ክፍል አንድ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
“እርጥብ እሬሳ ደረቁን ያስነሳ” የሚባል የአገራችን ብሂል አለ። ዛሬ ላይ ወዳጅ ዘመድ ሞቶ ሲለቀስ ከዓመታት ቀደም ብሎ የሞተውንም ዘመድ እያነሳሱ ማልቀስ ልማድ ነው። ለዚህ ነው “እርጥብ እሬሳ ደረቁን ያስነሳ” የሚባለው።
ሰሞኑን በአገራችን “የሳይበር ሳምንት” ተብሎ መከበሩ ይታወሳል። በዚሁ ወቅት የሳይበር ጥቃቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውና የሳይበሩ ዓለም ያሉበት ስጋቶች እየተነሱ የግንዛቤ ማስጨበጫና ሌሎች የተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄዱ ሰንብተዋል።
በዚህ ምክንያት ነው ታዲያ እኔም የሳይበር አዋጃችን ሲታወሰኝ ሕጉ ከመውጣቱ በፊትና ከወጣም በኋላ በአዋጁ ዙሪያ ሲነሱ የነበሩ ክርክሮች ትዝ ያሉኝ። እናም በአንድ በኩል ስለ አዋጁ ግንዛቤ ለመፍጠር፤ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ችግሮች ያሉባቸው ሕጎቻችን እየተሻሻሉ በመሆኑ የአዋጁን ሕጸጾች በመንቀስ የመሻሻል ዕጣ ከገጠመው ሊስተካከሉ ይገባቸዋል የምላቸውን ጉዳዮች ለማንሳት ምቹው ጊዜ አሁን ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የበይነ መረብ መሃንዲሶች (Internet Engineers) ስብስብ የሆነውና “ኢንተርኔት ሶሳይቲ” የተባለው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ግብረ-ኃይል የኢትዮጵያ መንግስት አዋጁን ለማሻሻል መወሰኑንና ግብረ-ኃይሉም በሕጉ ላይ የማሻሻያ ሐሳቦቹን እንዲሰጥ ግብዣ የቀረበለት መሆኑን በቅርቡ ማስታወቁ ደግሞ በእርግጥም ሕጉ ከሚሻሻሉት ሕጎች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ምክንያታዊ ግምት መውሰድ ይቻላል።
የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ላለንበት ዘመን ቁልፍ አጀንዳ ስለመሆኑ መናገር ጉንጭ ማልፋት ይሆናል። ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኤቲኤም፣ የኤሌክትሮኒክ የገንዘብ ዝውውርና የክፍያ ስርዓቶች ወዘተ… በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ። በአገራችን የእነዚህ የአይሲቲ አገልግሎቶችና አገልግሎቾቹን ተጠቅመው የሚያስጠቅሙን ተቋማት ተበራክተዋል።
ይሁንና የአይሲቲ አጠቃቀም ተገቢ ጥንቃቄና ጥበቃ ካልተደረገለት አጠቃላይ ስርዓቱ ለሳይበር ጥቃቶች ስለሚጋለጥ ጉዳቱ የከፋ መሆኑ አይቀሬ ነው። ከግል ነጻነት መደፈር እስከ አገር ሁለንተናዊ እድገት መሽመድመድ የዘለቀ ከባድ አደጋ ያደርሳል። ይህ ደግሞ የሳይበር ዓለሙ አይቀሬ እውነታ ነው።
በሳይበር ሳምንት ተደጋግሞ ሲነገር እንዳደመጥነውም በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። በ2011 ዓ.ም. በዘጠኝ ወራት ብቻ 488 የሳይበር ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል 40 በመቶው በድረ ገጾች ላይ የተፈጸሙ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ባንክና ቴሌኮምን በመሳሰሉ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የተፈጸሙ ናቸው።
እርግጥ ነው የአገራችን የአይሲቲ ጉዳዮች ዋነኛ ሰፊ ለጓሚ ተቋም የሆነው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የተቃጡትን የሳይበር ጥቃቶች በመመከትና ጥቃቶችም እንዳይፈጸሙ ቅድሚያ ጥንቃቄ በማድረግ ወሳኝ ሚና እየተወጣ መሆኑ ይነገራል።
