በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተተገበረ ያለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለአገራችን የዘመናት ችግር ፍቱን መድሃኒት መሆኑ አያጠራጥርም። እንደ ህብረቀለማዊ አበቦች በልዩነት ለፈኩት ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ልዩነትን አቻችሎ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን አጎናጽፎ ብሄሮች በማንነታቸው ተከብረው የሚኖሩበትን ዕድል ፈጥሯልና! ይሁንና ባልተገባ አያያዝ የተተገበረው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን አስፍቶና የከረረ ብሄረተኝነት እንዲሰፍን በማድረጉ፣ ዜጎች በአካባቢያቸው እንዲታጠሩና እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ በማድረጉ አገራዊ ህልውናችንን አደጋ ላይ ጥሎት ቆይቷል።
ይህ የተሳሳተ አካሄድ ክፉውንም ደጉንም በጋራ እየተቋደሱ ለዘመናት በአብሮነት የዘለቁትን የሀገራችንን ህዝቦች የጋራ እሴት በመሸርሸር ይህ የኔ ክልል፣ ወረዳ ወይም ዞን ወዘተ ነው በሚል ሰበብ ሂድልኝ እስከለማለት ለደረሰ ለመስማት ለሚቀፍ የሞራልና የስነምግባር ውድቀት ዳርጎናል። ዘመናዊ ትምህርት ባልተስፋፋበት ዘመን ቅድመ እናት አባቶቻችን ጠብቀው ያወረሱንን ተከባብሮና ተቻችሎ በአንድነት የመኖር እሴትንም በከፍተኛ ደረጃ ሸርሽሮታል። በአጠቃላይ ፌዴራሊዝሙ ልዩነትን ባከበረ መልኩ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብን የመፍጠር ውጥን ተይዞ ቢጠነስስም ዕቅድና ውጤት አራምባና ቆቦ ሆኖ ውጥንቅጡ ለጠፋው የፖለቲካ ውዥንብር ዳርጎናል።
በመሆኑም ላለፉት 28 ዓመታት አገራችንን የመራው ኢህአዴግ ለሰራቸው መልካም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ውዳሴውን እንደሚወስደው ሁሉ በተሳሳተ የፌዴራሊዝም አተገባበር ለፈጠረው አገራዊ ችግርም ኃላፊነቱን መውሰዱ አያጠያይቅም። ከዚህ ጋር በተያያዘም ኢህአዴግ ከዚህ በፊት በተለይም አገሪቱ በከፍተኛ ህዝባዊ አመጽ በታመሰችባቸው ጊዜያት ባደረጋቸው ስብሰባዎችና ጉባዔዎች በአገሪቱ ለተከሰቱ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወሰድና ለማስተካከል እንደሚሰራም መግለጹ አይረሳም። አህአዴግ ታላቅ አገርንና ህዝብን አንደሚመራ ፓርቲ አንድነቷ የተጠበቀ አገር መፍጠር የሚችለው በመጀመሪያ የራሱን አንድነት ማረጋገጥ ሲችል ብቻ ነው።
ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ላለፉት 28 ዓመታት አገር ሲመራ የነበረው በአገሪቱ የነበሩትን ሁሉንም ህዝቦች የሚወክሉ ፓርቲዎችን ባቀፈ መልኩ እዳልነበር በተለይም በአፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሶማሌና ሐረሪ ክልሎች ያሉ ፓርቲዎች በምሬት ሲያሰሙት የከረመ ጉዳይ ነው። እንደ ኢህአዴግ በግንባርነት ለዚህን ዓመታት ያህል የቆየ ፓርቲ የለም እያሉም በርካቶች ሲገልጹ ተደጋግሞ ተሰምቷል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው የተለያዩ ጉባዔዎችም የውህደቱ ጉዳይ ደጋግሞ ያሳስበውና ይወያይበት እንደነበር አንጋፋዎቹ የድርጅቱ አባላት አሁንም ድረስ የሚመሰክሩት ሀቅ ነው።
ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራምና ቢዘገይም እንኳ ኢህአዴግ ዘመኑን አስተውሎና የኢትዮጵያና የህዝቦቿን ፍላጎት ተረድቶ አሁን ላይ ውህደቱን በማፋጠን ላይ መሆኑ እሰየው የሚያስብል ነው። የኢህአዴግ መዋሃድ ተገፍተው የነበሩ ፓርቲዎች እንዲታቀፉና በአገራዊ ጉዳዮች እኩል የመወያየትና የመወሰን ዕደል እንዲገኙ ያደርጋል። የገዢው ፓርቲ ተጽዕኖም ከፍተኛ ነውና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሰብሰብ ብለው ጠንከር ያለ ፓርቲ እንዲፈጥሩ ትልቅ ትምህርት ይሆናቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአንድነት መንፈስ በአገራችን እንዲሰፍን ያደርጋልና ውህደቱ በናፍቆት የሚጠበቅ ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012