ለልብ ጤንነት ከልባቸው የሠሩት የሀገር ባለውለታ

የአንዳንድ ሰዎች የምድር ቆይታ ፍሬያማ ነው። ሙሉ ሕይወታቸው ያማረ ፍሬ የሚያፈራበት ነው። በሥራዎቻቸው በሞት የማይረታ ብርቱ ታሪክ ይከትባሉ። ለምድርም ለሰማዩም ክቡድ ይሆናል። መልካም ሥራቸው የስማቸው መታወሻ ሆኖ ሲታወሱበትና ሲዘከሩበት ይኖራሉ። ከግል ሕይወታቸው አልፈው ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅም ሥራ የሠሩ ሰዎች ደግሞ ከዚህም የላቀ የሕይወት ታሪክና ትርጉም ይኖራቸዋል።

ኢትዮጵያ እድሜያቸውን ሙሉ ለሙያቸው፣ ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው ታምነው በጎ ሠርተው በበጎነት ያለፉ ስመ ጥርና ስመጥሩ ሰዎችን ዐይታለች። በልብ ሕክምና ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያዊ የነበሩት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከእነዚህ መልካም ሰዎች መካከል የሚመደቡ አንጋፋ ሃኪምና በጎ አድራጊ ሰው ነበሩ፡፡

ዶክተር ፍቅሩ የተወለዱት በ1943 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዝነኛው ኮከበ ፅባህ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ትምህርት ቤት ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አሰላ በሚገኘው ራስ ዳርጌ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ሀገር ወዳድ በሆነ ቤተሰብና ማኅበረሰብ ውስጥ ያደጉ በመሆናቸው ይህ የሀገር ፍቅር ስሜት የጠራቸው ገና በማለዳው ነበር።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምልመላ ሲያከናውን የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ተቀላቀሉ። በወቅቱ አየር ኃይልን ለመቀላቀል ከተመለመሉት 27 እጩ አባላት መካከል በብቃት የአየር ኃይል ስልጠናን አጠናቀው በጀት አብራሪነት የተመረቁት እሳቸውና ሌሎች አራት ሰልጣኞች ብቻ ነበሩ። ብቸኛው ጀት ስኳዶር ሆነው የወጡት በእድሜ ትንሹም ዶክተር ፍቅሩ ሆኑ።

በለበሱት ልብስ ውስጥ ጭምር አየር ኃይሉን ለማስከበር ይጥሩ ነበር። ሕዝቡም በዛው ልክ ክብር ይሰጣቸው ነበር። አየር ኃይሉ እንደታሪክ የሚታይ አስደናቂ የሀገር ሀብት እንደሆነና የአየር ኃይሉ ዲሲፕሊን አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ነገሮችን ከማድረግ ይታደጋቸው እንደነበር በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል። አየር ኃይልን እስከመቶ አለቃነት የደረሰ ማዕረግንም ተቀዳጅተውበታል።

የስልሳ ስድስቱ አብዮት መፈንዳት ለዶክተር ፍቅሩ ጥሩ ነገር ይዞ አልመጣም። ለሕዝቦች እኩልነትና አንድነት መስፈን ይታገሉ ነበር። ይህም በደርግ ጥርስ እንዲነከስባቸው ምክንያት ሆነ። የአብዮቱን መፈንዳት ተከትሎ ደርግ ለስልጣኔ ስጋት ይሆናሉ ካላቸው መካከል ሆነው ተገኙ። ሌሎች ግለሰቦችን እያፈሰ ወደ እስር ቤት ማጋዝ ሲጀምር እሳቸውም ከተሳዳጆች መካከል ነበሩ።

ዶክተር ፍቅሩም በደርግ የመሳደዳቸው ነገር ሀገር አስጥሎ አስወጣቸው። ከሚወዷት ሀገራቸው ሳይወዱ ተለዩ። ወደ ሱዳን ተሰደዱ። ቀጣይ መዳረሻቸው እንግዳ ተቀባይ የሆነችላቸው ሁለተኛ ሀገራቸው ስዊድን ሆነች። የእሳቸው መሰደድ የእርሳቸውን እስትንፋስ ቢያስቀጥልም ለወንድሞቻቸው መልካም አልሆነም። እሳቸውን መያዝ ያልቻለው ደርግም የሁለት ወንድሞቻቸውን ሕይወት ነጠቀ።

