የ2005 ዓ.ም መሰናበቻና ወደ 2006 ዓ.ም መሸጋገሪያ የነበረችው ወርሃ ጳጉሜ ለወይዘሮ ፋንታነሽ አሰፋ መልካም ዜናን አላሰማቻቸውም:: አንዳች ዱብ ዕዳ ወረደባቸው እንጂ፡፡ በጉሮሮ ካንሠር ይሰቃዩ የነበሩት ባለቤታቸው አቶ መሐመድ ሰዒድ ያደረባቸው ጽኑ ሕመም 10 ዓመታት በዘለቀው ትዳራቸው ያፈሯቸውን ልጆችና ባለቤታቸውን እንኳ በወጉ እንዲሰናበቱ ዕድል ሳይሰጣቸው ከዚህች ምድር አሰናበታቸው፡፡
በዚህ መልኩ የትዳር አጋራቸውን ያጡት ወይዘሮ ፋንታነሽ ቀጣይ የሕይወት ጉዟቸውን እንዴት እንደሚመሩ ጭንቅ ጥብብ ይላቸዋል፡፡ በመተሳሰብና በፍቅር የተገነባ ትዳራቸው በአሳዛኝ ሁኔታ መቋጨቱም ነገን ጨለማ አድርጎ አሳያቸው፡፡ ሁኔታው ልባቸውን ቢሰብረውም ከትዳር ያፈሯቸው ሁለት ልጆች ግን ቀሪ ሀብቶቻቸው ናቸውና ዳግም ተስፋን ሰንቀው ኑሮን እንደ አዲስ ‹‹ሀ›› ብለው ጀመሩ፡፡
ምንም እንኳ መጠነኛ ገቢ የሚያስገኝላቸውና ወጥተው የሚገቡበት ሥራ ቢኖራቸውም በቂ ባለመሆኑ ብዙ የለመዱ ልጆቻቸው ሥነልቦና እንዳይጎዳ መጣርን የዘወትር ተግባራቸው አደረጉ:: ለዚህም ያግዛቸው ዘንድ ባለቤታቸው በሕይወት እያሉ ጥረው ግረው ያጠራቀሙትን ሀብት ባለቤትነት አሳወጁ፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስት ቅርንጫፎች ላይ በሟች ባለቤታቸው አቶ መሐመድ ሰዒድ አሊ ሥም ሦስት የሒሳብ ቁጥሮች እንደሚገኝም የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት አረጋግጦ ሰጣቸው፡፡
ይህን ምላሽ በመያዝ በተለይ ግማሽ ሚሊን የሚጠጋ ብር ወዳለበት ተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ ያቀናሉ፡፡ባንኩም አስፈላጊውን ማጣራት ካከናወነ በኋላ ገንዘቡን ወደራሳቸው የሒሳብ ቁጥር ያዘዋውራል:: ይሁን እንጂ ከተወሰኑ ወራት በኋላ በሥመ ሞክሼ ገንዘብ መውሰዳቸው ይገለጽላቸዋል፡፡ ጉዳዩም ወደ ፍርድ ቤት ያመራል፡፡ የዛሬው የፍረዱኝ ባለጉዳያችን ወይዘሮ ፋንታነሽ በሁኔታው የደረሰባቸውን ችግር እንዲህ ገልፀውልናል፡፡ እኛም የአቤቱታ አቅራቢዋን ቅሬታ ከባንኩ ምላሽና ከሰነድ ማስረጃዎች ጋር አዋህደን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ከአንደበታቸው
የአብራካቸው ክፋይ ልጆችን የማሳደጉ ኃላፊነት የተጣለባቸው ወይዘሮ ፋንታነሽ፤ ከባለቤታቸው እረፍት በኋላ ሚስትነታቸውንና የልጆቻቸውን አሳዳጊነት እንዳሳወጁ ያስታውሳሉ፡፡ ሟች ባለቤታቸው ገንዘብ በባንክ እንደነበራቸው ስለሚያውቁ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመሩ፡፡ ነገር ግን የባንክ ደብተሩ ስለጠፋባቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይጠይቃሉ፡፡ የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤትም ወደ ሕግ አገልግሎት ክፍል እንዲሄዱ ይመራቸዋል፡፡ ክፍሉም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ የሟችን ሥም ከፎቶግራፋቸው ጋር ካመሳከረ በኋላ በሟች ባለቤታቸው ሥም ሦስት የባንኩ ቅርንጫፎች ላይ ሒሳብ እንዳላቸው ያሳውቃቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገርጂ፣ ተክለሐይማኖት እንዲሁም አዲስ ከተማ ቅርንጫፎች ላይ በባለቤታቸው ሥም ተመዝግቦ የሚገኝ ሒሳብ እንዳለ በተነገራቸው መሠረት ከዋናው መሥሪያ ቤት ያገኙትን መረጃ ይዘው ወደ ተባሉት የባንኩ ቅርንጫፎች ማቅናታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ የሟች ባለቤታቸውን ፎቶ አሳይቷቸው በሒሳብ ቁጥሩ ተቀማጭ የነበረውን ብር እንደሰጣቸው ነው የሚናገሩት፡፡ ገርጂ ላይ ያለው ቅርንጫፍ ግን የእርሳቸው እንዳልሆነ እንደገለፀላቸውና በተቃራኒው የተክለሐይማት ቅርንጫፍ ከባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የተሰጣቸውን ማረጋገጫ መሠረት አድርጎ መረጃዎችን ሲመረምር የባለቤታቸው ገንዘብ መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ ይገኛል፡፡ መጠኑም ከ449 ሺህ ብር በላይ መሆኑን ያሳውቃቸዋል፡፡
ምንም እንኳ የሟች ባለቤታቸው ፎቶ ቢገኝም ገንዘቡን ለማዘዋወር ግን በፍርድ ቤት ወራሽነታቸውን እንዲያሳውጁ የተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ በጠየቃቸው መሠረት አሳውጀው መረጃውን መስጠታቸውን ይናገራሉ፡፡ ባንኩም አስፈላጊውን ማጥራት ካከናወነ በኋላ ገንዘቡ ይለቀቅላቸዋል:: ነገር ግን ገንዘቡ በተለቀቀ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል፡፡ ስለ ደብዳቤው ምንነት ሲጠይቁም የሠው ገንዘብ እንደወሰዱ እንደተገለጸላቸው ነው በሐዘን የሚናገሩት፡፡ እርሳቸውም የሟች ባለቤታቸውን ምስል አሳይቶና አረጋግጦ ገንዘቡን የሰጣቸው ባንክ ስለምን ይህን መሰል ክስ እንዳቀረበባቸው ብዥታን ይፈጥርባቸዋል::
እያንዳንዱ ጥፋት ወደ እርሳቸአው እንደዞረና የባለቤታቸው ሞክሼ የሆኑ 41 የባንኩ ተገልጋዮች እንዳሉ እንደተገለፀላቸው የሚያስታውሱት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ደርሶ እንደቆሙና ከፈጠራቸው አምላክ ውጪ ለእርሳቸው ጠበቃ እንዳልነበራቸው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ይናገራሉ፡፡ ከባለቤታቸው ጋር በትዳር ውስጥ በቆዩባቸው 10 ዓመታት ውስጥ በ1997 ዓ.ም በተለምዶ አጠራር ጨረቃ ቤት እንደገነቡ ይገልፃሉ:: በአሁኑ ወቅት ቤቱ በሰነድ አልባ እንደሚስተናገድና ይህንኑ ልጆቻቸውን ጓዳ ጎድጓዳቸውን ሸፍኖ የያዘላቸውን ለእርሳቸው የሙት ባለቤታቸው ማስታወሻ የልጆቻቸው ደግሞ ቅርስ የሆነ መኖሪያ ቤት ግን ባንኩ ባቀረበባቸው ክስ በፍርድ ቤት እንዲሸጥ እንደተወሰነባቸው ይገልፃሉ፡፡
ለቤቱ ሽያጭ ውሳኔ መነሻ የሆነው የሟች ባለቤታቸው ገንዘብ ነው በሚል በቅርንጫፉ ከተዘዋወረላቸው ገንዘብ 50 በመቶ የሚሆነውን እንዳጠፉት ይናገራሉ፡፡ በዚህም 220 ሺህ ብሩን በማውጣት ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዳዋሉትና የባለቤታቸው ሐቅ በመሆኑ የኔቢጤ አብልተው ዝክር አውጥተውበታል፡፡ ‹‹የሠው ሀብት አልፈልግም›› የሚሉት ወይዘሮ ፋንታነሽ፤ እርሳቸው በፋብሪካ ሥራ፤ ባለቤታቸው ደግሞ ነገን የተሻለ ለማድረግ በጋሪና በእንጨት ሽያጭ ሥራ ተሰማርተው ቀን ከሌት ያጠራቀሙት የላባቸውን ዋጋ ባንኩ በጠራራ ፀሐይ የሌላ ግለሰብ ነው ብሎ መወሰኑ ሐዘኔታን እንደፈጠረባቸውም ይናገራሉ፡፡
ባንኩ ገንዘቡን ከመስጠቱ አስቀድሞ አስፈላጊውን ማጥራት አከናውኖ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ፋንታነሽ፤ ገርጂ ቅርንጫፍ ገንዘብ እንዳላቸውም ነግሯቸው ሲያበቃ ጭራሽ በቅርንጫፉ የሚገኘውን ገንዘብ የባለቤታቸው አይደለም ብሎ መካዱ እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ፡፡ በሒሳብ ቁጥሩ የሚገኘው ገንዘብ ምንም ዓይነት ዕዳም ሆነ እገዳ እንደሌለበት መመስከሩንም ያስታውሳሉ፡፡