ያም ሆኖ የሳይበር ጥቃቶች በባህሪያቸው ፈጣን፣ ለመፈጸም ምቹና በአብዛኛው ፈጻሚያቸውም የማይታወቅ በመሆናቸው በየጊዜው የመመከት አቅምን ማጎልበት ያስፈልጋል። በሳይበር ጥቃቶች ተጎጂና የሳይበር ምህዳሩ ተዋንያን የሆኑትን ተጠቃሚዎችንና ድርጅቶችን በማንቃት የየድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግም ጠቃሚ ነው።
በተቋም፣ በአይሲቲ መሰረተ ልማትና በሰው ኃይል ረገድ ከሚከናወነው የአቅም ግንባታ ሥራ እንዲሁም የተጠቃሚዎችንና የባለድርሻዎችን ግንዛቤ ከማጎልበት ብሎም ቅንጅታቸውን ከማጠናከር በተጓዳኝ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን በጠንካራ መሰረት ላይ መዘርጋትም ጉልህ ሚና ይጫወታል። በዚሁ መነሻ በኢትዮጵያ በ2001 ዓ.ም. የአይሲቲ፤ በ2003 ዓ.ም. ደግሞ የመረጃ ደህንነት ፖሊሲዎች ወጥተዋል።
ይሁንና ፖሊሲ በሕግ ማዕቀፍ ካልተደገፈ የተሻለ ውጤት እንደማያመጣ እየታወቀ ሁለቱ ፖሊሲዎች ያለሕግ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ የተሟላ የኮምፒውተር ወንጀሎች ሕግ የወጣው በ2008 ዓ.ም. ነው። ከዚህ ሕግ አስቀድሞ ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት እና የወሳኝ ኩነቶች አዋጅ እንዲሁም ይድረስ ይድረስ በሚል ግድግዳው ሰንበሌጥ ዓይነት ሆኖ ጸድቆ እስካሁንም ከእነ ችግሩ በሥራ ላይ ያለው የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅም ወጥተዋል። በ1996 ዓ.ም. የወጣው የወንጀል ሕግም እፍኝ የማይሞሉ የሳይበር ወንጀል ድንጋጌዎችን አካቷል።
ነገር ግን ሕጎቹ ከአዳዲስ የቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር ተጣጥመው መጓዝ የተሳና ቸው፤ የሳይበር ምህዳሩን ደህንነት በማስጠበቅ የኮምፒውተር ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር፣ ለመመርመርና አጥፊዎችን ለፍትህ ለማቅረብ የማያስችሉ ሆነው ተገኝተዋል። እናም አዳዲስ የሳይበር ወንጀሎችን እንዲሁም የተለዩ የምርመራ፣ የማስረጃና የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎችን አካትቶ ራሱን የቻለና የፖሊሲ መሰረት ያለው የኮምፒውተር አዋጅ በ2008 ዓ.ም. ሊወጣ ችሏል።
የአዋጁ አስፈላጊነትና መልካም ጎኖቹ እንደተጠበቁ ሆነው ረቂቁ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ይበልጡንም አዋጁ ከጸደቀ በኋላ ሕጉ ከአገሪቱ ሕገ መንግስትና ተቀብላ በማጽደቅ የህጎቿ አካል ካደረገቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር ይቃረናል በሚል በዋናነት በግል የፕሬስ ውጤቶች የሰላ ትችት ሲሰነዘርበት እንደነበር አይዘነጋም።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚጻፉ የምርምር ውጤቶችና በዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች በሚወጡ ሪፖርቶችም ላይ አዋጁ በተለይም የሰዎችን ግላዊ የኮሚዩኒኬሽንና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ስጋት ላይ የጣለ ስለመሆኑ በሰፊው ተገልጿል። አዋጁ የጸደቀበት ወቅትም ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ጨምሮች ጦማርያን፣ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾችና ሐቀኛ አክቲቪስቶች ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ምክንያት ለእስር የሚዳረጉበት ወቅት ስለነበር መንግስት የአመለካከትና የሀሳብ ነጻነትን ለማፈን ያወጣው የጸረ-ሽብር አዋጁ ታናሽ ወንድም ተደርጎም ሲብጠለጠል ነበር።
