“መጽሐፍ መግዛት ብዙ ገንዘብን በትንሽ ገንዘብ መግዛት ነው” ይህን ጥቅስ ያገኘሁት ከሃያ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የሜጋ መጻሕፍት መደብር ውስጥ በአንዱ ነው። ድንቅ ጥቅስ ነው። ንባብ የሰውን አእምሮ ያዳብራል። የሰው ልጅ አርቆ አስተዋይ እንዲሆን ያደርጋል። መከራና አሳር በበዛበት ዓለም ውስጥ ስንኖር ሰው፣ ተፈጥሮ፣ ዓለም፣ ውበት፣ ሕይወትና ኑሮ ምን እንደሆኑ መጻሕፍት ያሳዩናል። ለዚህም ነው “በሰው ልጅ እሱነት ላይ የሚያነባቸው መጻሕፍት ሲታከሉ ሰው ያደርጉታል” የሚባለው።
መጻሕፍት፣ እውነትን፣ ውበትን፣ ሕይወትንና ፍቅርን የተጠሙ ምሁራን ተጨንቀውና ተጠበው በስጦታ ያቀረቡልን የአእምሮአቸው ውጤቶች ናቸው። ዓለምን ሊሰለጥንባትና ሊገራት ብርቱ ጥረት ለሚያደርገው ክፉውንና ደጉን፣ ጠቃሚውንና ረብ የለሹን ይለይበት ዘንድ አእምሮ ለተሰጠው የሰው ልጅ ፍኖተ ሕይወት በመሆን ያገለግላሉ። “ሕይወት ለብልህ ድራማ፣ ለሞኝ ጨዋታ፣ ለሀብታም አስቂኝ፣ ለድሃ ደግሞ አሳዛኝ” መሆኗን ገላልጠው የሚያሳዩ፤ ወረትን የማያውቁ እውነተኛ ጓደኛ ናቸው። ለሚወዳቸውና ለሚወዱት ማናቸውንም የማይደብቁ፣ ስስትና መሰልቸትን የማያውቁ ናቸው።
መጻሕፍት የአእምሮ ብርሃን፣ የኅሊና መሪ፣ የሥነ ጥበባት ምንጭ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቀያሽ መሐንዲስ ሲሆኑ መንፈስን እየመገቡ ሰውን ወደ ብቃት ያደርሳሉ። ምንጩ ካልታወቀ ጥቅስ ላይ ያገኘሁት “አእምሯቸው ከበሰለና አስተሳሰባቸው ከነጠረ ሰዎች ጋር ሸንጎ መቀመጥ የምንችለው በመጻሕፍት አማካይነት ነው፤ በመጻሕፍት ማዕድ ዙሪያ ስንቀመጥ ጠቢባን ያነጋግሩናል። ፈላስፎች ወደ አእምሯችን ጓዳ ይጋብዙናል” ይላል።
ታዋቂ መምህራንን፣ ፈላስፋዎችን፣ የጠፈር ተመራማ ሪዎችን፣ ባሕር ውስጥ ጠልቀውና የምድር ከርስ ውስጥ ገብተው የምድርን ገበና የገለጡ ከፍተኛ ጠበብቶችን፣ ታዋቂ ሐኪሞችን፣ የሀገርና የዓለም ብርቅዬ ምሁራንን ላሉበት ደረጃ ያደረሷቸው ማን ናቸው? መጻሕፍት አይደሉምን? ቅዱስ ያሬድን፣ ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብን፣ አራት ዓይና ጎሹን፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅንን፣ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን፣ አርስቶትልን፣ ኤዞፕን፣ ጠቢቡ ሰሎሞንን፣ ዲዮጋንን፣ ሶቅራጥስን፣ ሄሮዶትስን፣ ጋሊሊዮን፣ ሼክስፒርን፣ ዳቬንቼን፣ አይዛክ ኒውተንን፣ ሞዛርትን፣ ፑሽኪንን፣ ገትን፣ ይስሐቅ ኒውተንን፣ ሲግመንድ ፍሩድን፣ አንስታይንን፣ ማርክስን፣ ኤንግልስን፣ ሌኒንን፣ ናፖሊዮንን፣ ቸርችልን፣ ሊንከንን፣ ደጎልን፣ እና ሌሎች የሀገራችን እና የዓለማችን ኅሩያንን እና የቀለም ቀንዶችን እየኮተኮቱ እና እየቀረጹ ለዚህ ያደረሷቸው ማን ናቸው? መጻሕፍት አይደሉምን?