‹‹ባለቤቴ ገንዘብ ባይኖረውና እርግጠኛ ባልሆን እንዴት እጠይቃለሁ? እንኳንስ መንግሥት ዘንድ ግለሰብ ጋ እንኳ የሌለን ገንዘብ እንዴት ይጠየቃል?›› ሲሉም ይሞግታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ አግኝቶ እግዱ ይነሳ ቢባልም ባንኩ ግን ገንዘቡን ሊለቅላቸው አለመቻሉንም ይገልፃሉ:: ባለቤታቸው ለፍተው ያጠራቀሙት የልጆቻቸው ማሳደጊያ በመሆኑ ባንኩ እንዲለቅላቸው ይጠይቃሉ::
ሰነዶች
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕግ አገልግሎት በመዝገብ ቁጥር ሕአ/ምእአዲ/2027/2013 ታኅሣሥ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ለሟች አቶ መሐመድ ሰዒድ አሊ ሚስት ወይዘሮ ፋንታነሽ አሰፋ በሚል የሰጣቸውን ደብዳቤ ከሰነዶች መካከል ተመልክተነዋል፡፡ በደብዳቤው አመልካች ወይዘሮ ፋንታነሽ በሟች ሥም የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ አዋስ ወረዳ ፍርድ ቤት መዝገብ ቁጥር 42156 በቀን 11/3/2006 ዓ.ም የሰጠውን የሚስትነትና የሟች ወራሾች ለሆኑት የእነ ቶፊቅ መሐመድ አሳዳጊ መሆናቸውን የሰጠውን ውሳኔ በማቅረብ በቀን 14/3/2006 ዓ.ም ለሕግ ክፍሉ በጻፉት ማመልከቻ በሟች ሥም ሒሳብ መኖሩንና አለመኖሩን አጣርቶ ውጤቱን እንዲያሳውቃቸው መጠየቃቸውን ያትታል፡፡
ወይዘሮ ፋንታነሽ በጠየቁት መሠረት በማመልከቻቸው እንዲጣራላቸው ለጠቀሷቸው ቅርንጫፎች ትዕዛዝ ማስተላለፉን ደብዳቤው አስፍሯል፡፡ በዚህም በአቶ መሐመድ ሰዒድ አሊ ሥም በገርጂ ቅርንጫፍ በሒሳብ ቁጥር 1000050323769 ብር አንድ ሺህ 411 ብር ከ49 ሣንቲም፣ በተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ በሒሳብ ቁጥር1000058949276 ብር 14 ሺህ 122 ብር ከ85 ሣንቲም እንዲሁም በአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ በሒሳብ ቁጥር 1000045585925 ደግሞ ብር 815 ብር ከ66 ሣንቲም እና በሒሳብ ቁጥር 1000053183801 ብር 203 ከ05 ሣንቲም መኖሩን በመግለጽ እንዳሳወቃቸው ከደብዳቤው ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ 1000058949276 ከሆነው የሒሳብ ቁጥር ከአቶ መሐመድ ሰዒድ አሊ ወደ ወይዘሮ ፋንታነሽ አሰፋ የሂሳብ ቁጥር 1000208297116 እ.አ.አ. በቀን 05/06/2017 የተዘዋወረ ብር መጠኑ 449 ሺህ 216 ብር ከ12 ሣንቲም የሚያሳይ ሰነድ ተመልክተናል፡፡
ገንዘቡ ከወለድ ነፃ በሆነው የባንክ ሒሳባቸው ከተዘዋወረ በኋላም በተለያዩ ወቅቶች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ እንዳወጡ ከሰነድ ለመመልከት ችለናል:: በዚህም ወይዘሮ ፋንታነሽ ባንኩ ገንዘቡ ላይ እገዳ እንዲጣልበት አደረገ እንዳሉት እ.አ.