በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በተለይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚከተሉ አገራት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖር አዲስ አይደለም። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ይነሳሉ።
ከእነዚህ ውስጥ በአንድ በኩል የሰው ልጅ ፍላጎት እያደገ መሄድ የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት ባለማስቻሉ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች በመንግሥት ላይ በሚኖራቸው ቅሬታ የተነሳ የተለየ አማራጭ ይዞ ለመቅረብና የመንግሥነት ስልጣንን ለመቆጣጠር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ራሳቸው እንደ አንድ የሥራ መስክ እየታዩ መምጣታቸው ነው።
የፖለቲካ ድርጅቶች ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ካልቻሉ ግን ፋይዳቸው አጠያያቂ ነው። በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ኖረው ለህዝቡ የሚጠቅም ሥራ ካልሠሩና በአንጻሩ የሁከትና የብጥብጥ መንስኤ ከሆኑ ኪሳራ እንጂ ትርፍ ሊኖራቸው አይችልም። የፖለቲካ ድርጅቶቹ የተመሰረቱበት በቂ ምክንያት ኖሯቸው በመንግሥት ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን ወይም ችግሮችን ለማረም የሚያስችል የፖለቲካ ቁመና እስከሌላቸው ድረስ መኖራቸው ብቻውን ፋይዳ አይኖረውም።
በመሆኑም ለህዝብ የሚሠራ ፓርቲ ለህዝቦች ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር በጎ ፋይዳ ያለው ሊሆን ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በቅድሚያ የተነሳበትን ዓላማ አውቆና ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ለይቶ መሥራት አለበት። ከዚህ ጋር ተያይዞም ዓላማውን በግልፅ የሚያሳይ ፕሮግራምና ርዕዮተ ዓለም ይዞ ከሌላው ጋር ያለውን ልዩነት በግልጽ በማሳየት ለህዝብ ማቅረብ ይኖርበታል። ከዚህ ውጭ ግን ዕድሉ ስለተገኘ ብቻ ሁሉም እየተነሳ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ያለችውን ውስን የህዝብ ሀብት ከመቀራመት የዘለለ ፋይዳ የለውም።
በሌላ በኩል ሁሉም ያገኘውን ዕድል እየተጠቀመ በአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ከማድረግ ተቆጥቦ ቢያንስ ለሰላም የጋራ መግባባት ይዞ መሥራት ከእያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ይጠበቃል። ይህ ደግሞ ከሞራልም ሆነ ከሕግ አንፃር ከእያንዳንዱ ድርጅት የሚጠበቅ ግዴታ ነው።
በአገራችን ነባራዊ ሁኔታም የፖለቲካ ፓርቲዎች ግሽበት ይታያል። ለአንድ ብሔር እንታገላለን ከሚሉ ፓርቲዎች ጀምሮ ሀገራዊ አንድነትን እስከሚያቀነቅኑ ፓርቲዎች ድረስ በተለያየ ጎራ ተሰልፈው አንዱ ሌላውን ሲወነጅል ማየት አዲስ አይደለም። ይህ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ላይ ስጋት መፍጠሩ አልቀረም።
በተለይ ቀጣዩ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፓርቲዎቹ በዚህ ደረጃ አራምባና ቆቦ ሆኖ መነታረክ ትልቅ ፈተና እንደሚሆን የብዙዎች ስጋት ነው።
ይህንን ተከትሎ በአንዳንድ ክልሎች የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ለቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቅ ከወዲሁ ተስፋን ያጫረ ነው። ከዚህ አንፃር በኦሮሚያ፣ በአማራ፣በሶማሌና በአፋር የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ከስምምነት መድረሳቸው ለሰላም ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ይታመናል። ፓርቲዎቹ በሂደትም ለጋራ የህዝብ ጥቅም በጋራ የሚሠሩበትን መንፈስ ለመፍጠርና ለአንድ ዓላማ ተሰልፈው የሚሠሩበትን የሃሳብ አንድነት ለመገንባት ጠቃሚ በመሆኑ ጅምሩ የሚበረታታ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ሰላምና ብልፅግናን ነው። ህዝባችንን ለዘመናት ወደኋላ ካስቀረውና በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር መዘባበቻ ካደረገው ድህነትና ኋላቀርነት ተላቆ እንደበለፀጉት አገራት የተሻለ ኑሮ መኖርን ይመኛል። ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ ሰላምን የሚያረጋጥለት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚያስተዳድረው፤ ለዚህም የተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ የሚሠራለት መሪ ድርጅትና አመራር ይፈልጋል። ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ ፓርቲዎች ተቀራርበው ሲሠሩ ነው።
በመሆኑም አሁን ያሉት የፖለቲካ ፓቲዎችም ሆኑ መሪዎቻቸው ደጋግመው ሊያስቡና ከፓርቲ ህልውና ይልቅ የሃገር ህልውናና ዕድገት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ሊረዱ ይገባል። ከሚመሩት ፓርቲ ይልቅ የሀገር ህልውና እንደሚበልጥም ሊገነዘቡ ይገባል።
የፓርቲ ቁጥር ሲያንስ ወይም ጥምረት ሲፈጠር የመሪነት ሚናዬን አጣለሁ ከሚል መንፈስም ወጥተው መሪም ሳይሆኑ ለአገራቸው ጠቃሚ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ሊገነዘቡ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ፓርቲዎቻችን ከልዩነት ይልቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲሆን ህዝቡም የሚበጀውን ለመለየት አይቸገርም፤ የአገር ሀብትም አይባክንም፤ የምንፈልገው ዕድገትም ይከተላል።
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2012