂደዋል፡፡ ጥናቱ የሰላም አስተምሮ በኢትዮጵያ የትምህርት ሒደት ሊኖረው ስለሚችለው የፖሊሲ አቅጣጫና ትግበራ የሚመለከት ነው፤ በእርሳቸው አጠራር ደግሞ ‹‹አስተምሮ ዘ-ሰላም›› የሚል ነው፡፡ከእኚሁ በፖሊሲ ጥናት ላይ ከሚያተኩሩትና በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርትና የትምህርት ንፅፅር ጥናት ስፔሻሊስት መምህር ከሆኑት ዶክተር እንዳለው ፉፋ ጋር አዲስ ዘመን ያደረገውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጥናቱ ዋና ዓላማ ምንድን ነው?
ዶክተር እንዳለው፡- የመጀመሪያው በትምህርት ላይ ግጭቶች እንዳይነሱ፣ነገሮች ተካረው ወደአመፅ እንዳይሄዱ በምን አስተምሮ የመከላከል እርምጃ ቢወሰድ ጥሩ ይሆናል የሚለው አንዱ ሲሆን፣ይህም አስቀድሞ የመከላከል ስልት የሚባል (Prevention) ነው።በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መቼም በማህበረሰብ ውስጥ ግጭት አይከሰትም ብሎ መደምደም አይቻልምና ግጭቶች ሲከሰቱ የማህበረሰቡ መሰረት እንዳይናድ ችግሩን መለየትና መቆጣጠር (Protection) የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ነው።በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ከባህላችን አንፃር ማግኘት የነበረብንን ሰላምን የመገንባት አስተምሮ ምን ያህል እንደተጠቀምንበት ማሳየትና በሚገባ ማስተዋወቅ (Promotion) ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡-ጥናቱ የተጀመረው መቼ ነው? የትኩረት አቅጣጫውስ ምንድን ነው?
ዶክተር እንዳለው፡-ጥናቱ የተጀመረው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፤የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫ በኢትዮጵያ የትምህርት ሂደት ከፖሊሲና ትግበራ አንፃር የሰላም ጉዳይ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት መጣ? የሚለውን በተለይ ዘመናዊ ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረ አንስቶ ባሉት ጊዜያት ምን እንደሚመስል መመልከት ነው።
ጥናቱ ያተኮረው ከሰዎች መረጃ በማሰባሰብ ላይ አይደለም፤ እንደሚታወቀው ፖሊሲ ያለው በሰነድ ነው።የትግበራ ክትትልም ያለው በትምህርት ግምገማ ስለሆነ እነዚህ ነገሮች ምን ያህል በሰላም ላይ ትኩረት አድርገዋል? የሚለውን ጥናቱ ይመለከታል።እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት በግጭትና ጦርነት ውስጥ ኖራለች።ይህንን ጀግንነትም በይው ሌላ ፤ሰላምን በተመለከተ ምን አይነት አስተምሮ ነበር? ምንስ አለን? በሚለው ላይ ጥናቱ ትኩረት አድርጓል።ጥናቱ ፖሊሲንና አውድን መሰረት ያደረገና በሰነዶች እና ጥናቶች ላይ የተመረኮዘ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከተመረኮዘባቸው ሰነዶችና ጥናቶች መካከል ማሳያ ቢጠቅሱልኝ? ምናልባትም የእርስዎ ጥናት ከእነዚህ ጥናቶች በምን እንደሚለይ ቢጠቆሙኝ?
