ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም እኩለ ለሊት ላይ የተከሰተ ግጭት ለሰዎች ሕይወት መጥፋትና ለጉዳት ዳርጓል። ግጭቱን ተከትሎ በዋነኛነት በማህበራዊ ሚዲያው ቀጥሎም ራሳቸውን የአንድ ብሔር ተቆርቋሪ አድርገው ያስቀመጡ መገናኛ ብዙሀን በኩል ከክስተቱ ጋር ተመጣጣኝ ባልሆነ መልኩ የተሰራጩ ሐሰተኛ ዜናዎች (ዘገባዎች) እና ምስሎች በእሳት ላይ ቤንዚን ያርከፈከፈ እና ያለንበትም አስከፊ ሀገራዊ ቀውስ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሆኗል። ዩኒቨርሲቲው የተፈጠረውን ተጨባጭ ሁኔታ በተመለከተ ህዳር አንድ ቀን 2012 ዓ.ም ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥቷል።
“ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት 5:00 ስዓት ላይ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሁለት ተማሪዎቻችንን ህይወት የቀጠፈና በሌሎች 13 ተማሪዎቻችን ላይም ቀላል የሚባል ጉዳት መድረሱን የህክምና ምርመራ ውጤታቸው ላይ መረዳት ተችሏል።
ግጭቱ እንደተፈጠረ ወዲያውኑ የሰሜን ወሎ ዞንና የከተማ አስተዳደሩ ፀጥታ አካላት እንዲሁም የክልሉ አድማ በታኝ በተጨማሪም ሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን ጨምሮ የዞን አመራሮችና የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስረስ ንጉስ ችግሩ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ችግሩ እንዳይባባስ የመከላከል ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል። ተጨማሪ የፀጥታ አካላት እንዲመጣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም የመወያየት ስራ ተሰርቷል። የግጭቱን መንስኤ ለማጣራትም የምርመራ ቡድን ተቋቁሟል ።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው የዲኖች ስብስብ ያለበት ግብረ ሀይል አቋቁሙ ተማሪዎችን የማረጋጋትና ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎችን በመከታተል በወቅቱ ህክምና እንዲያገኙ የማስተባበር ሥራ እየሰራ ነው። በአሁኑ ሰዓትም በወልድያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ጉዳቱ ከደረሰባቸው መካከል አብዛኛዎቹ በቅርብ ከሆስፒታል እንደሚወጡ ይጠበቃል። ህይወታቸው ያለፈ ተማሪዎቻችን የቀበሌም ሆነ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆናቸውን የሚገልፅ ምንም አይነት መረጃ በኪሳቸው ባለመገኘቱ እንዲሁም ህንፃ ቁጥሩንና የዶርም ቁጥሩን መለየት ባለመቻሉ የተማሪዎቹን ማንነት ለመለየት ጊዜ የወሰደ ቢሆንም የተቋቋመው ግብረ ሀይል ሌሎች ተማሪዎችን በማፈላለግ የመለየት ስራ ተሰርቷል ።
የወልድያ ከተማ ነዋሪዎችም በሆስፒታሉ በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን ተማሪዎች በመጠየቅና በማፅናናት፡ ህይወታቸው ያለፉ ተማሪዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሸኘትና በግቢው ውስጥ ያሉ ተማሪዎችንም እያረጋጉ ይገኛል።
ጥቅምት 30 ቀን 2012 ጧት ላይ ቅሬታ የነበራቸው ተማሪዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ከዞኑ፡ ከከተማ አስተዳደሩና ከዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ የፀጥታ ሀይል እንዲገባ በጠየቁት መሠረትም የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ ገብተዋል። ከትናንት ወዲያ ከተፈጠረው ክስተት ውጭ ትናንት ቀንም ሆነ ለሊት የተፈጠረ አንዳችም የፀጥታ ችግር አልተከሰተም።
በአሁኑ ሰዓት የግቢው የፀጥታ ሁኔታም እየተረጋጋ ይገኛል። አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው የነበረውን መረጃ በማሰባሰብ በትላንትናው እለት ከሰዓት በፊት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢና በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር በኩል ለተለያዩ ሚዲያዎች መረጃዎችን በስልክ የማሳወቅ ስራም እየተሰራ ነው። በቀጣይም ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የምናሳውቅ ይሆናል….”
