አፈርን የማልማት፣ ሰብልን የማምረትና እንስሳትን የማርባት ጥበብ “ግብርና” ይሰኛል፡፡ ግብርና፤ የእጽዋትና የእንስሳት ምርቶች ለሰዎች ጥቅም ይውሉ ዘንድ ማዘጋጀትና ለገበያ ማቅረብንም ያካትታል፡፡ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ግሪክ፣ ሜሶፖታሚያና ሱመራዊያን ግብርናን በመጀመርና በማዘመን ታሪክ ውስጥ ቀዳሚነትን ይወስዳሉ፡፡ የኤፍራጠስና የጢግሮስ ወንዞች ለዓለም የግብርና እና የሥልጣኔ ታሪክ ምንጭ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡
ከዘመን ዘመን በርካታ የለውጥ ደረጃዎችን እያሳለፈ የመጣው ግብርና፣ በእጅ ከሚካሄድ ቁፋሮ ተነስቶ፣ እንጨትን በመቅረጽና ብረትን በማቅለጥ የተሠሩ መሣሪያዎችና ሌሎችንም ዘዴዎች አልፎ በ16ኛውና 19ኛው ክፍለ ዘመን መካከል እንግሊዝ በዘመናዊ ግብርና የላቀ ምርት እድገት እንድታስመዘግብ አድርጓል፡፡ ዛሬም ይህ ዘርፍ በየዘመኑ በሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች እየታገዘ የምግብ ዋስትናችንን እንድናረጋግጥ ረድቶናል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1843 ሳይንሳዊ የማዳበሪያ ምርምር ከመጀመሩም ባሻገር እንደ ሶዲየም ናይትሬትና ፎስፌት ያሉ ማዳበሪያዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም ተገንብተዋል። ግብርና በከፍተኛ ደረጃ መዘመን በታየበት፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በ1901 የመጀመሪያው በቤንዚን የሚሰራ ትራክተር ከተመረተ በኋላ የግብርና ሥራ በፍጥነትም በጥራትም ማደግ ችሏል፡፡ በመካናይዜሽንና በምርምር እየበለፀገ የመጣው ግብርና ከመነሻው አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የሰው ልጅ መሬትን አልምቶ፤ እንስሳትን አልምዶ ህልውናውን ያስቀጥልበት ዘንድ ከተፈጥሮ የተሰጠው ስጦታው ነው ማለት እንችላለን፡፡
ባለንበት ዘመን፣ በሀብት የበለጸጉ ሀገራት የረቀቀ ግብርናን የመወዳደሪያ ዘርፍ አድርገውታል፤ በየጊዜው ለሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮችም በምርምር የታገዘ መፍትሔን እየሰጡ ተጉዘዋል፡፡ በዚህም ሕዝባቸውን ከመመገብ አልፈው ለሌሎችም መትረፍ ችለዋል፡፡
ግብርና ለኢትዮጵያም የህልውናዋ መሠረት፤ ገበሬውም የሕዝቧ የዘመናት ባለውለታ ነው፡፡ የተለያዩ ዝርያዎችን ለማብቀል ምቹ የሆነ ሥነ ምህዳርንም ታድላለች፡፡ ዶ/ር አስናቀ ፍቅሬ፣ ‹‹ግብርናችን ሥልጣኔው ከእኛ እስከ ነጩ አብዮት›› (2010 ዓ.ም.) በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ኢትዮጵያ እድሜ ቆጠር ማረሻን ፈልስፋ 100 ሚሊየን እስክንደርስ ለነበሩት 1ሺህ 500 ዓመታት መግባናለች፡፡ በአሁኑ ሰዓትም 17 ሚሊየን ያህል አርሶ አደሮች 100 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ይመግባሉ፡፡
መጽሐፉ እንደሚናገረው፣ ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በሰው ኃይል ያላት አቅም በቀላሉ ምርታማ መሆን የሚያስችላት ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ግብርናችን መዘመንን ይሻል፡፡ ግብርናችንን የማዘመኑ ጉዞ ረጅም ርቀት የሚቀረው ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዘርፉ በጉልህ የሚታዩ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ምርታማነት ላይ ስትራቴጂካዊ ለውጥ በማምጣት ሰፋፊ ድሎችን አስመዝግባለች። በኢትዮጵያ የሚታረስ መሬትን በእጥፍ በመጨመር ምርታማነትን ማሻሻል ተችሏል። በተለይ በስንዴ፣ በጤፍ፣ በቆሎ እና ገብስ ምርቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አማካኝነትም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በመርሃ ግብሩም 40 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
ይህ ተጨባጭ ውጤት የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ)፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዓለም የምግብ ድርጅት(ፋኦ) በጋራ ያዘጋጁት ከረሀብ ነፃ ዓለም /world without hunger/ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መንስኤ ሆኗል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያን ተመራጭ ያደረገው በለውጥ መንገድ ላይ መሆኗን ተከትሎ የመጣ ነው ይላሉ። መሠረታዊውን የጉባኤውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ ጉባኤው ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄዱ ትርጉሙ ሰፋ ያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለይ በምግብ ራስን ለመቻል በጣም ሰፊ ሥራዎች ሰርታለች፡፡ በዚህ ሂደትም ደግሞ ብዙ ሀገራት ሊማሩበት የሚችሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝታበታለች፡፡
