የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግሥት ባለስልጣኖችን ሲወቅስ ሰማን፡፡ ደስ ተሰኝተን ፣ ለውጥማ አለ አልን:: ወቀሳው ለከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተጋነነ ዋጋ ተንቀሳቃሽ ስልክና ላፕቶፕ ኮምፒዩተር የሚገዙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንዳሉ የሚገልጽ ነው፡፡ ኤጀንሲው ለአንድ ባለስልጣን ተንቀሳቃሽ ስልክ እስከ መቶ ሺ ብር ግዥ መፈጸሙን ለምስኪኑ ታክስ ከፋይ ህዝብ አረዳ፡፡
እንዲህ ያለውን መርዶ በኑሮ ውጣ ውረድ ናላችን ከዞረ በኋላ በምሳ ሰዓትና በምሽት ዜና እወጃዎች ከሬዲዮና ቴሌቪዥን ድንገት ሰምተን ፍስስ እንዳንል ተጨንቆ ፣ የኤጀንሲውን ዳይሬክተር በመኮርኮር እንደ አገሪቱ የመርዶ አረዳድ ባህል በጠዋት ላረዳን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግን ምስጋና ይገባዋል።
ድርጊቱን ህገ ወጥ ሲሉ የኮነኑት የኤጀንሲው ዳይሬክተር “ውድ በሆነ ዋጋ መግዛት መፈለግ ጤነኝነት አይደለም” አሉ:: አንዳንዶችን ወትሮም የሚጠራጠሩት የአንዳንድ ባለስልጣናት የጤና ሁኔታ መንግሥታዊ በሆነ አካል ጥያቄ ውስጥ መግባቱ “ድሮም ብለን ነበር፤ ሰሚ አጣን እንጂ” አሰኝቷቸዋል፡፡ የዳይሬክተሯ ምስክርነት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በስልጣን ላይ ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የአዕምሮ ጤና ምርመራ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ሰልፍ እንዲጠሩ ሊያነሳሳቸው የሚችል ይመስለኛል::
ምናልባት ሰልፉ ተካሂዶ መንግሥት የቀጣዩን ምርጫ ለማሸነፍ ሲል ባለስልጣነቱ ሁሉ ምርመራውን እንዲያደርጉ ከፈቀደ ግን ጉድ ይፈላል፡፡ ከጤና ሚኒስትሩ በቀር አብዛኞቹ የመንግሥት ባለስልጣናት ሕንፃ ለመመረቅ ካልሆነ ወደ መንግሥት ሆስፒታል የመሄድ ልምድ ስለሌላቸው ዱባይና ታይላንድ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ሄደው በመንግሥት ወጪ በውድ ዋጋ ምርመራ ስለሚያደርጉ የአዕምሯቸው የጤና ሁኔታ አጠያያቂ ባይሆንም እንኳን ዞሮዞሮ ለምርመራው ባወጡት ውድ ዋጋ ፈተናውን መውደቃቸው አይቀርም:: ችግሩ ተቃዋሚዎችም ሰልፍ አይጠሩም ፤ መንግሥትም ባለስልጣናቱ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ አይፈቅድም፡፡ ተናጋሪ እንጂ ሰሚ ፖለቲከኛ የለማ !
ለነገሩ በዚህ ዘመን ማን ያለቀለት ጤነኛ ሆኖ ሊገኝ ይችላል ? ብልጭ ብሎበት ወደ ጤና ተቋማት አምርቶ ሙሉ የጤና ምርመራ የሚያደርግ ሰው ሁለትና ሦስት መርዶ ተነግሮት ከራሱ ጋር በቅጡ ተዋውቆ የሚመለስበት ጊዜ ላይ ነን፡፡
በሰሙት መርዶ ሙሾ ማውረድ ከመጀመራቸው “ውድ በሆነ ዋጋ ለመግዛት መፈለግ ጤነኝነት አይደለም” ያሉት የኤንጀንሲው ዳይሬክተር አመሻሽ ላይ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ “ጉዳዩ ገና በኦዲት ባለመረጋገጡ ዘገባው ተገቢ አይደለም” የሚል ማስተባበያ ሲያስነግሩ የሰሙ ዜጎች በተራቸው የዳይሬክተሯን ሁኔታ “የጤነኝነት አይደለም” ቢሉ ምን ይገርማል ?
ዳይሬክተሯ የሰጡት ማስተባበያ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በአንድ ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሑፍ ያስነበቡትን ታሪክ አስታወሰኝ፡፡ በዱሮው ማዘጋጃ ቤት ፍርድ ቤት ነበረ፡፡ አንድ ኢጣልያዊ የከባድ መኪና ሹፌር በመንግሥት መኪና የንግድ ዕቃ በመጫን ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ዳኛው መነጽራቸውን አፍንጫቸው ጫፍ ላይ አድርገው እየጻፉ እንዳቀረቀሩ “ጥፋተኛ ነህ አይደለህም?” ብለው ሲጠይቁት፣ “ኢኔ ሹፌር ኖ ፤ መኪና የራስ እንትና ኖ” ሲል ይመልሳል፡፡
ዳኛው የራስ እንትናን ስም ሲሰሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀና አሉና ዓቃቤ ሕጉን “ብለህ ብለህ ከማን ጋር ልታላትመኝ ነው?” አሉት:: ዓቃቤ ሕጉ ዳኛው ለጠየቁት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ትቶ ለሕግ በመቆርቆር “ባለቤቱ ራስ እንትና ከሆኑ እሳቸው መቅረብ አለባቸው” አለ:: እውነተኛው ዳኛም ቀበል አድርገው በዓቃቤ ሕጉ እያሾፉ “እኮ ራስ እንትና እዚህ እንዲመጡ!” አሉና ወደጣልያኑ ዞር ብለው “በል ሂድ ወዳጄ!” ብለው አሰናበቱት።
በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የቤት አበል 18 ሺ ብር እንዲሆን ሲወሰን ለተቀላጠፈ ሥራ በሚል ተመላሽ የማይሆን ተንቀሳቃሽ ስልክና የላፕቶፕ ኮምፒዩተር ግዥዎች እንዲፈጸሙላቸው ፈቅዷል፡፡ ነገር ግን መመሪያውን ተፈፃሚ ለማድረግ የቁሳቁሶች ደረጃ ፣ የገንዘብ ጣሪያና በጥቅል ተገዝተው ይከፋፈሉ ወይስ በየመስሪያ ቤቱ ይገዙ የሚሉና ተጨማሪ ዝርዝር መመሪያዎች አልተወሰኑም:: ኤጀንሲው “መመሪያውን ተፈፃሚ ለማድረግ ከደረጃዎች ኤጀንሲና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሠራሁ ነው፡፡
በቅርብም ዝርዝር መግለጫዎች ይወጣሉ፡፡ እስከዚያ ግን ምንም ዓይነት ግዥ እንዳይካሄድ” በማለት ለሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ለተጠሪ ተቋማት በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው ? የተሰጠው መመሪያ ተጥሶ ለአንድ ባለስልጣን አንድ ተንቀሳቃሽ ስልክ መቶ ሺ ብር ወጪ ተደርጎ ግዥ ተፈጽሟል:: ባለስልጣን መመሪያ ይሰጣል እንጂ አይተገብርማ !
የሆነው ሆኖ ዳይሬክተሯ ግን ቆራጥና ቆፍጣና ናቸው፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናቱን ሽቅብ እየተመለከቱ “የህዝብን ንብረት ለመዝረፍ ያለመ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ባለስልጣን ሲጠቀምበት የነበረው ላፕቶፕ ኮምፒዩተርና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ስላለው ከመመሪያ ውጪ ለመግዛት የሚያስቸኩል ነገር የለም፡፡ የሥራ ኃላፊዎች በርካታ ንብረቶችን የሚያስተዳድሩ በመሆ ናቸው ሕዝብን እንዲያገለግሉ የተሰጣቸውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል:: በዚህ ጊዜያዊ ውክልና የህዝብን ኃላፊነት በመዘንጋት የራስን ጥቅም ማካበት አመራርነትን የሚመጥን ባለመሆኑ መቅረት አለበት” በማለት እንቅጩን ነግረዋቸዋል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው ? ባለስልጣን ይናገራል እንጂ አይሰማማ !
በአንድ ወቅት አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የመንግሥት ባለስልጣናት ስለሚያባክኑት ሀብት ለአዲስ ዘመን አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡ ዶክተሩ አርባና ሃምሳ ኢንች ቴሌቪዥንና ሌሎች የቢሮ እቃዎችን በውድ ዋጋ መግዛት ፤ ለትናንሽ ስብሰባ የተጋነነ ወጪ ማውጣትና ባለስልጣናት በግል የሚገለገሉባቸውን ቁሳቁሶች ዋጋ ውድ መሆን በምሬት ገልጸው ነበር፡፡
የችግሩን ግዝፈት ለማሳየት በጃፓን የቶዮታ ኩባንያ ትልቁ መሆኑን ጠቅሰው የአስተዳደሩ ቢሮ ግን ምንጣፍ እንኳን የለውም። እዚህ አገር ግን ሹመት ሲሰጥ መኪናን ጨምሮ ለመደበኛ ሥራ የሚሟሉት ቁሳቁሶች በጣም ብክነት ያለባቸው ናቸው። በዚህ የተነሳ ኢኮኖሚው ካፒታል የሚፈጥር ሳይሆን የሚበላ ሆኗል፡፡ መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ወጪን በመቀነስ ቁጠባውን ማሳደግ መቻል አለበት ብለው ነበር:: ምን ዋጋ አለው መንግሥት ይናገራል እንጂ አይሰማማ !
አንዳንድ ባለስልጣናት ያገኙትን የትኛ ውንም ዓይነት አጋጣሚ ተጠቅመው የአገርን ሀብትና ንብረትን ለመዝረፍ ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡ በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች በሚራቡበት ፣ በርካቶች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙበት ፤ በተለይ በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የሥራ አጥነት በነገሠበት ፤ የመንግሥት ሠራተኛው ደሞዝና ወጪ ለየቅል በሆኑበትና የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ዜጎችና መንግሥትን እንደ መደመርና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሆድና ጀርባ ባደረገበት ዘመን እንዲህ ያለ መራር ቀልድ መሰማቱ አንጀት ይቆርጣል፡፡
ባለስልጣናቱ እንዲህ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚራወጡት ግን ምን ነክቷቸው ነው ? መጦሪያ ፈልገው ይሆን ? ከኃላፊነታቸው የሚነሱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የሚያገኟቸውን መብቶችና ጥቅማጥቅሞች ለመወሰን በ2009 ዓ.ም የመንግሥት ባላስልጣናት ፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን የወጣ አዋጅ ባለስልጣናት ከኃላፊነት ሲነሱ በሥራ ላይ እያሉ የሚሰጣቸው ደመወዝና አበል እንደማይቋረጥ፤ በመንግሥት ወጪ እስከ አምስት መኝታ ክፍል ያለው መኖሪያ ቤት እንደሚሰጣቸው ፤ የተሽከርካሪና የቢሮ አገልግሎት እንደሚያገኙ ፤ የግል ደህንነት ጥበቃ እንደሚሰጣቸው ፤ ሲታመሙ በአገር ውስጥ ወይም በወጭ አገር ሕክምና እንደሚያገኙ ይደነግጋል።
እንደኔ ነጂ ምክንያቱ ከልክ ያለፈ የነዋይ ፍቅር የወለደው ፈላጭ ቆራጭ የመሆን ፍላጎታቸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ባለ 8 ሲሊንደር ቪ8 ተሽከርካሪዎችን ከተማ ውስጥ እንዳይገለገሉ ተከልክለው በምትኩ የሚያሽከረክሩት አነስተኛ ጉልበት ያለው መኪና ተገዝቶላቸው ነበር። ነገር ግን ክልከላው ወጤት አላመጣም፡፡ እንዴ ምን ነካን ? ባለስልጣን ይከለክላል እንጂ አይከለከልማ !
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2012
የትናየት ፈሩ