በስደት ሀገር ሀዘን ቢበረታባቸውም እጅ ሰጥተው አልተቀመጡም። በስዊድን የሚያሳልፉትን የስደት ዘመናቸውን ፍሬያማ ለማድረግ ታጥቀው ተነሱ። ጄት አብራሪው ሀገር ወዳድ ሰው የሕክምና ትምህርት ተማሩ። በሕክምና ዘርፉም በልብ ሕክምና አንቱታን ያተረፉ ስመጥርና ስመጥሩ ባለሙያ ሆኑ። ከስዊድን አልፈው ምስጉን ሃኪም ሆኑ።

እንደ መልካም ዛፍ ቅርንጫፎቻቸውን አስፍተው የለመለመና መልካም ፍሬ ለማፍራት የታደሉት ዶክተር ፍቅሩ፣ ከሙያዊ ተግባራቸው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ሀገራቸው የሰላም፣ የዲሞክራሲና የልማት ብርሃን እንድታይ ዘርፈ ብዙ ጥረት ከማድረግ አልቦዘኑም። በአውሮፓ በነበረው የኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ተሳትፈዋል።

ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከአንድ ትውልድ ገደማ የስደት ሕይወት በኋላ ወደ ሀገራቸው ሲመጡ ለሀገራቸው ጥሪ ምላሽ ይዘው ነበር። ወቅቱ የ1990ዎቹ መጀመሪያ ነበር። የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭት እንደ ሀገር ስጋት የደቀነበት፣ ብዙዎች ያለ ወላጅና ጧሪ ቀባሪ የቀሩበት ጊዜ ነበር። የቫይረሱን ፈጣን ስርጭት ተከትሎ ሀገራዊ ጥሪ ተደርጎም ነበር።

ዶክተር ፍቅሩ ይህን ጥሪ ሰምተው እንዳልሰሙ ማለፍ አልፈለጉም። ምላሻቸውም ተገፍተው ለወጡበት ሀገር ‹‹አይመለከተኝም›› የሚል አልነበረም። ‹‹በሀገርና በሕዝብ ቂም የለም›› የሚል ፅኑ እምነት ባለቤቱ ዶክተር ፍቅሩ ለሀገራቸው ጥሪ ከብርሀን የፈጠነ ምላሻቸውን ሰጡ። ለችግሩ የመፍትሔ ባለቤት ያደረጉት ደግሞ ራሳቸውን ብቻ አይደለም። በስዊድን ያሉ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ወደ ሀገር ቤት ቀድመው ዘለቁ።

ሀገራቸው ገብተውም ሙያዊ ድጋፍ አደረጉ። ጠንካራውና ሀገር ወዳድ ሰው በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሌላ የቤት ሥራ የሚሆን ነገር ተመለከቱ። በበወቅቱ በስፋት ያስተዋሉት ችግር የልብ ሕመም ነበር። ሕክምናውን በማጣት ምክንያት የሚሞቱ ሕፃናትና ወጣቶች ቁጥር አሸቅቦ ነበር። ይሄ ጉዳይ ለዶክተር ፍቅሩ ችላ የሚባል ሆኖ አልተገኘም። ድጋሚ ሌላ ሀሳብና ሌላ ምላሻቸውን የሚሻ ጥያቄ ሆነ እንጂ፡፡

የችግሩን አሳሳቢነት የሚያሳይ አስፈላጊውን ጥናት አደረጉ። ወደ ስዊድን ሀገር ተመልሰው የሀገሪቱን መንግሥትና የስዊድን ፈንድ የመሳሰሉ አጋዥ ተቋማትን ደጅ ጠኑ። ተቋማቱን በማስተባበርም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መጡ። ይህ ጥረታቸውም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነውን የልብ ሕክምና ሆስፒታልን ወለደ።

ሰኔ ዘጠኝ ቀን 1999 ዓ.ም ‹‹አዲስ የልብ ሕክምና ማዕከል›› ተመሠረተ። ሆስፒታል ማቋቋም ብቻውን በዘርፉ ያለውን ችግር መቅረፍ አለመቻሉን ተገንዝበዋል። ለመፍትሄም ራሳቸውን አዘጋጁ። በመሆኑም በራሳቸው ወጪ ሀኪሞችን ማስተማር ጀመሩ። ይህ ተግባር ባለሙያዎቹን ስዊድን ድረስ በመላክ የታገዘ ነበር። በዚህም በልብ ሕክምናው ስፔሻላይዝድ ያደረጉ እውቅ ሀኪሞችን ማፍራት ቻሉ።

