በሀገራችን ኢትዮጵያ የብሄሮች መብት በከፋ ጭቆና ስር ማለፉ እርግጥ ነው። ይህንን ጨምሮ የኢኮኖሚና የሰብዓዊ መብት ጭቆናውን ለማስወገድ መላ ኢትዮጵያውያን ውድ የሆነ የአካልና የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ፌዴራላዊ ስርዓት ተመስርቶና ሥርዓቱም ህገመንግስታዊ ዋስትና አግኝቶ መተግበር ከጀመረም 28 ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሁንና በስመ ፌዴራሊዝም ሰፍኖ የቆየው አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትና ኢፍትሃዊነት እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ሲናፍቁ በነበሩ ህዝቦች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ አገራችንን ለከፍተኛ ችግር ዳርጓት እንደነበር አይረሳም።
ፌዴራሊዝሙ ወጣ ገባ በሆነና አቦ ሰጥ በሚመስል መልኩ ለመተግበሩ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ችግሮች አሉ። ከዚህም አንዱ የሲዳማ ህዝቦች የክልልነት ጥያቄ ሲሆን ይህ መብት ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት ታፍኖ የኖረም ነበር።
የሲዳማ ህዝቦች በተለያየ ጊዜ ይህን ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም ምላሹ መፈረጅና በተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶች አደባብሶ ማለፍ ነበር። ይሁንና ይህን ውዝፍ የቤት ሥራ የለውጥ አመራሩ ከመጣ ወዲህ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ ምላሽ እንዲሰጠው በማድረጉ በአሁኑ ወቅት በትግበራ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ፌዴራሊዝሙ ከስም በዘለለ እውን ሆኖ መሬት ባለመውረዱም ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት እንደተነፈጉ፣ ለህዝባቸውን ጥያቄ በነጻነት ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉ፣ ማጎብደድን እንደመስፈርት በመውሰድ መሪያቸውን ይመርጥላቸው የነበረው ሌላ አካል እንደነበርም በተለያዩ ጊዜያት ለጋዜጣችን ሀሳብ የሰጡ የቀድሞ የኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ ክልል አመራሮች ደጋግመው የገለጹት ሀቅ ነው።
ለዘረፋ አመቺ የሆነ ሥርዓት በመዘርጋትም የክልሎች ሀብት በጥገኞች እንዲዘረፍ ሲደረግ ይህን የተቃወሙ አመራሮች የተለያየ ታፔላ እየተለጠፈባቸው ወደ ወህኒ ሲወረወሩ እንደነበርም እነዚሁ አመራሮች በምሬት አውስተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በወርቅ፣ በጨው፣ በመሬትና በደን ላይ ከፍተኛ ብዝበዛ መፈጸሙ ተደጋግሞ የተነገረ ሀቅ ነው። ለአብነት ከላይ የተጠቃቀሱት እነዚህ ተግባራት እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ እንዳልነበር አመላካች ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ኢፍትሃዊ ድርጊቶች ሀዝብን ለቁጣ በመቀስቀሳቸው ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች በመላ ሀገሪቱ ተካሂደው የለውጥ አመራር በኢትዮጵያ እውን ሆኗል። የበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ሸክምን የተቀበለው የለውጥ አመራርም አገር የማስተዳደር ኃላፊነቱን ከተረከበ ማግስት አንስቶ እነዚህኑ የተከማቹ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።
ከርብርቡም ዋነኛው ፍትሃዊነት የተረጋገጠበት እውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓትን እውን ማድረግ ሲሆን በዚህም ክልሎች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የሚወስኑበት ከጣልቃ ገብነት የጸዳ አካሄድ ተግባራዊ ተደርጓል። ስለሆነም አሁን ለክልሎች ስኬትም ሆነ ውድቀት በሌላ ክልል ወይም ፓርቲ ላይ ጣት መቀሰር የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል።
የብሄር ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የመዳኘትና የመማር እንዲሁም ባህላቸውን የማበልጸግ መብት ሳይሸራረፍም አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር እውነተኛ ፌዴራሊዝም እውን ለማድረግም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የውህደት ጉዞ ላይ መሆኑም እጅግ ተስፋ ሰጪና እስካሁን ድረስ ምነው ባልዘገየ የሚያስብል ነው።
ምንም እንኳን አንዳንዶች መደመር እና መዋሃድን ከመጨፍለቅ ጋር አያይዘው የአዞ እንባ ቢያነቡም ከአጋር ድርጅቶችም ሆነ ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በሚሰጡ መግለጫዎች የኢህአዴግ ውህደት ለእውነተኛ ፌዴራሊዝም መሰረት መሆኑ እየተገለጸ ነው። ይህም ከዚህ ጉዳይ ለመቆመር የተዘጋጁ ኃይሎችን አንገት ሲያስደፋ እውነታውን ለተረዱ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እፎይታን ለግሷል።
የኢህአዴግ መዋሃድ ፌዴራሊዝምን ይደፍቃል ብሎም ጨፍላቂነትን ያሰፍናል የሚለው ትርክት ብዙ መንገድ የማያስጉዝ መሆኑን የደቡብ ህዝቦችን፣ የትግራይ እና የቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ በመመልከት መረዳት ይቻላል። በእነዚህ ክልሎች በርካታ ብሄረሰቦች ኖረው በአንድ ፓርቲ ይመሩ የነበረ ቢሆንም ማንነታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ከመከበር ያገደው ነገር አልነበረም።
ስለሆነም ዛሬ ኢህአዴግ ስለተዋሃደ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ የሚደርስ አደጋ ፈጽሞ ሊኖር እንደማይችል በዚህ ማረጋገጥ ይቻላል። ይልቁኑ ልዩነት ላይ አተኩሮ ይሰራበት የነበረውን የፌዴራሊዝም ስርዓት አንድነትን ወደሚያመጣና ሁሉንም ተጠቃሚ ወደሚያደርግ የፌዴራል ስርዓት ለማምጣት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው ዛሬ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚበጀው በ103 ፓርቲ ተከፋፍሎ በእንቶ ፈንቶ እና የብሽሽቅ ፖለቲካ ህዝብን ግራ ማጋባት ሳይሆን በተቀራራቢ የፓርቲ ዓላማዎች ዙሪያ ሰብሰብ ማለትና በምርጥ አማራጮች ለሀዝብና ለወገን የሚበጅ ፕሮግራም ቀርጾ መንቀሳቀሱ ነው።
ያን ጊዜ ብዙ ሀብት ሳይባክንና ህዝብም ግራ ሳይጋባና ድምጽ ሳይከፋፈል በአብላጫ ድምጽ ሀዝብ የሚወስንበትን ስርዓት እውን ለማድረግ ያግዛል። ከዚህ አንጻር ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እየሄደበት ያለው የውህደት ጉዞ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥሩ ተሞክሮ ከመሆኑም በላይ ልዩነትን ያከበረ አውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓትን ለመገንባት ወሳኝ ነውና ውህደቱ ሊፋጠን ይገባል!
አዲስ ዘመን ህዳር 2/2012