በታዳጊ አገር እንደመኖራችንና የተጠራቀሙ ብዙ ቅሬታዎች እንደመኖራቸው የሀገራችን ሕዝቦች እንዲመለሱላቸው አጥብቀው የሚሹት በርካታ ጥያቄዎች አሏቸው፡፡ ጥያቄዎቹም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለ መሸራረፍ መከበር፣ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እውን መሆኑንና ሌሎችም ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ መንግሥትን ሲጠይቁ ኖረዋል፤አሁንም ሆነ ወደፊትም መጠየቃቸውን አያቋርጡም፡፡
አሁን ያለው የለውጥ አመራር ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ከሕዝቡ ይነሱ የነበሩ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ የመልካም አስተዳደር እና የሥራ ዕድል…በተመለከተ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በፍጥነትና በጥራት ለመመለስ የተሰራው ሥራ በቂ ባለመሆኑ ተቃውሞ ተነስቶ አገሪቱን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጧት ቆይቷል። ሰፊው የሕዝብ ተቃውሞ መንግሥትንና ገዥውን ፓርቲን ወደ ለውጥ እንዲገቡ አስገድዷል፡፡ ስለሆነም የአመራር ለውጥ ተደርጓል፡፡
አዲሱ አመራር ነባር ጥያቄዎችንና አዳዲስ ጥያቄዎችን ለመመለስ በርካታ ሥራዎች ሰርቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል ኅዳር 10 ቀን 2012 የተካሄደውን የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ የመመለስ ተግባር በአብነት ማንሳት ይቻላል:: ቀደም ብሎም በርካታ እስረኞችን ፈትቷል፡፡ ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት እንቅፋት ናቸው የተባሉ ሕጎችን አሻሽሏል፡፡ እያሻሻለም ይገኛል:: ስለዚህ አመራሩ ለጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ረገድ እስካሁን የሰራቸው ሥራዎች በጅምር ደረጃ ተገቢና የሚበረታቱ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይሁንና ጅምሩ መልካም ቢሆንም አሁንም መፍትሄ የሚፈልጉ የሕዝብ ጥያቄዎች አሉና እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ በርትቶ መስራቱ ሊዘነነጋ አይገባም፡፡
የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሰላምና መረጋጋት፣ የሕግ የበላይነት ማስከበር፣ የኑሮ ውድነት ጫና መቀነስ፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝና የውጭ ምንዛሬ እጥረት መፍትሄ ማበጀት ወዘተ ናቸው፡፡ እነዚህን ወቅታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት ፖለቲካው እንዲረጋጋ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ያለ ሰላምና መረጋጋት አንዲትም ነገር መከወን አይቻልምና። በመሆኑም መንግሥት ቅድም ተከተል አስቀምጦ ለመፍትሄው መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር ከራሱ ጥቅም በፊት ሕዝብንና አገርን በማስቀደም ያለምንም መታከት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ ኃላፊነቱን የማይወጣና ሥልጣንን ለግል ጥቅም የሚያውል አመራር ላይም ያለምንም ርህራሄ ተገቢውን አስተማሪ ርምጃ መውሰድ ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡
በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የሚታየው ሥርዓት አልበኝነት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተስተዋለው የሰላም መደፍረስ፣ በእምነት ተቋማት እየደረሰ ያለው ጥቃት ላይ ከወዲሁ መፍትሄ ማበጀት ካልተቻለ አደጋው የከፋ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ስለሆነም መንግሥት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ግዴታው ነው ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በብቃት ሊወጣ ይገባል፡፡
መንግሥት ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣት እንዳለበት ሁሉ ጥያቄ ያላቸው ወገኖችም ጥያቄያቸውን በሕግ አግባብ ብቻና ብቻ መጠየቅ አለባቸው፡፡ፍላጎትን በጉልበት ለማስፈፀም የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም መንስኤ መሆኑ ከቀደሙ ድርጊቶች መማር ይገባል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በቅርቡ የተከሰቱ ግጭቶችም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ ብቻ መቅረብ የሚኖርበት ሲሆን መንግሥትም ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር የሲዳማ ዞን የክልል እንሁን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ ምላሽ የተሰጠበት ሂደትም ጥሩ ትምህርት እንደሚሆን ይታመናል፡፡
የሕዝቦች ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ፣ የኑሮ ውድነት ጫና መቀነስ፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት ከሚሰራው በተጨማሪ መላው የሀገራችን ሕዝቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶችና ታዋቂ ሰዎች አገሪቱ ላጋጠማት ችግር የመፍትሄ አካል በመሆን የድርሻቸውን ሊውጡ ይገባል፡፡ ስለሆነም ጠያቂዎች ሰከን በሉ፤ መንግሥትም ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ ግዴታውን ይወጣ፤ ጥያቄም በሕጋዊ መንገድ ብቻ ይቅረብ፤ ሕጋዊ ምላሽ መስጠቱም ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን!
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2012