ጉባኤው እዚህ መካሄዱ አንድም በዚህ ዘርፍ ያከናወነቻቸው ሥራዎች ለሌሎች ሀገራት የምታቀርብበትን ትልቅ እድል ፈጥሮላታል፡፡ በዛውም ደግሞ በሂደቱ ያጋጠሟትን ፈተናዎች የምትቀርፍበትን መንገድ ከሌሎች ሀገራት ልምድ የወሰደችበት ትልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ነበር፡፡
በጉባኤው ላይ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ገርድ ሙለር እንደገለፁት ኢትዮጵያ ምግብ ከመቀበል ወደ ምግብ መላክ ተሸጋግራለች፡፡ ይህ ምስክርነት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ንግግር እንደዚሁ ጉንጭ ለማልፋት ወይም በምላስ ወለምታ የተነገረ አይደለም፡፡
በመዝገበ ቃላት ጭምር የረሃብ ምልክት እስከ ማድረግ ደርሰው ከነበሩት፤ ምግብ ረዳናት ሲሉ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመግለጫዎች ያጨናንቁ ከነበሩ ተቋማት መካከል የተንፀባረቀ ነው፡፡ ውጤቱም የኢትዮጵያዊያን ጀግና አርሶ አደሮች የላብ ወዝ ነው፤ ስንዴ ልማት ሲል አቋሙን በቁርጠኛ ተግባር የገለጸው የመንግሥት ሥራ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
ባለፈው እኤአ ሐምሌ 2023 አልጀዚራ ኢትዮጵያ ስንዴ ከዩክሬን የተላከላት አስመስሎ እስከ መዘገብ ደርሶ ነበር፡፡ ይህንን ዘገባቸውን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ምግብ ተቀባይና የምትረዳ እንጂ በጠንካራ ሥራ ልትቀየር የምትችል ሀገር መሆኗን ለመግለጽ የሚተናነቃቸው ጥቂት አይደሉም። ሰርታ በተግባርም አሳይታ ስንዴ ከውጭ አላስገባም ማለቷ የጎረበጣቸው ብዙ ነበሩ፡፡
ታዲያ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ገርድ ሙለር ንግግር ክብደት እዚህ ጋር ዋጋው ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ የምግብ ላኪ ሆናለች፡፡ ይህን እውነታ ዓለም እንዲረዳው ከረሀብ ነፃ የዓለም ጉባኤን ማስተናገዳችን የሰጠን የመጀመሪያ ትሩፋት ሊባልም የሚችል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ ሥራ ሰርታለች፡፡ ነገር ግን በምግብ ሥርዓቱ ላይ ምርታማነቱን በመጫን፣ በማሰራጨትና ፍጆታ ላይ አሁንም የሚመጡ ፈተናዎች አሉ፡፡ ምርታማነትና የምርት ስብጥር፣ በግብዓት እጥረት ምክንያት እየተጓተቱ ነው፡፡ በአፈር ማዳበሪያ፣ ችግኞችና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ምክንያት፡፡ በተጨማሪም የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የእርሻ መስፋፋት ለመሬት መሸርሸር እና ለደን መጨፍጨፍ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ለዚህ ችግር እንደመፍትሔ የሚጠቀሰው የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርናው ሽግግርና ምርታማነት በተሰጠው ትኩረት በሰብል የተሸፈነው መሬታችንን በማሳደግ ለምርታማነቱ የተሰጠው ትኩረትም ሰብሉን ፍሬያማ እያደረገው ነው፡፡ ድርቅን መቋቋም ያስቻሉ እንደ ስንዴ፣ጤፍ፣ በቆሎና ማሽላ ያሉ ሰብሎች ላይ ምርታማነቱ ጨምሯል፡፡ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያሉ ከአምስት ዓመታት በፊት የተጀመሩ ሥራዎች የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችሉና የግብርናውን ምርታማነት የሚያሳድጉ መርሃ-ግብሮች እንደሆኑ ይታመንባቸዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም 40 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ የግብርና ምርትንና ምርታማነትን የማሳደግ ተሞክሮዋ ከረሃብ ለመውጣት ወሳኝ ርምጃ መሆኑን የዓለም ከረሃብ ነፃ መውጣት ጉባኤ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ በዓለም አቀፉ ጉባኤ የታደሙ ጉባኤተኞች እንዳሉት እሴት መጨመርና ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ቀጣይ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡
ዳግመኛ ስለልመና እንዲሁም ስለረሃብ ማሰብን ተረት ለማድረግ የዜጎች ጓዳ ሙሉ ሆኖ ረሃብን ከምድር ላይ በዘላቂነት ማጥፋት የጊዜው ተቀዳሚ አጀንዳ ሆኗል። በምግብ ራስን ከመቻል በዘለለ ከሚትረፈረፈው እርሻ ለሌሎች ማካፈልና ጥጋብ የሚለው ቃል በአንደበት ላይ ታትሞ ይቀር ዘንድ ነው የሚፈለገው፡፡ በኢትዮጵያ ለሶስት ቀን ቆይታ የነበረው ዓለምን ከረሃብ ነፃ የማድረግ ጉባኤ የግብርና ምርትን በማሳደግ፣ ምርት ላይ እሴትን በመጨመር ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባ አፅንኦት የተሰጠበት ነው፡፡
