ብዙ ነገሮችን የምናደርገው ዓመት ጠብቀን ነው:: ለ ም ሳ ሌ ዕቅድ የምናወጣው አዲስ ዓመት (መስከረም) ሲደርስ ነው፡፡ መስከረም ካለፈ በኋላ እንኳን አዲስ ዕቅድ ማውጣት የታቀደውም ይረሳል፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን (ለምሳሌ ህሙማንንና አቅመ ደካሞችን መርዳት) የምንሰራው እንደ እንቁጣጣሽ፣ ገና፣ ፋሲካ፣ መውሊድ ወይም አረፋ ያሉ በዓላት ሲመጡ ነው፡፡ እነዚህ በዓላት ሲያልፉ ይረሳል፡፡
ብዙ ነገሮችን የምናደርገው አሁንም ሁነት ጠብቀን ነው፡፡ ለምሳሌ ከተሞች የሚጸዱት በከተማዋ ውስጥ የሆነ ዝግጅት የሚደረግ ከሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ የከተሞች ሳምንት ወይም ሌላ መንግስታዊም በዓላት የሚደረጉ ከሆነ የዚያን ሰሞን ቀለሞች ይቀባሉ፤ ቆሻሻዎች ይጸዳሉ፡፡ ያ ዝግጅት ሲያልፍ ግን አይቀጥልም፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ በዝግጅቱ ምክንያት የወዳደቁ ተረፈ ምርቶች የሚያቆሽሹት ይበልጣል፡፡
በዚሁ ወደ ‹‹ህዳር ሲታጠን›› እንግባ፡፡ ትናንት ህዳር 12 ነበር፡፡ በየዓመቱ በዚህ ቀን ‹‹ህዳር ሲታጠን›› እየተባለ በየቦታው ቆሻሻ ይቃጠላል (ሌላ ቀን አይደረግም እንጂ) ዋና ዓላማውም ቆሻሻን ማቃጠልና ጽዱ አካባቢ መፍጠር ነው፡፡ የህዳር ወር የንጹህነት መገለጫ ነው፡፡ ምክንያቱም የጸደይ (መኸር) ወቅት ስለሆነ ከጭቃም ከአቧራም የጸዳ ነው፡፡ የክረምት ወቅት ጭቃ አለበት፤ የበጋ ወቅት አቧራ አለበት፤ የበልግ ወቅት ደግሞ የጭቃቅም የአቧረውም ቅልቅል ነው፡፡ የጸደይ ወቅት ግን እንደ ስሙ የጸዳ ነው፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ልማድ ‹‹ህዳር ሲታጠን›› የተባለው፡ ፡ ህዳር ሲታጠን ብዙ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ምክንያቶች ቢኖሩትም በዚህ ጽሁፍ ግን ስለጽዳቱ ብቻ እናውራ፡፡
እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች የማንቂያ ምክንያት ይሆኑናል፡፡ ቢያንስ በእንዲህ አይነት አጋጣሚ እንኳን አስታውሰን መነቃቃት ቢፈጠር ማለት ነው፡፡ ልቦና ቢሰጠን ደግሞ በዚያው ቢለምድብን ጥሩ ነበር፡፡
በነገራችን ላይ በህዳር ሲታጠን ምክንያት በዕለቱ የሚኖረው የቆሻሻ ማቃጠል ራሱን ችሎ ሌላ ብክለትም እንዳይሆን ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ አስታውሳለሁ፤ ባለፈው ዓመት ጠዋት ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ እየተጓዝን ነበር፡፡ ቀበና አካባቢ ስንደርስ አካባቢው በጭስ ተጥለቅልቋል፡፡ በታክሲው ውስጥ ያለው ሰው ሁሉ ህዳር 12 መሆኑ ስለገባው ‹‹ምንድነው!›› ብሎ የጠየቀ የለም፡፡ መነጋሪያ የነበረው ‹‹ይሄ ነገር ማጽዳት ነው ወይስ መበከል›› የሚለው ነበር፡፡ ምክንያቱም ከየመንደሩ የሚወጣው ጭስ እስከዋናው መንገድ ድረስ የማፈን አቅም ነበረው፡፡
ይሄ የሆነው እንግዲህ የማጽዳት ሥራው የዚያን ዕለት ብቻ ስለተሰራ ነው፡፡ ሁሌም የሚጸዳ ቢሆን ኖሮ እንዲያ የሚያጥለቀልቅ ጭስ ባልኖረ ነበር፡፡ ሰዎቹ ቆሻሻውን ሲያቃጥሉ የዚያን ቀን ብቻ ማድረግ የሚቻል ነው የመሰላቸው፡፡ ይሄ ማለት ዋና ዓላማው ቆሻሻን ማስወገድ ሳይሆን ባህል ስለሆነ ብቻ የወጉን ለማድረስ ነበር ማለት ነው፡፡
