የዛሬው እንግዳችን ፕሮፌሰር አደም ካሚል ፋሪስ ይባላሉ።የተወለዱት ሰሜን ወሎ ወርሳሚሳ በተባለች መንደር ነው፡ ፡በ1953 አካባቢ የተወለዱ ሲሆን ዛሬ የ63 ዓመት ጎልማሳ ናቸው፡፡እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ ከብት አግደዋል፡፡በሰባት ዓመታቸው አካባቢ በድንገት ወላጆቻቸውን በሞት ስለተነጠቁ ሳኡዲ አረቢያ የሚገኙት ወንድማቸውን አሳድገዋለሁ ብለው ወደ ሳኡዲ ወሰዷቸው፡፡የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ሳኡዲ አረቢያ ከተከታተሉ በኋላ ጥሩ ውጤት በማምጣታቸውም ንጉስ አብዱል አዚዝ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፡፡ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽንና በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ፡ ፡
በመቀጠለም ከንጉስ ሞሃመድ አል ኢማም ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ ዘርፍሁለተኛ ዲግሪያቸው ያዙ፡፡ኢትዮጵያ የእስልምናን ሃይማኖት ተከታዮችን ተቀብላ በማስተናገድ ያበረከተችውን አስተዋጽኦን በተመለከተ በሰሩት ጥናትና ምርምር የሶስተኛ ዲግሪያቸውን ሊያገኙ ችለዋል።በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዘዋወር ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት ያበረከተችውን አስተዋጽኦና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለሃይማኖቱ ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያትቱ አምስት የሚደርሱ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅተዋል፤ኢትዮጵያን የተመለከቱ ከ30 በላይ ጥናቶችንም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች አቅርበዋል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከእኒሁ አንጋፋ ምሁርና የሃይማኖት አባት ጋር ቆይታ አድርጓል ፤መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን ፦ኢትዮጵያ ለሙስሊሙ ዓለም ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እንዴት ያዩታል?
ፐሮፌሰር አደም ካሚል፦ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶችን በመቀበል ረገድ አቻ የማይገኝላት ሀገር ናት፡፡ሶስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶችን ማለትም የአይሁድ ፣ ክርስትናንና እስልምናን ተቀብላ ሃይማኖቶቹ እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ ያደረገች ሀገር ናት።ወደ እስልምናው ስንመጣ ደግሞ የተለየ ታሪክ አለው።እስልምና እንኳን በሌላው ዓለም በሳውዲ ዓረቢያ እንኳን መሰረቱ ሳይጠናከር ኢትዮጵያ እስልምናን ተቀብላ ያስተናገደች
ሀገር ነች።