አሁናችንን ስጋት ላይ የጣሉ የቅድም ችግሮች
ብዙዎቻችን በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተፈጠሩ ያሉ አሳሳቢ ችግሮች አሁን የተፈጠሩ ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ችግሮቹ ባለፉት ሥርዓቶች ጠልቀው የተተከሉ፣ በቂ ጊዜ አግኝተው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ያሉ፣ ሥር ይዘው አድገው፣ ፍሬ አፍርተውና በስለው እየተሰበሰቡ ያሉ መጥፎ የሃሳብ ዘሮች ናቸው፡፡ በተለይም ለዘመናት ያካበትነውን አብሮ የመኖር እሴታችንን ሽርሽረው እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንን ስጋት ላይ ጥለው ሁላችንንም እያስጨነቁን የሚገኙት “በማያለያዩ ልዩነቶች” የመለያየት፣ የመከፋፈልና ወደ አላስፈላጊ ጠላትነትና የእርስ በእርስ መጠፋፋት ችግር እንዲደርስብን ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ሆን ተብሎ ሲሰራበት የቆየ የስግብግቦቹ ፖለቲከኞች የጥፋት “ሌጋሲ” ነው፡፡
የራስን የማይጠግብ ምኞት ለማርካትና ዕኩይ የግል ዓላማን ለማሳካት ሆን ተብሎ በዕቅድ፣ በፖሊሲና በፕሮግራም ፣ በአዋጅና በመመሪያ በትጋት ሲተገበር የቆየው ሥራ አሁን ላይ ህዝብን በ “የማያለያዩ መለያያዎች” (በብሔርና በሃይማኖት) ከፋፍሎ እርስ በእርስ እያጠፋፋ ያለው ችግር ከ “ሰሞኑ” የተፈጠረ አይደለም፡፡
ራስን በራስ የማስተዳደር “መብት” እስከ መጠፋፋት
አሁናችንን ስጋት ላይ የጣለብን “የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና እስከ መገንጠል የመድረስ” የሚለው ህገ መንግስታዊ “መብት” እና ይህንኑ መሰረት አድርጎ የተተገበረው የሀገሪቱ አስተዳደራዊ መዋቅር በጥቅም ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የተተከለና አሁን ላይ በስፋት ማምረት የጀመረ የቆየ የጥፋት ማሽን ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ባለፉት ሃያ ዘጠኝ ዓመታት ሀገሪቱ በክልል ከተዋቀረችበት ጊዜ ጀምሮ በተለይም ከ1990ዎቹ መጨረሻ ወዲህ እስካሁን ድረስ ባሉት ከአስር በላይ ዓመታት ይኼ “የእኔ ክልል ነው፣ ከክልላችን ውጡ” በሚሉ ሰዎች ህዝብ ለበርካታ ዓመታት ከኖረበት ቀዬ በስፋት ሲፈናቀልና ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረግ ቆይቷል። ይህ ዜጎችን ከገዛ አገራቸው የማፈናቀል ድርጊት እንደ ቀላል እየታየ በዝምታ ሲታለፍ በመቆየቱ በአሁኑ ሰዓት ችግሩ ከምንጊዜውም በላይ ተባብሶ ለረጅም ዘመናት አብሮ በመኖር የምትታወቀውን አገር በተፈናቃዮች ብዛት ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ ያደረገ አገሪቱንና ህዝቦቿን የማይመጥን አሳፋሪ ታሪክ ተመዝግቧል፡፡
አሁንም ቢሆን ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው “ውጡልኝ” እየተባሉ በኃይል እየተፈናቀሉ፤ በገዛ አገራቸው ላይ ስደተኛ ሆነው አገራቸውን እየረገሙ በጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው በእርዳታ የሚኖሩ በርካታ ናቸው፡፡ ባለፉት ሳምንታት አንዴ በብሔር፣ የብሔሩ ሲነቃ ደግሞ በሃይማኖት መልኩን እየቀያየረ ህዝብን ከህዝብ እያባላ፣ ምንም የማያውቁ ንጹሃን ዜጎችን እየቀጠፈ የፍሬውን መራራነት አሳይቷል፡፡ ችግሩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብቶ ለነገ የአገር ተረካቢ ይሆናሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸውን ወጣቶች ማጥቃት ጀምሯል፡፡
ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርግ የፖለቲከኞች መልካም ጅምር
እናማ የገጠመን ችግር ከአቅማችን በላይ መስሎን አብዛኞቻችን ጭንቀት ውስጥ በገባንበትና ተስፋ ለመቁረጥ በተቃረብንበት በዚህ መጥፎ ሰዓት “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” እንዲሉ ተስፋችንን የሚያለመልም አዲስ ተስፋ ከወደ ፖለቲከኞች ዘንድ ከሰሞኑ ተወልዷል። ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም ተስፋ የሚያስቆርጡ የሚመስሉ አያሌ ችግሮች ገጥመዋት በጥበብ እየተሻገረች፣ አፈረስንሽ ሲሏት እነርሱ እየፈረሱ፣ ሁሌም በጠላቶቿ ላይ አኩሪ ድል እየተጎናጸፈች እዚህ የደረሰችው፣ ሁሌም በፈተና ፀንታ የምትኖረው ሚስጥራዊቷ አገር ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማትን ፈተና አሸንፋ በማንነቷ እንደምትፀና የሚያመላክቱ የተስፋ ጭላንጭሎች ብቅ ብለዋል፡፡
