የሀገር መልኩ – ሕብረብሔራዊ ቀለም ነው

ሀገር የብዙሀነት ጥርቅም ናት። ብዙሀነት ደግሞ የልዩ ልዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ታሪኮች፣ እሴቶችና ልማዶች ነጸብራቅ በመሆን ይገለጻል። ሀገር የሚለው ግዙፍ የወል ስምም ይሄን የልዩነት አጥር ታኮ የቆመ የብዙሀነት ስያሜ መሆኑ አያከራክርም። በየትኛውም የዓለም ጫፍ ሀገርና ሕዝብ በዚህ ትርጓሜ በኩል የሚገለጹ መሆናቸው እሙን ሲሆን በብዙ ልዩነት ውስጥ ደምቀንና ፈክተን የምንታየው የጋራችን በሆነች ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ እንደዚሁ የሚያስማመን ነው፡፡

ሀገር የሚለው ሶስት ቃል ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በክብር ተሸክሞ ሶስት ሺ ዘመናትን በድልና በሉአላዊነት ተሻግሯል። ይሄ ግዝፈት እንዴት መጣ? እንዴትስ ጸና? እንዴትስ ሳይንገዳገድ በብዙ ዘመን ውስጥ ተሻገረ ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ ኢትዮጵያዊ ትስስርን ነው። በእውነቱ ትስስራችን የሚገርም ነው።

ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ከሚያስደንቁኝ ባህሎች አንዱ የእርስ በርስ ጉርብትናችን፣ ትብብራችን፣ መቻቻላችን ሲሆኑ አሁን ላይ እነዚህ ውብ ትውፊቶቻችን በመጥፎ ትርክት መደብዘዛቸው እንደዚሁ የሚያስቆጨኝ ነው። የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም እነዚህን የጋራ እሴቶቻችንን ከጥቃት በመጠበቅ በአብሮነት ስም ማስቀጠል ነው፡፡

ስለሀገርና ሕዝብ ያጠኑ፣ የጻፉ፣ የተጠበቡ ልሂቃን ሀገር የሚለውን ሰፊ ግዛት ከብዙሀነት የታሪክ ውርርስ ጋር ያነካኩታል። ይሄ ማለት ከፍ ብዬ እንዳልኩት ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ በሚወርድ የጉርብትና ተዋረድ መንጭቶ የሚፈስ እንደሆነ ይመሰክራሉ። እንደዚሁም ስለለውጥና ስኬት የሚያጠኑ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሀገራዊ ለውጥ በግለሰባዊ ለውጥ ውስጥ እንዳለ እና እድገትና ዘመናዊነት የሚባሉት ማህበራዊ መሻቶች ከጤናማ ዜጋ፣ ከጤናማ ትውልድ፣ ከጤናማ የፖለቲካ እሳቤ እንደሚጀምርም አጽንኦት በመስጠት ሀሳባቸውን ያጋራሉ።

ጤናማ የሚለውን ሀሳብ ከብዙ አቅጣጫ ልናየው ብንችልም ከተነሳንበት የሀገርና ሕዝብ ጽንሰ ሀሳብ አኳያ ግን ከሰላምና ከደህንነት ጋር ልናቆራኘው እንችላለን። እንደሚታወቀው የሀገራችን አሁናዊ ሁኔታ በብዙ መልኩ የሰላም ጥያቄ የሚነሳበት ነው። የሰላም ጥያቄ ብዙ መነሻ ቢኖረውም በተረጩ የትርክት መርዞች የደፈረሰ እንደሆነ ብናገር ልክ እሆናለው። የረገቡና የላሉ የሕብረብሄራዊነት ቋጠሮዎቻችን በፖለቲካ የሚመዘኑ፣ በዘርና በብሄር የሚተመኑ አይደሉም። ሰውነትንና ተፈጥሮን መሰረት አድርገው ስለአብሮነት እንዳይላሉ ሆነው የጠበቁ እንጂ ሲፈልጉ የሚላሉና የሚጠብቁ አይነት አይደሉም፡፡

