ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአገሪቱ የታየውን ለውጥ ተከትሎ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በርካታ ሁነቶች ተከስተዋል። በለውጡ ሂደት የታዩ ብዙ መልካም ነገሮች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ በዚያው ልክ ለውጡን ብቻ ሳይሆን የሃገርና የህዝብን ህልውና ሳይቀር የሚፈታተኑ ከበድ ከበድ ያሉ ችግሮችም ተከስተዋል። መልካም ነገሮች “የተቀመሙ ሽቶዎች” በመሆናቸው በመልካሙ መዓዛቸው ዓለምን ያውዱታል፤ ክፋት ግን “ዝንብ” በመሆኑ መልካሙን መዓዛ ያበላሻልና እኔም በዛሬው ትዝብቴ በለውጡ ሂደት ስለተገኙት መልካም ውጤቶች ትቼ የለውጡን መልካም ፍሬዎች እያበላሹ ስለሚገኙት ጎታች ችግሮች ያለኝን ላካፍላችሁ ወደድኩ።
የችግሮቹ አሳሳቢነትና የተዋንያኖቹ አስቸጋሪነት
የታዩት ችግሮች በባህሪያቸው ከደህንነትና ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ከመሆናቸውም ባሻገር መልካቸውን እየቀያየሩ በተደጋጋሚ መከሰታቸውና አሁንም እየተከሰቱ መሆናቸው መንግስትና ህዝብን እረፍት ለመንሳት ሆን ተብለው የተሸረቡና ጊዜ እየጠበቁ እንዲፈነዱ ዕቅድ ተይዞላቸው የሚፈጸሙ ያስመስላቸዋል። በመንግስት በኩል በተደጋጋሚ ሲገለጽ የሚሰማው “ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት የሚፈጥሩት ሴራ ነው” የሚለው አባባል የችግር ፈጣሪዎችን ማንነት በተመለከተ ያለንን ግምት የበለጠ ያጠናክረዋል። ይሁን እንጂ በእኔ ዕምነት ችግር ፈጣሪዎቹ ማንም ይሁኑ ማን አንዱ ሳይፈታ ሌላው እየተተካ፤ ችግሮቹ በየጊዜው እየተባባሱ እንዲመጡ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት የችግር ፈጣሪዎቹ ማንነት ሳይሆን “ችግሮቹ እንዳይፈቱ የሚያደርጉበት ዘዴያቸው” ነው ብዬ አምናለሁ።
እነዚህ የጥፋት ተዋናዮች አንዱ ችግር ሳይፈታ በላዩ ላይ ሌላ ችግር እንዲጨመርና ችግሮች እየተወሳሰቡ ሄደው መፍትሔ እንዳያገኙ በማድረግ የራሳቸውን ዕድሜ የሚያራዝሙበት ስልት “ራስን የህጻናት ፉክክር ውስጥ ማስገባት” የሚል አዲስ የድራማ ዘውግ ውስጥ ሊመደብ ይችላል። ይህ አዲስ የድራማ ዘውግ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የችግር ፈጠራ ተዋናዮቹ የህጻናትን ገጸ ባህሪ በመላበስ የሚተውኑት አስገራሚ የቴአትር ስልት ነው።
መቼም ህጻናት ብዙውን ጊዜ የሚታወቁት በልብ ንጽህናቸው፣ ከተንኮልና ከሴራ በራቀ ፍጹም የዋህነታቸውና ገራገርነታቸው ነው። የችግርና የጥፋት አበጋዞቹ “የህጻናትን ገጸ ባህሪይ” ተላብሰው ነው ድራማቸውን የሚተውኑት ስል የትኛውን የህጻናት ባህሪይ ነው? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ እርግጠኛ ነኝ። ገራገርነትን፣ የዋህነትንና ንጹህነትን ቢጫወቱልንማ በማን ዕድላችን? አገር አስቸጋሪዎቹ የጥፋት ተዋናዮች የመረጡት የህጻናት ገጸ ባህሪይ ግን አስቸጋሪውን የህጻናት ባህሪይ ነው። ጥፋት አጥፍተው ለምን እንዲህ አደረጋችሁ ብለህ ልትቀጣቸው ስትል ጣታቸውን ወደ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እየቀሰሩ “እሱስ?”፣ “እሷስ?” እያሉ፣ የራሳቸውን ጥፋት ማመን ትተው፣ ጥፋት ባይሰራ እንኳን ጥፋት ፈልገው አቻዎቻቸውን ለመወንጀልና ለማስቀጣት የሚሟገቱበትን አስቸጋሪውን የህጻናት ባህሪይ ነው የመረጡት።
ህጻናቱ ጥፋት አጥፍተው “እሱ ካልተቀጣ ወይም እርሷ ካልተቀጣች፣ እኔም አልቀጣም” በማለታቸው ወላጆች በአጥፊው ልጅ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ይቸገራሉ። ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ከዚህና ከዚያ ግጭት እያስነሱ አገርና ህዝብን እረፍት የነሱ ሁሉ ችግር ፈጣሪ መሆናቸው ታውቆ ጥፋተኛ ናችሁ ተብለው ሲጠየቁ “እነ እንትና ሳይጠየቁ ለምን ተብሎ እኛ እንጠየቃለን” የሚል የህጻናት ሙግት ያቀርባሉ።
ወላጆች በህጻናቱ አጉል ሙግት የተነሳ አጥፊውን ልጃቸውን ለመቅጣት እንደሚቸገሩት ሁሉ የአገርን ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ “ችግር ፈጣሪዎችን” የመቅጣት ኃላፊነት ያለበት መንግስትም “አጥፊዎቹን ልጆቹን” ለመቅጣት ሲቸገር ይስተዋላል። በነገራችን ላይ መደበኛ ህጻናቱ (በተፈጥሮ ህጻናት የሆኑት) ለዳኝነት የማይመቹ በመሆናቸው ወላጆቻቸውን ከሚያስቸግሩት በላይ እነዚህኞቹ አገር አጥፊ ህጻናት የሚያስተዳድራቸውን አካል (መንግስት)ን ያስቸግራሉ።
ለምን? ባለሁለት ወላጆቹ አገር አስቸጋሪዎቹ ህጻናት ከተጠያቂነት ለማምለጥ ከሚጠቀሙበት “የጥፋት ተጋሪ ፍለጋ ሙግታቸው” ባሻገር ከእውነተኞቹ ህጻናት የበለጠ ለዳኝነት አስቸጋሪ የሆኑበት ሌላም ችግር አለባቸው። ይኸውም ህጻናቱ ቤት ውስጥ ችግር ፈጥረውና ጥፋት አጥፍተው ወላጆቻቸው ሊቀጧቸው ሲሉ ጣታቸውን ወደ እህቶቻቸውና ወንድሞቻቸው የሚቀስሩበት ምክንያት ከቅጣት ለማምለጥ ብቻ የሚፈጥሩት “የልጅ ብልሃት” ነው። “የእርሷ ጥፋትስ፣ የእርሱ ጥፋትስ” በሚል አቻዎቻቸውን በሀሰት የሚወነጅሉበት ምክንያትም እህት ወንድሞቻቸውን ስለሚጠሏቸውና እንዲጎዱላቸው ስለሚፈልጉም አይደለም።
“በጥፋቴ መቀጣት የለብኝም” በሚል ከወላጆቻቸው ጋር “የጅል ሙግት” ውስጥ የሚገቡበትም ሆን ብለው ወላጆቻቸውን ለማስቸገር አስበው አይደለም። በቃ ቁንጥጫ ወይም ግርፊያ በመፍራታቸው ነው ይህንን ሁሉ የሚያደርጉት። ያም ሆኖ ይህን ሁሉ ዘዴ ተጠቅመውም ከወላጆቻቸው ቅጣት ማምለጥ ካልቻሉና ቅጣቱ ከተፈጸመባቸው (ደግሞም ይቀጣሉ) “ለምን በጥፋቴ ተቀጣሁ” ብለው ወላጆቻቸውን አያኮርፉም። በወላጆቻቸውና በቤተሰቡ ላይ አያምጹም። ተቀጥተውም ወላጆቻቸውንና ቤታቸውን ጥለው አይሸሹም፤ “የልጅ ጣሙ ሲገርፉት እግር ላይ መጠምጠሙ” እንድትል እናቴ ቅጣታቸውን ተቀብለው፤ ጥፋታቸውን ትተው ከቤተሰባቸው ጋር በፍቅር አብረው ይኖራሉ እንጂ!
