አገራት እንደየእድገት ደረጃቸውና ሥልጣኔያቸው መጠን የተለያየ የፖለቲካ አቅጣጫዎችን ሲከተሉ ኖረዋል፡፡ አንዳንድ አገራት በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ አመራር ሲመሩ ሌሎቹ ደግሞ ፍፁም አምባገነናዊ ሥርዓት ስር ለዘመናት ኖረዋል፡፡ አሁን አሁን ግን አብዛኞቹ አምባገነን መንግሥታት በህዝቦች ትግል ሆነ በተለያዩ ጫናዎች እየወረዱ በዴሞክራሲዊ ወይም በከፊል ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት ሲተኩ ይስተዋላል፡፡ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ በኩል ለዘመናት ከተጫነበት የጭቆና ቀንበር ለመላቀቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከድህነት ለመውጣት በተለያዩ ትግሎች ውስጥ አልፏል፡፡ ከዘውዳዊው ሥርዓት ዘመን እስከ አሁን ድረስ ለዴሞክራሲና ፍትህ ታግሏል፤ እየታገለም ነው፡፡
ለ17ዓመታት የትጥቅ ትግል አካሂዶ ደርግን በማሸነፍ ሥልጣን ላይ የወጣው ኢህአዴግ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ላይ በማሰባሰብና የሽግግር መንግሥት መመስረት በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመፍጠር ያደረጉት ውይይትና አብሮ ለመሥራት የነበራቸው ቁርጠኝነት በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባትና ድህነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ለማድረግ የሚያስችል እንደሚሆን ተስፋን የሰነቀ ነበር፡፡ በሽግግሩ ዘመን ህገ መንግሥት ለመቅረጽና ለማጽደቅም ተችሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከዚያ ቀደም ባልነበረ ሁኔታ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተጀመረው የነፃ ፕሬስ እንቅስቃሴም በአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት እየሰፈነ ነው ለማለት የሚያስደፍር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱም በርካታ የግል ፕሬሶች እንደ አሸን የፈሉበት ነባራዊ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ነገር ግን ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የነፃ ፕሬሶቹ እንቅስቃሴ ብዙ ርቀት ሊጓዝ አልቻለም፡፡ ለኢትዮጵያውያን ዜጎችም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ አዲስ የነበረው ይህ የዴሞክራሲ ጭላንጭል በአግባቡ ባለመጠበቁ የነበረው የዴሞክራሲ ጭላንጭልም ተንዶ ቀስ በቀስ አንዱ ለሌላው ፍጹም ጠላት ወደ መሆንና ወደ መጠላለፍ ተገባ፡፡ ብዙ ርቀት ይጓዛል ተብሎ የተጠበቀው ዴሞክራሲም እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀረ፡፡ የአገራችን ዴሞክራሲም መልሶ ስሙ በአፈና መታማት ጀመረ፡፡ ዓለምአቀፍ ተቋማትም የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ በሰብዓዊ መብት ረገጣና በፀረ ዴሞክራሲ የሚከሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በርግጥ ኢህአዴግ ልማትን ለማምጣት የተጓዘበት መንገድ ረጅም እንደነበር አይካድም፡፡ ለዘመናት በጦርነት ሲንኮታኮት የነበረውን የአገራችን ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የተጀመሩት የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በነበረው የፖለቲካ አካሄድ ቀስ በቀስ መጠለፉ አልቀረም፡፡ በተለይ የሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መበራከት ከዴሞክራሲው መዳፈን ጋር ተያይዞ ልማቱም የሚፈለገውን ውጤት እንዳያስመዘግብ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ዜጎችም በሂደት የጠበቁት ትልቅ የዴሞክራሲና የልማት ተስፋ ብዙም ሳይጓዝ ፈተና አጋጥሞታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የታየው ለውጥ ግን አዲስ አቅጣጫና ተስፋን ይዞ መጥቷል፡፡በተለይ እነዚህን ለዘመናት የተከማቹ የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት የተወሰዱት እርምጃዎች በአገራችን ለዘመናት ሲናፈቅባቸው የነበሩትን ዴሞክራሲና ልማት እውን ለማድረግ አቅም እንዳላቸው ብዙዎች ተስፋ ጥለውበታል፡፡
በዚህ የለውጥ ሂደት መንግሥት ዴሞክራሲን ለማስፋት ሁሉንም በሮች በሰፊው የከፈተበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ኢትዮጵያም በዓለም መድረክ ምንም ጋዜጠኛ በማረሚያ ቤት የማይገኝባት አገር ለመባል የበቃችው በዚሁ የለውጥ ሂደት ነው፡፡ ከጎረቤት አገራት ጋር የነበረንን ችግርም በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ሰላማዊ አካባቢን በመፍጠር ስኬታማ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ የዴሞክራሲ ምህዳሩ በመጥበቡ በአገር ውስጥ ሆነው ሥርዓቱን ለመታገል ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሰላማዊ መንገድ አገራቸው ውስጥ ሆነው እንዲታገሉ እድሉን አግኝተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በአሸባሪነት የተፈረጁትና በውጭ ሆነው ሲታገሉ የነበሩትም በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እድሉን አግኝተዋል፡፡
ከዚህም በላይ እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማስፋት የሚያስችሉ የዴሞክራሲ ተቋማትንም ለመገንባት ጅምሮች ታይተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን በአዲስ መልኩ በገለልተኛ አካል ለማደራጀት የተሄደበት መንገድ ትልቅ ውጤት የታየበት ነው፡፡ በአገራችን የሚዲያ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲንቀሳቀሱም በተመሳሳይ ትልቅ እድል የተጎናፀፉበት ወቅት ተፈጥሯል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ከፖለቲካ ነፃ ሆነው የተበላሸውን የፍትህ ሥርዓት ለማስተካከል የሚያስችል እድል አግኝተዋል፡፡
በአጠቃላይ እነዚህና ሌሎች መሰል እቅስቃሴዎች አሁን አገራችን ከፊት ለፊቷ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችላት ሃዲድ ላይ መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ሃዲድ በትክክል የምንፈልገው ቦታ የሚያደርሰን ግን በትክክለኛው መንገድ ስንጓዝበት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዳግም ሃዲዱን የምንስት ከሆነ ግን ዳግም ወደማንፈልገው የተሳሳተ መንገድ እንዳንሄድና ይህንን የዴሞክራሲ ጭላንጭል እንዳናዳፍነው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ካለፉት ጊዜያትም ተምረን በአገራችን ዴሞክራሲዊ ሥርዓትን ለማስፈን ሁላችንም አስተውለን መራመድ ይጠበቅብናል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011