ባለፉት ጊዜያት በዓለማችን በተለያዩ ሥፍራዎች ተቃውሞ ተነስቶ አይተናል፤ አድምጠናል ። የአንዱ መነሻ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር ለማግኘት ሲል የነዳጅ ዋጋ ላይ ያደርገው የነበረውን ድጎማ እንደሚያቆም በማስታወቁ በኢኳዶር የተፈጸመ ነበር ።
የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ የመጓጓዣ አገልግሎቶች ላይ ጭማሪ ስለሚያስከትልና የምግብ ዋጋም እንዲንር ስለሚያደርግ ዋነኛ ተጎጂ የሚሆኑት አነስተኛ ገቢ ያላቸው ኢኳዶራውያን የሚኖሩባቸው የገጠር ክፍሎች መሆናቸውን ሰልፈኞቹ ጠቅሰዋል። መንግሥትም ውሳኔውን ቀልብሶ የነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገው ድጎማ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሌላዋ በህዝቧ ተቃውሞ ችግር ውስጥ ገብታ የነበረችው አገር ደግሞ ቺሊ ናት። የመጓጓዣ ክፍያዎች በእጅጉ መጨመራቸው ያማረራቸው ቺሊያውያን በዋና ዋና መንገዶች በመውጣት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። መንግሥት የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና የባቡር አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረግኩት ለኃይል ማመንጨት የማወጣው ወጪ ከፍ በማለቱና የአገሪቱ ምንዛሪ ደካማ በመሆኑ ነው ቢልም ዜጎች ግን ደሀውን ለመጫን ተብሎ የተደረገ ነው ሲሉ ብሶታቸውን በአደባባይ ገልጸዋል።
እነዚህ ከላይ ያየናቸው ተቃውሞዎች ምክንያታዊና ሰላማዊ ሲሆኑ፤ ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው የየአገራቱ መንግሥታት የሰጡዋቸው ምላሾች የህዝባቸውን ጥያቄ ያስተዋለ ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም ።
ኢትዮጵያውያን እንደሌሎቹ አገራት ያላቸውን ጥያቄ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ብርቃቸው ባይሆንም፤ አሁን ላይ እያሳዩት ያለው ባህርይ ግን ቀደም ሲል ከነበረው መልካምነት፣ አርቆ አስተዋይነትና ምክንያታዊነት የተለየ መሆኑ ለብዙዎች አስገራሚ ሆኗል ።
ኢትዮጵያውያን ብዙ ደክመው የለፉበት ጉዳይ ውጤት አልባ ሲሆንባቸው ‹‹ልፋ ያለው በህልሙ ዳውላ ይሸከማል›› ሲሉ ድካማቸውን በአነጋገር ዘዬ ለማስረዳት ይሞክራሉ። ልጅ ለፍቶ አሳድጎ፣ አስተምሮ ለወግ ይበቃልኛል ብሎ ሲጠብቅ ዩኒቨርሲቲ የገባ ተማሪ በቡድን ለፀብ መነሻ ባልሆነ ጉዳይ ሕይወት መጠፋፋት ደረጃ ሲደርስና ወላጆች የልጃቸውን አስከሬን ሲቀበሉ ማየት ልፋታቸው ከንቱ በመቅረቱ ምንኛ ያሳዝናል ።
‹‹ልጄ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ እኔ ሱባዔ ልግባ!›› እንዳሉት ወላጆች ዩኒቨርሲቲ መግባት በዕውቀት በልፅጎ፣ ለቀጣይ ኃላፊነት ራስን አዘጋጅቶ የሚወጣበት፣ ወላጆች የሚኮሩበትና የሚደሰቱበት ሳይሆን ከዛሬ ነገ ምን እንሰማ ይሆን ? የሚል ሰቀቀን ውስጥ የሚከርሙበት ሆኗል ።
ታዲያ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ፀብ መንስዔ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ሲደረግ መላምታዊ ምክንያቱ ኳስ ጨዋታም ፣ ስካርም፣ ብሄርም፣ ማህበራዊ ሚዲያም፣ መሆናቸው የተሻለ አመለካከት ይዞ አገር ይረከባል ተብሎ ተስፋ ከተጣለበት ትውልድ ይህንን መሰሉ ሰንካላ ምክንያት ፀብ ማስነሳቱ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል ።
ባለፉት ጥቂት ቀናት በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተው ብጥብጥና የጠፋው የሰው ሕይወት የሚያሳዝን ሲሆን፣ጠቡ ወደሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲዛመት የሚፈልጉ አካላት ያደረጉት ጥረት ቀናውን በሚያስቡ እንደ ጂማና አምቦ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ወጣቶች እርስ በርስ ሊያጋጫቸው የሚችል ምንም ምክንያት እንደሌለ በመረዳት ለመረጋጋት ያደረጉት ጥረት ለሌሎች በአርዓያነት ሊያስጠቅሳቸው የሚችል ተግባር ነው ።
ተምሮ ዕውቀት መገብየት፣ ክፉና ደጉን ማመዛዘን፣ የቤተሰብ ጭንቀት ሊወገድና ወጣቶች ተምረው ሥራ አጥ ከሚያደርጋቸው ችግር ሊላቀቁ የሚችሉት ፤ እንዲሁም የአገር ልማት ለማካሄድ አልሚ የሚሳበውና አገር መበልፀግ የሚችለው መረጋጋትን አማራጭ እንዳደረጉት የጂማና አምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁሉም ከተኛበት ነቅቶ ለሰላም ቅድሚያ ሲሰጥ በመሆኑ ለሕዝቡና ለአገሪቱ ሲባል ወጣቱ የሰላም ምንጭ ሊሆን ይገባል ። አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012