ጠቢባኑ የሀገራችን እና የዓለማችን ዓይነተኛ ሰዎች እኛ በማናስተውለው መንገድ ሲጓዙ ነበር። አብዛኛው ሕዝብ የልማድ እስረኛ ሆኖ ሲገፋ፣ የቁሳቁስ ጌታ ለመሆን ሲሯሯጥ፣ “ክቡር እከሌ” ለመባል አቋራጭ መንገድ ሲፈልግ፣ ጠቢባኑ ግን “በትንሽ ገንዘብ ብዙ ገንዘብን በመግዛት” ተዓምር ሲሰሩ፣ ብል በማይበላው፣ ጉልበተኛ በማይዘርፈው እና የግል ሀብት በሆነው ዕውቀት ሲነግዱ ነበር። ጠቢባኑ በዕውቀትና በኅሊና በመራቀቃቸውና በመጠበባቸው በመላው ዓለም ጥበብ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲራቀቅ አደረጉ። ለስማቸው መዘከሪያም በአእምሯችን ላይ ሐውልታቸውን ገነቡ።
እግዚአብሔር በራሱ አምሳል የፈጠረው በዓለም ውስጥ ተኪ ሚና የሌለው ክቡሩ የሰው ልጅ አይደለምን? ቸር እግዚአብሔር የሰው ልጅ ዓለምን ይሰለጥንበትና ይገራ ዘንድ ኃይልም ብርታትም የሰጠው ለማን ነው? ለሰው አይደለምን? ዓለምን በአእምሯው ሊገራ የሚባጀውስ በመጽሐፍ አይደለምን?
የንባብ ልምዳችን እንዲዳብር መንግሥት ድርሻውን ተወጥቷል ወይ? የሚለው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ሁሉንም እንደ ሥራው እንመሰክር ዘንድ የኅሊና እና የፈጣሪ አደራ ስላለብን ደርግ የንባብ ባህልን ለማዳበር ያደረገውን ጥረት መግለጽ የተገባ ነው።
ደርግ ያቋቋመው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በርካታ ደራስያንን አፍርቷል። መልካምን ነገር ያላቀፈ ክፉ ነገር፤ ክፋትን ያላቀፈ በጎ ነገር የለምና ደርግ ለንባብ ማደግ በጎ አስተዋጽኦ ቢያበረክትም በአንጻሩ ታላቁ ቆራጭ ሳንሱር (The great censor) መኖሩ ደግሞ ከአልማዝ የከበሩ ሐሳቦችን አምክኗል። ከቅድመ ምርመራ (censor) አፈትልኮ ለንባብ የበቃው “ኦሮማይ” መጽሐፍ ታላቁን ደራሲ በዓሉ ግርማን አሳጥቶናል።
ደርግ ለርዕዮተ ዓለሙ በሰጠው ትኩረት በከተሞች ቤተ መጻሕፍት እንዲቋቋም አድርጓል። ዓይነቱ ቢበዛም፣ መልኩ ቢለዋወጥም ሙያውና ግብሩም የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለምን መሰረት ያደረገ ቢሆንም፣ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በሙያው ብቃትና ጥራት ያላቸው አንጋፋ ባለሙያዎች ስለነበሩት የሥነ ጽሑፍ ጥራታቸውን የጠበቁ መጻሕፍትን በማሳተም በዝቅተኛ ዋጋ ያከፋፍል ነበር። ሚዲያዎችም ለንባብ መዳበር የበኩላቸውን ድርሻ ይወጡ እንደነበር አይዘነጋም።
አሁንስ? አንዳንድ የማተሚያ ቤት ባለቤቶችን እንዳነጋገርኩት የወረቀት ዋጋ በመናሩ የተነሳ የማሳተሚያ ዋጋ ጨምሯል። ኑሮ በተወደደበት በዚህ ዘመን፣ “ለእኔ ብጤው” መጻሕፍትን መግዛት ከባድ ነው። ከመንግሥት ምን ይጠበቃል? ትኁት ምክሬን እነሆ።
1. መጻሕፍት የመንፈስ ምግብ ናቸው። አንባቢ አለመሆን የኅሊና ድርቀትን ያመጣል። ሀገር በድርቅ ተመታች የምትባለው በጠኔ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የኅሊና ጠኔ ከምግብ ጠኔ የከፋ ነው። መንግሥት የዜጎችን አካል ብቻ ሳይሆን ኅሊናቸውም በመልካም እሴቶች እንዲለመልሙ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በዚህም አንጻር መንግሥት በወረቀት ላይ የጣለውን ቀረጥ ቢቀንስ፣