የመካ ቁሬሾች ነብዩ ሞሃመድንና ተከታዮቻቸውን እያሳደዱ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ መጠጊያ ሆና ሃይማኖቱ ዛሬ ላይ እንዲደርስ አድርጋለች፡፡ነብዩ ሞሃመድ ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያደረጉበት ያለምክንያት አይደለም፡፡ኢትዮጵያ የተለያዩ አመለካከቶችንና ሃይማኖቶችን የምታስተናግድ ሀገር መሆኗን ስለሚያውቁ ነው፡፡ለምን ወደ ግብጽ፣ወደ ሶርያ፣ወደ የመን፣ ወደ ኢራን ወዘተ ሂዱ አላሉም፤ ኢትዮጵያን ለምን መረጡ ብለህ ስትጠይቅ ነብይ እንደመሆናቸው መጠን ኢትዮጵያን በደንብ ጠንቅቀው ስላወቋት ነው፡፡ስለዚህም በሁለት ዙር ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል፡፡መካ ያሉት ሙስሊሞች እንኳን ጥቃት ቢደርስባቸው ኢትዮጵያ የመጡት ተከታዮቻቸው ደጀን ሆነው ሃይማኖቱ እንዲቀጥል የማድረግ ዓላማ ያለው ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የእምነቱ ተከታዮች በጣም ጠንካሮች ስለነበሩ በተለያዩ ሀገራት ሃይማኖቱ እንዲስፋፋ አድርገዋል።ጎረቤታችንን ግብጽን እንኳን ብንመለከት የእስልምና ሃይማኖትን የተቀበሉት ወደ ኢትዮጵያ በመጡ የእምነቱ ተከታዮች አማካኝነት ነው።ስለዚህም ኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት ይደርስበት ከነበረው የመሳደድ እንቅስቃሴ የታደገችና ወደ ሌላውም ዓለም እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገች ሀገር ነች፡፡
ሃይማኖቱ እንዲስፋፋም በርካታ ሃበሾች ሸሂድ(በጦርነት ህይወታቸውን አ ጥ ተ ዋ ል ) ሆ ነ ዋ ል ። ጊ ዜ ያ ቸ ው ን ፣ ጉልበታቸውን፣ሀብታቸውንና ንብረታቸውን ብሎም ህይወታቸውን ለሃይማኖቱ ሰውተዋል፡፡ነብዩ ሞሃመድ አባታቸው ገና በእርግዝና እያሉ እናታቸውን ደግሞ በስድስት ዓመታቸው ነበር በሞት ያጡት፡፡ በዚህ ጊዜ ከጎናቸው ሳትለይ ያሳደገቻቸውና እስከ ህይወቷ ፍጻሜ ድረስ ነብዩንና የእስልምና ሃይማኖትን ያገለገለችው ሀበሻዊቷ እሙ አይመን ናት፡፡
ነብዩ ሞሃመድም እናቴ እሙ አይመን ብለው ይጠሯት ነበር፡፡ ልጇ አይመንም ለእስልምና ሲዋጋ የተሰዋ ጀግና ነው፡፡ይህቺ ሀበሻዊት ሴት በእስልምና ሃይማኖት ከፍተኛ ክብር የሚሰጣት ሴት ናት፡ ፡በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እሙ አይመንና ቢላልን የመሳሰሉ ኢትዮጵያንም ለእስልምና ሃይማኖት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከቃላት በላይ ነው።ስለዚህም የተቀረው ዓለም የዚህች ሀገር ውለታ አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ፦የተቀረው ዓለም የኢትዮጵያ ውለታ አለበት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦ በአሁኑ ወቅት የእስልምና ሃይማኖት የማይገኝበት ሀገር የለም፡፡ስለዚህ ሃይማኖቱ እንዲስፋፋና ዛሬ ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡የእምነቱን ተከታዮች አክብራና ሸሽጋ በመያዝዋ ነው ሃይማኖቱ ሊስፋፋና ከዓለማችን ከሃይማኖቶች አንዱና ዋነኛው ሊሆን የቻለው።እዚህ ላይ ግን እስልምናን ብቻ ከውጭ ዓለም እንደመጣ የሚያስቡ በርካታ ሰዎች አጋጥመውኛል።
ሁሉም ሃይማኖቶች ከውጪው ዓለም በአብዛኛውም ከመካከለኛው ምስራቅ የመጡና በተለያዩ ጊዚያት ወደ ኢተዮጵያ የገቡ ናቸው።የሚለያዩት በገቡበት የጊዜ ቅደም ተከተል ነው፡፡ወደ ዋናው ጉዳዩ ስመለስ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩለህ እስልምና በየትኛውም ሀገርና አህጉር ይገኛል፡፡ሙሉ በሙሉም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑ ሀገራትም በርካታ ናቸው።ስለዚህም ሃይማኖቱ ባለበት ሀገር የሚገኙ ሙስሊሞች በሙሉ ይህን ዕድል ሊያገኙ የቻሉት ኢትዮጵያ ሃይማኖቱን ከአሳዳጆች በመታደጓ ነው።ሁሉም ሀገራት የኢትዮጵያ ዕዳ አለባቸው የምለው ከዚህ አንጻር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ታዲያ ውለታዋን ያልመለሱት ለምንድን ነው?