ይህም አገርን ከገባችበት የጥፋት አዘቅት ውስጥ ያወጣታል ብዬ በግሌ ተስፋ ያደረኩበትና ልቤን በደስታ ያሞቀው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቀራራቢነት በተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ከሰሞኑ የተካሄደው ውይይትና ውይይቱን ተከትሎ የመጣው “ሀገርን ማስቀደም” የሚለው የፖለቲከኞቹ ስምምነት ነው። ይህ በእርግጥም ትልቅ ተስፋን የሚያጭር ይበል የሚያሰኝ የፖለቲከኞች መልካም ጅምር ነው፡፡
መጽደቅ የጀመሩት የጠቅላዩ የተስፋ ችግኞች
ሲጀምር የብሔር ቀጥሎ ደግሞ የሃይማኖት መልክ ይዞ በተነሳውና ሰሞኑን የሰማንያ ስድስት ንጹሃንን ለህልፈት ከዳረገው ክስተት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ እየለፉለት የሚገኘው በጋራ ጉዳዮች ላይ የመተባበርና ሀገራዊ አንድነትን የማስጠበቅ ጉዳይ በጠበቁበት መንገድ እየሄደ ባለመሆኑ በእጅጉ ያሳዘናቸው ይመስላል፡፡
ነገር ግን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆነውም ሁልጊዜም ቢሆን ከጨለማው ይልቅ ቀጥሎ የሚመጣውን ብርሃን የሚመለከቱት ባለ አወንታዊ አመካከቱ መንፈሰ ጠንካራው መሪ ዶክተር አብይ በሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ተስፋ ሳይቆርጡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም ከሰሞኑ ከተከሰተው ተስፋ አስቆራጭ ክስተት በኋላም እንደ ወትሮው ሁሉ በችግሩ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ችግሮቹ መፍትሔ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ባደረጉት ያለሰለሰ ጥረት የአገርንና የህዝብን የጠወለገ ተስፋ የሚያለመልም መልካም ዜና ተሰምቷል፡፡
“የቻሉ ያግዙናል፤ ያልቻሉ ይተውናል፤ ያልገባቸው ይተቹናል፤ ያልፈለጉን ይቃወሙናል፤ እኛ ግን ወገባችንን ጠበቅ አድርገን የጀመርነውን ጨርሰን ሪባን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም” በሚለው መርሃቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ወገባቸውን ታጥቀው ጥረታቸውን የቀጠሉት ጠቅላዩ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ፤ “የቻሉ ያግዙናል” ያሉት ተሳክቶ የሚያግዛቸው አግኝተዋል፡፡
በዚህም ከገዥና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከምሁራንና ከባለሀብቶች እና ጉዳዩ ይመለከተናል ከሚሉ የአገሪቱ ልሂቃን ጋር ባደረጉት ፍሬያማ ውይይት የሚያለያዩ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በተለይም ችግሩ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መዛመቱን ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተማከሩት የተለያዩ ሃሳብና አመለካከቶችን የወከሉ የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ከራስ በፊት አገርን ለማስቀደም መስማማታቸው ነው ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ወጥተን በአዲስ ተስፋ እንድንሞላ ያደረገን፡፡
የስምምነቱ ዋና ይዘት
በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠረውን ሁከት ተከትሎ ችግሮቹ በተከሰቱባቸው በሁለቱ ትላልቅ ክልሎች የሚገኙ ከገዥውና ተፎካካሪ ወገን የተውጣጡ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከተወያዩ በኋላ በጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ መግለጫውን የሰጡት ከገዥው ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ራዕይ ግንባር ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ በሰጡት የጋራ መግለጫ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ በክልሎቹ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈፀመው ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፓርቲዎቹ የኦሮሞና የአማራ ህዝቦችን ትስስር ከሚያላሉና ወደ ብጥብጥ ከሚያመሩ ማናቸውም ተንኳሽ ጉዳዮች ለመቆጠብና በህዝብ ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን ለመቀልበስ ተባብሮ ለመስራት መወሰናቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀጥለውም “ልዩነቶች ቢኖሩንም ልዩነቶቻችን ከአገራችንና ከህዝባችን የማይበልጡ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል” ብለዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ለአገር ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው በጋራ ተባብረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎችና ዩኒቨርሲቲዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ የድርሻቸውን በመወጣት በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች አንድነት ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪም በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ባለሀብቶች፣ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችም ውይይት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክረታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከሰሞኑ በተከሰቱ ግጭቶች በህይወትና በንብረት ላይ የደረሱ ጉዳቶችንና በቀጣይ መወሰድ የሚገባቸውን የመፍትሔ እርምጃዎች አስመልክቶ ውይይት ከተደረገ በኋላ ባለሃብቶቹ ድጋፍ በሚያደርጉበት ሁኔታ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ስምምነቱ ተስፋ ሰጪ የተባለበት ምክንያት
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስምምነትና የፖለቲከኞቹ ውሳኔ አገሪቱን አሁን ካለችበት ችግር ያወጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ዋነኛው ምክንያት የችግሩን መሰረታዊ መንስኤ “ተገንዝቧል” የሚል ነው፡፡ ይኸውም አሁን ላይ እየተከሰቱ ያሉትን ጨምሮ አገርን የፊጥኝ ጠፍንገው ወደፊት አላራምድ ያሉት ሁሉም ችግሮች የሚፈልቁት ከፖለቲካ ባህላችን ነው የሚል ዕምነት ስላለኝ ነው፡፡ በተለይም ከላይ በመግቢያዬ በግልጽ እንዳስቀመጥኩት አሁን ላይ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉና ህልውናዋን እየተፈታተኑ የሚገኙ ችግሮች የተፈጠሩት ከአንድነትና ከትብብር ይልቅ ልዩነቶችን በማጎን ላይ የተመሰረተ የተሳሳተ መንገድን በተከተሉና ከአገር በላይ ራሳቸውን ባስቀደሙ ጥቅመኛ ፖለቲከኞች ነው፡፡
መፍትሔውም ይኸው ነው- ይህንን የተሳሳተ የፖለቲካ መንገድ በማስተካከል ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፤ ከፉክክር ይልቅ ትብብርን መሰረት ያደረገ ስልጡን የፖለቲካ ባህል መፍጠር! ፖለቲካውን ማሰልጠንና ሰውኛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የችግሩን መሰረታዊ መንስኤ ማወቅ! ዋነኛ መንስኤው ፖለቲካው ራሱ መሆኑን ካወቅን ደግሞ ሳንውል ሳናድር ይህንኑን ኋላ ቀሩን የፖለቲካ ባህላችንን መለወጥ ይጠበቅብናል፡፡ እንዴት ለሚለው ባጭሩ በመጠላለፍ፣ በመጠፋፋት፣ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተውን የሴራና የክፋት ፖለቲካችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ በመደጋገፍ፣ በመተባበር፣ በፍቅርና በመልካምነት ላይ የተመሰረተ ስልጡንና ሰናይ አዲስ የፖለቲካ ባህል መገንባት ይጠበቅብናል፡፡