ለሕክምናው ረብጣ ዶላሮች ሊኖር ይገባ ነበር። የዶክተር ፍቅሩ ያልተቋረጠ ልፋት ግን ትርጉም ኖረውና በሰለጠነው ዓለም ብቻ ይሰጥ የነበረውንና ውስብስብ የሆነውን የልብ ሕክምና ወደ ኢትዮጵያ አመጡት። ብዙ ሰው እፎይታ አገኘ። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጪ ይደረግ የነበረው ጉዞና እንግልት ቀረ። ሀገሪቱ ልታወጣ የምትችለውን የውጭ ምንዛሪም ማዳን ተቻለ። ይህ ተግባራቸውም በልብ ሕክምና ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች ዘርፉን ተቀላቅለው ወገናቸውን እንዲያገለግሉ ማድረግ ያስቻለ ወርቃማ አበርክቶ ሆኖ በደማቁ ተጽፏል።

ይህ የሕክምና አገልግሎት የልብ ቀዶ ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እፎይታን የፈጠረ ቢሆንም፣ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ፣ በልብ ቀዶ ሕክምና የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞችን ማፍራት እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነበር። ከስዊድን በመምጣት የልብ ቀዶ ሕክምና ያከናውኑ የነበሩ ባለሙያዎች ከልብ ቀዶ ሕክምናው ባሻገር ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በዘርፉ ብቁ እንዲሆኑ የእውቀትና ልምድ ሽግግር ተግባር አከናውነዋል። የዚህ ተግባር ዋና ቁልፍ ሰው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ነበሩ።

ዶክተር ፍቅሩ ጥረታቸውን ቀጠሉ። በአዲስ የልብ ሕክምና ማዕከል ውስጥ የማይሰጡ የልብ ሕክምናዎች የሚገኙበትን ‹‹ታዝማ የውስጥ ደዌ እና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል›› (TAZMA Medical and Surgical Spe­cialized Center)ን አቋቋሙ። በ‹‹ታዝማ›› መመስረት በርካታ ሕፃናትና ወጣቶችን በልብ ሕክምና እጦት ምክንያት ከሚነጥቀው ሞት መታደግ ተቻለ። ማዕከሉን መመስረት ብቻ ሳይሆን ዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ የሀገርን የሕዝብ መመኪያ እንዲሆን በማድረግ ረገድም የነበራቸው ሚና አይተኬ ነው።

የዶክተር ፍቅሩ ጥረት እጅግ ውስብስብ የሆኑና በኢትዮጵያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ይደረጋሉ ተብለው የማይገመቱ የሕክምና ዓይነቶች በሀገር ውስጥ እንዲከናወኑ በማድረግ ዜጎች ተስፋ እንዲኖራቸው፣ ሀገርም እንድትኮራ አድርጓል። ማዕከሉ የልብ ቀዶ ሕክምና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ብቻ እንዲከናወን ያደረገ የመጀመሪያው ተቋም ነው። እነዚህ ሕክምናዎች ኢትዮጵያን በዘርፉ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ፈር ቀዳጅ እንድትሆን በማስቻል ሀገር አኩርተዋል፤ሕይወት ታድገዋል። ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከጅቡቲ የመጡ ዜጎችም ወደ ማዕከሉ በመምጣት እነዚህን የሕክምና አገልግሎቶች አግኝተዋል። በዚህ ሁሉ ስኬት ውስጥ የዶክተር ፍቅሩ ጥረትና አበርክቶ የማይተካና በዋጋ የማይተመን ነበር።

ድካምና ጥረታቸው ለራሳቸው ማዕከል ብቻ የተደረገ አልነበረም። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚሠጠውን የልብ ሕክምና ለማዘመን ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። በተለያዩ ጊዜያት በውድ ዋጋ የሚገዙ የሕክምና መሳሪያዎችን ለተቋሙ ድጋፍ አድርገዋል። በጦርነቱ ወቅት የተጎዱ ትምህርት ቤቶችንና ተቋማትን ለማገዝ በሚደረግ ርብርብ ውስጥ ሰፊ አበርክቶ የነበራቸውም ታላቅ ሰው ነበሩ። በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይም ደማቅ አሻራ አላቸው። የግል የጤና ተቋማትን አስተባብረው ለግድቡ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሰበሰብ አድርገዋል።