የሳይበር/የኮምፒውተር ወንጀሎች
ከቃሎቹ አጠቃቀም ስንጀምር የሳይበር ወንጀል እና የኮምፒውተር ወንጀል በመተካካት ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው። የተለያዩ ጸሐፍትና ሕጎች ሁለቱንም ቃላት እያቀያየሩ ይጠቀማሉ። በእርግጥ በ”ሳይበር ወንጀል” እና በ”ኮምፒውተር ወንጀል” መካከል ቴክኒካዊ በሆነ የሙያው አገላለጽ ረገድ ልዩነቶች ስለመኖራቸው መናገር ይቻላል። “የሳይበር ወንጀል” የሚባለው ኦንላይን (Online) የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚመለከት ሲሆን፤ “የኮምፒውተር ወንጀል” ደግሞ የኢንተርኔት ኦንላይን መረብ ቢኖርም ባይኖርም ኮምፒውተሩን ራሱን፣ የኮምውተር ሥርዓቱን (ሲስተሙን) አልያም የኮምፒውተር ዳታውን ማጥቃት ወይም ያለፈቃድ መግባትን የሚያጠቃልል ሰፊ አገላለጽ ነው።
የእኛ አገር ሕግ ደግሞ “የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008” ይሰኛል። በሕጉ መሰረት የኮምፒውተር ወንጀሎች በሶስት ዓበይት ዘውጎች ተከፋፍለዋል። የመጀመሪያው በኮምፒውተር፣ በኮምፒ ውተር ሥርዓት፣ በኮምፒውተር ዳታ ወይም በኮምፒውተር ኔትወርክ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው።
ሁለተኛው እነዚህን ማለትም ኮምፒውተርን፣ የኮምፒውተር ሥርዓትን፣ የኮምፒውተር ዳታን ወይም ኔትወርክን በመጠቀም የሚፈጸም ወንጀል ነው። በኮምፒውተር፣ በኮምፒውተር ሥርዓት ወይም በኮምፒውተር ኔትወርክ አማካኝነት ሕገወጥ የኮምፒውተር ዳታ ይዘትን ማሰራጨት ደግሞ ሶስተኛው የኮምፒውተር ወንጀሎች ዘውግ ነው።
በእነዚህ በሶስቱም ዓበይት የኮምፒውተር ወንጀሎች ዘውግ ስር ደግሞ አዋጁ ዝርዝር የወንጀል ድንጋጌዎችን ከነቅጣቶቻቸው ይዟል። እናም በዚህና በቀጣዩ እትም በምናቀርበው ጽሁፍ በየወንጀሎቹ ሥር ኮምፒውተር ከሚለው ቃል ጀምሮ በእያንዳንዱ ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በሕጉ የተሰጠውን ትርጓሜ መመልከት ሳያስፈልገን የወንጀሎቹን ዓይነቶች እንዳስሳለን። ከሁሉም በላይ በወንጀል ድንጋጌዎቹ፤ ከምርመራ፣ ከማስረጃና ከሥነ ስርዓት እንዲሁም ከመከላከል ጋር በተያያዘ አዋጁ ያሉበትን ሕጸጾች እንዳስሳለን። የመፍትሔ ሃሳቦችንም እንጠቁማለን።
በኮምፒውተር ሥርዓትና በዳታ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች
በኮምፒውተር ሥርዓትና በዳታ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚባሉት ሕገወጥ ደራሽነት (Illegal Access)፣ ሕገወጥ ጠለፋ (Illegal Interception)፣ ጣልቃ መግባት (Interference)፣ በዳታ ላይ ጉዳት ማድረስ እንዲሁም ከኮምፒውተር መሳሪያና ዳታ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ናቸው።
ሕገወጥ ደራሽነት የሚባለው ሆነ ብሎ ያለፈቃድ ወይም ከተሰጠ ፈቃድ ውጪ በኮምፒውተር ስርዓት ወይም በዳታ ወይም በኔትዎርክ ላይ ደራሽነትን ማግኘት ነው። ደራሽነት የሚባለው ደግሞ ከኮምፒውተር ሥርዓት ጋር ግንኙነት የመፍጠር፤ ወደኮምፒውተር ሥርዓቱ የመግባት፣ ዳታ የማከማቸት፣ የተከማቸን ዳታ የማግኘት፣ የማየት፣ የመውሰድ፣ የማንቀሳቀስ፣ ወደሌላ የማከማቻ መሳሪያ (ለምሳሌ ፍላሽ ዲስክ) መገልበጥ እንዲሁም ማንኛውም ሌላ የዳታ ፕሮሰሲንግ አገልግሎት (ዳታ መቀበል፣ ማሰራጨት፣ መተንተን፣ መጓጓዝ ወዘተ) ማግኘት ነው።
