ብዙ የዓለም አገሮችን ጥበብ፣ ባህል፣ ታሪክ እና ቅርስ ስናይ መነሻቸው ሃይማኖት ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ እንደሚሉት እንኳን ጥበብ እና ባህል ሳይንስ ራሱ መነሻው ሃይማኖት ነው። ለምሳሌ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የተገኘው ከሃይማኖታዊ ቅርጾች ነው። የዘመን አቆጣጠርና ሌሎች ቀመራዊ ነገሮች መነሻቸው ሃይማኖት ነው።
ወደ አገራችን ኢትዮጵያም ስንመጣ ይሄው ነው። ብዙ የባህል፣ የኪነ ጥበብ፣ የታሪክ እና ቅርስ ሀብቶቻችን መነሻቸው ሃይማኖት ነው። እነዚህ ቅርሶቻችን ዛሬ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆነዋል።
ዛሬ የነቢዩ መሐመድ ልደት (መውሊድ ነው)። በቅድሚያ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በልካም በዓል እንበል። ለመሆኑ በእስልምና እምነት ውስጥ ምን ዓይነት የኪነ ጥበብ ሥራዎች አሉ? ዛሬ ላይ ሳይንሳዊ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት እንደ ትልቅ ጥበብ የሚታየው የኪነ ሕንፃ ጥበብ በእስልምና እምነት ውስጥ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። በእስልምና እና የኪነ ሕንፃ ጥበብ ላይ የተሠሩ የተለያዩ ጥናቶችንና ሰነዶችን ዋቢ አድርገን እንንገራችሁ። አፈንዲ ሙተቂ በ2007 ዓ.ም በጡመራ ገጹ ስለእስልምና እና የኪነ ሕንፃ ውበት ተከታዩን መረጃ አስፍሮ ነበር።
በ7ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የተጠነሰሰው እስላማዊ ኪነ ሕንፃ በአስራ አራት ክፍለ ዘመናት ውስጥ እያደገ ብዙ ፈርጆች ያሉት የጥበብ ዘይቤ ሊሆን በቅቷል። በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ አድናቆት የተቸራቸው ቋሚ ግንባታዎችንም አበርክቷል። በካይሮ ከተማ የሚገኘው የዓል አዝሃር መስጊድ፣ የደማስቆው ‹‹የበኑ ኡመያ›› መስጊድ፣ የኢስታንቡል ‹‹ሱሌይማኒያ›› መስጊድ፣ በኢስፋሓን የሚገኘው የኢማም አደባባይና መድረሳ፣ የህንዱ ታጅማሃል፣ ታላቂ የቁርጡባ መስጊድ፣ የግሪናዳ ከተማ መከላከያ ግንብ እና ልዩ ልዩ ግንባታዎች፤ የፌዝ ከተማ የመከላከያ ግንብና ጥንታዊው የቃራዊያን መስጊድ (ሞሮኮ)፣ ከጭቃ የተሠሩት የቲምቡክቱ መስጊዶች ወዘተ… ከተደናቂ እስላማዊ ግንባታዎች ጥቂቶች ናቸው።
እስላማዊ ኪነ ጥበብ ብዙ ፈርጆች እንዲኖሩት ያደረገው በባህሪው ‹‹ሆደ ሰፊ›› በመሆኑ ነው። ይህም ሲባል ከሙስሊሙ ዓለም የተገኙት የኪነ ሕንፃ ጠቢባን በየሀገራቸው የነበሩትን ጥንታዊ የንድፍ ዘይቤዎች ከእስልምና መርሆች ጋር በማጣጣም አዳዲስ የኪነ ሕንፃ ዘይቤዎችን ይፈጥሩ ነበር ለማለት ነው። ለምሳሌ በኢስታንቡል ከተማ የሚገኙት ታላላቅ መስጊዶች የተሠሩት የጥንቱን የቤዛንታይን ኪነ ሕንፃ ከዐረቢያና ከፋርስ ኪነ ሕንፃ ጋር በማዋሃድ በተፈጠረው የቱርክ ኪነ ሕንፃ ዘይቤ ነው። የቲምቡክቱ መስጊዶችም የማሊን ጥንታዊ የኪነ ሕንፃ ጥበብ መሰረት በማድረግ ነው የተሠሩት።
ጥንት ከተገነቡት እስላማዊ ቅርሶች መካከል ከፊሎቹ ጠፍተዋል። ግማሽ ያህሉ ግን ዛሬም ቋሚ ሆነው ታሪክን ይመሰክራሉ። በእስላማዊ ግንባታዎቻቸው በዓለም ዙሪያ ከተደነቁት ጥቂቶች የሚከተሉት ናቸው።