አ. እስከ 30/9/17 ከሒሳቡ ላይ ወጪ እንዳደረጉና 220 ሺህ 216 ብር መቅረቱ ይታያል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ በመዝገብ ቁጥር ተሃቅ/ብብ/0228/2017ሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ለፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሰበታ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የፍትሐብሔር ጉዳይ ቡድን የላከው ደብዳቤ ሌላው ሰነድ ነው፡፡ ደብዳቤው እንደሚያመላክተው በቀን 04/8/2009 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 02116 በተፃፈ ደብዳቤ በቅርንጫፉ በሟች ሥም በሒሳብ ቁጥር 1000058949276 ምን ያህል ገንዘብ እንዳለ እንዲሁም ዕዳ ወይንም እገዳ እንዳለበት አጣርቶ እንዲገልጽ ታዟል:: ትዕዛዙን መሠረት በማድረግ ቅርንጫፉ በሟች ሥም በተጠቀሰው ሒሳብ ቁጥር 445 ሺህ 319 ብር እ.አ.አ. በ18/04/2017 የሚገኝ መሆኑንና በሒሳቡ ላይ ዕዳም ሆነ እገዳ እንደሌለበት ለፍርድ ቤቱ ማሳወቁን ተሃቅ/ብብ/0228/2017 ሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈው ደብዳቤ ያሳያል፡፡
አቶ መሐመድ ሰዒድ በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጠቃሚ ለመሆን በቅርንጫፉ በቁጠባ ሒሳብ ቁጥር 1000058949276 የብር 401 ሺህ 263 ከ87 ከባንክ ሒሳባቸው ያለ አግባብ ስለወጣ ይኸው ታውቆ ገንዘቡ ተመልሶ በአካውንታቸው እንዲመለስ መጠየቃቸው ከማመልከቻቸው ይታያል፡፡
ከቅሬታ አቅራቢዋ ካገኘነው ሰነድ መካከል የሟች ባለቤታቸው በሥም ሞክሼ የሆኑት አቶ መሐመድና የባለቤታቸው ምስል ያረፈበት ተመሳሳይ የሒሳብ ቁጥር ያረፈበት የ40/60 ቤት ልማት ፕሮግራም ላይ ለመመዝገብ የቤት ፍላጎት ማሳወቂያ ማመልከቻ ቅጽ መመልከት ችለናል፡፡
የፍርድ ሒደት
በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሰበታ ወረዳ ከተማ ፍርድ ቤት በዋለው የፍትሐብሔር ችሎት ላይ አመልካች ወይዘሮ ፋንታነሽ እንደሆኑና ተጠሪ እንደሌለ፤ በመዝገብ ቁጥር 02116 በቀን 18/9/2009 ዓ.ም ወጪ የሆነው መዝገብ ግልባጭ ያሳያል፡፡ ችሎቱ በውሳኔው መነሻ የሆነው ጉዳይ በቀን 4/8/2009 ዓ.ም አመልካች በጽሁፍ ባቀረቡት ማመልከቻ መሠረት መሆኑን ያብራራል፡፡ ባለቤታቸው አቶ መሐመድ ሰበታ ከተማ ቀበሌ 07 ኗሪ የነበሩ ሲሆን፤ በቀን 1/13/2005 ሕይወታቸው ማለፉን ያሳያል፡፡
ከሟች ባለቤታቸው ጋር የ13 እና የስድስት ዓመት ሁለት ልጆች እንዳፈሩ በመግለጽ፤ ሚስትነታቸውንና የልጆቹ አሳዳጊ መሆናቸውን በመዝገብ ቁጥር 42156 ማረጋገጣቸውን በማልከቻቸው ማስፈራቸውን መዝገብ ግልባጩ ያሳያል፡፡ በመሆኑም የውርስ አጣሪ ሪፖርት በቀን 5/5/2009 ጽፈው ባቀረቡት መሠረት እንዲረጋገጥላቸው መጠየቃቸው በሰነዱ ሰፍሯል፡፡
የውርስ አጣሪ ሟች ከቅሬታ አቅራቢዋ ጋር ካፈሯቸው ሁለት ልጆች ብቻ እንዳላቸው፣ ከማንኛውም እዳ ነፃ፣ ውርስ እንዳላስቀመጠ፣ ባለቤታቸው አመልካች ብቻ መሆናቸውን፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገርጂ ቅርንጫፍ በሒሳብ ቁጥር 1000050323769 በሟች ሥም ብር 12 ሺህ 411 ብር ከ49 ሣንቲም፣ በተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ በሒሳብ ቁጥር1000058949276 በተመሳሳይ በሟች ሥም የተመዘገበ 443 ሺህ 351 ብር ከ57 ሣንቲም እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ ከዚህ ገንዘብ ላይ ግማሹ የወይዘሮ ፋንታነሽ ግማሹ ደግሞ የወራሾች መሆኑንና ዕድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ በመሆናቸው አሳዳጊዋ ለሚያሳድጓቸው ልጆች መሆኑን መረጋገጡን በግልባጩ ላይ አስፍሯል፡፡
ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን አጣርቶ ለባንኩ ገርጂ ቅርንጫፍ ባዘዘው መሠረት በአካል ተገኝተው የሒሳብ ቁጥሩ በሟች ሥም እንደሌለ ሲያረጋግጡ በሌላ በኩል የተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ ደግሞ በሒሳብ ቁጥር 1000058949276 በሟች ሥም የተመዘገበ 445 ሺህ 319 ብር ተመዝግቦ እንደሚገኝ ብሎም ከእዳና እገዳ ነፃ መሆኑን በቀን 10/8/2009 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ማቅረቡን መዝገብ ግልባጩ ያመለክታል:: በተያያዘ ችሎቱ ከሰነድ ማስረጃዎች በተጨማሪ የሠው ምስክሮችን ያደመጠ ሲሆን፤ ወይዘሮ ፋንታነሽ የሟች ባለቤትና የሁለቱ ልጆች አሳዳጊ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ አስፍሯል፡፡
ችሎቱ መዝገቡን አጣርቶ በሰጠው ውሳኔም በገርጂ ቅርንጫፍ በሟች ሥም የተመዘገበ ገንዘብ አለመኖሩ እንዳረጋገጠ በመግለጽ፤ በሌላ በኩል በተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ ግን የብር የውርስ አጣሪ ገንዘብ ያላቸው መሆኑን እንዳረጋገጠ መዝገብ ግልባጩ ያብራራል፡፡
በመዝገብ ቁጥር 02116 በቀን 23/9/2009 ዓ.ም ወጪ የተደረገው መዝገብ ግልባጭ ደግሞ በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሰበታ ወረዳ ከተማ ፍርድ ቤት አመልካች ወይዘሮ ፋንታነሽ ሲሆኑ ተጠሪ እንደሌለ ያሳያል፡፡ መዝገቡ አመልካች በተጠቀሰው ዕለት በጻፉት ማመልከቻ የሒሳብ ቁጥር 1000058949276 እንደጠፋባቸው ገልፀው የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ ግን ባለመካተቱ፤ የጠፋ መሆኑን በገለጹት መሠረት በውሳኔው ላይ እንዲጨመር ማዘዙ በሰነዱ ይታያል፡፡ ጉዳዩ በዚህ መልኩ በየደረጃ ባሉ ፍርድ ቤቶች ሲታይ ከቆየ በኋላ ባንኩ የፍርድ ባለመብት ሲሆን፤ ወይዘሮ ፋንታነሽ ደግሞ የፍርድ ባለዕዳ ሆነዋል፡፡
ሌላው በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐብሔር ችሎት፤ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 267930 ላይ ውሳኔ ሲሰጥ የፍርድ ባለመብት ወይንም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክርክር ያስነሳው ቤት በጨረታ ተሸጦ በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ከፍርድ ባለዕዳ ላይ የሚፈለገው ገንዘብ እንዲከፈለው ያቀረበው ጥያቄ መኖሩን ጠቅሷል፡፡ ነገር ግን ቤቱ ላይ በቁርጥ የፍርድ ባለዕዳ ሳይሆን ተቃውሞ አመልካች ከላዩ ላይ መብት ያላቸው መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ባንኩ መኖሪያ ቤቱ የፍርድ ባለዕዳ የሆኑት ወይዘሮ ፋንታነሽ ንብረት ነው በማለት ቢያቀርብም ቤቱ የተቃውሞ አመልካች መሆኑን ችሎቱ በመረዳት በፍርድ ባለዕዳ ወይንም በወይዘሮ ፋንታነሽ እዳ ምክንያት መሸጥ የለበትም በማለት ባንኩ በቀን 30/09/2010 ዓ.ም በጽሑፍ ያቀረበውን ማመልከቻ ውድቅ አድርጎ ውሳኔውን እንዳሰረፈ መዝገብ ግልባጩ ያሳያል፡፡ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የፍርድ ባለመብት ወይንም ባንኩ ሌላ ሊሸጥ የሚችል የወይዘሮ ፋንታነሽ ንብረት በሚገኝበት ጊዜ መዝገቡን የማንቀሳቀስ መብት ተጠብቆለት መዝገቡ መዘጋቱን ያሳያል፡፡
