የኮሪደር ልማት – የስኬትና የውበት ተምሳሌት

የኮሪደር ልማት በአብዛኛው የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን የሚያጠቃልል የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር የሚፈጥር፤ ውብና ማራኪ የከተማ ፕላንና የልማት ሂደት ነው። ለትራፊክ ለተጨናነቁ የመንገድ መሰረተ ልማቶችና ለከተማ ጽዳት ፍቱን መድሀኒት ናቸው።

በኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀሳብ አመንጭነት በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች እየተተገበረ ይገኛል። ልማቱ እንደ አሁኑ በስፋት ባይሰራበትም በጃንሆይ ዘመነ መንግስት እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች ተግባራዊ ስለመደረጉ አንዳንድ መሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

በዚህም በዘመኑ የተገነቡ አንዳንድ ሕንፃዎችና የንግድ ቤቶች ኮሪደር ነበራቸው። ሰዎች መንገድ ለመሄድም ሆነ ለማረፍ የሚቸገሩበት ሁኔታ አልነበረም። ከመኪና መንገድ የራቁ ስለሆነ እግረኞችን ከትራፊክ አደጋ የሚጠብቁ በዝናብም ሆነ ፀሐይ እንዳይጠቁ የሚረዱ ነበሩ።

ብሔራዊ ቲያትር ኮሪደር እንዲኖረው ተደርጎ እየተሠራ ነው። በመርካቶ አንዋር መስኪድ አካባቢ በተለምዶ ፍራሽ ተራ በመባል የሚጠራ ብዙ ሱቆች ያሉት የንግድ ቦታ ኮሪደር ነበራቸው። በአውቶቡስ ተራ ወደ ሰባተኛ መንገድ በሚወስደው ቦታ በስተግራ የነበሩ በተለምዶ ወሎ ፈረስ የሚባል አካባቢ የነበሩ ሱቆች የራሳቸው ኮሪደር ነበራቸው።

አራት ኪሎም ብንመለከት የትምህርት ሚኒስቴር ሕንጻ ኮሪደር ልማቱ ሲጀመር መልሶ ሰዎች ክፍት ሆነ እንጂ በገነት ዘውዴ ሚኒስትርነት ዘመን ጀምሮ ለእግረኛ ዝግ ሆኖ ነበር። ጆሊ ባርን ተከትሎ ወደ ብርሃንና ሰላምና አምስት ኪሎ መንገድ የነበሩ ሕንፃዎች የራሳቸው ኮሪደር ነበራቸው። ይህ በቀደምት ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ የሚስተዋል ነው።

በተለያዩ ምክንያቶች ይህንን በመልካም ጅማሮ ማስቀጠል አለመቻላችን፤ከብዙ ዓመታት በኋላ ወደኋላ ተመልሰን ትናንት ልንሰራው የሚገባንን የቤት ስራ ለመስራት ተገድደናል። ከተሞቻችንን ካሉበት ሁለንተናዊ ኋላቀርነት ለመታደግ፤ በከተሞች ያሉ ዜጎቻችንን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር አሁን ላይ እየከፈልነው ያለውን ዋጋ እንድንከፍል ሆነናል።

የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት ለሕዝብ ቃል ከገባቸው ጉዳዮች መካካል አንዱ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹና ተስማሚ ውብ ከተማ ማድረግ ነው። ከተሞችን መሰረተ ልማቶች በማሳደግ የነዋሪዎችን ሕይወት የሚያቀሉ ልማቶችን ማከናወን፤ የከተሞችን ደረጃ በማሳደግ ገቢ የማመንጨት አቅማቸውን ማሳደግ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ በመጀመሪያው ዙር በተካሄደው የኮሪደር ልማት የተገኙ ስኬታማ ተሞክሮዎች፤ አንድም መንግስት ለሕዝቡ የገባውን ቃል ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያመላከተ ነው። ከዚህም ባለፈ እንደ ሀገር በልማት ዙሪያ አዲስ ሀገራዊ የስራ ባህልንና ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ የመፈጸም አቅም መፍጠር ያስቻለ ነው።

ከተማዋንን እንደስሟ አዲስ ለማድረግ የተደረገው አሁናዊ ጥረትም ብዙዎችን ያስደመመ ነው። ከፒያሳ- አራት ኪሎ፤ ከአራት ኪሎ- መገናኛ፤ ከመስቀል አደባይ- ቦሌ፤ ከሜክሲኮ- ሳር ቤት፤ ከመገናኛ ሰሚት፤ ከፒያሳ ቸርችል ያለውን የኮርደር ልማት ገጽታን ከዓመት በፊት ከነበረው ገጽታ ጋር በማነጻጻር ማየት የልማቱን ፋይዳ መናገርና ምስክርነት መስጠት አያሻም።