አገር አስቸጋሪዎቹ የጥፋት ህጻናት ግን እንዲህ አይደሉም። አገርና ህዝብን የሚያውክ ችግር ፈጥረው፤ ሰላምና ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ከባድ ጥፋት አጥፍተው፤ ሃገርን ከጥፋት ተከላክሎ በሰላም የማስተዳደር ኃላፊነት የተጣለበት መንግስት በጥፋታቸው ሲጠይቃቸው ጥፋታቸውን ይክዳሉ። ይህን የሚያደርጉትም እንደምስኪኖቹ ህጻናት ቅጣትን በመፍራት ብቻ አይደለም። ሆን ብለው ከተጠያቂነት ለመሸሽ፤ ሃገርና ህዝብን ችግር ውስጥ ከትተው የራሳቸውን የግል ፍላጎትና ጥቅም ለማሟላት ነው።
“አዋቂ” እንደመሆናቸው መጠን ለእያንዳንዱ ድርጊት ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸውና ጥፋት አጥፍተው ሲገኙም በጥፋታቸው ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ እያወቁ “እገሌስ” እያሉ ጣታቸውን ወደ ሌላው የሚጠቁሙበትና ወገኖቻቸውን ውንጀላ ውስጥ የሚገቡበት ምክንያትም እንደ ህጻናቱ ከቅጣት ለማምለጥ ብቻ ሳይሆን ሌላውን በመወንጀል ራስን ለመጥቀም የሚያደርጉት ፍጹም ሰብዓዊነት የሌለው የክፋት መንገድ ነው።
በሌላው ወገናቸው ላይ ከሚያደርሱት በደል በተጨማሪ “በሰራሁት ጥፋት መጠየቅ የለብኝም” በሚል “የክህደት ሙግታቸው” ሃገርን በአግባቡ የመምራት ኃላፊነት የተጣለበትን መንግስትንም ሆን ብለው ችግር ውስጥ እንዲገባ ያደርጋሉ። ከዚህ ሁሉ ክፋትና ተንኮላቸው በላይ ግን አገር አጥፊ ህጻናቶቹ የፍትህ ፀር፤ በተለይ ለመንግስት ደግሞ “የመንግስታዊ ማንነቱ” ክፉ አሜኬላ የሆኑበት ምክንያት መንግስት በጥፋታቸው ተጠያቂ ሊያደርጋቸው በሚሞክርበት ጊዜ “ለምን እቀጣለሁ” በሚል በገዛ ጥፋታቸው መንግስትን ክፉኛ ከመጥላታቸው ባሻገር ለአመጻና ለበቀል መነሳታቸው ነው።
ከዚህም አልፈው መንግስትን ብቻ ሳይሆን እነርሱም ጭምር በቤተሰብነት የሚኖሩባትን ቤታቸውን (ሃገራቸውንም) ያኮርፋሉ። እንደ የዋሆቹ እውነተኞቹ ህጻናት ሳይሆን ከጥፋታችሁ ተመለሱ በሚላቸው አባታቸው (መንግስት) ላይ ቂም ይይዛሉ፤ የቀጣቸውን አባታቸውን ጠልተው ሌላ አባት ለማበጀት ይሞክራሉ። በጥፋታቸው ተጠያቂ በመሆናቸውና በመቀጣታቸው ቤታቸውንና ቤተሰባቸውን (ሃገራቸውንና ህዝባቸውን) ይጠላሉ፤ ጠልተው ጥለው ባይሄዱም እዚያው ሆነው በቤታቸው ውስጥ ሌላ ቤት፣ በአገራቸው ውስጥ ሌላ አገር፣ በቤተሰባቸው ውስጥ ሌላ ቤተሰብ፣ በህዝባቸው ውስጥ ሌላ ህዝብ ለመስራት ይሞክራሉ። ቤቱንና ቤተሰቡን በሚያስተዳድሩት ወላጆቻቸው ላይም ሌላ ወላጅ፣ በመንግስት ላይ ሌላ መንግስት፣ ለመፍጠር ይሰራሉ (ያሴራሉ)። ይህንንም የሚያደርጉት “አክቲቪስቶቻቸውን” በመጠቀም ነው።
ፍትህን ለማምጣትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት በጥፋታቸው ሲጠይቃቸው በወንጀላቸው ተጠያቂ እንዳይሆኑ አክቲቪስቶቻቸው ጠበቃ ይቆሙላቸዋል። ጥፋታቸው እየከፋ ሄዶ ከመንግስት አልፎ “ጥፋተኞቹ ይጠየቁ” ብሎ ህዝቡ ሲፈርድባቸው ደግሞ የጥፋት ተዋናዮቹ ከወንጀላቸው ለማምለጥ አስበው ወዳዘጋጁት ቤታቸው (ክልላቸው) ዘልለው ገብተው በእነርሱ አስተሳሰብ ለእኛ ያዳላልናል ያሉትን ህዝብ (ብሔር) ጥፋታቸውን እንዲደብቅላቸው ይማጸናሉ።