ይኸ ክስተት ከተሰማ በኋላ በዋንኛነት ማህበራዊ ሚዲያ በመቀጠል መደበኛ መገናኛ ብዙሃን ሥራ ላይ የተሠማሩ አንዳንድ ወገኖች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግጭቶችን የብሔር መልክ እያስያዙ የመዘገባቸው ነገር፣ ሐሰተኛ ፎቶግራፍ እና ቪዲዮ ማሰራጨታቸው ታዝበናል። አንዳንድ ሚዲያዎች ለሞቱትና ለቆሰሉት ወገኖች ከማዘን ይልቅ “የእገሌ ብሔር ተጠቃ” በሚል በስም ጠቅሶ የመዘገብ የሙያ ሥነምግባር አንጻር ጥሰቶች ታይተዋል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲም ይኼን በተመለከተ ያለው ነገር አለ። “… በተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ መንገዶች ስለ ዩኒቨርሲቲው እየተለቀቁ ያሉት መረጃዎች ከላይ ከተገለፁት በተቃራኒው መሆኑን ስንገነዘብ አንዳንድ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ግለሰቦች ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ የአደባባይ ሚሥጥር ነው። በዩኒቨርሲቲው ያልተፈጠሩ የሀሰት ምስሎችንና ቁጥሮችን በማሰራጨት ለተጠመዳችሁ ሁሉ ልቦና ይስጣችሁ። ለማንኛውም ለተማሪዎቻችን፣ ለተማሪ ወላጆች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ የተፈጠረው ሁኔታና መረጃ ይሄው ነው “ብሏል።
በቀውስ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምንድነው?
ባለፈው ሰኞ ጠዋት በኢትዮ ኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያ ከማከብራቸው ጓደኞቼ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ ጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ ጋር በወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ጋር ተያይዞ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን እንደሆነ ወይንም ሊሆን እንደሚገባ ተወያይተናል። የመገናኛ ብዙሀን ዋንኛ ሚና በአጭሩ ትክክለኛ መረጃ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ ነው። በዚህ ረገድ ገዘፍ ያሉ ጉድለቶች ስለመኖራቸው በመድረኩ ላይ ሰፊ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል። አንዳንዶቹን እዚህ ላይ ላንሳ።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ
በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ እና በመደበኛው ሚዲያ መካከል መደበላለቅ መኖሩ በገሀድ እየታየ ነው። መደበኛ ሚዲያው በንቃት አጀንዳ ቀርጾ በችግሮች ላይ የመፍትሔ ሀሳብ ከማመንጨት ይልቅ የማህበራዊ ሚዲያ አጀንዳ አራጋቢ ወደመሆን መሸጋገሩ ትልቅ ችግር ሆኗል።
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ተማሪዎች በግጭት ስለመሞታቸው ሲነገር ሚዲያው ተንደርድሮ ወደዘር ቆጠራ የገባበት ሁኔታ ታይቷል። “የእንቶኔ ብሔር ተጠቃ” የሚል ዘገባ በመስራት ግጭት ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ የታዩም አሉ። ይኼ ዓይነት ኢ-ሥነምግባራዊ ሁኔታ ትላንት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ባጋጠመ ግጭት ብቻ ሳይሆን በጥቅምት 12 ቀን 2012 በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት ላይም በተመሳሳይ መልኩ ተንጸባርቋል። “የእገሌ ብሔር ተጠቃ፣ ታረደ፣ ተጎተተ፣ ተሰቀለ…”ከሚለው ሰቅጣጭ ዜና ባሻገር በሀይማኖትም ቢሆን የእንቶኔ እምነት/ሀይማኖት ተከታዮች ተለይተው እንደተጨፈጨፉ በተደጋጋሚ የሚዘገብበት ሁኔታ ጥቂት አለመሆኑ ያስደነግጣል።
በዚህም ምክንያት ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሰሞኑን መግለጫ ሲሰጡ በፖሊስ የተረጋገጠ የሟቾች ቁጥር ብቻ ሳይሆን ብሔር እና እምነት ዘርዝረው ለመናገር ሁኔታው አስገድዷቸዋል።
አደገኛ የቃላት አጠቃቀም በተመለከተ፣
የቃላት አጠቃቀምን በሚመለከት አንድ ወጥ አረዳድ የለም። ወይንም መገናኛ ብዙሀን ይህን ቢጠቀሙ ጥሩ ነው ተብሎ በጥናት የተለየ ነገር ስለመኖሩ በግሌ አላውቅም። ቢያንስ ግን መገናኛ ብዙሀን ግጭትን በሚዘግቡበት ወቅት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ለአብነት ያህል የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ ይሰራበት የነበረ አንድ ጋዜጣ ላይ መሰል ግጭቶች ሲነሱ ወይንም መሰል የሀይማኖት አለመግባባቶች ሲከሰቱ “እገሌ እነ እገሌን አጠቃ፣ ገደለ፣ ወይንም ጉዳት አደረሰ” ተብሎ መዘገብ በኢዲቶሪያል ፖሊሲ ደረጃ ከልክሏል። በመሆኑም ችግሩ ሲከሰት ሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ እንጂ የብሔር ዝርዝር ውስጥ ስለማይገባ እንደአቅም ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ተጠቃሹ ሚዲያ በጎ ነገር እንዳደረገ በግሌ ይሰማኛል።
ይኽም ሆኖ አንዳንድ ሰዎች “በመገናኛ ብዙሀን የሰሙትን፣ ያዩትን እውነት ምንም ሳያስቀሩ ለሕብረሰተቡ ማቅረብ እንጂ እውነቱን መቀነስ አይገባቸውም፣ ይኽን ማድረግ የእነሱ ኃላፊነትም አይደለም” በሚል ሙግት ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ መገናኛ ብዙሀን ግጭትን በማቀጣጠል ረገድ ሚናቸው ዝቅ እንዲል የተሻለ የአሠራር መንገድ መከተላቸው ተገቢነቱ ስለማያከራርክር በዚሁ ማየቱ የሚገባ ይሆናል።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሀንን ወደዃላ መለስ ብለን ስናይ ብዙ ክፍተት እናገኛለን። በቅርብ የታዩ ግጭቶችን በሚመለከት የሰዎች ግድያ አፈጻጸምን እንደፊልም የሚተርኩ መገናኛ ብዙሃን ነበሩ። በማህበራዊ ድረገጾች ዘግናኝ ፎቶግራፎች እና ፊልሞች በብዛት ይለቀቁ ነበር። ችግሩ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው ለማለት የሚሄዱበት ርቀት በራሱ አስፈሪ ሆኖ ከርሟል።
ወገንተኝነት ማንጸባረቅ፣
መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊ ዘገባ እንዲያሰራጩ የሙያው ሥነምግባር ያስገድዳቸዋል። በተግባር ግን እየሆነ ያለው በተቃራኒው ነው። በብሔር ወይንም በሀይማኖት “የእኔ ወገን ነው” የሚሉትን ወግነው ሌሎች ጥቃት እንዳደረሱ ሲለፍፉ የሚውሉ፣ በሌላው ወገን ሞት የሚሳለቁ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች አሉ። በጋዜጠኝነት ሥነምግባር ደግሞ ወገንተኝነት በፍጹም የሚፈቀድ አይደለም። ሚዲያ ካለበት ከባድ ኃላፊነት አንጻርም ወገንተኛ መሆን የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ መሆኑን ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሀን ኃላፊዎች ሊዘነጉት አይገባም።
የፖለቲካው መታመም፣
ፖለቲካችን ታሟል። መገናኛ ብዙሃን ፈልገውም ይሁን ሳይፈልጉ የዚህ ሕመም ሰለባ ሆነዋል። የፖለቲካው መዋቅር ተከትሎ ባለፉት ዓመታት ብሔር ተኮር መገናኛ ብዙሃን ተቋቁመዋል። ክልሎችም የራሳቸው ልሳናትን ፈጥረዋል። እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ትኩረታቸው የራስን ብሔር ማጀገንና የሌላውን ማንኳሰስ ላይ ያነጣጠረ ነው። ትንሽ ችግር በተፈጠረ ቁጥር እያጋነኑ ትንታኔ በመስጠት ሕዝብን እርስ በእርስ እንዲጠፋፋ፣ እርስ በርስ መጠራጠር ውስጥ እንዲገባ እየሰበኩት ነው። ምንም እንኳን ይህ የብሔር ተኮር ፖለቲካው የዓመታት ፍሬ ውጤት ቢሆንም በአሁን ሰዓት እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች ዘላቂ እልባት እንዳያገኙ መገናኛ ብዙሀኑ የራሳቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ግን የማይካድ ሆኗል።
በጠቅላላው
መገናኛ ብዙሃን ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ በቂ መረጃ ሊያገኙ ይገባል። ከብሔርና ሀይማኖት ውግንና ሊጸዱ የግድ ነው። ጋዜጠኞች የሙያ ሥነምግባርን አክብረው እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ የሚዲያ ባለቤቶች (መንግሥትና የግሉ ዘርፍ) የድርሻቸው ሚና ሊወጡ ይገባል።