ዶክተር እንዳለው፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት በአንድ ፕሮፌሰር ‹‹በጎልማሶች ትምህርት ዙሪያ ያሉት ባህላዊ የሰላም አስተምሮዎች ምን ያህል ተተግብረዋል›› በሚል ፅንሰ ሐሳብ የተሰራ ጥናት ለእዚህ አንዱ ተጠቃሽ ነው።በትምህርት ላይ ባይሆንም በባህል ደረጃ ሰላምና ግጭትን በሚመለከት በኮንሶ፣በኦሮሞና በሌሎችም ብሄሮች ላይ የተካሄዱ ጥናቶችንም ተመልክ ቻለሁ።
እኔ ለጥናቴ ያግዙኛል ብዬ ያየኋቸው ጥናቶች በአገራችን ግጭት ሲፈጠርም ሆነ አለመግባባት ሲኖር ለመፍታት የምንጠቀምባቸውን ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ።በዚህ አይነት መንገድ ግጭትን መፍታት ይቻላል የሚለውን ነው የተመለከቱት እንጂ ከትምህርት ጋር በማስተሳሰር ትውልድ እንዴት ሊማርባቸው ይችላል የሚለውን አልዳሰስኩም። በእስካሁኖቹ ጥናቶች ማህበረሰቡ ግጭትን ለመፍታትም ሆነ እንዳይከሰት ለማድረግ የሚረዱ ዘዴዎች እንዳሉት የሚያመለክት ጥናት ነው የሰራሁት። ያንን ውስዶና በትምህርት መልክ ቀርፆ ለአገር በማቅረቡ በኩል እኔ ያካሄድኩት ጥናት እንደ አዲስ ሊታይ ይችላል ያልኩትም ከዚህ አንፃር ነው።ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ስርዓት እንዲኖረን እና በስርዓተ ትምህርት ደረጃ ተቀርፆ ሊያገለግል የሚችል ነገር ባለመኖሩም ነው የጥናት ትኩረቴን በዚህ አቅጣጫ ላይ ያደረኩት።
እኤአ በ1994 በሥራ ላይ የዋለው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በራሱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ይላል እንጂ በእዛ ውስጥ መምህሩ ምን ማድረግ እንዳለበት፣ስለሰላም እንዴት ማስተማር እንደሚኖርበት እንዲሁም ማህበረሰቡ ልጁ ምን አይነት ገፅታ ይዞ ወደ ትምህርት መቅረብ እንደሚኖርበት፣ልጁን በምን አይነት መንገድ መቅረፅ እንዳለበት፣ዘርፎችስ ምን ሚና መጫወት እንዳለባቸው የሚገልፅ ነገር በፖሊሲው ውስጥ የለም።በመሆኑም ያላስተማርነውንና ያልገነባነውን መጠበቅ የለብንም።
አዲስ ዘመን፡-ጥናቱን በመድረኮች ላይ አቅርበዋልን?አቅርበው ከሆነ ምን ግብረ መልስ ተገኘ?
ዶክተር እንዳለው፡- አዎ!ሁለት መድረኮች ላይ አቅርቤያለሁ፤አንደኛው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጉባኤ ላይ የቀረበው ሲሆን፣ሁለተኛው ደግሞ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ጉባኤ ላይ የቀረበው ነው።ከሁለቱም መድረኮች ገንቢ ግብረ መልስ አግኝቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እንደነገሩኝ ከሆነ ጥናቱን የጀመሩት በዩኒቨርሲቲው ጠያቂነት ሳይሆን፣ በራስዎ ተነሳሽነት ነው፤ለጥናትዎ መነሻው ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር እንዳለው፡-ምክንያቱ አንድ ጥያቄ ወደአዕምሮዬ እየመጣ ስለጎተጎተኝ ነው፤ ይኸውም ትምህርታችን ምን ያህል ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አዘጋጅቶናል የሚለው ነው።ሌላው ደግሞ የተማረ ነው፤በትምህርት ገፍቷል ከሚባለው እና ገና ብዙም አልተማረም ከሚባለው ክፍል የትኛው ነው ለግጭት የበለጠ የሚነሳሳው የሚለውም ነው።
እኔን የሚያሳስበኝ ኢትዮጵያ ሰውን ለማስተማር ሀብት የምትመድበው ሳይቀር ግጭቶችንም ለማብረድ ዋጋ እየከፈለች መሆኗ ነው።ለዚህ ምክንያቴ ደግሞ የተማረ ያልነው አካል ባለመረዳት ወይም ደግሞ ነገሮችን አለአግባብ በማግነን እንዲሁም አገራዊ ቱፊቶችን ባለማበልፀግ ስሜታዊ እየሆነ ያለበት ሁኔታ ነው፤በዚህ የተነሳም ችግር ከመፍታት ይልቅ ነገሮችን እያጋነነ ወደአመፅ እንዲገባ የተደረገበት ሁኔታ አለ።ይህ ነገር የእኔ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ቀደም ሲል በጥናቴ ዋና ዓላማ ላይ መከላከል፣መቆጣጠርና ማስተዋወቅ ብዬ እንደገለፅኩልሽ በእነዚህ ነገሮች ላይ ምን ያህል ሄደንበታል የሚለውን አይቻለሁ፤ከዚያም የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ እንደመሆኔ ፍሪፒስ አፕሮች በሚል ሥርዓት ትምህርት ቢሰራበት ጥሩ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በጥናትዎ መሰረት በዋናነት የሚፈታው ችግር የትኛው? ጥናቱ በቅርቡ በአንዳንድ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየታየ ካለው ችግር ጋር ምን ያህል ተያያዥነት አለው?
