ማዋዣ፤
በጅምላ ፍረጃ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አካሄድ መበየን ካስፈለገ ከልጆች “ዕቃ ዕቃ ጨዋታ” ጋር ማስተያየቱ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል። “ከዝንጀሮ ቆንጆ … ” እንዲሉ በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሥልጣንን ብቻ እያለሙ የሚፋተጉትን ቡድኖች ማንነት በጥልቀት እንፈትሽ ብንል “ቢከፍቱት ተልባ” ይሉት ዓይነት የጋራ ባህርይ መላበሳቸውን ለመረዳት እጅግም አያስቸግርም። ይህ ጥቅል ፍረጃ የሚጎረብጠው ካለ ሰይፉን ወደ ሰገባው ከትቶ በሃሳብ መሟገት ይችላል።
የልጆች ዕቃ ዕቃ ጨዋታ የሚቆየው ለደቂቃዎች፤ ከበዛም ከአንድ ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ ነው። ጨዋታው ሲጀመር ህፃናቱ በአለባበሳቸው ሳይቀር ራሳቸውን እንደ ትልቅ ሰው መስለው፣ ንግግርና ድርጊታቸውን መጥነው፣ ያልሆኑትን ለመሆን “የጨዋታ ትልቅነትን” ያሳያሉ። የወላጆቻቸውን ገበና በቴያትራቸው እየገለጡ አደባባይ ይዘረግፉታል።
የሰንሰል ቅጠልን እንደ እንጀራ፣ የአፈር ብጥብጥን እንደ ወጥ፣ የቆርኪ ድርድሮችን በቡና ስኒና ረከቦቱንም በአጠገባቸው ከሚያገኙት ቁስ በመጠቀም “ድግስ እየደገሱ ይጋባሉ፤ ይሞሸራሉ።” የመሰረቱትን ጎጆም በቤታቸው ካርቦን ኮፒነት መስለው የአባትና የእናት ሚናቸውን ይወጣሉ። ይህ የብላቴኖች የምኞት ትርዒት የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ነው። ማጠናቀቂያውም “ጨዋታ ፈረሰ፤ ዳቦ ተቆረሰ” ሆኖ “የጨረባ ተስካሩ” በካልቾ እየተለጋ ይበተናል። ቅጠልና የአፈር ብጥብጥ እየተጓረሱ የመሠረቱት የብላቴኖቹ ትዳርም ሰማኒያው ተቀዶ በረብሻና በመጯጯህ ይጠናቀቃል።
ይህን መሰሉ የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ብዙውን ጊዜ መልኩን እየሳተ “መታኝ፣ መታችኝ” በሚሉ ዓይነት መራበሾች ስለሚጠናቀቅ ጊዜያዊ ግጭታቸው ቤተሰቦቻቸውን እያናቆረ ወደ ማነካካት ሊያደርስም ይችላል። የሕጻናቱ “የጨዋታ ቅኔ” ቤት መምቻውም ሆነ ቤት መድፊያው ጠብና መጯጯህ ነው የሚባለውም ስለዚሁ ነው።
ማንፀሪያ፤
የሀገራችን ገዢም ይሁኑ “ተፎካካሪ” ተብዬ የፖለቲካ ቡድኖች የልጆችን የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ባህርይ ሙሉ ለሙሉ በካርቦን ግልባጭ ወርሰው “ትልልቆች እየመሰሉን በተግባር ግን ትንንሾች” የሆኑባቸውን ታሪካዊውንም ሆነ ነባራዊ ሁኔታዎችን ብንመዝን ተመሳስሎ ብቻ ሳይሆን ተቀራራቢነታቸውም የጎላ መሆኑን መገንዘብ አይገድም።
