በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ማውረድ አስፈላጊ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በተለያዩ ጊዜዎች እና የታሪክ አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሌላ በደል ተጠቂዎች የሆኑ ወይም ተጠቂዎች ነን ብለው የሚያምኑ ዜጎች በደላቸውን የሚናገሩበትና በደል ያደረሱ ዜጎች ላደረሱት ግፍ በግልፅ በማውጣት የሚፀፀቱበትና ይቅርታ የሚጠይቁበት መንገድ በማበጀትና እርቀ-ሰላም በማውረድ ዘላቂ ሰላም ማስፈን አስፈላጊ ሆኖም ሰንብቷል፡፡
በዚህም ሁኔታ በአገሪቱ ለዓመታት እርቅ እንዲደረግ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ለጥያቄው ‹‹ምን ሆነን? ማን ከማን ጋር ተጣልቶ ነው?›› የሚል ምላሽ በጥያቄ መልኩ ምላሽ ሲሰጥ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያስገነዝበው ደግሞ አለመግባባቶችን ለዘለቄታው ለመፍታት የእርቀ-ሰላም መንገድ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም ሰላምን መፍጠር ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር ደቡብ አፍሪካ የነጭ የበላይነት፣ ሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ያሳረፉትን ቀውስ ለመፍታት የመረጡት መንገድ እርቀ-ሰላም ነው፤ ይህም ውጤታማ አድርጓቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አገር እንደመሆኗ በመካከላቸው ምንም አይነት ቅሬታ የለም ማለት አያስችልም፡፡ የተበደለም፣ የበደለም አካል መኖሩ የሚካድ አይደለም፡፡ በዚህም ሂደት መጎዳዳት እንዳይኖር እርቀ-ሰላም ወሳኝ ነው፡፡ እርቅ ለታሪክ የሚቀመጥና ወደኋላ የማይመለስ ለአንዴና ለመጨረሻ የሚሆን ሥራ መሰራት እንዳለበት በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም እንደ አገር ለመቀጠልና እጅ ለእጅ ተያይዞ ልማትን ለማሳደግ ትንሽም ይሁን ትልቅ ቁርሾን ማስወገዱ ጠቃሚ ነው፡፡ ለሕብረተሰቡም ግጭት ከተከሰተ በኋላ መልሶ አብሮ ለመኖር የሚመረጠው በህግ ከሚገኝ ፍትህ ይልቅ በእርቀ-ሰላም የሚገኘው መፍትሄ ዘላቂ ፣ ሰላማዊና ተመራጭ ነው፡፡
የእርቁ ዋና አላማ ጥላቻ እየጎለበተ እንዳይሄድና ከወዲሁ እንዲደርቅ ማድረግ ነው፡፡ መሰል ችግሮችን በሃይማኖታዊ መንገድ ማስታረቅ እንደሚያስፈልግ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተከስቶ የነበረው ግጭት መልኩን ቀይሮ የሃይማኖት እና የብሔር ይዘት እንዲኖረው ቢደረግም ውድመቱን በህዝብና በመንግስት ጥረት ለመቆጣጠር መቻሉ ይበል የሚያስብል ነው፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ንፁሀን ዜጎች ህይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ ቤተ እምነቶችም የጥቃቱ ኢላማ ነበሩ፡፡
በሀገሪቱ ከላይ በተጠቀሰው እና በሌሎች ምክንያቶች በተለያዩ አካባቢዎች እየተቀሰቀሱ ያሉ ተቃውሞዎችና ግጭቶችን ተከትሎ የተፈጠሩ የህዝብ መቃቃሮች እንዲሽሩ የሃይማኖት አባቶች በእርቀ ሰላም ሥራ ላይ በስፋት ሊሰሩ ይገባል፤ ጊዜውም ያስገድዳል፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነው በባሌ ሮቤ እና ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እየተካሄዱ ያሉ እርቀ ሰላም ጉባኤዎች የጅምሩን ሂደት ተምሳሌት አድርጎ ማንሳት ይገባል፡፡
በጉባኤው የመጫ ቱለማ የገዳ አባቶች፣ ምሁራን እና የባሌ ሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በክልሉ በተፈጠረው ክስተት ምክንያት የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በኦሮሞ ባህል መሠረት እርቅ ለማውረድ በባሌ ሮቤ የመደ ወላቡ ስታዲየም ምክክር ተካሂዷል። በእርቀ ሰላም ጉባኤው ላይ ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ፤ የአገር ሽማግሌዎች፤ አባገዳዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡ ይህ ለሰላም ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ሰላም የሁሉም መሰረት ነውና፡፡
በአጠቃላይ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የእርቅ አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ወሳኝና አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ያሉ ቂምና በቀል ያረገዙ ስሜቶችን ፍርድ ቤት በመሄድ የሚዳኝ ባለመሆኑ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና የሀገር ሽማግሌዎች እጅና እግራቸውን አጣምረው የሚመለከቱበት ሳይሆን አይን የሚገልጥ ስራ መስራት አለባቸው፡፡
ለዚህ ዓላማ ስኬትም የተቋቋመው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን የጉዳዩ ባለቤት በመሆን ፋና ወጊ ስራ ሊሰራ እንጂ ዳር ተቀምጦ የሚመለከትበት ሊሆንም አይገባም፡፡ ስለሆነም ህዝብም እንደ ህዝብ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎችም ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የቂምና የቁርሾ ስሜቶችን በእርቅ ሊቋጩና አገራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ማድረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግስትና ህዝብም የድርሻቸውን ይወጡና ሰላም ይስፈን፡፡ እርቀ ሰላምም ይውረድ፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2012