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦እኔ እንደማምንበትም ሆነ በተጨባጭም እንዳየሁት ሁሉም ሀገር ሊባል በሚቻል መልኩ የኢትዮጵያን ውለታ መመለስ ይፈልጋሉ፡፡ከ300 በላይ የተለያዩ በረራዎችን ወደ ተለያዩ ሀገራት አድርጌአለሁ።በሁሉም ሀገራት ለኢትዮጵያውያን ልዩ ክብርና ቦታ አላቸው።እንደ ቱርክ ፣ፓኪስታን የመሳሰሉት ሀገራት ኢትዮጵያዊ ቤትህ ከገባ በረከት ወደ ቤትህ አብሮ ይገባል የሚል እምነት አላቸው።እኔ ቤት ግባ፤ እኔ ቤት ግባ በሚል ይሻሙብሃል።
ወደ ቤታቸው ከገባህም በደስታና በሀሴት ይሞላሉ፡፡ሳኡዲ አረቢያን የመሳሰሉት ሀገራትም ለኢትዮጵያ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ከሀበሻዊቷ የነብዩ ሙሃመድ አሳዳጊ ኡሙ ሃይመን ታሪክ በመነሳት ልጆቻቸውን እንኳን ኢትጵያውያን እንዲያሳድጉላቸው ይፈልጋሉ።ከኢትዮጵያ ጋር ልዩ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ለአብነት እንኳን ከየትኛውም ሀገር በተለየ መልኩ ኢትዮጵያውያን ወደ መካ ለጸሎት ሲሄዱ የሚያርፉበት ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
ሆኖም ግን በእኛ በኩል ያልሰራናቸው የቤት ስራዎች በርካታ ናቸው።በተለይም ቀደም ካሉት ነገስታት ጀምሮ ኢትዮጵያ ለእስልምና ሃይማኖት የተጫወተችውን ሚና ለማጉላት አይፈልጉም፡፡የሀገርን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገሪቱ ውለታዋ እንዲከፈላት የማግባባትና የማሳመን ስራዎች የሉም፡፡በተቀረው ዓለም ዘንድ ይህንን ውለታዋን ለመመለስ ፍላጎቶች ቢኖሩም በእኛ በኩል መድረኩን ዝግ አድርገነዋል።ስለዚህም ውለታዋን እንክፈል ቢሉ እንኳን የሚችሉበት ምንም ቀዳዳ አልነበረም፡፡ሌላው ቢቀር ኢትዮጵያን አትንኩ ብለው ነብዩ ሞሃመድ ያስተላለፉትን ትዕዛዝ የማያወቅ ሙስሊም የለም፡፡ለዚህም ነው ኢትዮጵያን የማክበር ፍላጎት በሁሉም የዓለም ሙስሊም ዘንድ የሚንጸባረቀው።ሆኖም ግን በእኛም ጥፋት ቢሆን ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እስካሁን አላገኘችም፡፡
አዲስ ዘመን ፦አሁንስ በዚህ ረገድ የሚታይ ለውጥ አለ?
