እንደ ንስር አሞራ ራስን የማደስ ፈተና

ኢትዮጵያ በርካታ የጀግንነት ታሪኮች ያሏት፤ የሥልጣኔ በር ከፋች ፤ አክሱም እና ላሊበላን … የመሳሰሉ እጅግ ውብና ከዘመኑ የቀደሙ አስደናቂ የኪነ ህንጻ ግንባታዎች ባለቤት የሆነች ፤ ልዩ ልዩ ጠቢባን የፈለቁባት ፤ በቀኝ ግዛት ያልተገዛች ፣ የራሷ ፊደል ያላት ፤ ዛሬ ያደጉ ለምንላቸው ሀገራት ድጋፍ ስታደርግ የነበረች የቀደሙ ሥልጣኔዎች ባለቤት ናት።

“የት ይደርሳል የተባለው …” ሆኖ የትናየት መድረስ ያለባት ሀገር አሁንም በድህነት ከዚህ በሚመነጭ ጠባቂነት ውስጥ ነች ። እውነታው በብዙ መልኩ ሲገለጽ ያማል። እነሱ ከፍታ ላይ ሆነው የእኛ ካለንበት ወርዶ መገኘት ያንገበግባል። አሁን ላይ ክስተቱን ቆም ብሎ ማሰብ የግድ ይላል።

ያለፈ የጀግንነት ታሪክን አያወደሱ መኖር ብቻ የትም አያደርስም ፣ በባለፈው ድክመታችን እያላዘኑ ሁሉን ድሮ ቀረ ብለን ድሮ ላይ መቆም ታሪክን አይቀይርም። ታሪክ የሚቀየረው ታሪክ ቀያሪ አስተሳሰብ ላይ ቆመን መንቀሳቀስ ስንችል ብቻ ነው። ይህን ሳስብ የንስር አሞራ ተፈጥሮ ትዝ አለኝ ። ንስር አሞራ አርባ ዓመታት በጥንካሬ ከኖረ በኋላ ፈታኝ የሆኑ ነገሮች ይገጥሙታል። እንደልቡ መብረር አይችልም ፣ በጥንካሬው ልክ አይዘልቅም ፤ ክንፉም ጥፍሩም መንቁሩም መድካማቸውን እድሜ ቆጥረው ያበስሩታል።

እነዚህን ፈታኝ የሆኑ ነገሮችን ማለፍ ከቻለ የኖረውን ያህል እድሜ ደግሞ መኖር ይችላል። ፈተናውን በድል መወጣት ካልቻለ ግን ሕይወቱ ያልፍና ታሪኩ በመጀመሪያው 40 ዓመቱ ይደመደማል።

ንስር አሞራ እድሜው በአጭሩ እንዳይቀጭ ከባድ የሆነውን መስዋዕትነት ለመክፈል እራሱን ያነሳሳል። ከመኖሪያ አካባቢው ርቆ እና ከዘመድ አዝማዱ ተለይቶ ወደ አንድ ተራራ ጫፍ ይወጣል ፤ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ አርጅቶና ተቆላሞ ምግቡን አላስበላ ያለውን መንቁሩን ከአለት ጋር አጋጭቶ ይነቅላል። መንቁሩ እስኪያድግለት ድረስ ህመሙን ታግሶ ረሃቡን ችሎ ይቆያል።

መንቁሩ ሲያድግለትና ሲጠነክርለት ደግሞ ምግቡን ፈልጎና ፈልፍሎ እንዳያገኝ ያደረገውን ያረጀውን ጥፍሮቹን በመንቁሩ አማካይነት ጭካኔ በተሞላው መንገድ መንቅሎ ይጥላል። ጥፍሮቹ እስኪያድጉለት በተለመደው ስቃይ ውስጥ ያሳልፋል። ጥፍሮቹ ጊዜያቸውን ጠብቀው ከበቀሉለት በኋላ ደግሞ ሌላውን አላስበርር ብሎ የከበደውን ክንፉ ላይ ያለውን ያረጀ ላባውን እያራገፈ ከላዩ ላይ ይጥላል።

ላባው እስኪያድግለትም መስዋትነት እየከፈለ ይቆያል ፤ ይራባል፣ ይጠማል ፣ በቁስሉ ይንገበገባል። ከዛም ላባው መብረር በሚያስችለው ደረጃ ላይ ሲደርስ እራሱን ሙሉ ለሙሉ ማደሱን አረጋግጦ ሌላ ረጅም ዓመታትን በሰላምና በደስታ ለመኖር አዲስ ሕይወት ይጀምራል።

የኢትዮጵያውያንም ሁኔታ ልከ እንደ ንስሩ አሞራ ሊሆን ይገባል ። ቀደም ሲል በሀገራችን የነበሩ የተሠሩ ታሪኮቻችን የንስር አሞራ የወጣትነት ዘመን ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል። ያ ዘመን በነበረበት ጥንካሬ አልቀጠለም። ብዙ ነገሮች ወደኋላ በሚመስል መልኩ ቀርተዋል።