በኮምፒውተር ሥርዓትና በዳታ ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ውስጥ ሁለተኛው ወንጀል ሕገወጥ ጠለፋ ነው። ይህም ያለፈቃድ ወይም ከተሰጠ ፈቃድ ውጪ ይፋዊ ያልሆነን የኮምፒውተር ዳታ ወይም የዳታ ፕሮሰሲንግ አገልግሎት መጥለፍ ነው። ጠለፋ በኮሚዩኒኬሽን ሂደት ላይ የሚገኝ ዳታ ወይም የዳታ ፕሮሰሲንግ አገልግሎት መከታተል፣ መቅዳት፣ ማዳመጥ፣ መውሰድ፣ ማየት ወይም መቆጣጠርን ይጨምራል።
ሶስተኛው ወንጀል ደግሞ በኮምፒውተር ሥርዓት ላይ ጣልቃ መግባት ሲሆን፤ ይኸውም ሆን ብሎ ወይም ከተሰጠ ፈቃድ ውጪ የኮምፒውተር ዳታን በማስገባት፣ በማሰራጨት፣ በማጥፋት ወይም በመለወጥ የኮምፒውተር ሥርዓትን ወይም ኔትዎርክን መደበኛ ተግባር በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ማደናቀፍ፣ ማወክ፣ ማውደም ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ማድረግ ነው።
አራተኛው ወንጀል በኮምፒውተር ዳታ ላይ ጉዳት ማድረስ ነው። ይህ ወንጀል ያለፈቃድ ወይም ከተሰጠ ፈቃድ ውጪ የኮምፒውተር ዳታን በመለወጥ፣ በማጥፋት፣ በማፈን፣ ትርጉም እንዳይኖረው ወይም ጥቅም እንዳይሰጥ ወይም ለሕጋዊ ተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዳይሆን በማድረግ የሚፈጸም ጥቃት ነው።
እነዚህ አራቱም ወንጀሎች እንደ የክብደታቸው መጠን እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣሉ። ጥቃቶቹ የተፈጸሙት ለወታደራዊ ጥቅም ወይም ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ በሚውል ምስጢራዊ የኮምፒውተር ሥርዓት፣ ዳታ ወይም ኔትዎርክ ላይ ከሆነ ወይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወይም አገሪቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ በምትገኝበት ወቅት (ይህ ምን ማለት ነው የሚለው በሕጉ ባለመተርጎሙ ለትርጉም የተጋለጠ ነው) የተፈጸመ ከሆነ ደግሞ እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣሉ።
በአምስተኛነት የሚጠቀሱት ወንጀሎች ከኮምፒውተር መሳሪያና ዳታ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ በኮምፒውተር ሥርዓት፣ ዳታና ኔትዎርክ ላይ ጉዳት ለማድረስ ዓላማ የተመረቱ (የተሻሻሉ) የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን ሆን ብሎ በኮምፒውተር ሥርዓት አማካኝነት ማሰራጨት፤ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከፋፈል ወይም ይዞ መገኘት እንዲሁም ደራሽነት ማግኘት የሚያስችል የኮምፒውተር ፕሮግራም የሚስጥር ኮድ፣ ቁልፍ፣ የይለፍ ቃል ወይም ሌላ መሰል ዳታ ያለፈቃድ ወይም ከፈቃድ ውጪ ይፋ ማድረግ ወይም ለሌላ ሰው መስጠት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ወንጀሎች እንደየክብደታቸው መጠን እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ወይም እስከ አምስት ዓመት ቀላል እስራት ያስቀጣሉ።