የጥላቻ ትርክት እንዳይለያየን ለሰላም ቅድሚያ መስጠት፣ ለአብሮነት እድል መስጠት፣ በመነጋገርና በመወያየት ልዩነትን ማጥበብ ቀዳሚ መፍትሄዎቻችን ናቸው። ሰላም ለናፈቀው ማህበረሰብ ሰላም ሰባኪ ድምጾች ያስፈልጉታል። የትናንት ታሪኮችን አጽመ ታሪክ እየበረበሩ በወንድማማች መሀል ጠብን መዝራት ለማንም የማይጠቅም የዝቅታ መገለጫ ነው። ዓላማችን ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ከሆነ በሀሳብና አሁናዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እናተኩር። ሰላም ትናንትን በመዘከር አይመጣም። ልማት ያለፈን በመውቀስ አይረጋገጥም። ችግሮቻችን በዛሬ የሀሳብ የበላይነት የሚረግቡ እንጂ የትናንት ስህተቶችን በማስታወስ የሚመክኑ አይደሉም። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምንም በላይ በሀሳብ የደለበ ጤነኛ ዜጋ፣ ጤነኛ ትውልድ፣ ጤናማ ፖለቲከኛ ትፈልጋለች፡፡

ፖለቲካው ካልዘመነ ሀገራችንን ማዘመን አንችልም። በአንድ ሀገር ላይ የፖለቲካ ድርቀት ሀገርን ለማቀንጨር የሚደርስበት የለም። የፖለቲካ ዝማኔ ደግሞ ከሀሳብ የሚወለድ፣ ለሀሳብ ያደላ፣ ስለሀሳብ የሚመክር ነው። በሀሳብ ካልዘመንን በጦርነት ሰልጥነን ገዳይና ሟች በመሆን በነውር መጠራታችን ይቀጥላል። በሀሳብ ካልሰለጠንን በትናንት ስህተት ዛሬን ማበላሸትና ለነገ ቁርሾ ማስቀመጥ ግብራችን ይሆናል፡፡

ዝማኔ የሀሳብ ብስለት ነው። ዝማኔ ወደ ጨለማዎች ብርሀን መርጨት ነው። ዝማኔ ለብዙሀን ውጋግ መሆን ማለት ነው። የሀገር መልክ የሕብረብሄራዊነት ቀለም ነው ብዬ መነሳቴ በእንዲህ አይነቱ ሰላምና እርቅን ባስቀደመ የወንድማማችነት አካሄድ እንጂ በይዋጣልን አይደለም። አንድም ሰው የሌለባት ሀገር ታውቃላችሁ? ጤነኛ ፖለቲካ የሌለባት ሀገር አንድ ሰው እንደሌለባት ሀገር ናት። ሰላም የራቀው ሕዝብ፣ በጥላቻና በቁርሾ የተዘባነነ ትውልድ በብዙሀነት ውስጥ በምንምነት የሚጠራ ነው። ትግላችን ሊሆን የሚገባው በጤናማ ፖለቲካ ጤናማ ሀገር መፍጠር ነው። ጤናማ ፖለቲካ ደግሞ ከአሰላሳይና ነገን አርቆ ከሚያስተውል ልቦና የሚሰራ ነው፡፡

በጥላቻ እዛና እዚህ የጎሪጥ በሚተያይ ማኅበረሰብ ውስጥ ሀገር የለችም። ብትኖርም በብዙሀነት መሀል እንደምንም ነን። ብዙሀነት ዋጋና ትርጉም ያለው በመዋደድና በመፋቀር፣ በመቻቻልና በመከባበር ውስጥ ነው። ለተነሳሁበት ዓላማ እና ላለንበት ሀገራዊ ውጥንቅጥ መፍትሄ በመሆን ተስፋ የሚሰጠን ጤነኛ ፖለቲካን በጤነኛ ፖለቲከኞች መገንባት የሚለው ነው። ሰላም የቀደመበት የትኛውም ጉርብትና ጤናማ ነው። ሀገር እና ማኅበረሰብ ከፖለቲካ መንጭተው ወደነገ የሚሄዱ ፈለግና ዳና በመተው ትውልዱ ላይ የሚያርፉ ዐሻራዎች ናቸው፡፡