ዶክተር እንዳለው፡-በነገራችን ላይ ግጭትን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አንችልም፤ምክንያቱም ሰው በተፈጥሮው ከራሱ ጋርም ይሁን ከሌላው ጋር በተለያየ ምክንያት ሊጋጭ ይችላልና።ምናልባት አስተውለሽ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ይባልና ሰው ገጀራ ይዞ ሲወጣ ይታያል።እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስተዋል ይቻላል፤ይኸውም ሰው ስለሰላም ያለው እውቀት እምን ድረስ ነው የሚለውን ነው።ሰላም ያለው በውስጣችን ነው? ወይስ ከእኛ ውጭ ነው? እኛው ነን መገንባት ያለብን ወይስ ሌላው አካል ነው የሚሰጠን? የሚለውን ስናስተውል በራሱ ችግር አለ።
ነገሩን አጎልቶ ሊያሳየን የሚችለውን ነገር ስናስተውል ደግሞ ግጭቱ በአንድ ሰው ምክንያት ይነሳና የአገር ጉዳይ ሆኖ ቁጭ ሲል ይስተዋላል።ወደ ብሄር ብሄረሰብ ዞሮም ሲቀጣጠል ይስተዋላል፤በግለሰብ መካከል ግጭት ቢኖር ሊያስታርቅ የሚችል ማህበረሰብ አለ።ግጭትን አስቀድመን የምንከላከልበት ስልት ባለመጠናከሩ ሳቢያ ወደከፋ ሁኔታ ውስጥ ሲገባ ይታያል።
የተለያዩ የበሽታ አይነቶች ሰዎችን እንዳያጠቁ አስቀድሞ እንደ በሽታው አይነት ክትባት እንደሚወሰድ ሁሉ ለሰላም መደፍረስ መነሻ ቦታው አዕምሮ ስለሆነ ሰው አስፍቶ ቢያነብና ስለአገሩም የበለጠ ቢያውቅ ችግሩን ማስወገድ ይቻላል፤ይህንንም ችግሩ አስቀድሞ እንደሚያስወግድ ክትባት መቁጠር ይቻላል ።
በማንበብ በአገራችን የባህል ብዝሃነት እንዳለም መረዳት ይችላል። ‹‹እኔ›› ብቻ ማለትንም ለመተው ይረዳል።አገሪቱ የተለያየ እሴት እንዳላትም በስርአተ ትምህርቱ በአግባቡ ቢካተትና ግንዛቤው ቢዳብር ዘሎ ወደአመፅ ሊገባ የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም።በመሆኑም ጥናቱ እነዚህን መሰል ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል።
አሁን አሁን ሰዎች ምንም በማያውቁት ሁኔታ ብቻ ሲጎዱ እየተመለከትን ነው።ለምሳሌ የእኔ ብሄረሰብ የሆነ አንድ ግለሰብ ከሌላ ብሄረሰብ ጋር አለመግባባት ከፈጠረ ምንም በማላውቀውና እንዲያውም በረጅም ርቀት ላይ ባለሁት እኔ ላይ ጉዳት ሲከሰት ይስተዋላል።‹‹የእነእገሌ ብሄር ነው››በሚል ብቻ ነፍስ ማጥፋትና ንብረት ማውደም ድረስ እየተሄደ ነውና በዚህ ላይ በሚገባ መስራት ይገባል።
እኛ እኮ ግጭትን ለንቆጣጠርባቸው የሚያስችሉ ባህላዊ ህጎች አሉን።ለምሳሌ በገዳ ስርዓት ውስጥ ማንም ሰው ቢሆን ለፀብ መሰረት የለውም፤በአሁኑ ወቅት ይህን ስርዓት በስልጣኔ አይሉት ባለማወቅ ሰዎች ረግጠው እያለፉት ናቸው።ሰዎች የከበረውን የገዳ ስርዓት ተረማምደው እያለፉ ስንት ወንጀል እየሰሩ መሆናቸውን እናውቃለን።ለዚህ ችግሩ ትውልዱ የገዳ ስርዓቱን የሚያውቀው በስም እንጂ በጥልቀት አለመሆኑ ነው።ስለዚህም በአንድ ጎን ስርዓቱ አለ እንላለን፤ግብራችን ግን የተለየ ነው።በአንድ በኩል ‹‹የገዳ ስርዓታችን በዩኔስኮ መመዝገብ አለበት››እያልን በሌላ በኩል ይህን ለማፍረስ መሯሯጣችን ይታየኛል።ለዚህም ነው እነዚህንና መሰል ባህላዊ እሴቶቻችንን ወደ ስርዓተ ትምህርቱ ማካተት አለብን በሚል በመንቀሳቀስ ላይ ያለሁት።