“እምቢ፤ የጥፋታችሁ ተባባሪ አልሆንም” እንዳይላቸው አዛኝና ተቆርቋሪ መስለው የገዛ ወገኑን “እንዲህ አድርጎሃል፣ እንዲህ በድሎሃል” እያሉ፤ ያልኖረበትን አዲስ የጥላቻ ታሪክ ፈጥረው እየተረኩ የጥፋት መርዛቸውን በልቡ ውስጥ በመዝራት የራሳቸው ለማድረግ ይጥራሉ። ሆኖም ሰውን ያህል ንቁ ፍጥረት ንቀውና ህዝብን እንደ ግዑዝ ነገር ቆጥረውት የእነርሱ ብቻ አድርገው ለብቻቸው ሊይዙት የሚፈልጉት “የእኔ ነው” ከሚሉት ህዝብ መካከል ብዙሃኑ ዕኩይ ተልዕኳቸውን ነቅቶባቸው እንደ ግርድ አንጓሎ ሲጥላቸው ማገናዘብ ወደማይችለውና እሳትና ውሃን ወደማይለየው ምስኪኑ ወጣት የጥፋት ኢላማቸውን ያነጣጥራሉ።
በሌላ በኩል “ወንጀለኞች ይያዙ፤ የህግ የበላይነት ይከበር” የሚለው ጥያቄ እየጨመረ መጥቶ የህዝብ እሮሮ በመንግስት ላይ ሲበረታ፤ መንግስት ኃላፊነቱን ለመወጣት አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግና ህግን ለማስከበር ቆርጦ በሚነሳበት ጊዜ ወንጀለኞቹ ከተጠለሉበት ቤታቸው (ክልላቸው) ካለው ህዝብ (ከብሔራቸው) ከኋላቸው ያሰለፏቸውን “ተከታዮቻቸውን” ቀስቅሰው ለአመጽ ይወጣሉ። እናም ለያዥ ለገራዥ፣ ለፈራጅ ለዳኛ አስቸጋሪ ይሆናሉ። የድህረ ለውጡ ዘመን የኢትዮጵያችን ዋነኛ ችግርም ይኸው ነው።
የችግር ኮትኳቾቹ ተልዕኮና ዓላማ
ለውጡን የሚመራው አካል ወይም የመንግስት ዋነኛ ችግር ተብሎ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው አጥፊዎችን ተጠያቂ አለማድረግና ተገቢውን የእርምት ርምጃ ያለመውሰድ፤ በአጭሩ “የህግ የበላይነትን ያለማስከበር ችግር” ለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። ችግር ፈጣሪዎች የጥፋት ሴራቸውን “ሀ” ብለው ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ጥፋታቸው ተጠናክሮ ቀጥሎ ህዝብን በብሔርና በሃይማኖት አቧድነው አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያስገባ የሚችል አደገኛ ወንጀል እስከሞከሩበት የሰሞኑ ክስተት ድረስ መንግስትንና ለውጡን የሚመራውን አካል ክፉኛ እያስተቸ የሚገኝ አሳሳቢ ችግር ሆኖ ቀጥሏል።
ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ሰዎችና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተከታታይ የሚከሰቱ የፀጥታና የደህንነት ችግሮችን ማስቆም ያለመቻሉ፣ መንስኤ በሆኑ አካላት ላይም በቂ እርምጃ ያለመወሰዱ መንግስትን ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ካልቻለ “ጥፋተኛው ራሱ መንግስት ነው ለችግሩ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል” እስከማለት ደርሰዋል።