ትናንትና በሰላም ካልመጣን ዛሬን በሰላም ለመኖርና ነገን በሰላም ለመቀበል መበርታት የእኛ ኃላፊነት ነው። ብዙዎቹ ጠበብት ‹የሀገርን ለውጥ ከግለሰብ ለውጥ ጋር፣ የትውልድን ለውጥ ደግሞ ከሀገር ለውጥ ጋር ያቆራኙታል። ከእኛ በቀር ሁሉም የዓለም ሕዝብ ይሄን እውነት ያውቃል። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ የለውጥ መሰረት ምን እንደሆነ ገና የገባን አይመስለኝም። ምክንያቱም ከትናንት እስከዛሬ የተራመድንባቸው ጎዳናዎች የለውጥን ሕግ የሳቱ መሆናቸው ነው፡፡

ዛሬም ድረስ እያደረግነው ያለው ነገር ከለውጥ ሕግ ጋር የሚቃረን መሆኑ ነው። ራሳችንን ሳንቀይር ሀገር ለመቀየር የቆምን ብዙዎች ነን። በአንድ ሀሳብ ሳንስማማ ሀገር ለመቀየር የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመን የምረጡኝ ቅስቀሳ የምናደርግ ብዙዎች ነን። ተነጋግረን ሳንግባባ ደጋፊና ተከታይ አቋቁመን የነገዋ የኢትዮጵያ ተስፋ ስንል ለራሳችን የማይገባ ስም ሰጥተን የምንቀሳቀስ ሞልተናል።

በዘርና በጎጥ ተቧድነን ስለኢትዮጵያዊነት ለመናገር ድፍረት ያለንም አለን። እኚህ አካሄዶች ምን ያክል አደገኛ እንደሆኑ ከደረሱብንና እያደረሱብን ካለው መከራ ለመታዘብ ችለናል። አሁንም በዛ መንገድ የምንጓዝ አለን። ይሄን መጥፎ ታሪክ ከመድገም ባለፈ ታሪክ አይቀይርም፣ ታሪክ አያድስም። የለውጥ ሕግ አልገባንም ስል መናገሬም ለዚህ ነው። እውነተኛ ለውጥ ራስን ከመቀየር፣ አስተሳሰብን ከማዘመን የሚነሳ ነው። እድገት ስልጣኔ ከእኔ ወደ ሌላው፣ ከሌላው ወደ እኔ ከዛም ማህበረሰብ ላይ የሚያርፍ ነው።

ራስን መቀየር ስንል በብስለት፣ በስክነት በብልህነት መቆም ማለት ነው። የማይጠቅሙ አስተሳሰቦችን፣ ልማዶችን፣ የኑሮ ዘይቤዎችን መቀየር ማለት ነው። የተግባቦት ስኪልን ማሳደግ፣ ለጋራ ጥቅም በጋራ ማበር፣ በሀገር ጉዳይ ላይ የያገባኛል ስሜትን መፍጠር የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ራስን መቀየር ማለት ከራስ በፊት ለሀገርና ሕዝብ የሚያስብ ሰውነትን መፍጠር በሚለውም ይገለጻል። እኛ ደግሞ እኚህ ሁሉ የሉንም። እኚህ ሁሉ በሌሉበት ነው ሀገር ለመፍጠር የምንፍጨረጨረው፡፡

መጀመሪያ ራሳችንን እንቀይር። ግለሰብ ሳይሰለጥን ሀገር አትሰለጥንም። ዜጋ ሳይለወጥ ሀገር አትለወጥም። መጀመሪያ እኛ እንለወጥ። መጀመሪያ አስተሳሰባችንን እንግራ። በእውቀት፣ በአንድነት መንፈስ መተባበርን ልማድ እናድርግ። ከዚህ እውነት ቀጥሎ ነው የሀገር ለውጥ የሚመጣው። ራሳችንን በጥላቻ፣ በመለያየት እያኖርን ብልጽግናን መጠበቅ ሞኝነት ነው። ራሳችንን ከአንድነት፣ ከወንድማማችነት አርቀን ስልጡን ሀገርና ሕዝብ መጠበቅ የማይታሰብ ነው፡፡

