ባለፉት 19 ወራት ለውጡ ካስገኛቸው ፍሬዎች ከሚጠቀሱት መካከል አወዛጋቢ የነበሩ ሕጎች የማሻሻል ሥራ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር፤ የበጎ አድራጎት እና የማህበራት አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅና የመሳሰሉትን አዋጆች ለማሻሻል ውይይት ሲያካሂድ መቆየቱም የሚታወስ ነው። የበጎ አድራጎትና የማህበራት አዋጅ ተሻሽሎም ወደሥራ መግባት የተቻለ ሲሆን ሌሎቹ በቀጣይ ወራት በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃሉ።
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ረቂቅ አዋጅ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየደረጃው ውይይት እየተደረገበት ይገኛል። መንግሥት አዋጁን በሥራ ላይ ባዋለበት አስር ዓመታት በተደጋጋሚ ከሚቀርቡበት ወቀሳዎች መካከል አዋጁ ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን ለማጥቃት እየተጠቀመበት ነው የሚለው ይገኛል። ይህ ክስ አዋጁን ለማሻሻል ጥረት በሚደረግበት በአሁኑ ወቅትም የሚነሳ መሆኑ አሳሳቢ ያደርገዋል። በቅርቡ ከሰኔ 15ቱ የባለሥልጣናት ግድያ ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው የታሰሩ የፓርቲ አመራሮች ይህ አዋጅ ተጠቅሶ መጠየቃቸው መንግሥት የፀረ ሽብር አዋጁን አፋኝነት በተመለከተ ከያዘው አቋም ጋር ይጋጫል በሚል ቅሬታ ሲያቀርብም ይስተዋላል።
የፀረ ሽብር አዋጁን አስመልክቶ ሰሞኑን በተካሄደ ውይይት ላይ በደህንነት መሥሪያ ቤት ብቻ በሚቀርብ መረጃ ተጠርጣሪዎችን ለብይን የሚዳርገው አሠራር ማስቀረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሂዷል።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሲሻሻል የቆየው ይኸ ሕግ በይዘትም ሆነ በአተገባበሩ ላይ በርካታ ችግሮች ሲስተዋሉበት ነበር። ይህንንም ተከትሎ 13 አባላት ያሉት የሕግ አማካሪ ጉባዔ ረቂቅ አዋጁን ሲፈትሽ ቆይቷል። በተለያዩ አካላትም ጥናትና ውይይት ሲካሄድበት ነበረ።
ሰሞኑን የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከህዝብ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል።
ረቂቁ ቀድሞ በነበረው የፀረ ሽብር አዋጅ ላይ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገውበት የተዘጋጀ ሲሆን አስፈፃሚ አካላትንም ተጠያቂ የሚያደርግ ድንጋጌ ይዟል።
ረቂቅ ሕጉን በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እየተሻሻለ የሚገኘው የፀረ ሽብር ሕግ መሰረታዊ የሕገ መንግሥት መብቶችን የሚያስከብር መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ሕጉ በሀገሪቱ ላይ ያለውን የሽብርተኝነት ሥጋት መቀነስ የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል።
ረቂቅ አዋጁ ለትርጉም ተጋላጭ እንዳይሆን መደረጉን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ እንደ ወንጀሉ ባህሪና መጠን ተመጣጣኝ ቅጣት ማስቀመጡን አንስተዋል።
በረቂቅ አዋጁ በደህንነት መስሪያ ቤት ብቻ በሚቀርብ መረጃ ተጠርጣሪዎች ለብይን የሚዳረጉበት አሠራር እንዲቀር መደረጉም ተጠቁሟል።
ረቂቅ ሕጉ የተቋማትን ኃላፊነት በግልፅ ያስቀመጠ፤ አስፈፃሚ አካላት በሽብርተኝነት የተጠረጠረ አካልን በቁጥጥር ሥር ሲያውሉና ሲመረምሩ ለሚፈፅሙት ስህተት ተጠያቂ የሚሆኑበት አንቀፅን ያካተተ ነው ተብሏል።
ሽብር ምንድነው?
አሸባሪ እና ሽብርተኝነትን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ጭምር እስከዛሬ አንድ ወጥ የሆነ ትርጓሜ እና መግባባት ላይ አለመድረሳቸውን በመስኩ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
የፀረ ሽብር አዋጁን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የሽብር ተግባር ሊባል የሚችለው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ፣ ሕዝብን ወይም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን ለማሸበር፣ ወይም መንግሥትን ለማስገደድ የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ይገልፃል። በዚህም በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፣ ለአደጋ ያጋለጠ፣ ሰውን ያገተ፣ የጠለፈ፣ በንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብት ወይም አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፣ የሕዝብ አገልግሎት እንዳይሰጥ ያስተጓጎለ ማንኛውም አካል ሕጉ በአሸባሪነት ይፈርጀዋል።
በሽብር ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ መሆኑ የተረጋገጠበትን ድርጅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹አሸባሪ›› ብሎ መሰየም እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል። ድርጅቱ በአሸባሪነት የሚሰየመው የሽብር ወንጀልን ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ከሆነ፣ የድርጀቱ አመራር ወንጀሉን ተቀብሎ ወይም አፈፃፀሙን ከመራ፣ የድርጀቱ ሠራተኛ ወንጀሉን በማያውቀው አኳኋን የሚያንቀሳቀስ ከሆነ ብቻ መሆኑን ረቂቁ ሕጉ ይገልፃል። ድርጅቱ ‹‹አሸባሪ›› ተብሎ ከተሰየመ በኋላ ስያሜው እንዲሰረዝ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቅረብና ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ሲያገኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሊነሳለት እንደሚችልና ሌሎች ዝርዝር ድንጋጌዎች በረቂቁ ተካተዋል።
የረቂቅ ሕጉ ማሻሻያ ትኩረት
‹‹የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር›› በሚል ስያሜ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ወንጀልን የመከላከል፣ የመመርመር ወይም የክርክር ሂደቱን የማስፈፀም ኃላፊነት የተሰጠው ማንኛውም ሰው፣ የተሰጠውን ኃላፊነት ሕግን በመተላለፍ በሚፈፀመው ማንኛውም ድርጊት እንደመተላለፉ ዓይነትና እንዳስከተለው የጉዳት ዓይነት በዲሲፕሊን፣ በፍትሐ ብሔርና በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ደንግጓል።
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተፈፀመውን የጥፋት ዓይነትና ድርጊቱን የፈፀሙ ተጠያቂ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለበትና ፍርድ ቤቱም በወንጀል ክርክር ሂደት የሕግ አስፈፃሚ አካላት የሕግ ጥሰት የፈፀሙ መሆኑን ካረጋገጠ፣ የሕግ ጥሰቱን የፈፀመው ሰው ወይም ተቋም ለተጎጂው አካል ከ1,000 ብር እስከ 50,000 ብር የሚደርስ የህሊና ጉዳት ካሳ እንዲከፈለው በያዘው የክርክር መዝገብ ላይ ሊወሰን እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል። ፍርድ ቤት ለተጎጂ የህሊና ካሳ መወሰኑ፣ ተጎጂው ከህሊና ውጭ ለደረሰበት ጉዳት፣ ጉዳቱን ባደረሰበት አካል ላይ የዲሲፕሊንና የወንጀል ክስ ከማቅረብ እንደማያግደው አክሏል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት፣ ከዘርፉ ምሁራንና ከተፎካካሪ የፖለቲካ አመራሮች ጋር በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተደረገ ውይይት፣ የረቂቅ ጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ ጠበቃው አቶ አመሐ መኮንን እንዳስረዱት፣ በሥራ ላይ ያለው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 በይዘቱም ሆነ በአፈፃፀሙ ብዙ ችግሮች አሉበት።
አዋጁ ትኩረት የሚያደርገው ሽብርን የሚከላከል ወይም ለመንግሥት ብቻ ጥበቃ የሚያደርግ ነው። በንፁኃን ሰዎችና በተጠርጣሪዎች ላይ ስለሚደርሰው ጉዳት ምንም የሚለው ነገር የለም ብለዋል። በመሆኑም የሚሻሻለውን አዋጅ ከስያሜው ጭምር አካታች እንዲሆን በማድረግ ‹‹የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ›› እንዲባል ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ ሕግጋትና የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔዎች አበክረው እንደሚገልፁት የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ሁለት ነገሮችን መያዝ እንዳለበት ያስረዱት አቶ አመሐ፣ የመጀመርያው የሽብር ወንጀልን በብቃት መከላከል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚያስከብር ወይም የማይጋፋ የማድረግ ጉዳይ ነው። የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ በአንዳንድ የዓለም አገሮች እንደ ሰብዓዊ መብት ማስጠበቂያ ሕግ እንደሚያገለግልም አክለዋል።
ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መረዳትና በጥንቃቄ መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ ይኼንን የሚያስገድድ በረቂቅ አዋጁ ላይ መካተቱን አስረድተዋል። አንድ ተጠርጣሪ ሰብዓዊ መብቱ በአስፈፃሚ አካል መጣሱን ለፍርድ ቤት ካመለከተ፣ ፍርድ ቤቱ ከሁሉም በፊት በማጣራት በያዘው መዝገብ ላይ ውሳኔ እንዲያሳልፍ የሚፈቅድ ድንጋጌም መካተቱን አክለዋል።
በረቂቅ ሕጉ የተካተቱ ድንጋጌዎች ተግባራዊ ሲሆኑ ችግር እንዳይፈጠር መጠበቂያ ድንጋጌ መቀመጡን የገለፁት አቶ አመሐ፣ የሽብር ወንጀል እየተጠነሰሰ ማወቁን ካልሆነ በስተቀር ጋዜጠኛ የመረጃ ምንጩን ያለ መግለፅ መብት እንዳለው በረቂቁ ተደንግጓል ብለዋል። በሰላማዊ ሰልፍ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ሆን ተብሎ በሰው ሕይወት፣ በአካልና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ ካልሆነ በስተቀር፣ በሽብርተኛነት ሊፈረጁና ሊጠየቁ እንደማይገባ በረቂቅ ሕጉ መደንገጉን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ ረቂቅ ሕጉ በስድስት ክፍሎችና በ54 አንቀጾች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በመጀመርያው ክፍል ስለጠቅላላ ድንጋጌዎች፣ በክፍል ሁለት ስለሽብርና ተያያዥ ወንጀሎች፣ በክፍል ሦስት ድርጅቶችን በአሸባሪነት ስለመሰየምና በሽብርተኝነት በተሰየመ ድርጅት ውስጥ መሳተፍ፣ በክፍል አራት ስለሽብር ወንጀል ምርመራና መከላከል፣ በክፍል አምስት ስለተቋማት ኃላፊነት፣ ትብብርና ተጠያቂነት፣ እንዲሁም በክፍል ስድስት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ማለትም ፈንድ ስለማቋቋምና ሌሎችም ድንጋጌዎች በረቂቁ ተካተዋል።
እንደ ወንጀል ድርጊቱ ጥንካሬ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የቅጣት ጣሪያ እስከ 25 ዓመት ፅኑ እሥራት የሚያስቀጣ መሆኑን ደንግጎ፣ በወንጀል ድርጊቱ የሰው ሕይወት የጠፋበት ከሆነ፣ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 539 የሚዳኝ በመሆኑ በፀረ ሽብር ሕጉ እንደማይሸፈን ተገልጿል። በሥራ ላይ በሚገኘው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 የተካተቱና በሌሎች ሕጎች መታየት የሚገባቸውን የክስና የቅጣት ዓይነቶች፣ በአዲሱ አዋጅ በመተው በነባሮቹ ሌሎች ሕጎች እንዲታዩ ማድረጉም ተገልጿል።
በረቂቅ አዋጁ ዋስትና መጠየቅ መብት መሆኑንና አፈፃፀሙ በሌሎች ሕጎች ተፈፃሚ የሚሆነው፣ በሽብር ወንጀል ተጠርጣሪም ላይ እንዲሠራ መተውን ይጠቁማል። በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ጊዜ ቀጠሮን በሚመለከት ከ28 ቀናት ያላነሰ ጊዜ እንደሚሰጥና ለአራት ጊዜ እንደሚፈቀድ የሚደነግገውን በማሻሻል፣ 14 ቀናት በመፍቀድ ለአራት ወራት መጠየቅ እንደሚቻል ደንግጓል።
ከቅጣት ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በትንሽ በትልቁ ድርጊት እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ ድንጋጌ ቢኖረውም፣ በረቂቁ ካለማስቀጣት እስከ ዕድሜ ልክ ብቻ መሆኑ ተደንግጓል።
በሚኒስትሮች ምክርቤት የረቂቅ ሕጉ መጽደቅ፣
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀረ ሽብር ሕጉ በዜጎች መብትና ነፃነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ነው በማለት እንዲሻሻል ውሳኔ የሰጠው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2001 የፀደቀው የፀረ ሽብር ሕግ የይዘትና የአፈፃፀም ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ ረቂቅ አዋጅ እንዲሻሻል ምክር ቤቱ ወስኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩ የሚዘነጋ አይደለም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ላይ እንደተመለከተው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀረ ሽብር ሕጉን በዜጎች መብትና ነፃነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ነው ብሎታል።
በይዘትም ሆነ በአፈፃፀም ክፍተቶች ያሉበት ሕግ ነው ያለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕጉ እንዲሻሻል ከውሳኔ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም፣ በተረጋጋና በነፃነት እንዲኖር ለማድረግ ነው በሚል የተቀረፀውና ፀድቆ አያሌ የፖለቲካና የመብት ተሟጋቾችን ለእስራት የዳረገው የፀረ ሽብር ሕጉ ዓለም ዓቀፍ ውግዘት ሲደርስበት ቆይቷል።
የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና የተለያዩ አገራት ሕጉ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ከመጨፍለቅ አንስቶ የኢትዮጵያ ህዝብን በአፈና ውስጥ እንዲኖር የሚያደርግ ነው በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ ቢቆዩም መንግሥት ሳይቀበለው ቀርቷል።
ምክር ቤቱ የፀረ ሽብር ሕግ መኖሩ ጠቀሜታውን በመግለፅ በፊት የነበረው ሕግ ግን የዜጎችን ነፃነት የሚጋፋ በመሆኑ ሊሻሻል ይገባዋል ብሏል።
በዚህም መሰረት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተዘጋጀውና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አገናዝቧል የተባለውን ረቂቅ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዝርዝር ተወያይቶ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል።
እንደመውጫ
በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት ወዲህ በሥራ ላይ ያለው የፀረ ሽብር አዋጅ ከይዘቱ ይልቅ አፈፃፀሙ ብዙ ውዝግቦችን ሲያስከትል ኖሯል። መንግሥት ሕጉን በተቃውሞ ጎራ የተለየ አመለካከት የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሐሳብን በነፃ የመግለፅ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በተጠቀሙ ጋዜጠኞች ወደሰዶ ማሳደድ መግባቱ ሕጉ ሆን ብሎ ሰዎችን ለማጥቃት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለመጨፍለቅ እየዋለ ነው የሚል ዓለም አቀፍ ውግዘትን ሲያስከትል ቆይቷል። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሕጎቹ በተለይ መንግሥት ተቃዋሚውን ኃይል ለማዳከም ሲከተለው የቆየው የሕጎቹ ስልታዊ አተገባበር ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ::
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር ሕጉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን ያስከተለ ነው የሚል አቋም በተደጋጋሚ በማስቀመጥ ሕጉ ተሻሽሎ ወደ ሥራ እንዲገባ ሲሠራ ቆይቷል።
በአጠቃላይ ረቂቅ ሕጉ ወንጀልን የመከላከል፣ የመመርመር ወይም የክርክር ሂደቱን የማስፈፀም ኃላፊነት የተሰጠው ማንኛውም ሰው፣ የተሰጠውን ኃላፊነት ሕግን በመተላለፍ በሚፈፀመው ማንኛውም ድርጊት እንደመተላለፉ ዓይነትና እንዳስከተለው የጉዳት ዓይነት በዲሲፕሊን፣ በፍትሐ ብሔርና በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ደንግጓል።
ረቂቅ አዋጁ ሕጉን ከለላ አድርገው በንፁሐን ዜጎችና በተጠርጣሪ ወገኖች ላይ ስልታዊ ጥቃት (የሰብዓዊ መብት ጥሰት) የሚያከናውኑ የፍትሕ አካላት በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆኑበት አንቀጾችን መያዙ እስከዛሬ አዋጁን አስመልክቶ የሚነሱ በርካታ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚረዳ ነው ተብሎ ይገመታል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በቡድን በመንቀሳቀስ የግድያ ወንጀሎችን የሚፈፅሙ፣ የሃይማኖት ተቋማትን የሚያቃጥሉ፣ የህዝብና የመንግሥት ንብረቶችን የሚያወድሙ፣ ሠላማዊ ሰዎች ከፍተኛ ሥጋት ላይ እንዲወድቁ፣ እንዲፈናቀሉ የሚሠሩ ኃይሎችን ከአድራጎታቸው ለማስታገስ የሕጉ ተሻሽሎ መውጣት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
(ማጣቀሻዎች፡- የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የጀርመን ድምጽ፣ የሪፖርተር ጋዜጣ፣ የፋና ዜናና ዘገባዎች…ናቸው)
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2012