ከአፍሪካ መዲና፤ ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ አዲስ አበባ የተወጠነው የኮሪደር ልማት በክልል ከተሞችና በዞን ከተሞች ጭምር በስፋት ተግባራዊ እየሆነ ነው። ለምሳሌ በደብረ ብርሃን ከተማ በ500 ሚሊየን ብር፤ ሰባት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተሠራ ነው።

ልማቱ ከተማዋን ስማርት ሲቲ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚረዱ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ያካተተ ነው። በአዲሱ በጀት ዓመት መጀመሪያ የተጀመረው የኮሪደር ልማቱ በበጀት ዓመቱ ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በተመሳሳይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጎንደር የተጀመረው የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የዐፄ ፋሲል ቤተመንግሥት እድሳትን ጨምሮ በከተማዋ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ሲሆን አፈጻጸሙም በጥሩ ደረጃ ይገኛል። በከተማው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በያዝነው በጀት ዓመት ሁለተኛ ሩብ ዓመት ተጀምሯል። የኮሪደር ልማቱ የጎንደር ጥንታዊነትና ታሪካዊነት በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ስለመሆኑ ከሰሞኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ በጎንደር ተገኝተው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል።

በጎንደር ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት 12 ኪሎ ሜትር የመንገድ ክፍል የሚለማ ይለማል፤ ከፒያሳ- አዘዞ፤ እስከ አየር ማረፊያ ያለውን የከተማ ቦታ የሚሸፍን ሲሆን የዲዛይን ሥራው ተጠናቆ ወደ ትግበራ ተገብቷል። ለዚህም የመንገድ ዳር ኮንቴይነሮችንና አጥሮችን የማንሳት ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑ የከተማዋ አስተዳደር ገልጧል። ተነሺዎችም በሦስት ክላስተሮች በተደራጁ ቦታዎች ዳግም ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትም እየተከናወኑ ነው።

የጎንደር ከተማው ኮሪደር ልማት እንደ አዲስ አበባ ከተማ ሕንፃዎችን የማስዋብ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን የመገንባት እንዲሁም መንገድ ዳር መብራቶችን የመትከልና የአስፋልት ማንጠፍ ሥራዎችን ያካተተ ነው። የአረንጓዴ ስፍራዎችና የመዝናኛ ፓርኮች ግንባታን፤ የመብራት፣ የውሃ፤ የስልክና የኢንተርኔት መስመሮችም አንድ ወጥ በሆነ መንገድ መዘርጋት የሚያስችል አሰራርን የተከተለ ሲሆን በኮሪደር ልማት የታወቁት ቻይናና የአፈሪካዋ ሀገር ሩዋንዳ ምሳሌ ናቸው፡፡

የጎንደር የኮሪደር ልማት በጥር ወር በታላቅ ኃይማታዊና ባህላዊ ሥርዓት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል በልዩ ድባብ ለማክበር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር፤ ለከተማው የቱሪስት ፍሰት ማደግም አዎንታዊ ሚናው ከፍያለ እንደሆነ ይታመናል። በአጠቃላይ በከተሞቻችን እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት አዲስ የሥራ ባህል የፈጠረ ነው።

በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የሥራ መነሳሳትን ያጫረ፤ ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል መፍጠር ያስቻለ ፕሮጀክት ነው። ወጣቱ በፈረቃ ጠዋትና ማታ ሥራዎችን በቅልጥፍና በጥራት አስውቦ ለመጨረስ ያለው ተነሳሽነት በራሱ የሚያኮራ እና ይበል የሚያሰኝ ነው።

በቀጣይ በከተሞች ለሚከናወኑ ግንባታዎች መልካም ተጨባጭ ተሞክሮ ነው። ስራው አለቃና ምንዝር ተናበው የሠሩበት፣ መንግሥት ትኩረት የሰጠበት፣ ክትትል ያደረገበት፣ ለሌሎች የመንግሥት ፕሮጀክቶች፤ ለከተሞች የኮሪደር ልማቱ የስኬትና የውበት ተምሳሌት ነው፡፡

እንደ ሀገር በተጀመረው የኮሪደር ልማት የታየው መነሳሳት፤ ስራን በጥካሬና ሰው አይቶ በሚመሰክረው ልክ እንደተሰራ ሁሉ በተመሳሳይ በሌሎች ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም ይህንኑ መተግባር የሚያስችል አቅም ማጎልበት፤ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር ተገቢ ነው።

ይቤ ከደጃች.ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You