ባለፈው ቅዳሜና ዕሁድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች በሁለቱም ፆታ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በሽንፈት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ቅዳሜ ዕለት ለ2021 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድባቸውን የመጀመሪያ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ አድርገው በማዳጋስካር አንድ ለምንም መሸነፋቸው ይታወሳል። የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ ደግሞ በመካከለኛውና ምሥራቅ አፍሪካ(ሴካፋ) ዋንጫ ዕሁድ ዕለት የምድባቸውን የመጀመሪያ ጨዋታ አድርገው በኬንያ ሁለት ለዜሮ ተረተዋል። ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ዛሬ ከሽንፈታቸው ማግስት ወሳኝ ፍልሚያ የሚጠብቃቸው ይሆናል።
በኬኒያ አቻቸው በሁለት ደቂቃ ውስጥ ሁለት ግብ አስተናግደው የተሸነፉት ሉሲዎቹ ከምድባቸው ለማለፍ ዛሬ ከዩጋንዳ ጋር የሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል። አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በዛሬው ጨዋታ መጠነኛ የተጫዋች ለውጥ እንደሚኖር ጠቅሰው፤ የሚችሉትን ሁሉ ሜዳላይ ለማድረግ ተጫዋቾቹ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ‹‹ተጫዋቾቹ ምንም የሚፈረድባቸው ነገር የለም፣ በርካታ ወራት አርፈው ነው የመጡት፣ ክለቦቻችን ዕረፍት ላይ ስለነበሩ የዝግጅት ጊዜ አልነበራቸውም፣ የኔ እና የተጫዋቾቼ ህልማችን በ2020 ብሔራዊ ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ ነው፣ ይህ ውድድር ደግሞ እንደ ዝግጅት ይጠቅመናል፣ ብናሸንፍም ጮቤ አንረግጥም ምክንያቱም አልሠራንም፣ ነገር ግን ያለንን ጊዜ በመጠቀም ህልማችንን እናሳካለን፣ ይህን ማድረግ ካልቻልን መጠየቅ ያለብኝ እኔ እንጂ ተጫዋቾቼ አይደሉም፣ ዝግጅት ሳይሠሩ ውጤት መጠበቅ እንጀራ ሳያዘጋጁ ወጥ አቅርቦ ምሳ እንብላ እንደማለት ነው፣ ስለዚህ ከዚህ ውድድር ብዙ እንማራለን ለአፍሪካ ዋንጫው ሠርተን ለማለፍ እንጥራለን›› በማለት ለሽንፈቱ ኃላፊነቱን እንደወሰዱ በስፍራው ለሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
በታንዛኒያ አዘጋጅነት የሚካሄደው የሴቶች ሴካፋ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ዩጋንዳና ጅቡቲ ጋር መደልደሏ ይታወቃል። ሉሲዎቹ የመጀመሪያውን ጨዋታ መሸነፋቸውን ተከትሎ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ያላቸውን ተስፋ የሚያለመልሙት ዛሬ ከዩጋንዳ ጋር በሚኖራቸው ወሳኝ ፍልሚያ ይሆናል። ይህን ጨዋታ በሽንፈት ደምድመው በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ጅቡቲን ቢያሸንፉ እንኳን ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋ አይኖራቸውም። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ቢሆንም በአቻ ውጤት መለያየት ከቻሉ የሌሎቹን ውጤት ጠብቀው ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ተስፋቸውን ሊያለመልሙ ይገደዳሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2021 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን የመጀመሪያ ጨዋታ ከማዳጋስካር ጋር ከሜዳው ውጪ አድርጎ በ 1 ለ 0 ውጤት መሸነፉ ይታወቃል።
ዋልያዎቹ በጨዋታው የታዩባቸውን በተለይም ኳስን ከመረብ የሚያገናኝ ጨራሽ አጥቂ ክፍተቶች ለመሸፈን አልጣኝ አብርሃም መብራቱ በውጭ ያሉ ተውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በቀጣይ ጨዋታዎች ለማካተት እንዳሰቡ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። አሰልጣኙ ‹‹በዛሬው ጨዋታ ቡድናችን ከሜዳ ውጪ ከዕረፍት በፊት በመከላከል ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ አድርጓል፣ ኳስን በመቆጣጠር ከዕረፍት መልስ በማጥቃት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴም አድርጓል›› ብለዋል።
የማዳጋስካር ቡድን ከወራት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ እነ ናይጄራያንና ኮንጎን አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜ የደረሰ መሆኑን ያስታወሱት አሰልጣኙ ቡድናቸው 1ለ0 መሸነፉ መጥፎ የሚባል ውጤት እንዳልሆነ አብራርተዋል። በዋልያዎቹ ስብስብ አብዛኞቹ ተጫዋቾች አዲስ መሆናቸውን የጠቆሙት አሰልጣኝ አብረሃም በቀጣዩ ጨዋታ ክፍተቶችን እንደሚያርሙ ተናግረዋል። ‹‹የቡድኑን የአጥቂ ችግር ለመቅረፍ ከአገር ውስጥም ወይም ከውጭ ያሉትን በቀጣይ ጨዋታ እናካትታለን›› ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዋልያዎቹ ከማዳጋስካሩ ጨዋታ ሽንፈት በኋላ ጊዜ ሳያጠፉ ወደ ባህርዳር ያቀኑ ሲሆን ዛሬ ጠንካራዋን ኮትዲቯር የሚገጥሙ ይሆናል። ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ ከኮትዲቯር፣ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር መደልደሏ ይታወቃል። ኮትዲቯር ቅዳሜ ዕለት ከሜዳዋ ውጪ ኒጀርን ገጥማ አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት ማሸነፏ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ህዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም
ቦጋለ አበበ