ጎዳናዎቻችን በደም የጨቀዩ አንድ አይነቶች ናቸው። ለሀሳብ ሳይሆን ለጸብ፣ ለእርቅ ሳይሆን ለትንቅንቅ እንድንመች ሆነን የቆምን ነን። የተቀየረ ምንም ነገር የለንም። ይሄ ማለት ራሳችንን አልቀየርንም፣ ፖለቲካውን አላዘመንም ማለት ነው። ይሄ ማለት ትናንታችንን አልረሳንም ማለት ነው። ለዛ ነው መለወጥ ያልቻልነው። በዚህም አልን በዚያ ግለሰባዊ ለውጥ የምንም ነገር ወሳኝ ነው። ፖለቲካው ወደ ሕዝብ ሕዝብም ወደ ፖለቲካው የሚያዩበት ጊዜ እስካልመጣ ድረስ የደም ፖለቲካን፣ የይዋጣልን ታሪኮቻችንን ማደስ አንችልም፡፡

በምድር ላይ አንደኝነትን የሚሹ በርካታ ነፍሶች ተፈጥሮዋል። ሁላችንም ለብኩርና የምንጋፋ ነን። ሁላችንም አንደኛ ለመሆን የምንኖር ነን። በሌላ መንገድ የሁሉም የሰው ልጅ ፍላጎት አንደኛ መሆን ነው እያልኩ ነው። ለማሸነፍ የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም። ለመብለጥ የማናደርገው የለም። የማሸነፍን ጥቅምና ዋጋ ያወቅንውን ያክል እንዴት ማሸነፍ እንዳለብን የምናውቅ ግን ጥቂቶች ነን። ለዚህም ነው ሕልመኞች ሆነን የቀረነው። ለዚህም ነው ከሙላታችን ጎላን የቆምነው። ማሸነፍ የማሰብ ውጤት ነው። አንደኝነት ከሩጫ ባለፈ የእውቀትና የአስተውሎት ጎዳና ነው።

እግሮቻችንን ሩጫ ሳናሰለጥን ለሩጫ የሚሆን ጥሩ ጫማ ብንገዛ ዋጋ የለውም። እጆቻችንን ስራ ሳናስለምዳቸው ብዙ እቅድ ብናወጣ ጥቅም የለውም። ልቦቻችንን እውነት ሳናስተምራቸው ጥሩ ለብሰን ለውድድር ብንቆም ትርፍ የለውም። ፖለቲካችን ሀገርና ሕዝብ ሳይገቡት ለሀገርና ሕዝብ የቆምኩ ነኝ ቢል ዋጋ የለውም። ከሀሳብ እንጀምር፣ በሀሳብም እናብቃ። በሁለት እግራችን መቆም ባቃተን በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ላይ በሀሳብ ጀምሮ በሀሳብ እንደማብቃት ያለ ጀግንት የለም። ራሳችንን አድሰን ለነጋችን ዋስትና፣ ለሀገራችን ደግሞ የመፍትሄ አካል መሆን በምንም የማናድበሰብሰው አበይት ጉዳያችን ሊሆን የሚገባው ነው፡፡

አብዛኞቹ ችግሮቻችን እኛው የፈጠርናቸው ናቸው። ችግሮቻችንን በገዛ እጃችን ስንፈጥር ለፈጠርናቸው ችግሮች የሚሆን መፍትሄ ግን የለንም። የሰው ልጅ አእምሮውን በሚገባ ከተጠቀመ ችግሮቹን በቁጥጥር ስር ማድረግ አያቅተውም። ይሄ ተፈጥሮአዊ እውነት ነው። በትንሽ አእምሮ ትልቅ ችግር የመፍጠርን ያክል አሳፋሪ ነገር የለም። እየሆነብን ያለው ደግሞ ይሄ ነው። በማሰብ ፈርጥመን በትልቅ ኃይል ችግሮቻችንን መርታት እስካቻልን ድረስ ከወሬ ባለፈ ቁም ነገር አይኖረንም። በሀሳብ ከፈረጠምን እጅ የሚሰጠን እንጂ እጅ የምንሰጠው ችግር አይኖረንም። እስካሁን ካለመነጋገር በስሜት ለችግሮቻችን እጅ ስንሰጥ ከርመናል። ቀሪው ጊዜ ችግሮቻችን እጅ ሰጥተው፣ ጦርነትን ሽረን፣ ሰላምን አውርደን፣ ወንድማማችነታችንን የምናስቀጥልበት እንዲሆን ኃላፊነት ወድቆብናል፡፡

