“ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው” የሚል የአገራችን አባባል አለ። በዚህ አባባል ውስጥ የተጠቀሰው “ወሬ” አሉባልታ ወይም የሃሰት መረጃ የሚል አንድምታ ያለው ነው። የተሳሳቱ መረጃዎች በጦር አውድማ ጭምር ሽንፈትን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የሚያመላክት አባባል ነው።
በአሁኑ ዘመን በ“ወሬ” አገር ሲፈርስ ተመልክተናል። ግጭቶች ሲከሰቱ፣ ዜጎችም ለዘመናት ያፈሩት ሀብትና ንብረት ሲወድምም ታዝበናል። እነዚህ “ወሬዎች” ደግሞ የቴክሎጂውን እድገት በመጠቀም ተደራሽታቸው በማደጉ የጥፋት መጠናቸውም በዚያው ልክ እየጨመረ መጥቷል።
ለምሳሌ በቅርቡ አንዳንድ የአረብ አገራት የፈረሱበትን መንገድ ማየቱ አንድ ማሳያ ነው። የግብጽ አመፅ የተለኮሰው በፌስቡክ አማካይነት ነው፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ የሩዋንዳ ዜጎች የተጨፈጨፉበት አሳዛኝ ክስተት የእኩይ ሚዲያ “ወሬ” ውጤት ነው፣ በሶርያና ሌሎች አገራትም በሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችና ወሬዎች የግጭቱ አባባሽ ምክንያቶች ነበሩ።
በአገራችንም “ወሬ” ትልቅ አደጋ እየሆነ ይገኛል። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎች አገራችንን ወደ ማፍረስ እየሄዱ መሆናቸው በግልጽ እየታየ ነው። ከዚያም አልፎ በመደበኛ ሚዲያና በተለያዩ መንገዶች በሚተላለፉ አሉባልታዎች በአገራችን ዜጎች ለርስ በርስ ግጭት ሲዳረጉ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ባልተረጋገጡ ወሬዎችና አሉባልታዎች የዜጎች ህይወት ሲጠፋ፣ ንብረት ሲወድምና አንዱ ማህበረሰብ ከሌላው ጋር ሲጋጭ ማየትም እየተለመደ መጥቷል።
ሰሞኑን በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች ላይ የደረሰው የሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም ወደ ሌሎች ዩኒቨርስዎች እንዲዛመት የተሞከረበት መንገድ መንስኤም “ወሬ” ነው።
በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ለተከሰተው ግጭት ዋነኛ መነሻ እግር ኳስ ጨዋታ ነው፤ ያውም በቀጥታ የማይመለከተን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ። ተማሪዎቹ አንደ ማንኛውም የአገራችን ወጣቶች ይህን ጨዋታ የመመልከት መብት አላቸው። ነገር ግን ይህንን ጨዋታ በሚመለከቱበት ወቅት ከመዝናናት ባለፈ ለግጭት እስከመድረስ የሚያስችል አተካራ ውስጥ የሚያስገባ አይደለም። ከዚያም አልፎ እነዚህ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው። ዩኒቨርስቲ ለመድረስ ቢያንስ ከ12 ዓመታት በላይ በትምህርት ገበታ ላይ የቆዩና በጎና ደጉን የለዩ፤ በአብዛኛውም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶች የሚገኙበት ስፍራ ነው።
እነዚህ ተማሪዎች እንዲህ አይነት በህይወታቸው ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አደጋ ለመገንዘብ በቂ ልምድና እውቀት የሚጨብጡበት እድሜና የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። በሌላ በኩል እነዚህ ተማሪዎች ነገ የተሻለ ውጤት ይዞ ለመውጣት ዋነኛ ትኩረታቸው ትምህርት ሊሆን ይገባል። ከዚያ ውጭ ጊዜያቸውን አልባሌ በሆኑ ስፍራዎች የሚያሳልፉ ከሆነ አንድም በቂ እውቀት ሳይጨብጡ ይቀራሉ፤ በሌላም በኩል ደግሞ ላልተገቡ ማህበራዊ፣ ስልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ይዳረጋሉ።
ትልቁ አሳዛኝ ነገር ደግሞ በዩኒቨርስዎች የሚከሰቱ ግጭቶች መንስኤ የተሳሳቱ መረጃዎችና ምክንያታዊ ያልሆኑ አስተሳሰቦች መሆናቸው ነው። ለምሳሌ በሰሞኑ ግጭት ዋነኛ መንስኤ የእግር ኳስ ጨዋታ ሆኖ እያለ የብሄር መልክ እንዲይዝ የተደረገበት መንገድ የተሳሳተና ሆን ተብሎ ተማሪዎችንም ሆነ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን እርስ በርስ ለማጋጨት የታለመ ነው።
ታዲያ ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለአገራቸው ትልቅ ቁምነገር ይሰራሉ ተብለው የሚጠበቁት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲህ አይነት ግጭቶች ሲከሰቱ ቆም ብለው ምክንያቱን የማጥናትና ትክክለኛውን መስመር የመያዝ አቅም ለምን ጎደላቸው? ጥቂት በግጭት የሚነግዱ አካላት ግጭቶች የብሄር መልክ እንዲይዙ ከጎናቸው ሆነው ሲሰሩስ እንዴት መለየትና ወደ መስመር ማስገባት አቃታቸው የሚለው አጠያያቂ ነው።
ወላጅ ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርስቲ ሲልክ አንድም ተምሮ ራሱን ይችላል፤ ከዚያም አልፎ ይጦረኛል፣ አገርንም ይጠቅማል ከሚል መንፈስ እንደሆነስ እንዴት መገንዘብ ያዳግታል። በሚፈጠረው ግጭትም ወላጅ መጎዳቱንስ እንዴት ማሰብ ተሳነን የሚለው ዛሬም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።
መማር የሚበረታታው አንድም እውቀት ለመያዝና በዚያ እውቀት ተጠቅሞ ለአገር የሚጠቅም ቁምነገር ለመስራት፤ በሌላም በኩል ከራስ አልፎ የሌሎችን ያልተማሩ ህዝቦች ችግር ለመፍታት ነው። ነገር ግን የሌላው ችግር መፍታት ቀርቶ ለራሳችን ሰላም መሆን አለመቻላችን የትምህርቱ ፋይዳ የቱ ላይ ነው እንድንል ያስገድደናል።
መንግስት በርካታ ዩኒቨርስዎችን የሚከፍተውና ትልቅ ሀብት የሚያፈሰው የበለፀገችና ሰላሟ የተረጋገጠ አገር ለመፍጠር እንጂ ራሱን የብሄር አጥር ውስጥ ወሽቆ እርስ በርስ የሚገዳደል ወይም በሱ ሞት ለሚነግዱ ሃይሎች ሸቀጥ የሚሆን ዜጋ ለማፍራት አይደለም። በመሆኑም ወጣቱ ራሱን ከዚህ ችግር ማላቀቅና የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት ነገ ሳይሆን ዛሬ ሊሰራው የሚገባው የቤት ስራ ነው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2012