ሌላው ችግራችን ደግሞ ባህላችንን እንደኋላ ቀር አድርገን ማየታችን ነው።አብዛኛዎቻችን ዋናው ችግራችንና ለመሞታችን መንስዔ የሆነው የምናማትረው ወደውጭ እንጂ ወዳለን መልካም ነገር አለመሆኑ ነው።ከዚህም የተነሳ የምንይዘውንና የምንጨብጠውን እያጣን ነው፤ነገር ግን በባህላችን ውስጥ መተሳሰቡ፣መከባበሩም ሆነ መረዳዳቱ አለ።ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ለተፈጠረ ቁርሾም ቢሆን ይቅርታ በመባባል መታረቅም አለ።በአሁኑ ጊዜ ግን ይቅር መባባሉ ከወዴት አለ?ይቅር ከመባባል ይልቅ ሰው ቡድን እየመሰረተ የትና እንዴት ልጉዳው መባባሉ እየበረታ ነው የመጣው።ይቅርታ ማለት አለመቻል ደግሞ ራስን መቀበል እንዳለመቻል ነው።ከዚያ ይልቅ እልህ በርትቶ ይታያል፤ከዚህም የተነሳ ነገ ለሚመጣው ትውልድ ቅራኔና ቂም እየዘራ መጓዝን እየመረጠ ይኖራል።ስለዚህ የሚፈለገው ባህላችን ያለውን መልካም እሴት በመጠቀም ችግር ፈቺ ሆኖ እንዲሰራ በሥርዓተ ትምህርቱም እንዲካተት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በበርካታ የመንግ ሥት ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ስጋቶች አይለው ይታያሉና ጥናትዎ ችግሩን ከመቅረፍ አኳያ ሚናውን እንዴት ይገልፁታል?
ዶክተር እንዳለው፡-ይህንን ጥናት ወደሴሚናር ፕሮጀክት ቀይሬው ነበር።በነገራችን ላይ ጥናቴን እንዳልኩሽ በራሴ ተነሳሽነት ያካሄድኩት እየታየ ያለው ችግር እንዲፈታ ካለኝ ፅኑ ፍላጎት በመነጨ ነው።ጥናቱን ባለፈው ዓመት ህዳር ላይ ወደ ምርምር ፕሮጀክትነት ቀይሬ ለሚመለከተው አካል አቅርቤም ነበር፤ነገር ግን ከሥራ መብዛት የተነሳ ሊሆን ይችላል ምላሹ ዘግይቶብኛል።እንዲያም ሆኖ ከቅርብ አጋሬ ጋር በመሆን በሶስት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ለማቅረብ እቅጃለሁ።አንዱ በማስተምርበት የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣የተቀሩት መደወላቡ እና አዳማ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።
ከዚህ ጎን ለጎንም የባህል ብዝሃነት ግንዛቤ በአግባቡ እንዲሰርጽ ጥረት እያደረግን ነው።በተለይ ደግሞ አባ ገዳዎችን፣ ሀደ ስንቄዎችን እንዲሁም ባህሉን በሚገባ የሚያውቁ አካላት ተማሪዎቻችንን እንዲያስተምሩልን እናደርጋለን።በእውነቱ ከሆነ ፍላጎታችን አስተማሪዎቹ እኛ ሳንሆን እነርሱ እንዲሆኑ ነው፤እኛ ሳይንሱን እናመጣለን፤እነርሱ ደግሞ ባህሉን እንዲያስርፁልን እንሻለን።በዚህም ጥምረት ለትውልድ አንዳች ነገር እንዲተርፍ እንጥራለን።
አዲስ ዘመን፡-ሶስቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዴት ተመረጡ?