ሀገር ታማኝና ለለውጥ የበረታ ዜጋ ከሌላት ዋጋ የላትም። ሀገር ለእርቅ ልቡን፣ ለድርድር በሩን የከፈተ መንግስትና ሕዝብ ከሌላት ተስፋ የላትም። በአንድ ሀገር ላይ ሁሉም እድሎች፣ ሁሉም ስኬቶች በግለሰብ ለውጥ የተፈጠሩ ናቸው። ሀገራችንን ለተሻለ ነገር የምናበቃት እኛ ነን። ሕይወት የምትሰምረው ዝም ብሎ በመኖር ሳይሆን እንዴት መኖር እንዳለብን ስንረዳ ነው። በዚህ መረዳት ውስጥ ነው አሸናፊነት።

እንደ ዜጋ በሕይወት ሩጫ ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ባለ ራዕይ መሪና ተመሪ መሆን ያስፈልጋል። እንደ ሀገር የተሻለ ኢኮኖሚ ለመገንባት ደግሞ ከትናንት የተሻለ ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብ ግድ ይለናል። አሸናፊ ለመሆን ከፍላጎት በላይ ጽናት ያስፈልጋል። ነገሮችን በተለየ መልኩ ማየት ግድ ይላል። ችግሮቻችን የበረቱብንም ከችግሮቻችን የገዘፍን ሆነን ስላልተገኘን ነው። ሀገራችንን ለመለወጥ በምናደርገው ትግል ልክ በሀገር ጉዳይ ላይ ስንግባባና አንድነት ሲኖረን አይታይም፡፡

ከአምና እና ካቻምና እንውጣ። የዓለም ስልጣኔ የአንድነት ስልጣኔ ነው። እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ከትላንትነት ውስጥ አልወጣንም። ለአንደኝነት ባላበቃን ትናንት ውስጥ ምን እናደርጋለን? አሸናፊነት የልምድና የተሞክሮ ውጤት ነው። አንደኝነት የፍቅርና የመቻቻል ነጸብራቅ ነው። እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ግለሰብ ፍቅርን ማወቅ ብዙ ትርፍን ያመጣልናል። ፍቅር አጥተን በጥላቻ እየኖርን የምናመጣው የጋራ ድል የለም፡፡

ሰው ፍቅር ከሌለው ደስታ የለውም። ሕዝብ አንድነት ከሌለው እድገት የለውም። ጉዳችንን አያችሁት? እናድግ ዘንድ፣ ከፍ እንል ዘንድ ፍቅር እና አንድነት ያስፈልጉናል። ዓለም ላይ ከኢኮኖሚ ባለፈ የደስተኝነትን ክብር ያገኙ ሀገራት ፍቅርና አንድነትን ያስቀደሙ ናቸው። ከትናንት እስከዛሬ በማሸነፍ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ እነሱ በፍቅር ኃይል ራሳቸውን ያደሱ ናቸው። ፍቅር የመጨረሻው ደህንነታችን ነው፡፡

ይሄ ዓለም በፍቅር ኃይል እንደሚመራ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? የምንፈልገው ጥሩ ነገር ሁሉ የእኛ የሚሆነው ልባችን ውስጥ ባለው ፍቅር ልክ እንደሆነስ ስንቶቻችሁ ገብቷችኋል? መልካምም ይሁን መጥፎ የምትፈልጉት ነገር ሁሉ በፍቅርና በጥላቻችሁ የሚሳብ ነው። እስከዛሬ ያላሸነፍነው በጥላቻ ልባችን ለማሸነፍ ስለሮጥን ነው። እስከዛሬ አንደኛ ያልወጣነው ይቅርታ በሌለው ልብ ስለተወዳደርን ነው። እስከዛሬ ነግደን ያላተረፍነው፣ ተምረን ስራ ያልያዝነው፣ ኖረን ለቁም ነገር ያልበቃነው የፍቅርን ኃይል ስላልተረዳን ነው። ሀገር ፍቅር ትሻለች። ሀገር ይቅር የሚል ልብ ያስፈልጋታል። ለዚህም ነው ራሳችንን እናድስ፤ የሀገር መልክ የሕብረብሄራዊነት ቀለም ነው ብዬ መጀገኔ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You