ዶክተር ፍቅሩ ለሀገራቸው በበደል የማይሻር እና እንክብካቤ በማጣት የማይገፋ ፅኑ ፍቅር አላቸው። ባለፉት ስርዓቶች በተለያየ ወቅት ለእስር ተዳርገዋል። ታድያ የ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ ከእስር ቤት ሲወጡ ዜግነት ወዳላቸው ስዊድን ሀገር ለሕክምና ይጓዛሉ። በዚያን ወቅት ተመልሰው አይመጡም ተብሎ ብዙ ሲወራ እርሳቸው ግን በጥቂት ሳምንታት ነበር ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የገቡት። ‹‹ይህ ሁሉ በደል ደርሶብዎ እንዴት ወደ ሀገርዎ ሊመለሱ ቻሉ?›› ተብለው ሲጠየቁ፣ ምላሻቸው አጭርና ግልፅ ነበር፤ ‹‹በሀገርና በሕዝብ ቂም የለም!›› ነበር። ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንደተለመደው ወገናቸውን በታማኝነትና በትጋት አገልግለዋል።

ላለፉት 19 ዓመታት በኪራይ ቤት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን ማዕከላቸውንም አልዘነጉም። ለመኖሪያነት በገዙት መሬት ላይ ደረጃውን የጠበቀ ባለ ስምንት ወለል ሕንፃ በመገንባት በቅርቡ ሆስፒታሉን ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር ሂደት ላይ ነበሩ።

ለሙያቸውና ለሀገራቸው ታምነው የኖሩት ዶክተር ፍቅሩ ያለእረፍት ሀገራቸውንና ወገናቸውን ሲያገለግሉ በመቆየታቸው ለራሳቸው ምቾት የሚጨነቁ አልነበሩም። አንጋፋው ሃኪም ካጋጠማቸው የጤና እክል ለመፈወስ ሕክምናቸውን በስዊድን ሲከታተሉ ቆይተው በ74 ዓመታቸው፣ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ዶክተር ፍቅሩ በሙያቸው ካተረፉት መልካም ስም ባሻገር መልካም ቤተሰብንም ማፍራት የቻሉ ሰው ነበሩ። የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፤ አራት የልጅ ልጆችንም ዐይተዋል። ጄት አብራሪውና የልብ ሃኪሙ ዶክተር ፍቅሩ የሰብዓዊነት አምባሳደርም ነበሩ። ሙያቸውን ብቻ ሳይሆን ገንዘባቸውንም ለወገናቸው ለመስጠት የማይሳሱ ለጋስ ሰው ነበሩ። በእርሳቸው እርዳታ የብዙዎች እንባ ታብሷል። በጎ አድራጊነታቸው የብዙ ሰዎችን ሕይወት ወደ መልካም ጎዳናና ተስፋ መርቷል።

ዶክተር ፍቅሩ ለሙያዊ አበርክቷቸውና ለበጎ ሥራዎቻቸው የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከእነዚህም መካከል ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሰጣቸው የእውቅናና ምስጋና የምስክር ወረቀት በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ነው። ዐቢይ (ዶ/ር) በ2014 ዓ.ም ‹‹ሕክምና ትጉህነትን፣ ርኅራኄንና ስነ-ምግባርን ብሎም ከራስ ይልቅ ሌሎችን ማስቀደምን የሚሻ ሞያ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ሀብቷን አፍስሳ የምታፈራቸው የሕክምና ባለሞያዎች በቅንነት ሲያገለግሏት ማየት ተስፋን ይሰጣል። እርስዎም የሕክምና ተግባርዎን ሲከውኑ ዕውቀትዎን ሳይቆጥቡ፣ ያለመታከት ላበረከቱት አስተዋፅዖ እና ስለሰጡት ትኅትና የተመላበት አገልግሎት ከልብ የሆነ ምስጋናዬ ይድረስዎ!›› በማለት ለዶክተር ፍቅሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዶክተር ፍቅሩ በግል ባህሪያቸው ጨዋታ አዋቂ እንደነበሩም የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክሩላቸዋል። ሁሉም ሰው ቀለል ያለ ስሜት እንዲሰማው ማድረግ የሚችሉና ከሁሉ ተግባቢ ነበሩ። ሳቅ ጫወታን ወዳጅ ለተቸገሩ ደራሽ መልካም ሰው ናቸው ካርዲኦሎጂስቱ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ። ለሁሉም ሰው እንደየባህሪውና እድሜው የሚሆን የተግባቦት ጥበብ ነበራቸው። ከወጣቱ ጋር እንደ ወጣት፣ ከአዛውንቱ ጋር እንደ አዛውንት፣ ከሕፃናት ጋርም እንደ ሕፃን ሆኖ የመግባባት ችሎታቸው እጅግ አስደናቂ ነው።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You