አዲስ ዘመን፡- የኢህአዴግ አጋር ድርጅት አባል ሳይሆኑ፣ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ወደ የአመራርነት ስልጣን እንዴት ሊመጡ ቻሉ?
አቶ ኦኬሎ፡- አዎ! የኢህአዴግ አጋር ድርጅት አባል አልነበርኩም፡፡ በወቅቱ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (ጋህዴኮ) የሚባለው የተፎካካሪ ፓርቲ አባል ነበርኩ፡፡ በዚሁ ፓርቲ ውስጥ ሆኜም ነው ፕሬዚዳንት የሆንኩት፡፡ ኢህአዴግ የራሱ የሚለውን ሰው እስኪያገኝ ድረስ ነበር እኔ ክልሉን እንድመራ ያደረገኝ እንጂ ደስተኛ ሆኖ አይደለም፡፡
በወቅቱ ሆን ተብሎ ብሄር ከብሄር እንዲጋጭ የሚደረግበት ጊዜ ነበር፡፡ እኔም ወንድማማች ህዝብ ማለቅ የለበትም በሚል የህወሓት ካድሬ ሲያጋጨው የነበረውን ህዝብ ለመታደግ ስል በባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ የእርቅ ስነ ስርዓት በማካሄድ ግጭቱ እንዲቆም ከፍተኛ ኃላፊነት ስወጣ ቆይቻለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእርስዎ ፕሬዚዳንት መሆን ኢህአዴግን ለምንድን ነው ደስተኛ ያላደረገው? በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉ አይደሉም እንዴ ክልሉን እንዲመሩ የሚደረገው?
አቶ ኦኬሎ፡- እኔ ምንም እንኳ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረኝም ፣ለውጥና ችግር የመጣባቸው ግን እኔ ወደ ፕሬዚዳንትነት ከመጣሁ በኋላ ነበር። እኔ ፕሬዚዳንት በሆንኩበት ጊዜ በአማካሪ ስም የተቀመጡትን የህወሓትን ካድሬዎች በሙሉ አስወግጄ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን እና ተወላጆች ቦታ እንዲይዙ አድረግሁ፡፡ ይህን በማድረጌና ሌላ መዋቅር በማበጀቴ ችግር ደርሶብኛል፡፡ መዋቅሩ ካድሬዎቹን በማንሳፈፉ በህወሓት ዘንድ ንዴት አስከተለ፤ ችግሩ እስከ ግድያ ድረስ የዘለቀ ነበር፡፡
እስከአሁን ድረስ የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት ሁሉ በህዝብ ፍላጎት ተመርጠው የመጡ አይደሉም፡፡ እኔ ወደ ፕሬዚዳንትነት ከመምጣቴ በፊትና በተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ በቆየሁበት ወቅት በህዝብ ተመርጬ ነበር፡፡ ይሁንና ካድሬዎቹ አንድን አካል የጋምቤላ ህዝብ ስለፈለገው አይደለም ስልጣን ላይ እንዲቀመጥ የሚያደርጉት፡፡ እንደ ህዝቡ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ በመጀመሪያ አካባቢ በተመረጥኩበት በ1993 ዓ.ም ላይ ፕሬዚዳንት በሆንኩ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ህወሓት ሰው ሲያጣ በ1995 ዓ.ም የክልሉ ፕሬዚዳንት ያደረገኝ ሲሆን፣ በወቅቱም አካሄዴ ስላላማራቸው የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ አደረጉ፡፡
