ለዓመታት ሲንከባለል የቆየው እና ለሲዳማ ብሔር የክልልነት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ሲዳማ ዞን ተከናውኗል። በ1,692 የምርጫ ጣቢያዎች በተከናወነው በዚሁ ድምጽ አሰጣጥ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምፅ በመስጠት የምርጫ ሂደቱ በሰላም ተጠናቋል። ይህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከተመሠረተ የመጀመሪያው የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ በመሆኑ ሁኔታውን የተለየ ያደርገዋል።
የሲዳማ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ከጸደቀና ሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ የክልልነት ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቷል። ይሁንና በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 47/2 ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው የተደነገገ ቢሆንም ይህ ሕገመንግሥታዊ መብት ተግባራዊ ሳይሆን 25 ዓመታት ተቆጥረዋል። በነዚህ ዓመታት ይህ ሕገመንግሥታዊ መብት ተግባራዊ እንዲሆን የሲዳማ ሕዝብ ታግሏል፤ መስዋዕትነትም ከፍሏል። ሕዝቡ ጥያቄውን ለማሰማት አደባባይ ሲወጣ በግፍ ተገድሏል። በርካቶችም ለእስር እና ለስደት መዳረጋቸውም አይዘነጋም።
ይህን ሕዝባዊ ጥያቄ በውል የተረዳው አሁን ያለው የለውጥ አመራር መራር ተግል የተደረገበትን ይህ የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ከ25 ዓመታት በኋላ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ አድርጓል። የለውጥ አመራሩ ሥልጣን ከያዘበት ቅጽበት አንስቶ ለሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ትኩረት በመስጠት ጉዳዩ በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲፈጸም አቅጣጫ በማስቀመጥ የሲዳማ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ ኅዳር 10 ቀን 2012 ምላሽ እንዲያኝ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ የሲዳማ ሕዝብ ከጠዋቱ 12 ጀምሮ በነቂስ ወጥቶ ምርጫውን አካሂዷል። ይበጀኛል የሚለውንም በነፃነት መርጧል።
አዲሱ የለውጥ አመራር በበርካታ ጥያቄዎችም ውስጥ ሆኖ ለዘመናት የተነፈጉ የሕዝብ ጥያቄዎችን ያለምንም ማቅማማት በአፋጣኝ ለመመለስ መሞከሩ ያለውን ሕዝባዊ ወገንተኝነት የሚያሳይ ነው። ለዚህም አድናቆት ሊቸረው እንደሚገባ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። የሲዳማ ሕዝብና የተለያዩ ኃላፊዎችም ለ25 ዓመታት ሰሚ አጥቶ የቆየው ጥያቄያቸው በለውጥ አመራሩ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ መደረጉ ምስጋና ሊያሰጠው እንደሚገባ ደጋግመው ሲናገሩት ተደምጠዋል።
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሕገመንግሥታዊ የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች በየተራ ምላሽ እንደሚያገኙ ማሳያ ከመሆኑም ባሻገር ሂደቱ ልዩነትን በውይይትና በድምጽ መስጫ ሳጥን የመፍታት ዴሞክራሲያዊ ሂደት የበላይነቱን እንዲቀጥል የማድረግ አቋምን የሚያሳይ ነው። ዜጎች ያሏቸውን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ አቅርበው መፍትሄ ማግኘት እንደሚችሉና የተለያዩ ሃሳቦችም ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ በሕዝቡ ተሳትፎ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚችሉም ያመላከተ ነው።
በተለይም ደግሞ ሀገራችን በያዝነው ዓመት ለምታካሂደው ምርጫ እንደ ጥሩ ማሳያ የሚወሰድና የተለያዩ ፍላጎቶችም በምርጫ ሳጥን ብቻ ሊፈቱ እንደሚችሉ ያሳየ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነው ይበል ሊሰኝ ይገባል!
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012