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦አሁንም ቢሆን ምንም የታየ ለውጥ የለም፡፡ዶክተር አብይን ጨምሮ በቅርብ ጊዜያት የነበሩ መሪዎች በሙሉ በዚህ ረገድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አላይም፡፡በሌሎች ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ካልሆነ በስተቀር የቀድሞ የሀገሪቱን ውለታ በማስታወስና በማስተዋወቅ ሌሎች ሀገራት ግዴታቸውን እንዲወጡ ሲደረግ አይታይም።ሆኖም ግን ጥቅሙ የጋራ ነው።ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑም ወይም ሌሎች ሀገራት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በጋራ ነው ተጠቃሚ የሚሆነው፡፡ታሪኩንም እኮ የሰሩት በጋራ ነው፡፡ስለዚህም ይህ ያልተነካ የዲፕሎማሲያዊ ስራ የሀገሪቱን በጎነት እንደገና ከተቀበረበት እንዲወጣ የሚያደርግና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶችን ተቀብላ ከማስተናገዷ ባሻገር በተፈጥሮ ሀብት ረገድ ያላትን ጸጋ እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦ኢትዮጵያ በሁሉም ረገድ የታደለች ሀገር ነች፡፡ከላይ እንዳነሳነው ነብዩ ሞሃመድ የመረጧት፣ እንግዳ ተቀባይና የፍትህ ተምሳሌት የሆነች ሀገር ነች፡፡ከዚህ በተጨማሪም ተስማሚ አየርና ለግብርና ስራ አመቺ ለም መሬት ያላት ሀገር ነች፡፡በርካታ ሀገራትን ዞሬያለሁ እንደ ኢትዮጵያ ተስማሚ አየር ያለው ሀገር አላየሁም፡፡ሌሎች ሀገራት በነዳጅና በሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ምክንያት ወደ ሃብት ጎራ ቢቀላቀሉም ለኑሮ ግን የሚመረጡ አይደሉም፡፡በተለይም አረብ ሀገራትን ያየ ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ሀሩሩ ከፍተኛ በመሆኑ ለአፍታም ለመቆየት እጅግ አዳጋች ነው።
መሬታቸውም ሳር እንኳን የማያበቅል በረሃ ነው፡፡ስለዚህም ኢትዮጵያን ከነዚህ ሀገራት ጋር ማነጻጸር ተገቢ አይደለም፡ ፡በእኛው ስንፍናና መቆራቆዝ ምክንያት ከብልጽግና ወደ ኋላ ስለቀረን እንጂ ኢትዮጵያ የሀብታሞች ሀብታም ነች፡፡ለጊዜው ድህነትና ቴክኖሎጂ እጥረት ከልሎን ነው እንጂ ነዳጅና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችም የማይኖርበት ምንም ምክንያት የለም።
ከእኛ ይልቅ ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋ ሌላው አለም ጠንቅቆ ያውቀዋል።በርካታ የአረብ ሀገራት ሀገሪቱ ያላትን ዕምቅ ሀብት ስለሚያውቁ በስፋት ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት አላቸው።ብዙም
የማስተዋወቅ ስራ ሳንሰራ እንኳን በርካታ የሳኡዲ፣የቱርክ፣የተባበሩት አረብ ኢምሬትና የኳታር ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡እኛ መርገም ካለብን መርገም ያለብን ስንፍናችንን ነው።ሀገሪቱ በሁሉም ረገድ ሞልቶ የተረፋት ነች።ሌሎች ሀገራትን ብናይ እኮ ምንም የተፈጥሮ ሀብት ሳይኖራቸው ጠንክረው በመስራታቸው ዛሬ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች መትረፍ ችለዋል።የተባበሩት አረብ ኢምሬትንና ኳታርን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ በቱሪዝምም እንኳን ቢሆን ከየትኛውም ሀገር የተሻለ ተፈጥሯዊ፣ባህላዊና ሰው ሰራሽ ቱሪስት መስህብ ያላት ሀገር ነች፡፡
አዲስ ዘመን ፦እዚህ ላይ ኢስላማዊ ቅርሶችን በተመለከተ ሀገሪቱ ከዘርፉ ምን ያህል ተጠቅማለች
