በ2011/12 የምርት ዘመን 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። ከዚህም 406 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። እቅዱን እውን ለማድረግም ሰፋፊ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በግብአት አቅርቦት እና አጠቃቀም፣ በክላስተር አሠራር በተለይም ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት፣ አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች እንዲጠቀም በማበረታታት ጭምር ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች ተሰርተዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የነበረው ወቅቱን የጠበቀና የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት በምርታማነቱ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል። በመሆኑም በሀገሪቱ በመኸር ሰብል አምራች አካባቢዎች እጅግ በጣም አስደሳችና አጓጊ የሆነ ምርት እንዲጠበቅ አድርጓል።
በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ዋና ዋና የመኸር ሰብሎች እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ የቆላና የደጋ ጥራጥሬዎች ለአጨዳ ደርሰዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ከደረሱ ሰብሎች መካከልም 40 ከመቶው ታጭዶ ተሰብስቧል። ይሄ በጣም ደስ ይላል። ሆኖም ግን አሁን በመሬት ላይ ያለው ከተሰበሰው ምርት በእጅጉ የሚበልጠው ማለትም 60 ከመቶው ነው።
በመሆኑም ይሄ ያልተሰበሰበ ምርት ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በፍጥነት ማጨድና መሰብሰብ ያስፈልጋል። አርሶ አደሩም ምርቱን የመሰብሰብ ዋነኛ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም አሁን ባለው ወቅታዊ የአየር ንብረት ሁኔታ ግን ብቻውን ሊወጣው አይችልም።
ስለዚህ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደምንተባበረው በራስነት ስሜት ተነሳስተን አርሶ አደሩን በአጨዳ እና የታጨደውን በማሰባሰብ ልናግዝና ልንደግፍ ይገባል። ይሄንን ስናደርግ ነው የወገን አለኝታነታችን የሚገለጸው።
በዚህ ወቅት አርሶ አደሩን በማገዝ በኩል መተባበር ያለበት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ቢሆንም በተለይ በቅርበት የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በጉልበታቸው በመርዳት እንዲሁም ባለሀብቶች የማጨጃ ኮምባይነር በማቅረብና በማከራየት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።
በአሁኑ ወቅት እየጣለ ካለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጋር ተዳምሮ ሌሎች በሰብሉ ላይ ያንዣበቡ አደጋዎች እና ስጋቶችም አሉ። በቅርቡ በስድስት ክልሎችና በ61 ወረዳዎች ተከስቶ የነበረው የበረሀ አንበጣ መንጋ እንዲሁም አልፎ አልፎም ቢሆን ብቅ እያለ ያለው የግሪሳ ወፍ ዛሬ አርሶ አደሩን እየተፈታተነው ይገኛል። ጉልበቱንና ጊዜውንም እየተሻመበት ነው።
የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በመንግሥት በኩል ሰፊ ጥረት ተደርጓል። እስካሁንም በአራት አውሮፕላኖች፣ በተሽከርካሪ ላይ በተገጠመ መርጫና የሰው ኃይል በመጠቀም ርጭት በማካሄድ የአንበጣ መንጋውን የመመከት ሥራ እየተሰራ ነው።
ሆኖም አሁንም ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የተቻለበትና ከስጋት የተላቀቅንበት ወቅት ላይ አይደለንም። አንበጣውን መከላከል እና በወቅቱ ምርቱን እንዲሰበሰብ ማድረግ እንደ ሀገር ትልቅ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ሁሉም ሰው የችግሩን ስፋትና አሳሳቢነት ግንዛቤ ውስጥ በመክተት አርሶ አደሩን ለማገዝ መተባበር ይኖርበታል።
ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው ደግሞ በገንዘቡ በመረዳዳት አሁን በአርሶ አደሩ ምርት ላይ ያንዣበበውን አደጋ አስከፊ ጥፋት ከመድረሱ በፊት ማስቆም እንደ ዜጋ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅ ግዴታ ነው።
አርሶ አደሩን ማገዘ ራስን ማገዝ ነው። ምክንያቱም ዛሬ የሰብል ምርቱ በዋነኛነት የአርሶ አደሩ ይሁን እንጂ የምርቱ ዋነኛ ተጠቃሚ ሸማቹና የከተማው ሕዝብ ነው። ችግሩም ቢያጋጥም አደጋው የጋራ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱን ሥራ ስንሰራና ትብብር ስናደርግ ለራስና ለሀገር ከሚል የእኔነት ስሜት በመነጨ መልኩ ሊሆን ይገባዋል።
ኢትዮጵያውያን ቀድሞም ቢሆን በችግር ወቅት ደራሽ፣ የተራበ አጉራሽ መሆናቸው ሃቅ ነው። ስለሆነም አሁንም የአርሶ አደሩን ጭንቀት ተረድተንና ጉዳዩ የጋራ ጉዳያችን መሆኑን ተገንዝበን በሰብል አጨዳና መሰብሰብ ሥራው ላይ ወንድ ሴት ፤ወጣት አዛውንት ሳንል በቅንጅት ልንረባረብ ይገባል!
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2012