2. በደርግ ዘመን እንደነበረው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ዓይነት መንግሥታዊ ተቋም ቢያቋቋም፣
3. በንጉሠ ነገሥቱም ሆነ በደርግ ዘመን ትምህርት ሚንስቴር የታላላቅ ደራስያን ሥራዎችን (ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ የከበደ ሚካኤልን፣ የሐዲስ አለማየሁን እና የሌሎችንም)ያሳትም ነበር። የቋንቋ መምህራንም የትላልቅ ደራስያንን ሥራዎች ክፍል ውስጥ ያነቡልን ነበር። በከበደ ሚካኤል፣ በቀኛዝማች ያሬድ እና በሌሎችም ደራስያን መጻሕፍት የተማርን የዚያን ዘመን ተማሪዎች ሥራቸው ዛሬም ድረስ በኅሊናችን ተጽፎ አለ። የሕጻናት አእምሮ እንደ ንጹሕ ወረቀት ነውና ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ በሕጻናት ላይ ሊሰራ ይገባል፣
4. መንግሥት የጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ መጻሕፍት ጉልህ ድርሻ አላቸው። በዚህም አንጻር ስለ ፍቅርና በፍቅር ስለ መኖር ስለ ሀገርና ለሀገር የመኖር ምስጢርን የሚገልጹልን፤ የትናንት መነሻችንን፣ የዛሬ ኑባሬያችንን እና የነገ መዛለቂያችንን የሚያመላክቱን መጻሕፍት ያስፈልጉናል። በሀገር ውስጥና ውጭ የሚገኙ ባለሀብቶች፣ መልካም ፍሬ ያላቸው መጻሕፍት ታትመው በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሰራጩ የበኩላቸውን ድርሻ ቢያበረክቱ፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርም በትጋት ቢሰራ፣
5. ትምህርት ቤቶች እና ሚዲያዎች እንዲሁም ቤተ መጻሕፍት ያላቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ቤተ መጻሕፍትን በበጀት ጭምር ቢያጠናክሩ፤ ቤተ መጻሕፍት የሌላቸው ደግሞ እንዲያቋቋሙ ቢደረግ ከፍቅር ጋር “ብዙ ገንዘብን በትንሽ ገንዘብ እንድንገዛ” ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ፡
6. ደርግ ከቀበሌ ጀምሮ ቤተ መጽሐፍትን በመክፈት ለንባብ መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አዲስ ቤተ መጻሕፍት ሲከፈት አላጋጠመኝም። ያሉትም ቢሆኑ ያሏቸው ያረጁ የድሮ መጻሕፍት ናቸው። የምኖረው በየካ አባዶ ኮንዶሚኒየም ነው። አንድ የሚመለከተው ባለስልጣን እንደ ነገሩኝ ከሆነ ከሰማንያ እስከ ዘጠና ሺ የሚደርስ ሕዝብ ይኖራል ተብሎ ይገመታል። መለስተኛ ከተማ ለሆነው መኖሪያ አንድ ቤተ መጻሕፍት አለመከፈቱ ይገርመኛል። ይህ ችግር ሌሎች የኮንዶሚኒየም መኖሪያዎችን ይመለከታል። በመሆኑም የሚመለከተው ክፍል ለጉዳዩ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ መልእክቴን አስተላልፋለሁ። ከፍቅር ጋር ብዙ ገንዘብን በትንሽ ገንዘብ እንግዛ
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
በዕዝራ ኃ/ማርያም