ፕሮፌሰር አደም ካሚል ፦ቅድም እንዳልኩህ ነው፡፡ሀገሪቱ ከእስልምና ጋር ባላት ግንኙነት ካፈራቻቸው ሀብቶች ተጠቃሚ አልሆነችም፡፡በየትኛውም ዓለም ብትዞር በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተሰራ ነጃሺን መሰል መስኪድ አታገኝም፡፡የነብዩ ቤተሰቦችና በእስልምና ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውና አለም በሙሉ የሚወዳቸው ሶሃባዎች( ነብዩ በነበሩ ወቅት የነበሩ የእምነቱ ተከታዮች) ኢትዮጵያ ውስጥ ኖረው እዚሁ ተቀብረዋል።መቃብራቸውም እስካሁን በአግባቡ ተጠብቆ ዛሬ ላይ መድረስ ችሏል።ይህንን ያደረገችው ኢትዮጵያ ነች።
ሌሎችም በአራቱም መዓዘናት ዓለምን የሚያስደምሙ እስላማዊ ቅርሶች ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡በየዘመናቱ በሃይማኖቱ ታላላቅ ምሁራን የተጻፉ ሃይማኖታዊ መጽሐፎችና ሰነዶችም ዛሬ ትልቅ ዋጋ ያላቸውና በእስልምና ጥናት ውስትም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው።አንዳንዶች ጽሁፎችና ሰነዶች የማየት ዕድል የገጠማቸው የውጭ ሀገር አጥኚዎች ነገሩን ለማመን እስኪያዳግታቸው ድረስ በመጽሃፎቹ እና በሰነዶቹ የሃሳብ ምጥቀትና ጥልቀት ተደምመዋል።እነዚህ የጽሁፍ ሀብቶች ለእስልምናው አለም ትልቅ ሀብቶች ናቸው፡፡
ያሉንን ዕምቅ ሀብቶች ውጪው ዓለም አስተዋውቀን ሀብት መሰብሰብ አልቻልንም።ከየትኛውም ነዳጅና ማዕድን የበለጠ የማያቋርጥ የገቢ ምንጭ መሆን የሚችሉና ማንኛውም ሙስሊም በህይወት ዘመኑ ሊያያቸው የሚጓጓላቸው የቱሪስት መስህቦች ናቸው፡፡ይህንኑ በመረዳት ሁሉም የአረብ ሀገራት እነዚህን እስላማዊ ቅርሶች ማልማትና መደገፍ ይፈልጋሉ።ነጃሺን መስኪድ ገብቶ በዛውም ወደ መካ ሃጂ ጉዞ ለማድረግ ታስቦ ከቱርክ ብቻ በአንድ ጊዜ እስከ ሃምሳ ሺህ ጎብኚዎች በየዓመቱ ለመምጣት ተዘጋጅተው ነበር።ሌሎችም ሀገራት ከዚህ የላቀ ፍላጎት ነበራቸው።ሆኖም ግን ይህን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ጎብኚ ለማስተናገድ የሚያስችል ትራንስፖርት፣መሰረተ ልማት ሆቴል ባለመኖሩ ፍላጎቱን ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ለቱሪዝም ብቻ ሳኡዲዎች 10 ቢሊዮን ዶላር፣ ገልፎች32 ሚሊዮን ዶላር፣ኢምሬቶች 5 ቢሊዮን ዶላር፣ባህሬን 3 ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ።ምንም እስላማዊ ቅርስ የሌላት ኬንያ 1.5 ሚሊዮን ቱሪስቶችን አስተናግዳለች፡፡
እንግዲህ ልብ በል ይህ ሁሉ ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል የኢኮኖሚ ችግራችን ሊቃለል እንደሚችል መገመት አያዳግትም።ዛሬ መንግስትንና ባለሀብቱን አላላውስ ያለው የዶላር ዕጥረት ለኢትዮጵያ ችግር አይሆንም ነበር፡፡በርካታ ወጣቶችንም ስራ ማስያዝ ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህ ከነዳጅና ከወርቅ የከበረ ሀብት እንደዋዛ ተዘንግቶ ሀገሪቱ የሀብታም ድሃ እንድትሆን ተደርጋለች፡፡በሀገራችን አንድ እስላማዊ ሙዚየም እንኳን የለም፡፡ሌላው ቢቀር በሳኡዲ አረብያና በኩዌት በነቢላልና በነጃሺ የተሰየመ አደባባይ እኮ አለ፡፡በእኛ ሀገር ግን ግማሽ የሚሆነው የሀገሪቱ ታሪክ ተዘንግቶ ለዘመናት ቆይቷል፡፡ይህ አሳፋሪ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ በየዘመናቱ የነበሩ መሪዎች፣የቱሪዝም ኮሚሽንና የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት(መጅሊስ) ሊወቀሱ ይገባል።ኃላፊነታቸውን ሁሉም አልተወጡም፡፡
አዲስ ዘመን፦ካነሱት ላይቀር አሁንም ቢሆን እኮ እስላማዊ ቅርሶችን በዩኒስኮ ለማስመዘገብ የሚደረጉ ጥረቶች አናሳ ናቸው፤ ለምንድን ነው?
