ከአራተኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ጀምሮ ስለውህደት ቢነሳም “ጊዜው አሁን አይደለም” በሚል ሲዳፈን የቆየው ሃሳብ ዛሬ ለፍሬ የመብቃት ዋዜማ ላይ ደርሷል፡፡ ፓርቲው ኢትዮጵያን በመንግስትነት መምራት ከጀመረበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ ጉዳይ ሲወስኑ የነበሩት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች፤ ማለትም የህዝበ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፤ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደህዴን ) ብቻ ነበሩ፡፡ በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ በሚወሰነው ውሳኔ በእነዚህ ፓርቲዎች ብቻ አልፎ አልፎም ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሰፊውን ሚና ወስደው ቆይተዋል፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ አጋር ፓርቲዎች እንደ እህት ድርጅቶች ሁሉ በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማስተላለፍ ካለመቻላቸው ባሻገር ከአራቱ ውጪ የሚገኙት ፓርቲዎች ምንም እንኳን የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶችን ባይቀናቀኑም በውሳኔዎች ላይ እንዲገደቡ ተደርገዋል፡፡ የኢህአዴግ ገደቡ አጋር ፓርቲዎች ላይ ያነጣጠረ ብቻ አልነበረም፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ብሔራዊ ድርጅቶች እንጂ የብሔራዊ ድርጅቱ አባል ግለሰቦች ድርጅቴ ብለው የሚጠሩትና ሃሳባቸውንም የሚያስተላልፉት በአባል ድርጅቱ ውስጥ ብቻ የተገደበ ነበር፡፡ ይህም የሃሳብ ብዝሃነትን ከማቀጨጭም በላይ የሌሎች ሰዎች ሃሳብ ተደማጭነት እንዳይኖረው፤ ግለሰቦች ድርጅቱ የኔ ነው ብለው እንዳይቆረቆሩ አድርጓል፡፡
“ሃሳባችን እንዲደመጥ እንድንስተናገድ እንፈልጋለን እንቀላቀል” በሚል ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ የኖሩት አጋር ፓርቲዎች አሳማኝ ያልሆኑ መልሶች እየተሰጣቸው ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች በተቃዋሚነት ተፈርጀው ሃሳባቸው መስተናገድ ባይችልም፤ አጋር ፓርቲዎች ግን ኢህአዴግ “ስጋ ሰጥቶ ቢላዋ የመከልከል” የሚመስል ዕድል ሰጥቷቸው ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግ በ“እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” አይነት ቀረቤታ ይዟቸው መቆየቱ፤ አጋር ፓርቲዎች ምንም አይነት ብቃት ያለው ሰው ቢኖራቸውም የአገር መሪ መሆን እንዳይችሉ፤ ህልሙም እንዳይኖራቸው የሐሳብ እስር ቤት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ በአገራዊ ውሳኔዎች ላይ ድምፅ የላቸውም፤ ነገር ግን የሚራመዱበት መስመር፤ የሚያቀነቅኑት ርዕዮተ ዓለም፤ የሚመሩበት አቅጣጫ ከኢህአዴግ የተለየ አይደለም፡፡ አጋር ናቸው ነገር ግን፤ በውሳኔ ላይ መሳተፍም ሆነ መቃወም አይችሉም፡፡
አሁን የኢህአዴግ ውህደት እውን ከሆነ ግን አጋሮችን ጨምሮ ሁሉም ያለገደብ የሚሳተፉበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ በዚህ ውስጥ ቀድሞ ኢህአዴግን ሲያስተች የነበረው የመንግስትና የፓርቲ አለመለያየት ችግር ይቀረፋል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን፤ በብሔር፤ በኮታ የነበሩ የስራ ድርሻዎች በብቃት፤ በውድድር ሆነው የተቋማት ጥንካሬ ተረጋግጦ፤ ኢህአዴግ ለአገሪቷ ዘላቂ ዕድገት ሰፊ መሰረት የሚጥልበት ዕድል ይመቻቻል፡፡ የነበረው የመንግስትና የፓርቲ አለመለያየት ችግር ተቃልሎ፤ በብሔሮች መካከል የተፈጠረው ሰፊ ልዩነት ጠብቦ ትብብር እና አንድነት ጎልብቶ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን እንዲሆን ይህ ውህደት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
ውህደቱ ዕውን ሲሆን እንደቀደመው አራቱ ፓርቲዎች ብቻቸውን በአገራዊ ጉዳይ ላይ አይወስኑም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በእኩል ተሳትፏቸው መላው ኢትዮጵያውያን እኩል ተፈላጊ መሆናቸውንም ያረጋግጣሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው በጠላትነት ለመፈራረጅና ለመጠላለፍ ሳይሆን ለልማት ይፈላለጋሉ፡፡ በመናናቅ የበላይነትን ለማስመስከር መሯሯጥ ሳይሆን፤ በመከባበር ይኖራሉ፡፡ አስቦ፤ አድብቶና አሰላስሎ ያለፈውን አስታውሶ በጥላቻ ለማጥቃት ሳይሆን በመፈቃቀር ይጠራራሉ፡፡
አንዱ ከሌላው ለመንጠቅ በመንገብገብ ሳይሆን በመተሳሰብ በአንድነት መጓዝ ይችላሉ፡፡ ይህ መንፈስ ከኢህአዴግ ውህደት የሚጀምር ሲሆን፤ የዜጎች የሃሳብ ብዝሃነት ያለምንም ገደብ ሲስተናገድ፤ እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን ሲሆን ያለምናትን ትልቋን ኢትዮጵያን መገንባት አያዳግትም፡፡ የነበረው አግላይነት እንዲቀጥል ከተጋን ግን የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ስለሚወድቅ የውሳኔው አካል የሆነው ኢህአዴግ ከወዲሁ ሊያስብበት ይገባል!
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012