መንግሥትም በእጁ የሚገኙ መረጃዎችን በፍጥነት ለመገናኛ ብዙሀን የሚያቀርብበት አግባብ ይፈትሽ። የተለያዩ ድጋፎችን ያድርግ። ለአብነት ያህል ከፍተኛ የንግድ ማስታወቂያ ያለው በመንግስት እጅ በመሆኑ ለመገናኛ ብዙሃን ፍትሐዊ የማስታወቂያ ስርጭት እንዲኖር ማድረግ አለበት። የዚህ ዓይነቱ ድጋፍ መገኘት መገናኛ ብዙሀን የፋይናንስ አቅማቸው ጠንክሮ በገበያ ላይ ጥሩ የሚባሉ ባለሙያዎችን ለመቅጠር፣ ለባለሙያዎቻቸው የተሻለ የክፍያና የማበረታቻ ሥርዓት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይኸ ማለት በአቅም የጠነከሩ ተወዳዳሪ ሚዲያዎችን ለማፍራት ያስችላል። በተጨማሪም በሥልጠና እና በአቅም ግንባታ ረገድ የግል እና የመንግሥት የሚሉ ክፍፍሎችን ወደጎን ትቶ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን ድጋፍ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል።
አንዳንድ ወገኖች ሰሞኑን በሚኒስትሮች ምክርቤት ጸድቆ ወደፓርላማ የተመራው የጥላቻና የሀሰተኛ መረጃ መቆጣጠሪያ አዋጅ እና የመገናኛ ብዙሀን አዋጅ በቅርብ ጸድቆ ሲወጣ የተሻለ ቁጥጥር በማድረግ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያምናሉ። በዚህ ጹሑፍ አቅራቢ እምነት ግን ቁጥጥርን በማጥበቅ ብቻ የመገናኛ ብዙሀን የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል የሚል እምነት የለውም። ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ቢሆንም በቅድሚያ ግን ብሔር ተኮር ፖለቲካው በመገናኛ ብዙሀን ላይ ያሳረፈው ግልጽና ግልጽ ያልሆነ ተጽእኖ መፈተሽና ተገቢውን ማስተካከያ ማድረግ ይቀድማል። የታመመውን ፖለቲካውን በአግባቡ ማከም ይገባል። አንዳንድ ብሔር ተኮር መገናኛ ብዙሀን አስፈላጊነት በድጋሚ ማየትና ማጥናትም ይገባል። ምን ጥቅም ሰጡ፣ ምን ጉዳት አስከተሉ የሚለውን በጥናት መመለሱ ወደፊት ለመራመድ ወሳኝ ይሆናል።
አምና ብቻ በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የተከሰቱ ግጭቶች ጋር ተያይዞ አምስት ተማሪዎች ለሞት መዳረጋቸው ተሰምቷል። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በቅርብ የተካሄደው የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና የቦርድ ሰብሳቢዎች በዩኒቨርሲቲዎች በሚስተዋሉ ግጭቶች ላይ ተወያይተውም ነበር።
በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚነሱ ግለሰባዊ ግጭቶች የብሄር መልክ እየያዙ የመማር ማስተማር ሂደቱን እያስተጓጎሉ በመሆኑ ለነዚህ ችግሮች እልባት ለመስጠት እንዲያስችል የተዘጋጀ ውይይት ነው ተብሏል።
በውይይቱ ላይ “በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዴት መፍጠር ይቻላል?” የሚል ጥናታዊ ሪፖርት ቀርቧል።
በዩኒቨርሲቲዎች የተሟላ የአመራር ምደባ አለማድረግና በምክትል ወይም በተወካይ ፕሬዝዳንት የሚመሩ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥራቸው ቀላል አለመሆኑ ስራውን በተሟላ መልኩ ለማካሄድ አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል።
የቦርድ አመራር አባላትን የሙያ ስብጥር አለመጠበቅ፣ በቅንጅት የመምራት ችግር፣ የዩኒቨርሲቲ አመራር አካላት በየዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ቅቡልነት ማጣት እና የመምህራንና የመሰረተ ልማት አለመሟላት በችግርነት ተነስተዋል።
የተማሪዎችን ውጤት የግዜ መርሃ-ግብሩን ጠብቆ ያለመለጠፍና መሰል ችግሮች ሲነሱ የዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራሮች አፋጣኝ ምላሽ ያለመስጠት በጥናቱ ከተዳሰሱ ችግሮች መካከል ነው።
በዚህ ዓመት በዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ የአምስት ተማሪዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም መኖራቸው ተገልጿል።
እናም ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲዎቻችን የመማር ማስተማሩ ሒደት የተሳካ እንዲሆን ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። በተለይ የመገናኛ ብዙሀን (ማህበራዊ ድረገጾችን ጨምሮ) ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀሱ ግድ ነው። በተቻለ መጠን ግጭት አባባሽ የሆኑ ዜናና ዘገባዎች ከማሰራጨት በመቆጠብ ሠላምና መረጋጋት በመላ ሀገሪቱ እንዲሰፍን የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅም3/2012