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦ ለእኔ በዩኒስኮ ማስመዝገብን እንደትልቅ ግብ አላየውም፡፡እነዚህ እስላማዊ ቅርሶች በዩኒስኮ ተመዘገቡም አልተመዘገቡም አብዛኛው አለም የሚያውቃቸው ናቸው።የነጃሺን መስኪድ የማያውቅ ሙስሊም አለ ለማለት አይቻልም፡፡ቢያንስ የእስልምና ታሪክ ሲነሳ የንጉስ ነጃሺ እና የሶሃቦቹ ታሪክ መነሳቱ አይቀርም።ስለዚህም ማስተናገድ አቅማችን ካልገደበን በስተቀር የጎብኚዎች ቁጥር ከምንገምተው በላይ ነው፡፡በየትኛውም ዓለም በዩኒስኮ የሚመዘገቡትን ቅርሶች ልብ ብትል ኢትዮጵያ ካሏት እስላማዊ ቅርሶች ጋር የሚነጻጸሩ አይደሉም፡፡ከዚህ በላይ የሚያሳስበኝ በነዚህ ሀብቶች ሀገሪቱ መጠቀም አለመቻሏ ነው።ወይንም የተለያዩ አካላት አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ነገሩን አይተው እንዳላዩ ማለፋቸው ነው፡፡ከነዚህ ቅርሶች ያነሱትን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ እርብርብ ሲደረግ ስለነዚህ ቅርሶች ያገባኛል የሚል አካል መታጣቱ ቁጭትን የሚያጭር ነው፡፡
እኛ የነጃሺንና የሶሃቦቹን ታሪክ አይተን እንዳላየን በማለፋችንና ዝምታን በመምረጣችን ሌሎች የታሪኩ ባለቤት ለመሆን እየተሾሙበት ይገኛሉ፡፡በአንድ ወቅት ሱዳኖች ታሪኩን የእራሳቸው አድርገው ሲያቀርቡ ሰምቼ ተከራክሬ ረትቻቸዋለሁ፡ ፡በዚህ ሁኔታም በጣም አዝኜ ይህ ታላቅ ታሪክ የኢትዮጵያውያን መሆኑን እያወቅችሁ እንዴት የእኛ ነው ብላችሁ ትናገራላችሁ ስላቸው‹‹ ምን እናድርግ እናንተ ስትተውት ባለቤት የለውም ብለን የእራሳችን ለማድረግ መሞከራችን የሚያስወቅሰን አይደለም፡፡እናንተ ካልተጠቀማችሁበት እኛ ብንጠቀምበት አይሻልም ወይ›› የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል።ስለዚህ በእጅ ያለወርቅ እንደሚባለው አለም የሚጓጓለትን ታሪክና ቅርስ እኛ አቅለነዋል፡፡
አዲስ ዘመን ፦በእርስዎ በኩል እስላማዊ ቅርሶችን በመንከባከብና በመጠበቅ ምን ያህል ተራምደዋል፡፡
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦ እኔ በግሌ ከኪሴ ገንዘብ በማውጣት በተለያዩ የሃይማኖት አባቶች የተጻፉ መጽሐፎችንና ሰነዶች እያሰባሰብኩ እገኛለሁ፡፡እነዚህ ታሪካዊ ሰነዶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ በመሆኑ በግለሰቦች ጥረት ብቻ መወጣት የሚቻል አይደለም፡፡ግን የሚመለከተው አካል ኃላፊነቱን እስኪወጣ ድረስ እነዚህ ቅርሶች እንዳይጠፉና እንዳይበላሹ የተወሰኑትንም ቢሆን ባለሙያዎችን በማሰማራት እንዲሰበሰቡ እያደረግኩ እገኛለሁ፡፡እንደነገርኩህ ግን ከቅርሶቹ ብዛትና ከሚገኙበትም ቦታ አካባቢ ስፋት በተቋም ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በግለሰብ ጥረት ብቻ ቅርሶቹን መሰብሰብና መታደግ አይሞከርም፡፡ስለዚህም የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናት ተቋምና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን የመሳሰሉት ተቋማት የአንበሳውን ድርሻ ወስደው ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በሃይማኖት መቻቻልና አብሮ በመኖር ዙሪያ ተምሳሌት መሆኑዋን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል፤ይስማሙበታል