የዓለም የሰብዓዊ መብቶች እናት በሚባሉት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (Universal Declaration On Human Rights) በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (International Covenant On Civil and Political Rights) አንቀጽ 19 ላይ የተጠቀሰውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መነሻ በማድረግ የተቋቋመው “አርቲክል 19” (Article 19) የተሰኘው የመብት ተሟጋች በአዋጁ ዙሪያ ባሰፈረው ጽሑፍ ውስጥ እነዚህ በአምስተኛው ቋት ውስጥ የተካተቱት ድርጊቶች በራሳቸው የሚያስቀጡ ወንጀሎች መሆን እንደማይገባቸው ይሞግታል። ይልቁንም ድርጊቶቹ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ድረስ የተዘረዘሩትን ወንጀሎች ለመፈጸሚያነት ውለው ወይም ከባድ ጉዳት አስከትለው ከሆነ ወንጀል ተደርገው ሊደነገጉ እንደሚገባ በማንሳት አዋጁን ይነቅፋል።
ከዚህም ሌላ ለእነዚህ ወንጀሎች የተቀ መጠላቸው ቅጣት ከባድ መሆኑን በማንሳት ቅጣቱ ከድርጊቶቹ ጋር የተመጣጠነ አለመ ሆኑንም ነው “አርቲክል 19” የሚግል ጸው። ከዚሁ ጋር በማያያዝም አንድ ሰው የሚስጥር ኮድ፣ ቁልፍ ወይም የይለፍ ቃል በቸልተኝነት ለሌላ ሰው ቢሰጥ የእስራት ቅጣትና የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣልበት በሕጉ የተደነገገውን በመንቀፍም በተለይም እንደኢትዮጵያ ባለ ንቃተ-ቴክኖሎጂ ባልዳ በረበት አገር ውስጥ በድርጊቱ ምክንያት ጉዳት መድረስ ያለመድረሱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በቸልተኝነት የተፈጸመን ድርጊት በእስራት መቅጣት አግባብ እንዳልሆነም ነው የሚገልጸው።
በኮምፒውተር አማካኝነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች
በኮምፒውተር አማካኝነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው በዚህ ዘውግ ሥር የሚመደቡት የማጭበርበር፣ የማታለልና የሥርቆት ወንጀሎች ናቸው። በኮምፒውተር አማካኝነት የሚፈጸም የማጭበርበር ወንጀል የሚባለው አንድ ሰው የሌላን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ማናቸውንም መብት ወይም ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ሕጋዊ ውጤት ያለውን ወይም ሊኖረው የሚችለውን የኮምፒውተር ዳታን ወደ ሐሰት የለወጠ ወይም ሐሰተኛ ዳታ ያዘጋጀ ወይም በዚሁ የተገለገለ እንደሆነ ነው።
በኮምፒውተር አማካኝነት የሚፈጸም የማታለል ወንጀል የሚባለው ደግሞ አንድ ሰው አሳሳች ዳታዎችን በማሰራጨት፣ የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር ወይም መግለጽ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ ዕምነት በመጠቀም ሌላውን ሰው አታልሎ የራሱን ወይም የሶስተኛ ወገንን ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት እንዲፈጽም ካደረገው ነው። በተጨማሪም በተጭበረበረ መንገድ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ዳታን በመለወጥ፣ በማጥፋት ወይም ሌላ ጉዳት በማድረስ በሌላ ሰው ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዲደርስበት ማድረግም የማታለል ድርጊት ነው።
በኮምፒውተር አማካኝነት ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ውስጥ ሶስተኛው የኤሌክትሮኒክ ማንነት ስርቆት ነው። ይኸውም ከላይ የተገለጸውን የአታላይነት ወንጀል ለመፈጸም ወይም ለሌላ ለማንኛውም ዓላማ ለማዋል በማሰብ የኤሌክትሮኒክ ማንነት የሚያረጋግጥ ዳታ ያለባለቤቱ ፈቃድ በኮምፒውተር ስርዓት አማካኝነት የማምረት፣ የመሸጥ፣ የማግኘት፣ ይዞ የመገኘት ወይም ለሌላ ሰው የማስተላለፍ ወንጀል ነው።
ተከታዩን የጽሁፉን ክፍል ሳምንት ይጠብቁ፤ በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2012
በገብረክርስቶስ