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሄደችበት ያለው መንገድ የሚደነቅ ነው፡፡ ምርት እንዲትረፈረፍ ውጤታማ በሚያደርግ ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሠራው ሥራ ሌሎች እንዲማሩበት አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራን ለማዘመንና የአርሶ አደሩን የእርሻ ሥራ ሙሉ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አስደናቂ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በግብርናው ለውጥን በማምጣት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ዘርፍ የተሄደበት መንገድ ለተቀረው የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተካሄደው ይህ ጉባኤ ሀገሪቱ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ ለተቀሩት አፍሪካ ሀገራት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው። ቀሪ ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ማስኬድ ከተቻለ ውጤቱ አመርቂ እየሆነ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ግብርና በምግብ እህል ራስን ለመቻል ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚውም ማደግ አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ስንዴን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር እያደረገው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረትና ክትትል ዘርፉ ስኬታማ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ስንዴን ጨምሮ በሌሎችም አነስተኛ እርሻ ሥራዎች ላይ የተደረገው ድጋፍ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህንን ተሞክሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በስንዴ፣ በሩዝና በሌሎች ምርቶች ላይም ውጤት ማየት ተችሏል። በሀገሪቱ ግብርና ከፍተኛ እመርታ በማምጣት ላይ ነው። ከተናጠል ይልቅ በኩታ ገጠም መሬት እንዲታረስ በማድረግም ምርታማነት ጨምሯል፡፡ የአርሶ አደሩ ኑሮ እንዲሻሻል የተወሰደው ሌላኛው ርምጃ የሚበረታታ ነው፡፡ ኑሮን ከማሻሻል አልፎ ገበያ ተኮር የእርሻ ሥራ ማከናውን ተመራጭ ተደርጓል፡፡
በስንዴ ምርትና ምርታማነት የተመዘገበው ውጤት ግን አሁንም ቀሪ ሥራዎች አሉት፡፡ ዘንድሮ 30 ሺህ ቶን ለማምረት ታቅዷል፡፡ ለዚህም የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ቴክኖሎጂንና ሌሎች ዘመኑን የዋጁ ግብዓቶችን መጠቀም ይገባል፡፡ መሰል እውቅናዎችን በልካቸው በማፍታታትም የበለጠ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ህልውናዋ ከግብርና ጋር የተቆራኘና ለግብርና እሴት ሰንሰለት ልማት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠች በመሆኗ ዘርፉን በጠንካራ ምርምርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማገዝ የግድ ይላል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በዓይነትና በጥራት የሚጨምሩ፣ የአካባቢ ጉዳትን ለመቋቋምና ለመቀነስ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማመንጨትና በማቅረብ በዋናነት የግብርናውንና የግብርና ኢንዱስትሪውን አዋጭነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ሀገራዊ ኃላፊነትና ወሳኝ ሚና ያለው ተቋም መሆኑን ተገንዝቦ ይበልጥ ሊተጋ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ለግብርና የተሰጠ ምቹና ሰፊ ፀጋ ያላት ብትሆንም፣ ይህን ፀጋ በተገቢ ልክ ሳትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን፣ ተስፋ ሰጪ ጥረቶችና ውጤቶች ታይተዋል፡፡ ጥረቶቹ ይበሉ የሚያሰኙ ቢሆኑም፣ ዛሬም ግብርናችንን ከበሬ ቀንበር ለማውረድ ገና ረዥም ርቀት መጓዝ ይቀረናል፡፡ ስለሆነም፣ ዘርፉን ለማዘመን በመስኩ የሚካሄዱ ምርምሮችን ማበረታታት፣ የምርምር ሥራዎች በሰነድ ላይ ብቻ እንዳይቀሩና ወደ ውጤት እንዲቀየሩ በፋይናንስና በቴክኖሎጂ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ በስንዴ የታየውን ምርታማነት በሌሎችም ሰብሎች ለመድገም እንበርታ!
ታሪኩ ዘለቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም