በሰው ልጅ የዕድገት ሂደት ውስጥ ለአገር ዕድገትና ልማት ትልቅ ሃይል ተደርጎ የሚወሰደው የዕድሜ ክልል የወጣትነት እድሜ ነው፡፡ ይህ የእድሜ ክልል በአንድ በኩል በእውቀት የሚታደግበት፣ ለስራ ዝግጁ የሚኮንበትና ለቀጣዩ የዕድሜ ዘመን ጥሪት የሚያዝበት የዝግጅት ምዕራፍ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለአገራዊ ልማት አንድ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው ጉልበት የሚገኝበት የእድሜ ክልል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዕድሜ በአግባቡ ካልተያዘና ካልተመራ ለውድመትም በቀላሉ ሊውል የሚችል ሃይል እንደሆነ ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያን ለዕድገት ቅርብ ናት የሚሉ አካላት በአስረጂነት ከሚያነሱዋቸው ምክያቶችም ውስጥ አንዱ በወጣት የተገነባ ትልቅ የሰው ሃብት ያላት ሀገር መሆኗ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ ሚሊየን ከሚልቀው ህዝቧ ውስጥ 70 ከመቶ የሚሆነው በዚህ የዕድሜ ክልልና ከዚያ በታች የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ሃይል በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በቀላሉ ተደራሽና ለሚፈለገው የልማት ዓላማ የሚውል ሃይል በስፋት መኖሩን ያመላክታል፡፡
በአንጻሩ ግን ይህ ከፍተኛ ሃይል በቂ ስራና ምቹ ሁኔታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የወጣቶች ቁጥር እና ከዚሁ ጋር ተያይዞም የተማረው የሰው ሃይል ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ቢመጣም ለዚህ ሃይል በቂ የስራ እድሎችን ከመፍጠርም ሆነ ለስራ ዝግጁ ከማድረግ አንጻር ግን በቂ ስራ አልተሰራም፡፡
በዚህ የተነሳ የወጣቱ ቁጥር እየጨመረ የመሄዱን ያህል የስራ አጥ ቁጥሩም በዚያው ልክ እያደረገ መጥል፡፡ በተለይ ካለፉት ሁለት አስርት አመታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እያደጉ ከመጡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ቁጥር እያደገ ቢሄድም በቂ የስራ እድሎች ባለመፈጠራቸው ላለፉት 15 አመታት በየአመቱ አንድ ሚሊዮን ወጣቶች የስራ አጥነትን ጎራ እንዲቀላቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል በግሉ ስራ የሚፈጥረው ወጣት ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ ለዚህም የትምህርት ተቋማት ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን የማፍራት አቅማቸው አነስተኛ መሆን፤ በህብረተሰቡ ውስጥ ስራን የማማረጥ ባህል እየዳበረ መሄድ እንዲሁም ስራን ከመፍጠር ይልቅ የተቀጣሪነት ባህል እያደገ መሄድ በምክያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
በነዚህና በሌሎች ምክንያቶችም ወጣቱ ቀስ በቀስ ለአገሩ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይልቅ ከአገሩ የሚጠብቀው ፍላጎት እየበረከተ መጥቷል፡፡ በአንጻሩም አገሪቱ በአንድ በኩል በኢንቨስትመንትም ሆነ በመንግስት አቅም በቂ የስራ እድሎችን ለመፍጠር አለመቻሏና በሌላ በኩል ቢሮክራሲው በሂደት በመበላሸቱ የተነሳ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመስፋፋታቸው በርካታ ወጣቶች በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል፡፡
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች መንስኤም ከዚሁ የልማት እጦትና ከስራ አጥነት የመነጩ ችግሮች ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ በየቦታው የሚያምፀው ወጣት ቁጥር እየደገ መጥቶ አሁን ለመጣው ለውጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
ይሁን እንጂ ወጣቶች አሁን ለመጣው ለውጥ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ያህል ከለውጡ በኋላ የሚታየውን መፈናቀልና የርስ በርስ ግጭት ለማስቆምና ሰላምን ለማረጋገጥ ያበረከቱት አስተዋፅኦ አነስተኛ እንደሆነ ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ ይባስ ብሎም አንዳንድ ወጣቶች ራሳቸው የሰላም መደፍረስ መንስኤ ሲሆኑ ይስተዋላሉ፡፡
ምንም እንኳን ከነዚህ ግጭቶች በስተጀርባ ሰላምን የማይፈልጉ የተለያዩ ሃይሎች ቢኖሩም የግጭቶቹ ተዋናዮችም ሆኑ ዋነኛ ሰለባዎች ግን ራሳቸው ወጣቶች መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል፡፡ በተለይ የሰላም እጦት በኢንቨስመንቱ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ የላቀ ነው፡፡ አንድ ጊዜ የተበላሸን የአገር ገፅታ መመለስም ከባድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋ በማድረግ አሁንም በከፍተኛ ማነቆ ውስጥ ያለውን የስራ አጥነት ችግሮች ማባባሱ አይቀርም፡፡
በመሆኑም ወጣቶች በተለይ በአገራቸው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሰላምን ከማይፈልጉ ሃይሎች ጋር ባለመተባበርና ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላማቸውን ማስጠበቅ ዋነኛ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር ስራን ባለማማረጥ በተገኘው የስራ መስክ ሁሉ ተሰማርቶ በመስራት ልማቱን ማፋጠን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዛሬ የምናጣው ሰላም ለነገ ሌላ ድህነትን ከመጨመር ውጭ አንዳችም የሚፈይደው ቁምነገር አለመኖሩን ተገንዝበንም ለነገው ህይወታችን ዛሬ ላይ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል!
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2012