ግንባሩ ቀደም ሲል ብሄርን ከብሄር ያጋጭ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በወንድምና በወንድም ብሄረሰብ መካከል የተፈጠረ ግጭት እንዲበርድና ሌላ ግጭትም እንዳይፈጠር ቀደም ሲል እንደገለፅኩልሽ ክልሉ ባለው ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ ተጠቅሜ እንዲፈታ ማድረግ በመቻሌ ህወሓት ሁሉም ነገር ተዘጋበት፡፡ ይህ በመሆኑም ህወሓት እቅድ በማውጣት የሰው ህይወት ወደማጥፋት አኩይ ተግባር ተሰማራ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ ዝም ብዬ ማለፍ አልፈለኩምና መልሼ ያዝኳቸው፡፡
መጀመሪያ ላይ እኔ የክልሉ ፕሬዚዳንት ከመሆኔ አስቀድሞ አኙዋኩን ከኑዌር፣ መዠንገሩን ከአኙዋክ ጋር ሲያጋጩ ነበር፡፡ ወደ አመራር ከመጣሁ በኋላ ግን እነዚህን ክፍተቶች ከሌሎቹ ጋር በመሆን ጉቶም በሚባል ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ ደፈንኳቸው፡፡ ህወሓት ራሱ እቅድ በማውጣት አኝዋክ እንዲጨፈጨፍ አደረገ፡፡ ይህም ከታህሳስ 3 ቀን 1996 ዓ.ም እስከ ግንቦት 1996 ዓ.ም ድረስ ዘልቋል፡፡
በወቅቱም መንግሥት ይህ ሁኔታ እንዲጣራ ለማድረግ አጣሪ ኮሚሽን አቋቁሞ ምርመራ አካሂዷል፡፡ የምርመራ ውጤቱም አቶ መለስ ዜናዊ ባሉበት ለፓርላማ ቀርቦ እርሳቸውም አምነዋል፡፡ የሟቾቹ ቁጥር 61 መሆኑን ኢህአዴግ/ህወሓት አስታውቋል፡፡ እኔ በወቅቱ ሊገድሉኝ ስለሚፈልጉ ከሀገር ወጥቼ ነበር፤ጉዳዩን እከታተል ነበርና ግንባሩ የጠቀሰው ቁጥር ስህተት መሆኑን አስታውቄያለሁ፡፡የተገደሉት አኙዋኮች ከ400 በላይ መሆኑን ገልጫለሁ፡፡ ከዚህ መረጃ በኋላ ሂዩማን ራይትስ ዎች አጣርቶ ገዳዮቹ እነማን እንደሆኑም ገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሟቾች ቁጥር የዚያን ያህል ስለመሆኑ እንዴት እርግጠኛ ሆኑ? ገዳዩስ ኢህአዴግ/ህወሓት ስለመሆኑ እንዴት ሊያውቁ ቻሉ?
አቶ ኦኬሎ፡- ይህ እኮ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ከሂዩማን ራይትስ ዎች በተጨማሪም የዘር ጭፍጨፋውን አስመልክቶ ከስድስት ዓመት በኋላ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ሪፖርቱም አኙዋኮች ከመገደላቸው በፊት ኢህአዴግ እቅድ እንደነበረው የሚገልፅ ነው፡፡ እቅዱ ደግሞ የተቀነባረው በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አማካይነት ሲሆን፣ ወቅቱም እኤአ መስከረም 24 ቀን 2003 ነው፡፡ በእቅዱ ወስጥ የሚገደሉ አኙዋኮች ስም ዝርዝርም ወጥቶ ነበር፡፡
እኤአ ከታህሳስ ወር 2003 እስከ ግንቦት 2004 ድረስ ሁለት ሺህ 500 ወንድ አኙዋኮች ተገድለዋል፤ 164 ሴቶች ደግሞ ተደፍረዋል፤ ንብረትም ተዘርፏል፡፡ በማሳ ላይ ያለ ሰብል ተመንጥሯል፡፡ ከሁለት ሺህ በላይ ቤቶችም ተቃጥለዋል፡፡ ይህ ሁሉ በደል በአኙዋክ ላይ በመደራረቡ ምክንያት ከ20 ሺ በላይ አኙዋኮች አገር ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ እነዚህም ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን፣ በዑጋንዳ፣ በኬንያ፣ አሜሪካ፣ አውስትሪሊያ፣ ካናዳ እንዲሁም በተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ አገራት ያሉ የአኙዋክ ስደተኞች ኑሮ በስደተኞች ካምፕም ጭምር ስለመሆኑ ምን ያህል ስቃይ እያሳለፉ ስለመሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አኙዋኮችን መግደል ውስጥ መግባት ለምን አስፈለገ ?