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦መስማማት ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረግኩ በመሆኑ በዚህ ረገድ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ነብዩ ሞሃመድ እኮ ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ብለው ሲያዙና ኢትዮጵያንም አትንኩ ብለው ትዕዛዝ ሲሰጡ ያለምክንያት አይደለም፡፡ኢትዮጵያ መከባበርና መቻቻልን ለአለም ህዝብ ያስተዋወቀች፤የሁሉም ሃይማኖቶች መጠጊያና የሁሉም እምነት ተከታዮች ያለምንም ልዩነትና አድልኦ የሚኖሩባት ድንቅ ሀገር መሆኗን ስለሚያውቁ ነው፡፡አላህ በሰጣቸው ነብያዊ ጸጋ በመታገዝም ኢትዮጵያን ቀድመው አውቀዋታል፡፡ፍትሃዊ መንግስትና ህዝብ ያላት ቀድማ እኩልነትንና ፍትሃዊነትን ያነገሰች ሀገር መሆኗን ተረድተዋል፡፡ስለዚህም የመቻቻልና አብሮነት ተምሳሌት የሚለው ቢያንስባት እንጂ አይበዛባትም፡፡
አዲስ ዘመን፦ በአሁኑ ወቅት በሃይማኖቶች መካከል የሚታዩ አለመግባባቶች ይህንን ታሪካዊ ዳራ ሊያጠፋው ይችላል የሚል ስጋት የለዎትም
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦ በኢትዮጵያውያን መካከል ድሮም ሆነ አሁን የሚካሄዱ ግጭቶች በህዝቦች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች አይደሉም።የተለያዩ አካላት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚወጥኗቸው ሴራዎች ናቸው እንጂ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለአንድ ቀንም ቢሆን ተጣልተው አያውቁም፡፡አንዱ ህዝብ ሌላውን የሚጠላበት ምንም አይነት ታሪካዊ መሰረት የለውም።እንደውም የጠነከረ አንድነትና መከባበሩ ስላለ ነው እንጂ በፖለቲኞች እንደሚጎነጎነው ሴራ ቢሆን ይህ ህዝብ እርስ በእራሱ ተጫርሶ ባለቀ ነበር፡፡ባለፉት 27 ዓመታት የተሰራውን ደባ እንኳን ብትመለከት ዜጎች ኢትዮጵያዊነታቸውን እንዲጠሉና በጎሳ ብቻ ተከልለው እንዲኖሩ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