ህዝቡም እንደዚሁ በተመሳሳይ “ከመጠን ባለፈ ትግስትና ቸልተኝነት” መንግስትን እየወቀሰ ይገኛል። የግጭት ፈብራኪዎችና የጥፋት ተዋናዮች ዋነኛ ተልዕኮም ይኸው ይመስላል። ጠቢቡ እንዳለው ዝንቦች የተቀመመውን ሽቶ እንደሚያበላሹ ሁሉ ሰነፎችና ክፉዎች እንዲሁ ናቸውና፤ እነዚህ የቃየል ልጆችም በአገራዊ ለውጡ የመጣውን መልካም ነገር በክፉ ሥራ እንዲበለጥና ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኖ እንዲታይ በማድረግ፤ በዚህም የነጻነት ረሃብና የሃገር ፍቅር ጥማት ከዘመናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በፍቅር ዓይን እንዲተያዩ ያደረጋቸውን ህዝብና መንግስትን ማለያየት ነው ዋነኛው ዓላማቸው።
በእነርሱ ክፉ ሥራ የተነሳ “የወንጀለኞችን ጥፋት ማስቆም፣ የህግ የበላይነትን ማስከበር አልቻለም” በሚል ህዝቡ ለውጡን በጥርጣሬ ዓይን መመልከትና በመንግስት ላይም ማጉረምረም መጀመሩም በከፊልም ቢሆን እኩይ ዓላማቸው ፍሬ እያፈራ በመሆኑ ችግር አምራቾቹን ማስደሰቱ የማይቀር ነው።
እንደ መፍትሔ
ስለሆነም እዚህ ጋር ህዝብና መንግስት ከምንጊዜውም በላይ መንቃት ይጠበቅባቸዋል። በተለይም መንግስት በህዝብ እንዲጠላ እያደረጉ ያሉትንና መንግስትነቱንም እየተፈታተኑ የሚገኙትን እነዚህን የህዝብና የሃገር ጸሮች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጥንቃቄና በጥበብ መራመድ ይጠበቅበታል። ከሁሉም አስቀድሞ በችግር ላይ ችግር እየደራረቡ አገርንና ህዝብን በጥፋት ጎዳና ላይ እየመሩ የሚገኙ እነዚህን የእፉኝት ልጆች በየጊዜው የሚፈጥሩትን ችግር በአፋጣኝ ማስቆም የሚችል ከእነርሱ የጥፋት ስልት በልጦ ሃሳባቸውን የሚያከሽፍ፤ ድርጊታቸውን የሚያሸንፍ የላቀ ሃሳብ ማመንጨት ይኖርበታል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ሙት ይዞ ይሞታል” እንዳሉት ከላይ እንደጠቀስነው በህዝብ ውስጥ የተደበቁ የጥፋት አረሞች ሲነቀሉ ሰብል ይዘው እንዳይነቀሉ በጥንቃቄ እንክርዳዱ ከስንዴው ተለይቶ የሚነቀልበትን ጥበብ መዘየድ ይገባል።
በአንጻሩ ከዚህ ጎን ለጎን የጥፋተኞችን ተግባር ለማስቆምና የህዝብንና አገርን ደህንነት ለማስጠበቅ ሌላው በትልቁ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ “ጥፋተኞቹ ህዝብ ውስጥ ከለላ አግኝተዋልና በእነርሱ ላይ ርምጃ ቢወሰድ ገና ለገና ከህዝብ ጋር እጋጫለሁ” በሚል መንግስት አጥፊዎችን ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የለበትም። ምክንያቱም በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ እነርሱ እንደሚሉት አብዛኛው ህዝብ የጥፋት መሪዎቹ ደጋፊ አይደለም።