ፖለቲከኞቻችን የጨዋታውን ሜዳ ሲቀላቀሉ ሁሉን አወቅና መፍትሔ አመንጭ እንደሆኑ እንድንቆጥራቸው ራሳቸውን በኮሜድ “ከስቹም” (በቴያትር ወቅት የሚለበሱ አልባሳት) ተጎናጽፈው በሚዲያ ዲስኩር እያጣደፉ ለአሜንታ ያዋክቡናል። በጊዜያዊ ሞቅታ እየተነቃቁም እከሌ የተባለው የፖለቲካ ቡድን እንቶኔ ከተባለው ቡድን ጋር “ተጋባ” (ተዋሃደ) የሚል ማስታወቂያ ያስነግራሉ። “ፍቅር ሲጠና ቆሎ ያጓርሳል” እንዲሉ ለወራት ያህል ብን ያሉበት ፍቅር ቆርፍዶ ወደ ሰማይ ያጎኗት ኳስ መሬት ሳትደርስ ፍቺ መፈጸማቸውን ለማወጅ ስማ በለው ያስነግራሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የጀርባ ታሪክ በአብዛኛው ከዚህን መሰሉ እውነታ አይርቅም።
ከፍ ሲልም ተካሰውና ተወነጃጅለው በጠላትነት ሲፈላለጉ እናስተውላለን። ሊያቦኩት ያሰቡት የፖለቲካ መፍትሔ ሊጥ ዳቦ ሆኖ ሳይጋገር ገና ከሃሳብ ምጣድ ላይ እንዳለ እንደለመዱት “ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ” ተባብለው ይፋታሉ። ፍቺያቸውን እንዲያፀድቁላቸውና ዳረጎታቸው እንዳይቋረጥባቸው የባዕድ መንግሥታት ኤምባሲ ጽ/ቤቶችን ደጅ መጥናት ይጀምራሉ። የሀገራችን የፖለቲካ ቅኔ መልክ ይህንን ይመስላል።
መራር ትዝብት፤
ይህን መሰሉ የፖለቲካ ቅኔ ለምን በፍሩንዱስ እንደተመሰለ ወደ ኋላ ግድም እመለስበታለሁ። ስለፍሩንዱስ ቅኔ ምንነት ከመናገራችን አስቀድሞ ግን በመደበኛው የሀገራችን ቅኔ የትመጣና ባህርይ ዙሪያ ጥቂት እውነታዎችን መፈነጣጠቅ ግድ ይሏል። “የሀገራችንን የግዕዝ ቅኔ ማን ጀመረው?” የሚለው የባለቤትነት መብት በተመለከተ እንደ ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ሁሉ ጥልል ብሎ ስላልሰከነ እዚያም ሠፈር የሀገራችን ሊቃውንት በሙሉ ተስማምተው “የቅኔ ጀማሪው እከሌ የተባለው ሊቅ ነው” ብለው ውሳኔያቸውን በአሜንታ ሊያጸድቁ የቻሉ አልመሰለኝም።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እጅግ ረቂቅ ምሥጢር ለተላበሰው ለሀገሬ ነገረ ቅኔ እውቀት ሩቅ ስለሆነ ዋቢ አድርጎ የሚጠቅሰው የኮሌጅ መምህሩ የነበሩትን የግዕዝና የቅኔ ሊቅ ነፍሰ ኄር የኔታ ዓለማየሁ ሞገስ ከጻፉት “ሰዋሰወ ግዕዝ” መጽሐፍ ላይ ጥቂት አናቅጽ በመዋስ ይሆናል።
“ቀነየ፣ ተቀነየ – ተቀኘ፣ ዘመረ፣ በምሥጢርና በስልት ተናገረ የሚለው ግሥ ጥሬ ዘር ስለሆነ ምሥጢር የተጎናጸፈ መዝሙር ማለት ነው። ደራሲው የጎንጅ (ጎጃም) ተወላጅ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ተዋነይ የሚባል ሊቅ ነው። እሱም ከልጅነቱ ጀምሮ የድርሰትና የፍልስፍና ተውህቦ የተሰጠው ስለነበር በየአድባራቱና ሊቃውንቱ ተምሮ አገባብን ካጠናቀቀ በኋላ፣ ደቅ እስጢፋኖስ (የጣና ደሴት) ገብቶ ብዙ መጻሕፍት አንብቦ የቅኔን መንገድና ዐይነት አስማምቶ አውጥቶ፣ ለተማሪ ቶሎ እንዲገባው፣ እንደ ዋድላ ሳያስረዝም፣ አገባቡን ወስኖ አዋጁን አሳጥሮ፣ ለሁሉም መርሕ የሚሆን አብነቱን ጽፎ ወጥቶ፣ በጎንጅ ሲያስተምር ኑሮ ሙቷል።