ለአለም ተምሳሌት የሆነችና ብርካቶች የሚመኟት ሀገር ወደታች እንድታንስ ያልተሰራ ስራ የለም።ሆኖም ግን በህዝቡ ልብ ውስጥ ለዚች ሀገር ታላቅነት ተጽፎ የሚገኝ በመሆኑ ዛሬ ድረስ ይህንን ጠንካራ ምሶሶ ሊያፈርሰው የሚችል ኃይል አልተገኘም።በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የኢትዮጵያን ገናናነት እንደገና ለመመለስ የሚሰሩትን ስራዎች በግሌ ሳላደንቅ አላልፍም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአጭር ጊዚያት የሰሯቸው ስራዎችም ፍሬ አፍርተው የአለም ሰላም ኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።ይህ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካውያን ትልቅ ኩራት ነው።በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን፣በሶማሊያ፣በኤርትራ በአጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ የሰሯቸው ሰላምን ማስፈን ተግባራት የኢትዮጵያን ታላቅነት ያስመሰከሩ ናቸው። በዚህ ስራቸው የተደመሙ የየመን፣የሳኡዲና የኳታር ዜጎች በሀገራቸው ሰላም እንዲሰፍን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲረዷቸው እየተማጸኑ ይገኛሉ።
በዋነኝነት የእኛ ችግር ያለንን ሀብትና ጸጋ መረዳት አለመቻላችን ነው።አሁን ያሉን ጠቅላይ ሚኒስትር በመላው ዓለም ክብርና ሞገስ የሚሰጣቸው ታላቅ ሰው ናቸው፡ ፡እኛ ግን በብሄርና ጎሳ ተቧድነን ያለንን ክብርና ዝና ቁልቁል ለማውረድ ስንታትር እንታያለን፡፡ዞሮ ዞሮ ግን ከጊዜያዊ ችግር ባለፈ ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ መጓዟ የማይቀር ነው።ነብዩ ሞሃመድ ኢትዮጵያን አትንኩ ስላሉም ኢትዮጵያን የነካ በራሱ ላይ ችግር ማምጣት የፈለገ ብቻ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የመውሊድ በዓልንና ኢትዮጵያን እንዴት ያያይዟቸዋል
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦ መውሊድ ከሳኡዲ አረብያ በስተቀር በሁሉም ሀገራት ይከበራል፡፡እንደየ ሀገራቱም ነባራዊ ሁኔታ አከባበሩም የተለያየ ነው።የኢትዮጵያ ግን ከሁሉም ለየት ያለ ነው።ሀበሻ ለነብዩ ሞሃመድ ልዩ ክብርና ፍቅር አለው።የተወለዱበትን ዕለትም(የመውሊድ በዓልን) የእሳቸውን ስም እየጠራና ያዘዟቸውንም ተግባራት እየፈጸመ ይውላል፡፡ለነብዩ ሞሃመድ ያለውን ፍቅር በመንዙማ እያወደሰ ቀኑን በልዩ ድምቀት ያሳልፋል፡፡በአጠቃላይ ሙስሊሞች በአንድነት ተሰብስበው በአማረና በደመቀ ሁኔታ የመውሊድን በዓል ሲያከብሩ ልዩ ድባብ አለው።
በእለቱም የተለያዩ እርዶች ስለሚፈጸሙ ድሃው ጠግቦ የሚውልበት ቀን ነው።በዓሉ በኢትዮጵያ ለየት ባለና እስላማዊ ገጽታውን ጠብቆ ለዘመናት ሲከበር ቆይቷል፡፡ ወደፊት ደግሞ ኢትዮጵያ ለእስልምና ሃይማኖት መጠናከርና መስፋፋት ያደረገችውን አስተዋጽኦ የምንዘክርበትና በርካታ ቱሪስቶችንም ጠርተን የምናስተናግድበት ልዩ በዓል እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን ፦ለነበርን ቆይታ በአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ስም ምስጋናዩን አቀርባለሁ፡፡
ፕሮፌሰር አደም ካሚል፦እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012
እስማኤል አረቦ