ጥያቄዎች
በተመለከትናቸው ሰነዶችና ቅሬታ አቅራቢዋ በአቤቱታቸው እንደገለጹት፤ በሥመ ሞክሼ ገንዘብ ወስደዋል የተባለው የሌላኛው ግለሰብ የሂሳብ ቁጥር የሚያመለክተው የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ቁጠባ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ቅሬታ አቅራቢዋ ካላቸው የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጋር ምን አገናኘው? የጋራ መኖሪያ ቤት ቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሒሳብስ ተመሳሳይ ናቸው ወይ? የሚል ጥያቄን ይፈጥራል፡፡
በተያያዘ አቶ መሐመድ አለአግባብ ከሒሳባቸው ላይ ወጪ እንደተደረገባቸው ለባንኩ ባስገቡት ማመልከቻ የጠቀሱት ገንዘብ ልክ 401 ሺህ 263 ከ87 ሣንቲም ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተክለሐይማኖት ቅርንጫፍ ሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ በሟች አቶ መሐመድ ሥም በሒሳብ ቁጥር 1000058949276 ላይ 445 ሺህ 319 ብር ከሁለት ሣንቲም እንደሚገኝ ነውና ያረጋገጠው በስመ ሞክሼ ተዘዋውሮ ከሆነ የገንዘብ መጠኑ ስለምን ተለያየ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡
በተጨማሪም ገንዘቡ የቅሬታ አቅራቢዋ ካልሆነ እንዴት ግማሽ ሚሊዮን የሚደርስ ብር ሊያዘዋውርላቸው ቻለ? ከተዘዋወረላቸው ገንዘብ ላይ ለሰባት ጊዜያት ያክል ወጪ አድርገው ሲጠቀሙስ ስለምን ዝምታን መረጠ? ይህን ተግባር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ባከናወኑ ሠራተኞችስ ላይ ምን ዓይነት ተጠያቂነት አረፈ? ስንል ባንኩን አነጋግረናል፡፡ ሆኖም ይህን መሰል መረጃ በዋና መሥሪያ ቤት በኩል እንደሚሰጥ ስለተገለጸልን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳይሬክተር ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽንን ለማነጋገር ሞክረናል፡፡
ባንኩስ ምን ይላል?
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ “ቅሬታ አቅራቢዋ የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ የሚመለከታቸውን አካላት አሳስተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመጨረሻ እልባት ያላገኘ ጉዳይ በመሆኑ ባንኩ በቀጣይ የተሟላ ምላሽ ይሰጣል” ብለዋል፡፡
ትክክለኛ የሒሳቡ ባለቤት ናቸው የተባሉትን አቶ መሐመድ ሰዒድ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ሙከራ አድርገን ነበር። ሆኖም ግን ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ለማካተት አልተቻለም።
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2012
ፍዮሪ ተወልደ