ከፋፋዩንና አውዳሚውን የብሄር ፖለቲካ ፍቅርና አንድነትን በሚያለመልም የተሻለ የአብሮነት ፖለቲካ መተካትም ተቀዳሚ አገራዊ ተግባራችን ሊሆን ይገባል። በሌላ አነጋገር ፖለቲካውን “ሰውኛ” ማድረግ ይገባል። ምክንያቱም ፖለቲካ ማለት እኛ እንደምናስበው “ያለ ሴራ የማይሆን”፣ “ውሸት ግድ የሚልበት”፣ “ስልጣን መያዣና ብዙሃኑን ማስገበሪያ” አይደለም፡፡
ሮማውያን እንደሚሉት እንዲያውም “ፖለቲካ ማለት ህዝብን ባለጸጋና የተሻለ ማድረጊያ መሳሪያ፣ ፖለቲከኛ ማለት ደግሞ የግል ህይወቱን ለህዝብ የሚሰዋ” ማለት ነውና ለፖለቲካ ያለንን አመለካከትና ግንዛቤ ማስተካከል የሁላችንም የቤት ሥራ ይሁን፡፡ ታዲያ የገጠመን ችግር ሁሉ የተፈጠረው ከአገር በፊት ራሳቸውን ባስቀደሙ ፖለቲከኞች ምክንያት ከሆነ “አገራችንን ማስቀደም ይገባናል” የሚሉ ፖለቲከኞችን ስንሰማ እንዴት አንደሰት? እንዴትስ በተስፋ አንሞላ!?
ለህዝብ ጥቅም እንታገላለን የሚሉና የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች “ልዩነቶች ቢኖሩንም ልዩነቶቻችን ከሀገራችንና ከህዝባችን የማይበልጡ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል” ሲሉ ከመስማት በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ?። የተለመደውን የመከፋፈልና የመለያየት ስንኩል የፖለቲካ አስተሳሰብ ትተው “ለአገር ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተን በጋራ ተባብረን እንሰራለን” ማለታቸው በእርግጥም አገራችንን ለምንወድ ሁሉ ብሩህ ተስፋን የሚያጭር ታላቅ የምስራች ነው፡፡
እዚህ ላይ ሳናሳስብ ማለፍ የማይገባን አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ፡፡ እርሱም የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ የሆነውን የልዩነት ፖለቲካ ለማሻሻልና ለህዝብና ለአገር የሚበጀውን መንገድ ለመከተል፤ “ልዩነትን አቻችሎ ለሀገር ቅድሚያ ሰጥቶ፤ የህዝብና የአገርን ጥቅም አስቀድሞ በጋራ ለመስራትና ለመተባበር” የተደረገው የፖለቲከኞቻችን መልካም እሳቤ “ጅምር” ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም የሚል ነው፡፡ ተስፋችን ዕውን ሆኖ አገራችን ከገባችበት ችግር ትወጣ ዘንድና ህዝቦቿም ደህንነታቸውና ሰላማቸው ተጠብቆ እንደ ወትሮው ሁሉ በፍቅርና በአንድነት አብረው መኖር ይችሉ ዘንድ ጅምሩ ተጠናክሮ በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት ይኖርበታል የሚለውን አበክረን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
የ“መደመር” ን ዕሴቶች እንደ መውጫ
በቅርቡ ታትሞ ገበያ ላይ በዋለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “መደመር” የተሰኘው መጽሃፋቸው በገጽ 47 የመደመርን ዕሴቶች በሚያብራራው ክፍል ላይ “የመደመር ዕሴቶች በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነቡ የምንፈልጋቸውን ጥቅል ዕሴቶች ታሳቢ ያደረጉ….የመደመር ምሰሶዎች ናቸው” ሁለት መሰረታዊ ዕሴቶችንም እንደሚከተለው አስቀምጠዋቸዋል፡፡
“ከመደመር ዕሴቶች መካከል አንዱ “አገራዊ አንድነት” ነው፡፡ አገራዊ አንድነት ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተጋመደ፣ የተሰናሰለና የተዋደደ መሆኑን አመላካች ነው። የአገራችን ብሔሮች እጣ ፋንታ በጋራ ለማደግ የተሰራ ብቻ እንጂ ተለያይተን ወይም ተነጣጥለን ሉዓላዊ አገር ሆነን፤ የነጠላ ህልውናችንን አስጠብቀን በሰላም መቆየት አንችልም። አገራዊ አንድነታችን የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ማስጠበቅ ጉዳይ ጭምር ነው”፡፡
እኔም እላለሁ የሚበጀን ብቻ ሳይሆን ከሰሞኑ ዓይነት ህልውናችንን የሚፈታተን ችግር ብቸኛ መውጫችን ይኸው ነው፡፡ ምክንያቱም ዜጋን በሃይማኖትና በብሔር እየለዩ ባላገርን ከአገሩ የሚያፈናቅሉ “ክልሎች” ዶክተር አብይ እንዳሉት “በሰላም የሚኖሩት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ማደግ ሲችሉ ብቻ እንጅ ነጠላ ማንነታቸውን ለማስጠበቅ ሌላውን በመግፋት አይደለም”፡፡ ደግሞስ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሉ ድረስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ መኖሪያዎች እንጂ የአንድ ብሔር ወይም ሃማኖት ብቻ የግል ጎጆ ማን አደረጋቸው?