አቶ ኦኬሎ፡- የሚገርመው እሱ ብቻ ሳይሆን፤ አኙዋኮቹ እንዲገደሉ የስም ዝርዝር በማውጣት ሲተባበር የነበረው የአኙዋክ ተወላጅ መሆኑም ነው፤ እሱም በአቶ መለስ ዜናዊ ታዝዞ የፈፀመ ነው፡፡ በዚህም መሰረት 762 አኙዋኮች እንዲገደሉ ነው እቅድ የወጣው፡፡ ለዚህ ሁሉ ግዲያ ምክንያቱ በጋምቤላ ነዳጅ ከመውጣቱ በፊት በመጀመሪያ አኙዋኮችን በመግደል እንዲፈሩ ማድረግ ነው። ነዳጅ በሚወጣበት ጊዜ ምንም ዓይነት ንግግር እንዳይኖርና አፋቸውን ለማዘጋት በመታሰቡ ነው፡፡ የስም ዝርዝር በመስጠት የተባባረው ሰው ከአቶ መለስ ሞት በኋላ በኢህአዴግ አስገዳጅነት ወደ ፊሊፒንስ እንዲሄድ ተደርጓል፤ ግለሰቡም ባልታወቀ ሁኔታ እዚያው ሞቶ አስክሬኑ ወደ አገር ቤት መጥቶ ተቀብሯል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ቀደም ሲል እንደጠቀሱት የኢህአዴግን ውህደት ይደግፋሉ፤ ለዚህ ምክንያትዎ ምን ይሆን?
አቶ ኦኬሎ፡- ኢህአዴግ ከአጋር ድርጅቱ ጋር ውህደት መፍጠሩ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል እንደጠቀስኩልሽ አጋር የተባሉት በተለይ ደግሞ በጋምቤላ ክልል የነበረው የክልል ስልጣን ለይስሙላ ብቻ የክልሉ ህዝብ የሚተዳደረው በክልሉ ተወላጅ ነው ይባል እንጂ ይህ በአግባቡ ሲተገበር እንዳልነበረ እኔ ምስክር ነኝ፡፡ ይህ የሆነው ታዲያ አገር በአራት ብሄራዊ ድርጅቶች፣ የእኛ ክልልም ሆነ መሰል አጋር ድርጅቶችን በሞግዚትነት የሚያሾሯቸው ካድሬዎች ነበሩ፡፡ ይህ ዓይነቱ አስተዳደር ኢህአዴግ ከአጋሮቹ ጋር ውህደት ካደረገ በኋላ አንድ ወጥ ፓርቲ ስለሚሆን ጣልቃ ገብነቱንም ሆነ በክልላችን ያለውን ሀብት ባለመጠቀም የበይ ተመልካች መሆናችንን ያስቀረዋል የሚል እምነት አድሮብኛል፡፡ ውህደቱ መገፋፋትንና በነጣቂዎች መበላትን እንደሚያስቀር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (ጋህዴኮ) አባል ነበሩ፤ አሁንስ በየትኛው ፓርቲ ውስጥ ነው ያሉት?
አቶ ኦኬሎ፡- በአሁኑ ወቅት የኢዜማ አባል ነኝ፡፡ በጋምቤላ ክልል በመገኘት እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ከፓርቲው ጋር በተያያዘ የማደራጀት ሥራ እየሠራሁ ነው፡፡ የፓርቲው መዋቅር ሲሠራ በፓርቲው ውስጥ ምን ልሆን እንደምችል ለጊዜው አላውቅም፡፡ ምክንያቱም በክልል ደረጃ ገና መሪውና ሊቀመንበሩ አልተለየም፡፡ ስለሆነም የእኔ ስልጣን በአሁኑ ወቅት ይህ ነው ብዬ ልገልፅልሽ አልችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ኦኬሎ፡- እኔም ዕድሉን ስላገኘሁ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 9/ 2012 ዓ.ም
አስቴር ኤልያስ