በተለያዩ በይነ መረቦችና ማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን ለጥቃት የሚያነሳሱ፣የግድያንና መፈናቀልን የሚቀሰቅሱ መልዕክቶች በተለያዩ ጊዜያት ይስተዋላሉ። በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በማህበረሰቡ ዘንድ መጠራጠርና ፍራቻ ነግሶ የሰው ልጅ በአደባባይ እንዲሰቀል፣ ለትምህርት እና ምርምር ስራ የወጡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎች ተወግረው ተገድለዋል በሃሰተኛ መረጃ።የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ከአገራችን ባህል እና እሴት ጋር በተቃርኖ በጆሮ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ሀሰተኛ መረጃዎች የተሰራጩበትና የተሰሙበት ሆኖ በአገሪቱም ላይ ጠባሳን እየተው ይገኛል።
በዚህ ተግባር ተራ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ማህበረሰቡን የሚመሩ የመብት አራማጆች ነን የሚሉ ሕዝብን እርስ በእርስ በማጋጨት ክፉኛ ቢወቀሱም ከመጥፎ ተግባራቸው ሊታቀቡ ግን አልቻሉም። በዚህ ተግባራቸው የተካኑት ሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አራማጆች የአንዳንድ የመንግሥት ሃላፊዎች ንግግር ሳይቀር ከአውድ ውጭ እየወሰዱና እየተረጎሙ በሚፈጥሩት መከፋፈል በእሳት ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ ሆኖ ለአንዳንድ ጥላቻዎችና መራራቆች እንዲሁም ለተከሰቱ ግጭቶችን ለማቀጣጠል መንስኤ ሆነዋል።ይህ ሁኔታ ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መልሶች በሙሉ ጥላቻንና ጥቃትን ምላሽ ያደረጉና ሃይ ባይ ያጡ መልዕክቶች ለፖለቲካዊ ቀውስ ገፊ ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ።
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ግድያ፣ ጦርነት፣ ዘር ማጥፋት እንደተለመደ ነገር ተደርጎ መቀስቀሱ፣ በሀሰተኛ ምስል አስደግፈው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጫረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።ይህን ክስተት የሚያስቆመው ያጣ እስኪመስል መቀጠሉን በግልፅ እንመለከታለን።ግጭቶችን ከሚገባው በላይ በማቀጣጠልና በማጦዝ ክፉ ጥላቻን በመዝራት መሰረተ ቢስ አመክንዮ በመያዝ አንዱ በሌላው ላይ በጥላቻ እንዲነሳ ሰፊ እድል እየያዘ ይገኛል።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ደግሞ ሰሞኑን በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች በህንድ እና በደቡብ አፍሪካ የተከሰተን ዘግናኝ ድርጊት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተፈፀመ አስመስለው በማህበራዊ ሚዲያ ለቀቁ።ይህን ተከትሎም ‹‹በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ተማሪዎች ተገደሉ›› የሚል ፍፁም ሀሰት የሆነ መረጃ ተለቀቀ።ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ‹‹በግቢው የሞተ ተማሪ የለም›› ሲል ሀሰተኛ መረጃውን አጋልጧል፡፡ይህ ተግባር ሃሰተኛ መረጃዎች ምን ያህል የግጭት ማባባሻ እንደሆኑ ማሳያ ነው፡፡ስለሆነም መወገዝ ይገባዋል።
በሃሰተኛ መረጃና በጥላቻ ንግግር ምክንያት ባለፉት አመታት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት እንዲፈናቀሉ ሆኗል፤ በርካቶችንም ለሞት ዳርጓል።በዚህ የተነሳ ብዙዎች በሀገራቸው የሰቆቃ ኑሮ ውስጥ ከቷቸዋል። በዚህም የተነሳ አገሪቷ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ጥልቅ ጥናት ከተደረገ በኋላ ተግባራዊ ለመሆን የተቃረበው የጸረ ጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ረቂቅ አዋጅ ጉልበት አልሆነም።
የኢፌዴሪ መንግስት የተመድ የፕሬስ ነፃነትን የሚመለከተውን አንቀፅ 19ን በመፈረም ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት አጎናጽፏል፡፡በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 በቃልም ሆነ በፅሁፍ ወይም በህትመት፤ በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ሀሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ደንግጓል፡፡ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ ቅስቀሳዎችን እንዲሁም ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትም አንዱን ከአንዱ በማጋጨት ሌሎችንም ሰዎች አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ ከተገኘ በህግ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባም ይደነግጋል።
ከዚህም በተጨማሪ የጸረ ጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ረቂቅ አዋጅ “የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፤ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልፅ በሆነ መልኩ ከፍ ያለ መረጃን ሆን ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ” እንደሚያስቀጣ አስፍሯል፡፡ህጉ ስላልጸደቀ ግን ተግባራዊ አልሆነም።ይህ ተግባራዊ እስኪሆን ግን ዜጎችና መንግስት ምን ማድረግ አለባቸው? የሚለው መልስ ይፈልጋል፡፡
በመፍትሄነት ልናያቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡አንደኛው ወጣቶች የትኛውንም ስሜት ቀስቃሽ ምስሎችን ወይም ፅሁፎች ሲያዩ መጀመሪያ ያሉንን የእውነት ማረጋገጫ እሴቶች መጠቀም ያሥፈልጋል።ለምሳሌ በኦሮሞ ባህል ‹‹ዱቢን ሀቡልቱ›› ይባላል።ይህ ማለት ለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት በፊት ጉዳዩን አቆይቶ ወይም በአንክሮ መመልከት የሚል ነው።ጉዳዩን ጊዜ ሰጥቶ የመመልከት ጥበብን መጠቀም አለብን ማለት ነው።ሁለተኛው አማራጭ ቴክኖሎጂን መረዳት ነው።የትኛውንም የሀሰተኛ መረጃ ማመሳከር የሚያሥችሉ ቴክኖሎጂዎችን መቃኘት ያስፈልጋል።ሶስተኛ ግምታችንን በማስቀመጥ ‹‹ይሆናልና አይሆንምን›› ጊዜ ሰጥቶ መፈተሽ ይገባል።
መንግስትም እንዲህ አይነቱን ህገ ወጥ ድርጊት ለመቆጣጠር የሚያሥችለውን ህግ ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅበታል።የግለሰቦችን ነጻነት በማይነካ መንገድ የማህበራዊ ሚዲያ ተቋማትን መከታተል ይኖርበታል።ጧትና ማታ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሠራጩ ሀገር ውስጥም ሆነ ውጭ የሚገኙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድና እንዲወሰድ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።
ሀሰተኛ መረጃዎች እንደ ሀገር ጉዳት እያደረሱብን በመሆኑ እርስ በርስ የመማሪያ መድረኮችን መፍጠርም አስፈላጊ ነው።ሚዲያዎችን በመጠቀም ምሳሌዎችን እያሳዩ ሀሰተኛ ዜናዎችንና ፎቶዎችን በማጋለጥ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል።አክቲቪስቶችም ሆኑ ፖለቲከኞች ቢቻል ቢቻል ሀገርን የመገንባት ስራ ለድርድር ማቅረብ ትተው ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል።ምክንያቱም ሃገር በሃሰተኛ መረጃዎች መታመስ የለባትም።
አዲስ ዘመን ጥቅም4/2012