ኢትዮጵያ እኮ የሁሉም አገር ነች፤ ሀገርም የጋራ ሆና ሳለ ሰው መርጦ በኖረበት የአገሩ መሬት ላይ እንዳይኖር መከልከል ይቻላልን? የአገሩን ሰው ከአገሩ ማፈናቀልስ ትክክል ሊሆን ይችላልን? ክልሎችስ በአገር ውስጥ እስካሉ ድረስ ህዝብ የጋራ መኖሪያዎች እንጂ የአንድ ብሔር አባላት ወይም የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ የግል መኖሪያ ናቸውን? ክልሎች የአገር አካሎች፤ አገር ደግሞ የጋራ ናትና “ይሔ የእኔ ክልል ነው፤ ከክልሌ ውጡ ማለት አይቻልም! “አገር የጋራ ነው፣ ሃይማኖት የግል ነው” እንዲል ታላቁ ሊቅ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ክልሎች በሃይማኖትና በብሔር በግል ሊያዙ አይችሉም፣ በአገር ውስጥ የሚገኙ የጋራ መኖሪያዎች ናቸውና፡፡
ሁለተኛው የመደመር ዕሴት ደግሞ “የዜጎች ክብር” ነው፡፡ “የዜጎች ክብር ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገር ክብራቸው ተጠብቆና አገራቸውን መከታ አድርገው እንዲኖሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የመስራት ፍላጎት ነው፡፡ ክብር የጋራ ጥቅምና ስጋትን የማስጠበቅ መርህ ነው፡፡ ሰዎች ሁልጊዜም ወደ ግብ መቅረቢያ መንገድ ሳይሆን ራሳቸው ግቦች እንደሆኑ የማመን ዕሴት ነው፡፡”
“የሰዎች ክብር በሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር፣ በቡድንና በግለሰብ ደረጃ ሊታይ ይችላል፡፡ ሌሎች ማንኛውም ዕሴቶች የሰውን ክብር የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው። በሥራዎቻችን ሁሉ ዜጎችን አክብሮ ማገልገል፣ በማንኛውም ጉዳይ ላይ በክብር ማማከርና መያዝ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ መደመር ከዚህ አንጻር ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን በማስወገድ “ሰው” ሰው በመሆኑ ብቻ ክብሩና ነጻነቱ እንዲከበር ዘብ መቆም ማለት ነው፡፡ መደመር በዚህ ጊዜ ግለሰባዊ ነጻነትና ማህበረሰባዊ ደህንነትን ማቀንቀን ይሆናል”፡፡
እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲመጣ ከፊት ሆነው መልካሙን መንገድ የመሩንን ዶክተር አብይን አለማመስገንም ንፉግነት ነው፡፡ የ “እኛ” እና “እነርሱ” ዋልታ ረገጥ የጠላትነት ፖለቲካ በፈጠረው ከባድ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለዚች አገርና ህዝቦቿ የሚበጀውን “አብሮ የመኖር” የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሁሌም በተስፋ እየሮጡ የተስፋ ጭላንጭል ያሳዩንን መሪ መልካም መንገዳቸውን አለመከተልም ስንፍና ነው፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2012
ይበል ካሳ