የሩቁን ትተን ከሰሞኑ በሃገራችን የተከሰተውን የጥፋት አበጋዞች እኩይ ድርጊት እንኳን ብንመለከት በቢሾፍቱ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋና በሃረር ከተሞች የሆነው በቂ ማሳያ ነው። በህዝብ ላይ ከፈጸሙት ዘግናኝ ወንጀል በኋላ ህዝቡ በብዛት ወጥቶ ሲቃወማቸው ከተጠያቂነት ለማምለጥና በቀጣይም ጥፋታቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበትን ዕድል ለማግኘት ሴረኞቹ እንደለመደባቸው “ከእንትን አካባቢ የመጡ ናቸው የተቃወሙን” የሚል ሃሰተኛ ክሳቸውን ይዘው ከህዝብና ከመንግስት ጋር አጉል የህጻናት ሙግት ውስጥ ሲገቡ ቢታዩም እውነታው ግን ከላይ እንደተገለጸው ነው።
በማያውቁት ነገር በጥፋት መረባቸው አጥምደው ወይንም አውቀውም ቢሆን በጥቅም አታልለው “ተከታዮቻቸው” ካደረጓቸው የራሳቸው ሰዎች በስተቀር ብዙሃኑ ህዝብ አይከተላቸውም፤ አይደግፋቸውምም። ታዋቂው የመብት ተሟጋች ታማኝ በየነ የአገር አጥፊዎችን እኩይ ድርጊት ባወገዘበት ንግግሩ እንዳለው፤ “ከዘጠና ዘጠኝ በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብማ አብሮ መኖር ነው የለመደው፤ የሚፈልገውም አብሮ መኖር ነው”።
ህዝቡ ሴረኞችንና የጥፋት አጋፋሪዎችን እንደማይፈልጋቸውና እንደማይከተላቸው ያሳየበት አጋጣሚ ይሔ ብቻ አይደለም። “ለደህንነታችሁ ጥሩ አይደለም፤ ወደዚህ ክልል አትሄዱም” ተብለው በገዛ አገራቸው ውስጥ በፈለጉት ቦታ በነፃነት ተንቀሳቅሰው እንዳይኖሩና እንዳይማሩ የተከለከሉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “እኛ ፍቅርን የሚያስተምር ህዝብን እንጂ ጥላቻን የሚሰብኩ ፖለቲከኞችን አናምንም፤ እምቢ እንሄዳለን” ብለው የሴረኞችን የጥላቻ ትርክት ያከሸፉት ወጣቶችም ህዝብን ከፍ አድርገው ያሳዩ የህዝቡ አስተሳሰብ ምንነት ማሳያዎች ናቸው።
እናማ ብዙ አስመስለው “ህዝቤ” የሚሏቸው ተከታዮቻቸውም አንድ ቀን እነርሱንም ሊያጠፏቸው እንደሚችሉ ገብቷቸው ከጥፋት ድርጊታቸው እስኪርቁ፤ የጥፋት መሪዎችም በሂደት ከአጃቢዎቻቸው ተነጥለው ብቻቸውን እስኪቀሩ ድረስ መንግስት የጥፋት ፈልፋዮችን “የህዝቡ የእኛ ነው” አጉል ማስፈራሪያ ትቶ አገርና ህዝብን በሚያምሱ ወንጀለኞች ላይ አግባብ ያለው ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። አለበለዚያ “ነገ ይተው ይሆናል” በሚል አጉል መልካምነትና ተስፋ የጥፋት መሪዎቹ በሂደት ከዚህም በላይ ኃይላቸውን አጠናክረው ለባሰ ጥፋት ጊዜ እንዳያገኙ፤ መንግስትም የመንግስትነት ሚናውን በጊዜው ባለመወጣቱ እንኳንስ ይጠብቀኛል ብሎ ለሚተማመንበት ህዝብ ለራሱም መሆን አቅቶት “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” አይነት እንዳይሆን ያሰጋል።
አዲስ ዘመን ጥቅም3/2012
ይበል ካሳ