ስለ ተዋናይና ስለ ቅዱስ ያሬድ ብዙ የባልቴት ተረት ይተረታል። ከእርሱ በፊት የነበረው መልክና ግጥም እንጂ ቅኔ አይደለም። የዜማ ቤት ሰዎች ቅዱስ ያሬድ ነው የደረሰው ይላሉ፤ ግን የሱው ተራ ግጥም እንጂ ቅኔ ስላልሆነ ጉንጭ አልፋ ክርክር ከመሆን አይዘልም። ዋድሎችም ዮሐንስ ገብላዊ ተናግሮታል ይላሉ፤ እሱም ሰዋሰው እንጂ የቅኔን ሕግ ስላልጻፈ ቀዳማዊውና ደንበኛው ደራሲ ተዋነይ መሆኑ የማይጠረጠር ነው። ከርሱ በኋላም የተነሱ ሊቃውንት የሱን መሠረት ተከትለው እያስፋፉ እንደሄዱ አይካድም።” (ሰዋሰወ ግዕዝ፣ ገጽ 117)
የቅኔ አመጣጥ ታሪክ በርካታ የዘርፉን ጠበብት እንደሚያወዛግበው ሁሉ የሀገራችን የፖለቲካ ቅኔ አፈታትም እነሆ ከማከራከር አልፎ እስከ ማጠፋፋት ጎልምሶ ለአቅመ ሰይፍ ማማዘዝ እንዲደርስ መዳላድሉ ተነጥፎለታል።
“የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ ቀድሞ የበራለት ዋለልኝ መኮንን ነው”፣ “የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ብቸኛ ፈጣሪ እከሌ ነው – የእርሱ ፍልስፍና የተነካ ዕለት ምድር ቀውጢ ትሆናለች፣ ገጠሩን ያማከለ ዕድገት በማለት በነፍሱ እንደተወራረደ ለአርሶ አደሩ ልዕልና ሲሟገት ኖሮ ያለፈው እከሌ ነው፣ እከሌ ለተባለው ብሔር የስደት፣ የእንግልት፣ የላብና የደም ዋጋ የከፈለው እንቶኔ የተባለው ብቸኛ ድርጅት ነው፣ ወዘተ…” በሚሉና በመሰል ሌሎች በርካታ “የፖለቲካ ቅኔዎች” አፈታት ዙሪያ ያልተቋሰለና ያልተታኮሰ የሀገሬ የፖለቲካ ቡድን ፈልጎ ለማግኘት ያዳግታል። ሰላማዊ ቋንቋ ተነጋግረው የሀገሬን “ቅኔ” ለመፍታት የሞከሩ የፖለቲካ ልሂቃን አሉ ማለት ፌዝና ፍዝነት ካልሆነ በስተቀር ምንም ማለት አይቻልም።
በዘመናት ሲቀነቀን የኖረው የሀገራችን “የፖለቲካ ፍልስፍና” በሙሉ በፍሩንዱስ ቅኔ ቢመስል አግባብ ይሆናል። አሃ! ለካንስ የፍሩንዱስ ቅኔ ምንነት ለአንባቢያን አልተገለጸም። ፍሩንዱስ ቅኔን በአጭሩ ደንግገን ከፖለቲካችን ጋር ምስስሉን ከማዋደዳችን አስቀድሞ ለግዕዝ ቅኔም ሆነ ለፍሩንዱስ ቅኔ የተሰጠውን ብያኔ በጥቂት ቃላት እናስተዋውቅ።
“የግዕዝ ቅኔ ከጉባዔ ቃና እስከ ዕጣነ ሞገር የሚቀኙት ቅኔ፣ የሰዋሰው መንገድ ነው።” በአንጻሩ ይሄው ምሥጢረ ረቂቅ የግዕዝ ቅኔ አንዳንዴ ያለባህርይውና ያለ ደንቡ ከአማርኛ፣ ከኦሮምኛ ወይንም ከሀገራችን ከአንደኛው ቋንቋ ወይንም ከእንግሊዝኛ ጋር እየተደባለቀና እየተሰባጠረ (ዘመንኛው አገላለጽ ሚስቶ እንደሚለው ይሆን!?) ሲነገር ፍሩንዱስ ቅኔ ተብሎ ይጠራል። አማርኛ ከግዕዝ ጋር ተሰባጥሮ የተቀኙትን አንድ ጉባዔ ቃና ፍሩንዱስ ቅኔ እናስታውስ፤
«ልጆች ተማሩ/ የፍርድን ሥራ ቀጥታ፣
አይጥ በበላ ስንዴን/ አምጣነ ዳዋ ተመታ።»
ምሥጢሩ፤ አጥፊ ሳለ ያላጠፋ አይጎዳ ማለት ነው።
ወደ ፖለቲካው ፍሩንዱስ ጉዳይ እንመለስና ጥቂት እንቆዝም። የፖለቲካ መጫወቻው መድረክ ኢትዮጵያ ነች። የፖለቲካ ትሩፋትን ፍሬ ይገምጣል ተብሎ እንዲጎመዥ የተፈረደበት ደግሞ አሳረኛው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ሕዝብ ብለን በጅምላ እንዳንጠራ ብሔር ብሔረሰብ በሉ ተብለን ተፈርዶብን የለ “ይሁን ግድ የለም በሉ እንዳሉን እንላለን።”
