አንድ ከፈጣሪ የተላኩ አባት ናቸው አሉ። ወደ ህዝብ ወርደው ህዝብ ሊደረግለት፣ ሊሟላለት የሚፈልገውን ነገር አንድ በአንድ ለማወቅ ፈለጉና እንዲህ ሲሉ አንድ ጥያቄ አቀረቡ። “በዚህ ምድር ላይ ስትኖሩ ምን እንዲሟላላችሁ ትፈልጋላችሁ?” ከተጠየቁት አንዱ እጅግ ሀብታም ሰው ናቸው። ነገር ግን ልጅ የላቸውምና “እኔ ፈጣሪ ልጆች ወንድ ከሴት አቀላቅሎ እንዲሰጠኝ እሻለሁ” አሉ።
ጠያቂው ወደሌላኛው ቀጠሉ ይሄኛው ደግሞ “ሀብት እፈልጋለሁ፤ የተደረደረ ፎቅ፣ ዘመናዊ መኪና እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። ቤተሰቤን በጥሩ ሁኔታ እንዳስተዳድር፤ ልጆቼን በመረጡበት ትምህርት ቤት እንዳስተምር” እያለ ፍላጎቱን ሁሉ ዘረዘረ። አደመጡት። ቀጠሉ ወደ ሦስተኛው ሰው እሱ ደግሞ የሚፈልገው ስልጣን ነበር። “ሀገር ማስተዳደር ፣ ከላይ ሆኖ ማዘዝ ፣ የህዝብ ቁንጮ” የመሆን ፍላጎት እንዳለው ተናገረ። ከአንገታቸው ጎንበስ ብለው አደመጡት።
እስኪ የሴቶቹ ፍላጎት ደግሞ ይሰማ ብለው ሴቶች ወዳሉበት ቦታ አመሩና መጀመሪያ ላገኟት ሴት ለወንዶቹ ያቀረቡትን ጥያቄ አቀረቡላት። እሷም አንገቷን ዘንበል ድምጿን ለስለስ አድርጋ እንዲህ ስትል ጠየቀች። “ እውነት ፈጣሪ እኔ የምፈልገውን ሁሉ ያሟላልኛል”አለች።” አትጠራጠሪ “ሲሉ መለሱ። ቀጠለች “እንግዲያውስ ይሄ የነገሩኝ የሰዎች ፍላጎት ሁሉ ፎቁ፣ መኪናው፣ ትምህርቱ…የሚሳካው ሀገር ሰላም ሲሆን ነው። ስለዚህ እኔ የምፈልገው ሁሉም ሰው የምኞቱን መሆን እንዲችል የሀገር ሰላም ነው።
የህዝብ ፍቅር ደግሞም አንድ ሆኖ መተሳሰብን ነው “ ብላ ያልጠበቁትን ተናገረች። “ፈጣሪንም የምጠይቀው በሀገራችን ሰላም እንዲያሰፍን ነው። ሰላም ካለ ሁሉም ሰው የሚፈልገው ደረጃ ይደርሳል፤ ሰላም ከጠፋ ደግሞ የያዝነውንም ያጣል።” ስትል ፍላጎቷን ተናገረች። እርሳቸውም ራሳቸውን እየነቀነቁ ሃሳቧ ትክክል መሆኑን ገለጹ። በምድር ላይ ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር ከንቱ መሆኑን ለሁሉም አስረድተው ተለዩ ይባላል።
ይሄ ምሳሌያዊ አነጋገር ዛሬ የሚያስፈልገን ለእኛ ነው። መሆን የምንፈልገውን ፣ልናገኘው የምንሻውን መፈለግና ማለም ብቻውን በቂ አይደለም። የምንፈልገውን ለማግኘት አስቀድመን መሥራት ያለብንን መሥራት አለብን። የመጀመሪያው ሥራ መሆን ያለበት ደግሞ ሰላምን መሻትና ማረጋገጥ ነው። የሰላም ጉዳይ ከምንም በፊት ቀዳሚ ነውና።
ትናንት የነብዩ መሀመድ 1494ኛው የመውሊድ በዓል በመላ ሀገሪቱ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ያከበሩት በሃይማኖታዊ ስነስርዓት ነው። ከወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ጎረቤትና ጓደኞቻቸው፣ ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር ተጠራርተው በመገባበዝ ነው። ይሄ በሀገራችን በየትኛውም እምነት ተከታዮች ዘንድ የነበረውን አብሮነት በሚያጠናክር ወደፊትም በሃይማኖት የማንለያይ የአንድ ሀገር ውህድ ዜጎች መሆናችንን የሚያሳይና የሚያረጋግጥ ነው።