መካ፣ መዲና፣ እየሩሳሌም፣ ባግዳድ (ኢራቅ)፣ ሰመራ (ኢራቅ)፣ ቡኻራ (ኡዝቤኪስታን)፣ ሰመርቀንድ (ኡዝቤኪስታን)፣ ደማስቆ (ሶሪያ)፣፣ ኢስታንቡል (ቱርክ)፣ ሂራት (አፍጋኒስታን)፣ መዘር-ኢ-ሸሪፍ (አፍጋኒስታን)፣ ቁርጡባ (ስፔን)፣ ግሪናዳ (ስፔን)፣ ካይሮ (ግብጽ)፣ሰንዓ (የመን)፣ ዘቢድ (የመን)፣ ፌዝ (ሞሮኮ)፣ መራኪሽ (ሞሮኮ)፣ ቱኒስ (ቱኒዚያ)፣ ቲምቡክቱ (ማሊ)፣ ጄኔ (ማሊ)፣ ሀረር (ኢትዮጵያ)፣ ዛንዚባር (ታንዛኒያ)፣ ኒሻፑር (ኢራን)፣ ኢስፋሓን (ኢራን)፣ሺራዝ (ኢራን)፣ ቴህራን (ኢራን)፣ ጠብሪዝ (ኢራን)፣ ዴልሂ (ህንድ)፣አግራ (ህንድ) ይጠቀሳሉ።
እስላማዊ ኪነ ሕንፃ ሲጠቀስ በቀዳሚነት ከሚወሱት ጠቢባን መካከል አንዱ ከ1489 እስከ 1588 የኖረው ቱርካዊው ‹‹ሲናን›› ነው። ቱርኮች ይህንን ሰው ሲጠሩት ‹‹ኮጃ ሚማር ሲናን››፤ ማለትም ‹‹ታላቁ አርክቴክት ሲናን›› ይሉታል። ችሎታውን ሲገልጹም ‹‹እርሱን የመሰለ የኪነ ሕንፃ ጠቢብ አልተፈጠረም›› ነው የሚሉት። በእርግጥም በመቶ የሚቆጠሩ ‹‹እጹብ ድንቅ›› የተባሉ ሥራዎቹን ያየ ሰው በከፊልም ቢሆን የቱርኮችን አባባል መጋራቱ የማይቀር ነው።
ሲናን የተወለደው ‹‹አጊርናዝ›› በተባለች የቱርክ አነስተኛ ከተማ ነው። በልጅነቱ በአባቱ ስር የአናጺነትና ድንጋይ የማሳመር ጥበብን ተማረ። አንድ ቀን ግን ህይወቱን የቀየረ አጋጣሚ ተፈጠረ። በዚያ ቀን (በ1521) የኦቶማን ቱርክ ወታደራዊ ኦፊሰሮች ወደ ሲናን መንደር ሄደው ለውትድርና የሚቀጠሩ ወጣቶችን ይመዘግቡ ነበር። የሲናን ወታደራዊ አቋም የሚያመረቃ ሆኖ ስለተገኘ እርሱንም መዘገቡትና ወደ ቁስጥንጥንያ (የአሁኗ ኢስታንቡል) ወሰዱት። እዚያም ልዩ ልዩ ትምህርቶችን እንዲያጠና አደረጉት።
የሲናን የጥበብ ተሰጥዖ መታየት የጀመረው በ1530 ድልድዮችንና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ግንባታዎችን መሥራት ሲጀምር ነው። በ1539 ግን ከውትድርናው ዓለም ተሰናብቶ የሲቪል ግንባታዎችን ጀመረ። በቀጣዮቹ 40 ዓመታትም ቱርክን በዓለም ዙሪያ ያስጠሯትን የልዩ ልዩ ግንባታዎችን ንድፍ እየወጠነ በራሱ አመራር በማስገንባት ለአገልግሎት አበቃ።
ሲናን በህይወት ዘመኑ 79 መስጊዶችን፣ 34 ቤተ መንግሥቶችን፣ 33 የህዝብ የመታጠቢያ ገንዳዎችን (በተለምዶ ‹‹Turkish bath›› የሚባሉት)፣ 19 የመቃብር ስፍራዎችን፣ 55 ትምህርት ቤቶችን፣ 16 የድኾች መኖሪያ ማዕከላትን፣ 7 የከፍተኛ ደረጃ መድረሳዎችን፣ 12 ታላላቅ ምግብ ቤቶችን ሠርቷል። የፍሳሽ መውረጃዎች፣ ፋውንቴኖች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎችንም ገንብቷል። የሁሉንም ግንባታዎች ንድፍ (ዲዛይን) የሠራው ራሱ ሲሆን በመሃንዲስነት አስጀምሮ የሚጨርሰውም እርሱ ነበረ።
ከሲናን ግንባታዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የሱሌይማኒያ መስጊድ፣ የሻሕ ዛድ መስጊድ እና የሰሊም መስጊድ ናቸው (የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በኢስታንቡል ነው የሚገኙት፤ የሰሊም መስጊድ ግን በኢድሪን ከተማ ነው የተሠራው)። ሲናን የእኔ ምርጥ ሥራ ነው የሚለው የሻህ ዛድ መስጊድን ነው። የኪነ ሕንፃ ጠበብት በጣም የሚያደንቁት ግን የሱለይማኒያ መስጊድን ነው።
እንግዲህ ልብ በሉ የሲናን ጥበብ። አሁን ሳይንሳዊ ይዘት ላላቸው የኪነ ሕንፃ ትምህርቶች መሰረት ጥሏል ማለት ነው። ከመጀመሪያዎቹ ሳይንቲስቶች ይመደባል ማለት ነው። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የቅርጻቅርጽና ንድፍ ሙያው አድጎ እንዲህ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸውን ሥራዎች ለመሥራት በቃ ማለት ነው።