ዶክተር እንዳለው፡- ለጊዜው ጥናቱን በኦሮሚያ ባሉት ዩኒቨርሲቲዎች ለማድረግ ያቀድነው በተለይ አዳማ ብዙ ጊዜ ችግር ስለሚበዛበት ነው።እነዚህ ሶስቱን ይዘን እንጀምርና በቀጣይ ወደ ሌሎቹ እንደርሳለን የሚል ሐሳብ ስለያዝን ነው።ከዚያም ወደ ጎንደር፣ባህርዳርና ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንሄዳለን።ይቅር መባባልን፣ መደጋገፍን፣ መተሳሰብን እያባዛን ለመሄድ አቅደናል። በዚህም አንድ እርምጃ ወደፊት ለመሄድ አስበናል፤ግጭትን አስቀድሞ ከመከላከልና ከመቆጣጠር አኳያ ምሁራንም ሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ምንም እያደረጉ እንዳልሆነ ተደርጎ መታሰብ የለበትም።መንግሥትም ሊያበረታታን ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ጥናቱ ለፖሊሲ አውጪዎችም እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፤በዚህ ላይ ትንሽ ቢያብራሩልኝ?
ዶክተር እንዳለው፡- ሞራል ዲቨሎፕመንት የሚባል አንድ ሞጁል ለአንደኛ ዓመት ተማሪዎች እንዲሰጥ ተዘጋጅቷል። አንድ ነገር ግን መታወቅ አለበት።ይኸውም ስለሰላም፣ ስለስነምግባር መታሰብ አለበት፤ኮርሱ ሲሰጥ የሚታው ዝግጅት ለፈተና ብቻ እንዳይሆን ማስተዋል ይጠይቃል፤ለባህሪ ለውጥም ሊሆን ይገባል።
እኛ ስለሰላም አስተምሮ ስናመጣ መጀመር ያለብን በኮርስ መሆን የለበትም።በእንዲህ አይነት ሁኔታ ፈተና እየተሰጠና እየታረመ ከሆነ ተማሪው ከፈተና በኋላ ዞር ብሎ ለማየት አይፈልግም።እንዲያውም እንደ ተጨማሪ ጫና መመልከት ይጀምራል።እንደሱ አይነት ችግር እንዳይፈጠር እኛ ካለው ችግር እንጀምራለን።ለምሳሌ በቅርቡ ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ላይ የተማሪዎች ህይወት ተቀጥፏል።ለዚህ ያደረሰው ፀብ ቢታወቅ ኖሮ እዚያው እርቅ እንዲኖር ይደረግ ነበር።ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን ‹‹አማራ ኦሮሞን ገደለ›› ወደሚለው ሄደ።ለምን ትናንት አልገደለም ? ብሎ ህዝባችንም አይናገርም።ችግሩን ግን እያገዘፈና ውሃ እያጠጣው አተልቆ ወደእርስ በርስ ግድያ እንዲሄድ ያደርጋል።ትውልዱ ባህልን ሊያውቅ ይገባል።ስለዚህ ይህ ጥናት ወደ ሥርዓተ ትምህርት ብሎም ወደ መማር ማስተማር እንዲመጣ እፈልጋለሁ።ይህ ደግሞ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ መረጃ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር እንዳለው፡- እኔም እድሉን ስላገኘሁ አመሰግናለሁ።
ዶክተር እንዳለው ፉፋ፤
አዲስ ዘመን ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም
አስቴር ኤልያስ