የህዳር ሲታጠን ባህላዊና ልማዳዊ ይዘት ቆሻሻን ማጽዳት ነው፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች ባለው ባህል አካላዊ ቆሻሻዎችን ማጽዳት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ቆሻሻዎችንም ያጸዳል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ከተማ ውስጥ በየመንደሩ በር ላይ ብናየውም ገጠር አካባቢ ግን ከመንደር ራቅ ብሎ ነው የሚደረገው፡ ፡ ብዙ ጊዜም ሰብል አካባቢ ነው፡፡ በዚህ የማቃጠል ባህል ውስጥ በምርት ዘመኑ የሚያጋጥሙ አሉታዊ ነገሮች ሁሉ አብረው ይቃጠላሉ ተብሎ ይታመናል፡፡
ይሄው ባህል ሲወርድ ሲወራረድ መጣና በከተሞች አካባቢ ቀኑ የሚከበረው ውጫዊ ቆሻሻዎችን በማጽዳትና በማቃጠል ሆነ፡፡ ይሄ ነገር በተለይም ለአዲስ አበባ በጣም ጥሩ ነው፡ ፡ በእንዲህ አይነት አጋጣሚ እንኳን ቆሻሻዋ ትንሽ ቢቀንስ፡፡
በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ንጹህ የምትሆነው በማጽዳት ሳይሆን ባለማቆሸሽ ነው፡፡ የከተማዋ ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ ሁሉንም ቆሻሻ ጠራርጎና አጽድቶ ቢገባ የአስተሳሰብ ለውጥ ከሌለ በአንድ ቀን ማበለሻሸት ይቻላል፡፡ የወንዝ ዳርቻዎች እኮ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል፡ ፡ በክረምት ጎርፍ ጠራርጎ ሲወስደው ወንዙ ንጹህ ይሆናል፤ ወዲያውኑ ግን ረፋድ እንኳን ሳይሆን አፍንጫ ተይዞ የሚታለፍበት ይሆናል፡፡ በግንብ እና በአጥር ዙሪያ ያለው አፍንጫ የሚበረቅስ መጥፎ ሽታ አብሮ የተገነባ አልነበረም፤ በሰዎች ሽንት እና የቆሻሻ መጣያነት ነው እንዲያ የሚሆነው፡፡
መቼም እንግዲህ ገና ለገና ይቆሽሻል ተብሎ ዝም መባል የለበትም፡፡ የሚያቆሽሸውን ያህል በዚያው መጠን ደግሞ ቶሎ ቶሎ የሚያጸዳ ቢኖር ችግሩ ይቀንሳል፡ ፡ ኧረ እንዲያውም በጣም ይቀንሳል፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙ ጊዜ ሽንት የሚሸናው ከዚህ በፊት የተሸናበት ቦታ ላይ ነው፤ ቆሻሻ የሚጣለው ቆሽሾ የሚታይ ቦታ ላይ ነው፡ ፡ የያዝነውን ሶፍት እንኳን ንጹህ ቦታ ላይ ለመጣል ይከብደናል፡፡ ቆሻሻ ቦታ ከጠፋ ብዙ ሰው ሊጥለው ያሰበውን ነገር በኪሱ ይከተዋል፤ ቆሻሻ ያለበት ቦታ ለመጣል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ሁሉም አካባቢ ንጹህ ቢሆን ሁሉም ለንጽህና እንደሚበረታታ ነው፡፡
የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? የፕላስቲክ ውሃ የታሸገበትን ወረቀት ለመጣል ሰዎች ዘወር ዘወር ብለው የሚጥሉበትን ቦታ ያማትራሉ፡፡ የተጣለ ካለ ሁሉም ይጥላል፡፡ የተጣለ ከሌለ ግን ፕላሲቲኩ ወገብ ላይ ካለው ሽፋን ውስጥ ያደርጉታል፤ ወይም ኪሳቸው ይከቱታል (እኔ ብዙ ቀን ኪሴ ከትቻለሁ)፡፡ እንግዲህ መሬት ላይ በመጣል የሚጀምረው አንድ ሰው ነው ማለት ነው፤ ከዚያ በኋላ መቼም አንዴ ተጥሎበታል በሚል ሁሉም እየጣለ ወለሉ የፕላስቲክ ፋብሪካ ይመስላል፡፡
በህዳር ሲታጠን ስም ብዙ አካባቢዎች ጸድተው ይሆናል፤ ግን እንዲህ አይነት ዓመታዊ ነገሮችን ሌላ ቀንም ብንደጋግማቸው ጥቅሙ ለራሳችን ነው፡፡ በዚያው ይልመድብን፡፡ በተለይም የመዲናችን መጥፎ ሽታ ውበት ከማበላሸቱም ባለፈ ለጤና ጠንቅ እየሆነ ስለሆነ ጽዳቱ ላይ ብንበረታ ከተማችንን እንደ ስሟ ውብና ጽዱ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይህን እንድናደርግ ህዳር ሲታጠን ልቦና ይስጠን!
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ዋለልኝ አየለ