የእስልምና ሃይማኖት በስነ ጽሑፍ ውስጥ በርካታ ዓለም አቀፍ ሰዎችን አፍርቷል። ለምሳሌ የኢራን የስነ ጽሑፍ ሰዎች እነ ባባ ጣሂር እና ዑመር ካያም በዓለም የስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው የሚጠቀስ ነው። የአገራችን ገጣሚዎች እነ በረከት በላይነህም የነባባ ጣሂርን ግጥሞች ወደ አማርኛ ተርጉመው ለኢትዮጵያ አንባቢ አድርሰዋል። የነኢማም ሆሚኒ፣ኦማር ኻያም፣ ሩሚ እና ሳዒድና የግጥም ሥራዎች ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን ያተረፉ የስነ ጽሑፍ ፈርጥ ናቸው።
አንጋፋው ኢራናዊ ባለቅኔ ሊቀ ሊቃውንትና የሥነ ክዋክብት ተመራማሪው ኦማር ኻያም የስነ ጽሑፍ ሰው ብቻ ሳይሆን ሳይንቲስት ጭምር ነበር። እ.ኤ.አ በ1048 የተወለደው ኦማር ኻያም በዚህች ምድር ላይ ለሰባ አራት ዓመታት የኖረና በ1122 ያረፈ ነው። ይህ የጥንታዊት ፋርስ (ፐርሺያ) አንጋፋ ባለቅኔ የፃፋቸውን ግጥሞችና ቅኔዎች ሁሉ በፃፈበት ሥፍራ ነው ትቶ የሚሄደው። ኡመር ኻያም ባለቅኔ ብቻ ሳይሆን ሳይንቲስትና ሊቀ ሊቃውንት መሆኑን፤ አሜሪካዊው ተመራማሪና የዩኒቨርሲቲ ሌክቸረር ዶክተር ዋይኒ ደብሊው ዳየር ከፃፋቸው ሃያ የምርምር መፃሕፍት አንዱ በሆነው ‹‹wisdom of the ages sixty days to Enlightenment›› ላይ፤ ኦማር ኻያም የአስትሮኖሚ ሊቅ እንደነበር አስቀምጧል። ግጥሞቹ በውስጡ ያለውን የአስተሳሰብ ልህቀት ይገልጻሉ ሲል መስክሯል።
ጋዜጠኛ እና የታሪክ ፀሐፊው ጥበቡ በለጠ ስለእስልምና ቅርሶች የሚከተለውን አስፍሮ ነበር።
የእስልምና ተቋማት በራሳቸው ታሪካዊ ናቸው። ከብሔረሰቦቻችን መካከል የአርጐባውን፣ የሐረሪውን፣ የቤኒሻንጉሉን፣ የአፋሩን፣ የሱማሌውን እና የኦሮሞውን እስልምና እና እሱን ተከትሎ ያለውን ባህላዊ አተገባበር ማጥናቱና እንደ ቅርስ ማስፋፋቱ ትልቅ ፋይዳ አለው።
ወደ ሐረርና አካባቢዋ ስንሄድ የሐረሪዎችን እና የሐረር ኦሮሞዎችን የጋራ የሆነ እስላማዊ ቅርስ እናገኛለን። የአያሌ መስኪዶች ደብር የሆነችው ሐረር እስልምናን ከተቀበለች ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ሼህ አባድር እና ተከታዮቻቸው የሐረርን ምድር ከረገጡባት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ጊዜ አያሌ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ተፈጥረዋል። ለምሳሌ ‹‹አሹራ›› ተብሎ የሚታወቀው እስላማዊ በዓል በሐረር ውስጥ በተለየ መልኩ ይከበራል። ይህም ጅቦችን ገንፎ በማብላትና ከጅቦች ጋር ሠላማዊ ኑሮ ከመመስረት ጋር የተገናኘ ልዩ የአካባቢር ስርዓት አለው። ይሄ ኢትዮጵያዊ የሆነ የሙስሊሞች ባህላዊ ቅርስ ነው።
ወደ ወሎ ስንጓዝ ደግሞ መንዙማው ልብን ውክክ እያደረገ በሚንቆረቆረው የወለዬዎች ድምፅና ምርቃት ታጅቦ ይቀርባል። በሙዚቃው ዓለም ይሄ ሌላኛው መንፈሣዊ ስልት ነው። የወለዬዎች የሆነው ይህ ሙዚቃዊ ስልት ብዙ ሊባልለት የሚችል ነው። ዓለም አቀፋዊቷ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ይህንን የመንዙማ የሙዚቃ ስልት ወስዳ በአሁኑ ጊዜ ልዩ ልዩ ዘፈኖቿን ሠርታበታለች።