ለእድገቷ ጸር የሆኑ ነገሮች ስንፍና ፣ ሙስና፤ መገፋፋት ፤ሴራ ፣ መልካም ነገርን አለማድነቅ፣ መጥፎውን አለማውገዝ … በዝተው ህልውናዋን አደጋ ውስጥ ከተውታል። እንደቀደመው ዘመን ወደከፍታ መብረር እንዳትችል አድርገዋታል። ካለችበት የህልውና ስጋት ለመውጣት ለልማትና ለብልጽግና ጸር የሆኑትን ሁሉ አራግፋ ወደ ከፍታ መብረር እንድትችል ራሷን ማደስ ይጠበቅባታል።

በልማት ለመቀየር ፣ቴክኖሎጂ ለመታጠቅ ዓለም የደረሰበት ብልጽግና ላይ ለመድረስ ዛሬ እንደ ንስር አሞራው የማይቀረው መስዋዕትነት መከፈል አለበት። ይህንን ብልጽግና እንደሚፈልግ ፤ ዳግም ከፍታውን እንደሚናፍቅ ሕዝብ በአግባቡ ልንረዳው ይገባል።

በሽታን ለማከም የሚደረግ የቀዶ ጥገና ህመም እንዳለው ሁሉ ወደ ብልጽግና እና የቀድሞ ከፍታ የሚደረግ የሀገር ጉዞም ህመም አለው ። በህክምና ሂደት ውስጥ ያለ ጣር ፈውስን ለማጽናት እንደመሆኑ፤ ሀገርን በማሻገር ሂደት የሚፈጠርም የዜጎች የሕይወት መጎረባበጥም ግቡ የተሻለች ሀገር መፍጠር ነው ።

የኮሪደር ልማትን በምሳሌነት እንየው። የኮሪደር ልማት እንደ ንስር አሞራ ሁሉ ለከተማዋ እድገት ፤ ለነዋሪዎቿ ምቾት ፈተና የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ መልክ ማስያዝ ነው ፤ ለዚህ ሲባል የሚፈርሱ አካባቢዎች፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከአካባቢያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች ይኖራሉ።

የለመዱትን አካባቢ የኖሩበትን ማህበራዊ ሕይወት መተው ያስገድዳል። ይሄ በማህበራዊ ሕይወት ለረጅም ዓመታት ተሳስሮና ተጋምዶ ለኖረ ማህበረሰበ ከባድ ፈተና መሆኑ አይቀርም ። ግን ደግሞ ለተሻለ ሀገራዊ ጉዳዮች ይሄንን ሁሉ ህመም ታግሶና ችሎ ማለፍ ያስፈልጋል።

አላራምድ ያለውን እንቅፋት ከፊት ለፊት አንስቶ ወደፊት መራመድ ካልተቻለ ነገም ወሬው ከድህነት በታች የሚለው ተረት ተረት ይሆናል። ለነገ ለልጆቻችን የምናተርፈው አዲስ ነገር አይኖርም። የበለጸጉ ሀገራት ከማለት ባለፈ በብልጽግና ላይ ቆመን መናገር አንችልም።

ሀገር በቀደመ ታሪክ ብቻ አትኖርም ፤እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ዘመኑን የሚመጥን ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ይጠበቅበታል ። ይህም ትውልድ በዚህ የታሪክ ሂደት ውስጥ ነው።

አሁን የምናየው የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የንስሩ አሞራ እራስን የማደስ አንድ ክፍል ነው። ሌሎች የሚገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ሠርቶ ማጠናቀቅ ደግሞ የንስር አሞራ ሌላው እራስን የማደስ ክፍል ነው። እንደ ንስር አሞራው ሶስተኛ እና አራተኛ እያሉ ሀገርን ማደስ ያስፈልጋል። ሁሉንም ነገር ለማደስ የሚደረገው ጥረት ግን አልጋ በአልጋ ሳይሆን ብዙ ጥርስ የሚያስነክሱ ህመሞችን በጽናት ማስታመም የሚጠይቅ ነው።

የሠለጠነ ሀገር ያደገው በዚሁ መልኩ ነው። እንደ ንስር አሞራ ራሱን በብዙ ስቃይ ውስጥ አድሶ ነው ። ለእዚህ ደግሞ ሁሉም እራሱን ማዘጋጀት እንደ ሀገርም ተባብረን መቆም ይኖርብናል። ዛሬ ያደከመን ፣ ያሰለቸን የልማት እንቅስቃሴ ነገ ሙሉ ሆኖ እንደሚያስደስተን ዛሬ ላይ ቆም ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው።

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You