የመውሊድ በዓል ሲከበር ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ያከበረው በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ካጋጠማት ወቅታዊ ችግር እንድትወጣ በመመኘት ፣ በፍቅርና በአንድነት ነው። ስለ ሰላም በመጸለይ ጭምር ነው። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። በየትኛውም ቦታ እና ሁኔታ የሃይማኖት አባቶች ለምዕመናኖቻቸው ማስተማር ያለባቸው ስለ ሰላም ነው። ሰላም ከሌለ ሃይማኖትዊ በዓላትን ቀን ቆጥሮ ማክበር አይቻልም። ለበዓል ተጠራርቶና በእምነት ስፍራዎች ላይ በጋራ ተገናኝቶ በደስታ ማክበርና ማሳለፍም አይቻልም።
ዛሬ በሀገራችን አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ ምክንያት ህዝበ ሙስሊሙ በተለያየ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሃይማኖታዊ ስርዓት በሚካሄዱባቸው ቦታዎች ላይ ተገኝቶ በዓሉን በህብረት ማክበር ችሏል። ለዛሬ ዓመትም በደህና ያድርሰን ብሎ ተመራርቆ ተለያይቷል። ይኸ የሆነው ሀገር ሰላም ስለሆነ ነው። ሰላም ባይኖር እንኳን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ማምለክ እና ማከበር ቀርቶ በቤት ውስጥም በጥሞና ዱአ ማድረስ እንደማይቻል የተረጋገጠ ነው። ስለዚህ ሰላም ለሁሉም ነገር ወሳኝ እና መሰረት ነው። ያለምንም መጠራጠር ሰላም ከሁሉም ነገርም ይቀድማል።
የመውሊድን በዓል ስለአገር በመጸለይና ሁሉም ለሰላም እንዲሠራ በማሳሰብ መከበሩ ተገቢ እና አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ ምክንያቶችን በመጠቀም ግጭት የማጫር ተግባራት ይታያሉና። ህዝብ ቅሬታውን ለመግለጽ የሚወጣባቸውን ሰልፎች በመጠቀም የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ሲሞከርም ደጋግመን አስተውለናል። ይሁንና ህዝባችን የተሳሰረበት የፍቅር ገመድ ለጥፋት ከተሸረቡት ሴራዎች ይልቅ እጅግ የጠነከረ ነበርና የጥፋት ኃይሎቹ በዜጎቻችን መካከል ሊፈጥሩ ያሰቡት እልቂት አልተሳካም። ይሁንና ሙከራው አልተሳካም ተብሎ መዘናጋት ደግሞ የከፋ አደጋ አለውና የሃይማኖት አባቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሰላምን ሊሰብኩ፣ ለሰላም ሊተጉና ስለሰላም ሊኖሩ ግድ ይላል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የሀገሪቱ የሰላምና የአንድነት ጉዳይ አሳሳቢ ነውና የሃይማኖት አባቶች ተግተው ማስተማርና መጸለይ ይጠበቅባቸዋል። ምዕመናኑም የእምነት አባቶቹን አስተምህሮ በመቀበል ስለሰላም መሥራትና መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድነት ከሌለ ሰላም፤ ሰላም ከሌለ ልማት አይኖርምና!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2012