ከመንዙማው ባልተናነሰ የድሬ ሼህ ሁሴን ታሪክም አንዱ አካል ነው። ወደ ድሬ ሼህ ሁሴን ስንጓዝ ግጥምና ዜማ አውራጆች ከልዩ ልዩ ቦታዎች እየመጡ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እና ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚያከብሩበት ስርዓት በእስልምና ሃይማኖታችን ውስጥ የሚገኝ ቅርስ ነው።
ወደ ባሌ ስንጓዝም የሶፍ ዑመር ዋሻ አካባቢ የሚደረጉ ባህላዊ ድርጊቶች እና ክብረበዓሎች ሌላኛው ገፅታችን ናቸው። በዚህ ቦታ ላይም ሶፍ ዑመር የተባሉት የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ እና ቅዱስ የሚባሉ ሊቅ በስፍራው ይኖሩ ነበር። የእኚህን ሰው ገድል ለማድነቅ እና ፈጣሪያቸውን ለማመስገን በየዓመቱ አያሌ የሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮች ወደ ስፍራው በማምራት ይገናኛሉ። በጋራ ይጸልያሉ።
ከእነዚህ ሌላም በርካታ እስላማዊ ቅርሶች በሀገራችን ውስጥ አሉ። ሁሉንም መጠቃቀስ ባንችልም እነዚህ ይበቁናል። ግን ሳይጠቀስ የማያልፈው ደግሞ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ባህላዊ አለባበሳቸውም ቅርስ ነውና መጠናት እንዳለበት ዶክተር ሐሰን ሰኢድ ይመክራሉ።
በ2004 ዓ.ም በቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን አማካይነት በታተመው ‹‹ቅርስ›› በተሰኘው መጽሔት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነ- ጽሑፍ ክፍል የዓረብኛ ንዑስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ መሐመድ ሰዒድ አብደላ ‹‹ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ የኢትዮጵያ እስላማዊ የሥነ-ጽሑፍ ቅርሶች›› በሚል ርዕስ አንድ ጥናት አቅርበው ነበር። በዚህም ጥናታቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡትን የእስልምና ሃይማኖት መፃሕፍት ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ መፃሕፍት መካከልም ከዛሬ 700 ዓመታት በፊት የተፃፈውን፣ ሺሃቡዲን ዓብዱ አልቃድር (ዓረብ ፈቂህ) የአሕመድ ግራኝ መዋዕለ ዜና ፀሐፊው ‹‹ፋቱህ ዓል ሐበሻ›› በሚል ርዕስ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፃፈው፣ ዳውድ አቡ በከር እ.ኤ.አ. በ1818 አካባቢ የፃፏቸው በርካታ እስላማዊ መፃሕፍት፣ ቡሽራ መሐመድ የተባሉ ሊቅ በ1863 እ.ኤ.አ የፃፏቸውን ኢትዮጵያዊ መፃሕፍቶች፣ በ1881 እ.ኤ.አ መሐመድ ጀማል አደን አልዓሊ (አባ ወልዬ) በድርሰት ሥራዎቻቸው አያሌ ነገሮችን መፃፋቸው ተገልጿል። ሑሴን ሐቢብ (ባሆች) እ.ኤ.አ በ1916 ዓ.ም ከሃይማኖት አባትነታቸው በላይ በርካታ መፃሕፍትን አዘጋጅተዋል።
ሐጂ ጃዕፈር በዓረብኛና በአማርኛ ቋንቋ እ.ኤ.አ 1936 አካባቢ መፃፋቸው እና ሸምሰዲን መሐመድ እ.ኤ.አ 1924፣ ሰኢድ ኢብራሂም ያሲን (ጫሎች) በ1940ዎቹ የፃፏቸውና ሌሎችም ተጠቅሰዋል።
እነዚህን ሃይማኖታዊ ቅርሶቻችንን ልንጠበቅ ይገባል። የሌላውን ዓለም ቅርሶች ስናደንቅ የራሳችንን እየረሳን መሆን የለበትም።
ኢድ ሙባረክ! አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012