በሰም ለበስ ዕንቁ የምትመሰለው ኢትዮጵያ በዚህች ፕላኔታችን ላይ ረቂቅ የታሪክ አሻራ ካኖሩ ጥቂት ሀገራት ተርታ ትመደባለች እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት የመቶ ዓመት ንብርብር ኩነት የፈጠራት ምድር አይደለችም። ኢትዮጵያ ቅኔ ነች። ቅኔዋ የረቀቀ፣ ምሥጢሯ የመጠቀ እናት ነች። ለዚህች ቅኔ ሀገር ፍቺውን እንሰጣለን ብለው የተነሱት የሀገራችን ቀደምትና የዛሬ ፖለቲከኞች በሙሉ “ቅኔዋን ሀገሬን” በወጉና በአግባቡ ከመፍታት ይልቅ የራሳቸውን ፍሩንዱስ ቅኔ ፈጥረው በቋንቋና በዘር እየበከሏት እነሆ የ“ቅኔያችንን” መልክ አደብዝዘው እምዬን ማዲያት አልብሰዋታል።
የፖለቲከኞቻችን ፍሩንዱስ ቅኔ መሠረት ያደረገው ቋንቋና ዘርን ነው። አንድነቷንና ኅብረ ቀለማቷን አሳድፈው በራሳቸው ቋንቋና ዘር ልክ ጥብቆ ሰፍተውላት ታላቋን ሀገር እንደ አሻንጉሊት እየተጫወቱባት ማየት ከጀመርን ሰነባብተናል። ባለ ፍሩንዱስ ቅኔ ፈጣሪዎችና ዘራፊዎች ከየትና እንዴት እንደበቀሉ ታሪክም ሕዝብም ምስክርነት ይሠጣሉ።
በመከራዋ ጊዜ የካዷት፣ በችግሯ ዘመን የረሷት “የድል አጥቢያ አርበኞች” ፀሐይዋ ወገግ ማለት ስትጀምር ከጎሬያቸው ብቅ እያሉ ደረታቸውን ነፍተው ዱታ ነኝ እያሉ ፍሩንዱስ ቅኔያቸውን ሲቀኙ ብዙዎች እያጨበጨቡ ስላደነቋቸው የልብ ልብ ተሰምቷቸው “ከእኛ ወዲያ ላሳር እያሉ” በመፎከር “ጀግንነታቸውን በደም ግብር” እያስመሰከሩ ይንጎማለላሉ። የሀገሬ ነገር አዋቂ የመረረ ትዝብቱን በእንጉርጉሮ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤
«ለጌሾ ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ፣
ለመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ።» ግሩም ትዝብት ነው።
የ1960ዎቹ ትውልዶች መከራ አሸክመውን አለፉ። ያለፉት ቢያልፉም ቅሪቶቹም አልቦዘኑም። በሰለለ ጉሮሯቸው፣ በሚጓጉጥ ህልማቸው በዛሬ ሃምሳ ዓመት ቅኝት ፍሩንዱስ ቅኔያቸውን እያንጎራጎሩ አሰልችተው ያደናቁሩናል። “ቅኔዋን ኢትዮጵያ” ትተው ለራሳቸው ሥልጣን ፍሩንዱስ ዜማ ፈጥረው ግራ ያጋቡናል።
በረሃ በደደረ ጡንቻና ምድረ በዳ በታለመ ህልም ሀገር ሲመሩ የኖሩ “አብዮታውያንም” ቅኔዋን ሀገሬን ለሦስት አስርት ዓመታት ዘርፈውና አዘርፈው ከጠገቡ በኋላ ጊዜ እንደከዳቸው ቢያውቁም “ካፈርኩ አይመልሰኝ” እንዲሉ እየተንፈራገጡ አላርፍ ብለው እረፍት ነስተውናል።
ሀገሬ ቅኔ ነች። በቱማታ የሚዘረፍ ፍሩንዱስ ቅኔ አይመጥናትም። ዛሬ በድብልቅ የቋንቋ ፖለቲካ እየተዋዛ የሚቀነቀነውና የሚመሳጠረው ፍሩንዱስ ቅኔ ዕድሜው ረጅም አይሆንም። ይልቅስ የሀገሬ ፖለቲከኞች የታወሩት እውርነታቸው ገብቷቸው፣ የደነቆሩት ድንቁርናቸው ተሰምቷቸው የህሊናቸውን ጆሮ ከፍተው ከዘመን ጋር ቢታረቁ መልካም ይሆናል። ከዘመን ተኳርፎ መመሸግ የሚያስከትለው ውጤት የከፋ መሆኑን ቢገነዘቡትና ከሤረኛ ተግባራቸው ተፀፅተው ቢመለሱ አንድም ለነፍስ፤ አንድም ለፈውስ ይሆንላቸዋል። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥቅም3/2012